Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በኢትዮጵያ በኖራ አብዮት አማካይነት ከአሲድ ተፅዕኖ የሚያላቅቅ የአፈር ሕክምና ይከናወናል››

ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር)፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር

በምዕራብና በምሥራቁ ዓለም የግብርና አብዮት ከተካሄደ በርካታ አሠርት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ገና አሁን የግብርና አብዮት ለማካሄድ የተዘጋጀች መስላለች፡፡ መንግሥት የቀድሞውን ግብርና ሚኒስቴር ለሁለት እንዲከፈል አድርጎ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴርን ካቋቋመ በኋላ፣ ለሁለቱም ዘርፎች ለውጦች የሚያመጡ ማሟሻ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ታይቷል፡፡ በተለይ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ፣ የተለያዩ የመዋቅር ለውጦች ከመደረጋቸው በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ለሦስት ሺሕ ዘመናት ያልተሞከረ የሜካናይዜሽን ግብርና ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአግሮ ኢኮሎጂ ዞኖችን ለመለየትና የአፈር ለምነትን ለማወቅ ከተሠሩ ሥራዎች ባሻገር፣ የማዳበሪያ አቅርቦትና የምርጥ ዘር አቅርቦትን የሚያሻሽሉ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ካለመቻልና በተደጋጋሚ ድርቅ ምክንያት በጠኔ ከመመታት ወጥታ፣ ትርፍ ለማምረት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ ውድነህ ዘነበ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩን ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከመጡ በኋላ፣ ላለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ያልተካሄደ የግብርና ሜካናይዜሽን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች (ደጋና ወይና ደጋ) ተጀምሯል፡፡ መንግሥት በከፍተኛ ቦታዎች የሚካሄደው የግብርና ልማት በሰው ጉልበት ላይ መሠረት ያደረገ ነው የሚል አቋም ነበረው፡፡ ከዚህ አንፃር የተለወጠ ነገር አለ?

ዶ/ር ኢያሱ፡- እንደምታውቀው የግብርና ሥራችን ዋና መነሻ ፖሊሲያችን ነው፡፡ ፖሊሲያችን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ ዋና ዋና አራት ጉዳዮችን አስቀምጧል፡፡ የመጀመርያው የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ነው፡፡ ምክንያቱም 23 በመቶ ከድህነት ወለል በታች የሆነ ሕዝብ ይዘን የምንኩራራበት ነገር አይኖርም፡፡ ስለዚህ ፖሊሲያችን በመጀመርያ ያስቀመጠው ድህነትን ከመቅረፍ አኳያ ግብርና ላይ መሠራት አለበት፡፡ ሁለተኛው የመዋቅር ለውጥ ነው፡፡ ኤክስፖርት መር የግብርና ልማት፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ገቢ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት ላይ መሠራት ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ሦስት ነገሮች ሥራ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ገቢም የሚያስገኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዕቅዱ ላይ እንደተቀመጠው የምግብ ዋስትናን ችግር ፈተን፣ ትርፍ አምርተን ወደ ገበያ የምንገባበት ነው፡፡ ሦስተኛው ነጥብ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ መገንባት ነው፡፡

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው ቁም ነገሩ፡፡ እኛ በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ ነው ያደረግነው እንጂ ያመጣነው አዲስ ነገር የለም፡፡ ያለውን ይዞ መቀጠል ነው፡፡ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የዘር አቅርቦት ላይ የሞት የሽረት ጉዳይ አድርገን መሥራት ይኖርብናል፡፡ አርሶ አደሩ ዘር አጥቻለሁ እንዳይል ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ከውጭ የምናመጣውን ስንዴ፣ ከውጭ የምናመጣውን ዘይት፣ ከውጭ የምናመጣውን ብቅል ማቆም ይኖርብናል፡፡ እነዚህን ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየሠራን ነው፡፡ ለዘይት በዓመት 365 ሚሊዮን ዶላር እናወጣለን፡፡ ለስንዴም ብዙ የውጭ ምንዛሪ እናወጣለን፡፡ ስለዚህ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ዋነኛው ዘር ነው፡፡ ምርታማነትን ለማሳደግ ዘር ከ30 እስከ 40 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ከምርምር ተቋማት ጋር ተነጋግረን ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲኖር አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- የዘር እጥረት አለ፡፡ ከምርምር ተቋማት መሥራች ዘር በማውጣት በምርጥ ዘር ድርጅቶች አማካይነት ለማስፋፋት ተግዳሮት ያጋጥማል፡፡ በፌዴራል ምርጥ ዘር ድርጅት ደረጃ የጥራት ጉዳይ ባይነሳም፣ በክልሎች የጥራት ችግር እንዳለ አርሶ አደሮች ይናገራሉ፡፡ እዚህ ላይ ያስተካከላችሁት ምንድነው?

ዶ/ር ኢያሱ፡- አንደኛ የአደረጃጀት ለውጥና ዘርፉን የሚመለከት የመዋቅር ለውጥ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ተጠያቂነት ባለው መንገድ ሥራዎች እንዲከናወኑ አሠራሩን ለውጠናል፡፡ በግሉ ዘርፍ ተሠማርተው ዘር የሚያባዙና የፌዴራል ምርጥ ዘር ድርጅት የሚያበዛው፣ የክልል ምርጥ ዘር ድርጅቶች የሚያባዙት እስከ ተጠያቂነት ድረስ እንዲሆን አዋቅረናል፡፡ የዘር ስትራቴጂ አውጥተናል፡፡ በጥራትና በብዛት፣ በወቅቱ ከማቅረብ አኳያ ግልጽ ሰንሰለት አበጅተንለታል፡፡ አደረጃጀቱ ባለቤት እንዲኖረው አድርገናል፡፡ ለየት የሚያደርገው አንዱ ይኼ ነው፣ ይህን እያስተካከልን ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ችግሩን ፈተናል ባንልም ሥራችን ጥሩ መሠረት ይዟል፡፡ ቅድሚያ ዘር እንዲያወጡ የምርምር ተቋማት በመሥራች ዘር በኩል ያሉትን ችግሮች ደግሞ የግሉ ዘርፍ ይፈታል፡፡ ፈቃድ ሰጥተናል፣ ተጠያቂም ይሆናሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ዓመቱ መጀመርያ ላይ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ ቀጥሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ እርስዎም ደጋግመው የሚናገሩት በተያዘው ምርት ዘመን የዘር አቅርቦት ችግር በፍፁም እንደማይኖር ነው፡፡ ገና አደረጃጀቱን እያስተካከላችሁ እንደ መሆናችሁ በእርግጥ በዚህ ዓመት ሊፈታ ይችላል ወይ? በሠራችሁት ሥራ ፍሬው ሊደርስላችሁ ይችላል?

ዶ/ር ኢያሱ፡- በትክክል ይደርስልናል፡፡ በየክልሉ እየሄድን ስምምነት እየተፈራረምን ነው፡፡ ባህር ዳር ሄደን የሜካናይዜሽን ኮንቬንሽን አድርገናል፡፡ የአዝዕርትና ልማት ጥበቃ ሐዋሳ ላይ ተስማምተናል፡፡ የሐዋሳ ኮንቬንሽን ብለነዋል፡፡ ትግራይ ሄደን ደግሞ በዘር ማባዛት ላይ ሁሉም አካል በተገኘበት ተስማምተናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ዘንድሮ እንፈታዋለን ማለት ግን አይደለም፡፡ አሁን በመስኖ ማባዛት ያለብንን በመስኖ፣ በዝናብ ማባዛት ያለብንን በዝናብ አድርገን 90 በመቶ እናደርሳለን፡፡ በዚህ ደረጃ እንፈታለን ብለናል፡፡ ሊቀርብን የሚችለው ባቄላ ነው፡፡ ባቄላ ወቅቱ እያለፈብን ስለሆነ እንደፈለግነው ላይሆንልን ይችላል፡፡ ስለዚህ አደረጃጀቱንና ቴክኖሎጂውን እያስተካከልን ነው፡፡ በአማራ ክልል በመስኖ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ባቄላ እያባዛን ነው፡፡ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ስንዴ ጭምር እያባዛን ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- ዘር ላይ መንግሥት ብዙ ለውጥ ማምጣት ይፈልጋል፡፡ የዘር ፍላጎቱ አገር ውስጥ ካልተሟላ ከውጭ እንዲመጣ ሊደረግ ይችላል፡፡ ነገር ግን በውጭ ያለው ዘር ከኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት አንፃር ላይስማማ፣ ይልቁኑም በዘረመል ምሕንድስና (GMO) የተመረተ ሊሆንም ይችላል፡፡ በዚህ ላይ መሥሪያ ቤትዎ ያለው አቋም ምንድነው? ሰዎች መንግሥት ካለው የዘር ፍላጎት አንፃር ለዘረመል ምሕንድስና በሩን ሊከፍት ይችላል የሚልም ሥጋት አላቸውና የመንግሥትን አቋም ቢያስረዱኝ?

ዶ/ር ኢያሱ፡- በነገራችን ላይ በዘር ሥርዓታችን ላይ የዘረመል ምሕንድስና አይፈቀድም፡፡ ኢትዮጵያ የብዘኃ ሕይወት አገር ስለሆነች በጭራሽ አይፈቀድም፡፡ ይህን ዓይነት ዘር ይዞ የተገኘ ጠንከር ያለ ቅጣት አለው፡፡ የትኛውም አካል ዘረመል ዘር ይዞ ከተገኘ በቀላሉ መለየት ይቻላል፡፡ ለ15 ዓመታት እስር ቤት ይገባል፡፡ ስለዚህ ይህ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህንን የዘር ሥርዓታችንን ግልጽ አድርገናል፡፡ ሊያመልጥ የሚችል ካለ እየተከታተልን ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ በዚህ ምሕረት የለም፡፡ ከውጭ የምናመጣው ብዙ ምርት የሚሰጥ ምርጥ ዘር ነው፡፡ የፍራፍሬ ዘር እናመጣለን፣ ቲማቲም ከእስራኤል በኔዘርላንድ እናመጣለን፡፡ አውሮፓ የዘረመል ምሕንድስና አይጠቀሙም፡፡    

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በዘረመል ምሕንድስና የተዳቀሉ ዘሮችን ማስገባት የሚፈልገው የአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ ሞንሳንቶ ነው?

ዶ/ር ኢያሱ፡- ሞንሳንቶ ነው፡፡ ከሞንሳንቶ ጋር ወደፊት የምንነጋገረው ጥጥ ላይ ነው፡፡ ጥጥ የኢትዮጵያ አይደለም፡፡ በአብዛኛው ጥጥ የሚበላ ሳይሆን የሚለበስ ነው፡፡ ምናልባት ምርታማነቱ የተሻለ ስለሆነ፣ ዓለምም እየተጠቀመበት ስለሆነ እኛም ለምርምር ያመጣነው ጥጥ ነው፡፡ እሱም እንድናየው ነው፡፡ ነገር ግን ከጥጥ ምርምር ምርጥ ዘር የምናገኝ ከሆነ ይህንንም ሊያስቆመው ይችላል፡፡    

ሪፖርተር፡- ቢቲ ኮተን (በዘረመል ምሕንድስና የተፈጠረ) ላይ ምርምር እያደረጋችሁ ነው፡፡ እስካሁን ያለው ውጤት እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር ኢያሱ፡- ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ በነባሩ ዘር ይገኝ የነበረው በሔክታር አሥር ኩንታል ከሆነ፣ በዚህ ቢቲ ኮተን እስከ 40 ኩንታል በሔክታር ይገኛል፡፡ ምርምሩ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ነገር ግን የዘላቂነቱን ጉዳይ አሁንም እያየነው ነው፡፡ በአጠቃላይ በሌሎች ሰብሎች ግን በኢትዮጵያ የዘረመል ዘር የተከለከለ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ማዳበሪያን እዚሁ ለመቀላቀል አራት ያህል የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች የጀመሩት ሥራ ነበር፡፡ ፋብሪካም አቋቁመው ነበር፡፡ ነገር ግን እንደተፈለገው አልሄደም፡፡ እንዲያውም አገር ውስጥ ያስገቡት ማዳበሪያም የተበላሸ ነው ተብሎ እንዲጣል ተወስኖም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ምን ላይ ይገኛል? የተጋረጠባቸው ኪሳራ እንዴት ሊካካስ ይችላል?

ዶ/ር ኢያሱ፡- በማዳበሪያ ሥርዓታችን ለአርሶ አደሩ በቀጥታ ከአምራቾች እየገዛን በመሆኑ ጥራት አለው፡፡ በዋጋም የተሻለ የቀነሰ ነው፡፡ ዓምና የጀመርነውን አሠራር ዘንድሮም ቀጥለንበታል፡፡ የጠቀስከው የመቀየጥ (ብሌንዲንግ) ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ማምረት ስትችል፣ እዚሁ እንደ አካባቢው ሥነ ምኅዳር እየቀየጥን ለመጠቀም ያሰብነው ነው፡፡ ለዚያ ነው ፋብሪካዎቹ የተተከሉት፡፡ እዚህ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች ነበሩ፡፡ አንደኛ የአቅም፣ ሁለተኛ የተገዛው ማዳበሪያ ጥራት ነበር፡፡ ነገር ግን ጥራት የለውም ስለተባለ ትልቅ ችግር አጋጥሞ ነበር፡፡ እኛ ምንድነው ያደረግነው አዳዲሶቹ አመራሮች እንደመጣን ይህን ችግር ለመፍታት ቁጭ ብለን ገምግመናል፡፡ ጥሩ መፍትሔ ይዘን መጥተናል፡፡ የሞሮኮ ኩባንያ ኦሲፒ የሚባል አለ፡፡ ይህ ኩባንያ የማዳበሪያ አምራችና በማዳበሪያ ደግሞ ትልቅ የካበተ ልምድ ያለው ነው፡፡ ከዚህ ኩባንያ ጋር ተነጋግረን ፋብሪካዎቹ በተተከሉባቸው አራት ክልሎች ሄዶ እንዲያጠና አድርገናል፡፡ ኩባንያው ሄዶ አጥንቶ አይሠራም፣ ሊጣል ይገባዋል የተባለውን ማዳበሪያ እንደሚሠራ አረጋግጦልናል፡፡ ስለዚህ ኪሣራ የተጋረጠባቸውና የተገዛውን ማዳበሪያ እንዲጥሉ ተገልጾላቸው የነበሩ ዩኒየኖች፣ ኪሳራ እንደሌለባቸው ተነግሮአቸዋል፡፡ የሞሮኮው ኩባንያ በቀረበው ጥናት አገር ውስጥ የገባው ፖታሺየም ክሎራይድ ማዳበሪያ ለመደባለቅ ሊውል የሚችል ነው፡፡ ባሮን የተሰኘውም ማዳበሪያ ለመደባለቅ ሊውል ይችላል፡፡ ኤንፒኤስ ማዳበሪያም ከውጭ የምናመጣው ነው፡፡ ስለዚህ ማኔጅመንቱን የሞሮኮው ኩባንያ እንዲይዘው፣ ዩኒየኖቹ ደግሞ ቀይጠው መቶ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ላሉ አካባቢዎች ያከፋፍላሉ፡፡     

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የአግሮ ኢኮሎጂ ዞን ለይታለች፡፡ የአፈር ለምነትን ለማወቅም ካርታ ሠርታለች፡፡ ከዚህ አንፃር የሚያስፈልጉ የማዳበሪያ ዓይነቶችና ሌሎች ግብዓቶችን እስካሁን ከመለየት አንፃር ምን ተሠርቷል?

ዶ/ር ኢያሱ፡- በትክክል፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ቀደም ብላ የአፈር ለምነት ካርታ ሠርታለች፡፡ ለዚህ ሥራ ብዙ ገንዘብ ወጪ ተደርጓል፡፡ በተሠራው ካርታ በደቡብ ክልል 50 በመቶ የሚሆነው አፈር አሲድ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል 43 በመቶ አሲድ ነው፡፡ በአማራ ክልል 27 በመቶ አሲድ ነው፡፡ በሌሎችም ክልሎች መጠኑ ይነስ እንጂ የአፈር ምርታማነቱ ላይ አሲድ ተጭኖታል፡፡ ስለዚህ ምርትና ምርታማነት እንድናሳድግ ስንል፣ በአፈሩ ላይ የአሲድ ተፅዕኖ እንዳለው ተረድተናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ በኖራ አብዮት አማካይነት ከአሲድ ተፅዕኖ የሚያላቅቅ የአፈር ሕክምና ይከናወናል፡፡ በስፋት የኖራ ሥርጭት ይደረጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- አፈሩን ለማከም የሚስፈልገው ኖራ የሚመረተው በኦሮሚያ ክልል አምቦ አካባቢ የሚገኘው ሰንቀሌ ኖራ ፋብሪካ ነው፡፡ ይህ ፋብሪካ የሚያመርተው ምርት ሊበቃ ስለማይችል ምን የታቀደ ነገር አለ?

ዶ/ር ኢያሱ፡- እያየን ነው፡፡ ወጣቶችን አደራጅተን እየሠራን ነው፡ በሦስቱ ክልሎች ማሽኖች ገዝተን በወጣቶች እያስመረትን ነው፡፡ የሚገርምህ አሲድ ባለባቸው አካባቢዎች ኖራ የለም፡፡ ስለዚህ ትልቁ ወጪ የትራንስፖርት ነው፡፡ ወጣቶችን አደራጅተን እንዲያቀርቡ እያደረግን ነው፡፡ ምርታማነትን ለማሳደግ፡፡ አንደኛ የአፈር ለምነት፣ ሁለተኛ የማዳበሪያ መቀየጥ፣ ሦስተኛ በወቅቱ ማዳበሪያ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በማዳበሪያ ላይ ዓምና በኩንታል 350 ብር ቅናሽ አድርገን ለአርሶ አደሩ አቅርበናል፡፡ በእነዚህ መስኮች ብዙ ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን እያከናወንን ነው፡፡         

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት ከማዳበሪያ ግዥ ያገኛችሁትን ልምድ በዚህ ዓመት ለመጠቀም ያቀዳችሁ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ዓመት ከማዳበሪያ አምራቾች ጋር በመደራደር ግዥ ፈጽማችሁ 2.6 ቢሊዮን ብር ሊባክን የነበረ ገንዘብ አስቀርታችኋል፡፡ በዚህ ዓመት ከዚህ የተሻለ ድርድር በማድረግ ጥሩ ዋጋና ጥራት ያለው ማዳበሪያ ለመግዛት መመርያ ቢዘጋጅም እርስዎ መመርያውን አላደቁም፡፡ ለምን መመርያውን ያዝ አደረጉት?

ዶ/ር ኢያሱ፡- እሱን እኮ ጨርሰናል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ማዳበሪያ አገዛዛችን እንደዚያ ነው የሚሆነው፡፡ የግድ ከደላላ ግዛ የሚል ነገር የለም፡፡ ቀጥታ ማዳበሪያው ጥራቱን ጠብቆ መምጣት አለበት፡፡ ስለዚህ ማዳበሪያ በቀጥታ ከአምራቹ ነው የምንገዛው፡፡ በሚቀጥለውም ዓመት እንደዚያ ነው የሚሆነው፡፡    

ሪፖርተር፡-መመርያውን ካላፀደቃችሁ ለአሠራር አይመችም ለማለት ነው የጠየቅኩዎት?

ዶ/ር ኢያሱ፡- መመርያውን በራሳችን ነው የምናፀድቀው፡፡ በቢሮአችን ስለምናፀድቀው የሚያስቸግረን ነገር የለም፡፡ አዋጁና ደንቡ እስከፈቀደ ድረስ መመርያ በራሳችን አፅድቀን መሄድ እንችላለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለዚህ መመርያው ፀድቆ እየተሠራበት ነው?

ዶ/ር ኢያሱ፡- በትክክል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የማዳበሪያ ወጪ ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ኢያሱ፡- ከዶላር ጋር በምናይበት ጊዜ ዓምና 13 ሚሊዮን ኩንታል ለመግዛት 400 ሚሊዮን ዶላር አውጥተናል፡፡ ዘንድሮ 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት 600 ሚሊዮን ዶላር እናወጣለን፡፡ ዘንድሮ በመስኖ የምናካሂደው እርሻ ስፋት ይኖረዋል፡፡ በ2008/2009 ዓ.ም. ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ተጠቅመናል፡፡ ዘንድሮ ያደረውን ማዳበሪያ ትተን የሦስት ሚሊዮን ጭማሪ አለው፡፡ ከዓምና ጋር ሲነፃፀር ይኼ ትልቅ ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአርሶ አደሩ ማዳበሪያ አጠቃቀም አነስተኛ ነው፡፡ ከአቅርቦትና ከአቅም ጋር ሊያያዝ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አፈር በሰጡት ግብዓት ልክ ምርት የሚሰጥ እንደ መሆኑ አቅርቦቱንና አጠቃቀሙን ለማሻሻል ምን እየሠራችሁ ነው?

ዶ/ር ኢያሱ፡- የማዳበሪያ አጠቃቀምን አርሶ አደሩ ይወስነዋል፡፡ የእኛ ሥራ ቅኝትና ምርምር እያካሄድን መረጃ መስጠት ነው፡፡ ይጠቅምሃል ተጠቀም እንላለን፡፡ በተለይ  አሁን መሻሻል ታይቷል፡፡ አንድ ተኩል ዳፕ፣ ሦስት ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያዎችን በሔክታር እየተጠቀመ ነው፡፡ በዚህም በሔክታር ከ70 እስከ 80 ኩንታል እየተገኘ ነው፡፡ በክላስተር ጥሩ እየሠራን በመሆኑ ጤፍን ጨምሮ በተለያዩ ሰብሎች ውጤት እየተገኘ ነው፡፡ በደብረ ብርሃን ለምሳሌ በመረሬ አፈር ላይ እስከ 64 ኩንታል ስንዴ በሔክታር ተገኝቷል፡፡ በመረሬ አፈር ይህ ከተገኘ ባሌና አርሲ ላይ ከዚህ በላይ ይገኛል፡፡ በግብፅ በሔክታር ሰባት ቶን (700 ኩንታል) እያገኙ ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ዘር ላይ ያሉ ችግሮች ከፈታን፣ የአፈር ለምነትን ካዳበርንና የአርሶ አደሮች ማሠልጠኛዎች ላይ ከሠራን ትራንስፎርሜሽን መጣ ማለት ነው፡፡ 460 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እናገኛለን ያልነው በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ በ2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በአምስት ዓመት መካከል ላይ (2010) ሆነን ዘንድሮ 345 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህ ከዕቅዱ ዘመን መጠናቀቂያ ቀድመን ዕቅዱን እናሳካለን ብለን እንገምታለን፡፡ ዘንድሮ ተመሳሳይ ዕድገት እንደሚኖርና ትርፍ ምርት እንደሚገኝ እንገምታለን፡፡ ስለዚህ በ2008 ዓ.ም. ድርቅ ያጣነውን ምርት ለማካካስ ጭምር እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች (ደጋና ወይና ደጋ) የአገሪቱን 60 በመቶ ይሸፍናሉ፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚኖርባቸው ናቸው፡፡ የእርሻ ይዞታው የተበጣጠሰ ከመሆኑ አንፃር፣ እንዲሁም አርሶ አደሩን ሥራ ሊያሳጣ ይችላል ከሚል እሳቤ በሜካናይዜሽን ከመጠቀም ይልቅ በሰውና በእንስሳት ጉልበት ላይ ያነጣጠረ ግብርና እንዲካሄድ መንግሥት አቋም ይዞ ነበር፡፡ አሁን ምን ተገኝቶ ነው መንግሥት ሐሳቡን የለወጠው? በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ድንበሩን አፍርሶ ቅንጭብና ቁልቋል አጥሩን መንጥሮ በጋራ በትራክተር ሲያርስ፣ በኮምባይነር ሲሰበሰብ እየታየ ነውና እንዴትስ መተማመን ላይ ተደረሰ?

ዶ/ር ኢያሱ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ፖሊሲያችን ውስጥ የተቀመጡ አምስት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ የመሬት ምርታማነትን መጨመር፣ ሁለተኛ የጉልበት ምርታማነት ማሳደግ፣ ሦስተኛ ግብርና በቅንጅት ካልተሠራ ያለበለዚያ እንደሚወድቅ፣ አራተኛ የኩታ ገጠም አሠራር፣ አምስተኛ አንድ እግር በመሬት አንድ እግር በሰማይ አድርጎ መሥራት፣ ይህ ማለት ምርጥ ተሞክሮዎችን እንጠቀም የሚል ነው፡፡ እኛ እያልን ያለነው ጉልበት ቁጠባ አይደለም፡፡ የጉልበት ምርታማነትን እናሳድግ ነው፡፡ ምርጥ ተሞክሮዎችን ከመደርደርያ ላይ እናውርድ ነው እያልን ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ደጋው ላይ ጉልበትን መሠረት ያደረገ፣  ማሽኖችን መሠረት ያደረገ ግብርና እንደሚካሄድ አስምሮ ስለነበር ነው ይህን የምጠይቅዎ፡፡ ምክንያቱም በደጋው አካባቢ ሊጨምር የሚችለውን ምርት ያህል ሥራ አጡም ሊጨምር ስለሚችል ሁለቱ ሐሳቦች አይጋጩም ወይ?

ዶ/ር ኢያሱ፡- አይጋጭም፡፡ በጥናት ላይ ተመሠረተ አካሄድ ነው፡፡ ከመጀመርያውም የሚከለክል አይደለም፡፡ በተበጣጠሰ ማሳ ምርታማ አይሆንም አልተባለም፡፡ በተበጣጠሰ መሬት ላይ ነው ምርታማ የሆነው፡፡ ነገር ግን ምን እያደረግን ነው? የስንዴ፣ የገብስ፣ የጤፍ፣ የበቆሎ ክላስተር አደራጅተን ለሜካናይዜሽን እንዲሆን አድርገናል፡፡ ስቴት ፋርም ሆነ ማለት ነው፡፡ ለሜካናይዜሽን ይመቻል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ግልጽ ስትራቴጂ አለን፡፡ ለአነስተኛ ባለይዞታዎች የሜካናይዜሽን ጉዳይ በየትኛው አቅጣጫ እንግባ የሚል ጥናት አዘጋጅተናል፡፡ አንደኛ የመሬት ዝግጅት፣ በሬው አራት ወራት አርሶ ስምንት ወራት ነው የሚያርፈው፡፡ ስለዚህ ዓመት ሙሉ ወተት የምትሰጠውን ላም ቢያረባ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች እንዲገባ እያደረግን ነው፡፡ ወደ መስኖ እንዲሄድ እያደረግን ነው፡፡ ተጨማሪ ሥራ እየፈጠርን ነው፡፡ ስለዚህ የሜካናይዜሽኑን ሥራ በሦስት ስንከፍለው የመሬት ዝግጅታችን፣ በነገራችን ላይ በአሥር ሴንቲ ሜትር ማረሻ እየታረሰ ነው ለዘመናት የተጎዳነው፡፡ ሁለተኛ በብተና ስለምንዘራ ምርታማነት ማሳደግ አልቻልንም፡፡ ስለዚህ በመስመር እንዝራ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ እርሻ ቀኑን ሙሉ አሥር ሰው ይውላል፡፡ ይህ የሰው ኃይል ወደ መስኖ፣ ወደ እንስሳት ዕርባታ፣ ወደ ሌላ ሥራ ቢሄድ ነው ውጤታማ የሚኮነው፡፡ ሦስተኛ በድኅረ ምርት ስብሰባ ነው እንሥራ ያልነው፡፡ ለምሳሌ ያጭዳል፣ ይከምራል፣ አውድማ ይሠራል፣ ይወቃል፣ ሆ ብሎ ምርቱን ያጠራል፡፡ አንድ ቀን ለሚፈጅ ሥራ አሥር ቀን ታግቶ ይውላል፡፡ ለምን ወደ ሌላ ሥራ አይሄድም? ወደ ሌላ ሥራ ሲሄድ ነው ተጨማሪ ውጤት የሚገኘው፡፡ ስለዚህ እያካሄድን ያለነው ጉልበት ቁጠባ ሳይሆን፣ የጉልበት ውጤታማነት ነው፡፡ እንስሳ ማርባት መስኖ ማልማት ይቻላል፡፡ የምነግርህ አርሶ አደሩ አንድ ሔክታር መሬት ለማረስ 50 ኪሎ ሜትር፣ ለመድገም 50 ኪሎ ሜትር፣ ለመዝራት 50 ኪሎ ሜትር ይጓዛል፡፡ ከበሬው ጋር በአንድ ላይ 150 ኪሎ ሜትር ይጓዛል፡፡ ይህ ጉልበት ለምን ይባክናል? ለምን ይደክማል?

ሪፖርተር፡- የግብርና ሰዎች ውኃ አዘል መሬቶችን አጠንፍፋችሁ እርሻ ለማድረግ ትሠራላችሁ፡፡ የወል ቦታዎችን (የጋራ መጠቀሚያ) ወደ እርሻ ቦታ ለመቀየር ትሠራላችሁ፡፡ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ግን ውኃ አዘል ቦታዎችን መነካካት አደገኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የወል ቦታዎች ለማኅበራዊ ጉዳዮችና ለከብቶች ግጦሽ የሚውሉ ናቸው፡፡ የግብርና ሰዎች ግን አዝመራ ሊያሳጡን ነውም እየተባላችሁ ነው፡፡ በዚህ ላይ መሥሪያ ቤትዎ ያለው አቋም ምንድነው?

ዶ/ር ኢያሱ፡- በነገራችን ላይ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ፣ ዘላቂነቱን ከማረጋገጥ አንፃር የአካባቢ ጉዳይ ወሳኝ ነው፡፡ የመጀመርያ ሥራችን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ኢትዮጵያ በረሃማነትን በመከላከል የተሸለመች አገር ነች፡፡ ሂዱ ከኢትዮጵያ ልምድ ውሰዱ እየተባለ ነው፡፡ ውኃ አዘል መሬትን ከመጠበቅ አንፃር አዋጅና ደንብ አለን፡፡ ውኃ አዘል መሬቶች አይነኩም፡፡ ያልተነካ መሬት አለን፡፡ የውኃ ሀብታችንን በካርታ እያመላከትን ነው፡፡ ለአርሶ አደሩ ካርታ እየሰጠን ነው ጉድጓድ እንዲቆፍርና ውኃ እንዲያወጣ የምንሠራው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መሥራት ዋነኛ ሥራችን ነው፡፡ የአካባቢ ዘላቄታዊነት፣ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራችን አጥብቀን የያዝነውና በፖሊሲ ደረጃም ያሰፈርነው፣ ነገር ግን አልፎ አልፎ እዚያም እዚህም የተነካበት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ውኃ አዘል ጥብቅ ነው፡፡ ልቅ ግጦሽ አጥፊ ነው፡፡ እንስሳትን አንድ ቦታ አቁሞ መቀለብ ያስፈልጋል፡፡ ተፈጥሮ ሀብታችንን ካመናመኑት መካከል አንዱ ልቅ ግጦሽ ነው፡፡ ዝም ብሎ ማሰርም አይደለም፡፡ አስሮም አዟዙሮም በመቀለብ ምርታማ መሆን ይቻላል፡፡ በሜካናይዜሽን በመጠቀም 50 በመቶ የሚያርስ በሬ ወደ ሥጋ ምርት ይገባል ብለናል፡፡ በዚህ ላይ ብዙ ሥራ እያከናወንን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሜካናይዜሽን በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውል ታስቦ እየተሠራ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አሠራር አዲስ እንደ መሆኑ መጠን አቅርቦት ላይ ችግር አለ፡፡ ማሽኖቹ ወደ አገር ሲገቡም ቀረጥም ይጣላል፡፡ ቀደም ብለው የገቡትም ብልሽት ገጥሟቸው በመዛግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ያላችሁ ስትራቴጂ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ኢያሱ፡- ለሦስት ሺሕ ዓመት የያዝነው አመለካከት አለ፡፡ አርሶ አደሩ ብሎን የለውም፡፡ አርሶ አደሩ አንድ ብሎን ከተሰበረ ማሽኑን በቃ ይተወዋል፡፡ ለመጠገን አለመሞከር አለ፡፡ ወዲያውኑ ወደ በሬው ይመለሳል፡፡ ስለዚህ መግባታችን ካልቀረ ወደ አነስተኛ ሜካናይዜሽን እንግባ፡፡ ለቆላ አካባቢዎች ጉልበት ነው እጥረቱ፣ ትልልቅ ማሽኖች ይግቡ፡፡ በደጋው አካባቢ የጉልበት እጥረት የለም፣ ያለው ችግር የጉልበት ምርታማነት ነው፡፡ በአነስተኛ ደረጃ እንግባ ስንል ወጣቶቹን አደራጅተን ሊዝ ማሽን እንዲወስዱ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስፈላጊውን ሊዝ ማሽን እንዲያቀርብ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ በየክልሉ እነዚህን የሚጠግን ወርክሾፕም ይኖራል፡፡ ለምሳሌ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ትራክተር እያመረተ ነው፡፡ ሜቴክ የማሠልጠኛ ማዕከልና የጥገና ወርክሾፕ እንዲከፍት እየተነጋገርን ነው፡፡ ሁለተኛው መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነርንግ ነው፡፡ መስፍን ትራክተር አመርታለሁ ብሏል፡፡ መስፍን በሚያመርትበት ቦታ ላይ ማሠልጠኛና የጥገና ወርክሾፕ እንዲኖረው እያደረገ ነው፡፡ መንግሥት የገበያ ችግር ባለበት ቦታ ነው የሚገባው፡፡ የግሉ ዘርፍ ነው ይሠራዋል ብለን የምንጠብቀው፡፡ የአርሶ አደሮች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖችም እንደዚያው ትልቆቹ ባለድርሻዎች ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ለግብርና ሊውሉ የሚችሉ ፓምፖች፣ የግብርና ማሽኖች፣ ለእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያና ለመስኖ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቅዷል፡፡        

ሪፖርተር፡- ቆላማው አካባቢ የገቡ የግል ዘርፍ ባለሀብቶች ውጤታማ አይደሉም፡፡ የፋይናንስና የመንግሥት ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ባለሀብቶቹ ይናገራሉ፡፡ ቅሬታም እያቀረቡ ነው፡፡ መሥሪያ ቤትዎ ያለው አቋም ምንድነው?

ዶ/ር ኢያሱ፡- ዋናው ነገር ቁጭ ብሎ መወያየቱ ላይ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ቢረከብም ውጤታማ አልሆነም፡፡ እኛ እርሻን አፍቅሩ ነው የምንለው፡፡ የግሉ ዘርፍ የተወሰነ ገንዘብ ወስዶ ግማሹን ወደ እርሻ፣ ግማሹን ወደ ሌላ ዘርፍ ያስገባል፡፡ ስለዚህ ይኼ ቅር ነው የምንለው፡፡ ከግሉ ዘርፍ ነበር ብዙ ምርት ሊገኝ ይገባ የነበረው፡፡ ነገር ግን የተገላቢጦሽ ነው የሆነው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ ሥራ እየተሠራ ስላልሆነ ነው፡፡ ዘንድሮ በግሉ ዘርፍ ብዙ አቅደናል፡፡ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ትክክለኛ ሃዲዱ እንዲገባ እንፈልጋለን፡፡ ብድር በትክክል እንዲያገኙ፣ የመንግሥትንም ትክክለኛ ድጋፍ እንዲያገኙ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ተቋም ተበጅቷል፡፡ ከእኛም ጋር ተጣጥሞ ለመሄድ በየሩብ ዓመቱ እየተገናኘን በጋራ እንመክራለን፡፡   

  

   

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...