በቅርቡ ከኢትዮጵያ የንግድ ልዑካን ጋር ወደ አውስትራሊያ ተጉዘው ሳይመለሱ እንደቀሩ የሚነገርላቸው የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው፣ በሰባት ቀናት ውስጥ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ቦርድ ያስተላለፈው ጥሪ ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱ ተገለጸ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለቦርዱ ሪፖርት ሳያደርጉ አውስትራሊያ ሄደው ቀርተዋል የሚለው መረጃ እንደተሰማ፣ የዘርፍ ምክር ቤቱ የቦርድ አባላት ባለፈው ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ እንደወጡ ቀሩ ያሏቸው የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ሙሲሳና ምክትላቸው አቶ ልሳኑ በለጠ እስካሁን ሳያሳውቁ የቀሩበትን ምክንያት ሪፖርት እያደረጉ የአንድ ሳምንት የጊዜ ገደብ እንዲሰጣቸው ስምንት አባላት ያሉት ቦርድ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡
የቦርዱን ውሳኔ በግልባጭ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያሳወቁት የምክር ቤቱ ቦርድ አባላት፣ ለፕሬዚዳንቱና ለምክትል ፕሬዚዳንቱ በኢሜል አድራሻቸው ስለተላለፈው ውሳኔና በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚገልጽ ጥሪ እንዲደርሳቸው መደረጉን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ይሁን እንጂ ሁለቱም የምክር ቤቱ ኃላፊዎች ለዘርፍ ምክር ቤቱ ምላሽ ሳይሰጡ የተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ ባለፈው ታኅሳስ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. መጠናቀቁ ታውቋል፡፡
ስለጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው የዘርፍ ምክር ቤቱ የቦርድ አባል እንደገለጹት፣ በቦርዱ ውሳኔ መሠረት የተሰጠው የሰባት ቀናት ማስጠንቀቂያ በመጠናቀቁ ይህን ተከትሎ ምን ይደረግ? በሚለው ሐሳብ ላይ ለመወሰን፣ ቦርዱ አስቸኳይ በድጋሚ ስብሰባ ይቀመጣል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሁለቱ የዘርፍ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች መቅረት ሳቢያ ሊፈጠር የሚችለውን የሥራ ክፍተት ለመሸፈን ስምንቱ የቦርድ አባላት በጊዜያዊነት አንዳንድ ሥራዎችን ተከፋፍለው የሚያስፈጽሙ ተወካዮችን ሰይመዋል፡፡
ቦርዱ በጊዜያዊነት ከሰማቸው ውስጥ ቼክ የሚፈርሙ አንድ ተወካይን ጨምሮ፣ የውጭ ጉዞዎችን የሚመለከት ኮሚቴም በአንድ የቦርድ አባል እንዲመራ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዘርፍ ምክር ቤቱን እንግዶች ለማስተናገድና አስቸኳይ ጉዳዮች ሲኖሩም ውሳኔ ማሳለፍ የሚችል አንድ የቦርድ አባል በጊዜያዊነት መሰየሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከኢትዮጵያ የንግድ ልዑካን ጋር ወደ አውስትራሊያ በሄዱበት ወቅት በዚያው ቀርተዋል የተባሉት የዘርፍ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ሞሲሳ፣ የኦሮሚያ የዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እንዲሁም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል ነበሩ፡፡ አቶ ልሳኑ በለጠ ደግሞ ከኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው ባሻገር፣ የአማራ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆን ሲሠሩ የቆዩ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ኢያሱ ለሥራ ጉዳይ ከአገር እንደወጡ በዚያው ቀርተዋል የሚለውን መረጃ በመንተራስ፣ የኦሮሚያ የዘርፍ ምክር ቤት ቦርድም በግለሰቡ ቦታ ላይ ስለሚተካው ሰውና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ለመወሰን ዝግጅት ስለማድረጉም የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡