Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያን የቡና ሀብትና አገር በቀል ዕውቀት በቋሚነት የሚዘክር ዓውደ ርዕይ መካሄድ ሊጀምር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ በእንግሊዝ የምርምር ተቋም ይፋ በተደረገ ጥናት፣ የዓለም ሙቀት መጨመርና የአየር ንብረት ለውጥ በቡና አብቃይነት የሚታወቁ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እንደሚያስከትልና እንደ ሐረሪ ያሉ አካባቢዎች ከነጭራሹ ቡና አምራችነታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡ ቡና አብቃይነታቸው የታወቁ የዓለም አገሮም በከፋ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቡና የማብቀል ተፈጥሯዊ አቅማቸው ሊነጥፍ እንደሚችል በጥናቱ ተገልጿል፡፡

ሊከሰት የሚችለው የአየር ንብረት ለውጥ በቡና አብቃይነት በሚታወቁ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ሰፊ ጉዳት ሊያደርስ ቢችል እንኳ፣ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የዓለም ቡና አቅራቢ እስከ መሆን ሊያደርሳት የሚያስችል ቡና የማብቀል አቅም እንደሚኖራት በዚሁ ጥናት ውስጥ የተሳተፉ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ የቡና ዘር ምንጭና ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀች አገር ብቻ አይደለችም፡፡ ለዓለም ሕዝብ ቡናን እስከ ወዲያኛው ዘመን እያቀረበች መኖር የሚቻልበትን ተስፋ የሰጠች ብቸኛዋ አገር እንደሆነችም የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎች በምርምር ያረጋገጡት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እንደ ዘር ምንጭነቷ እንዲሁም ቡናን ለዓለም እንዳስተዋወቀች አገር ከምርቱ የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ዕውቅና ጎዶሎ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህንን የተጠቃሚነት ጉድለት ለመቀየር ያቀደ ኩባንያ ለየት ያለ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ግሪን ፓዝ ኤቨንትስ የተባለው ይህ ድርጅት፣ ለየት ያለ ዓመታዊ የቡና ዓውደ ርዕይ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ ለማካሄድ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ሲሆን፣ መሠረቱን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ካፀና በኋላም ወደፈት በዓለም እየተዘዋወረ ዓውደ ርዕዩ በማካሄድ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዝግጅቶችን ለማካሄድ ወጥኗል፡፡

ዓውደ ርዕዩን በማዘጋጀት ላይ የሚገኘው ግሪን ፓዝ ኤቨንትስ፣ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ሻይ፣ ቅባትና ጥራጥሬ እህሎች ልማትና ግብይት ባለሥልጣን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትና ከኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት በትብብር ለመሥራት ፍላጎት የግሪን ፓዝ ኤቨንትስ ኩባንያ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ወይዘሪት ቤዛዊት ጠንክር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በመጪው ጥር ወር 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄደው የቡና ዓውደ ርዕይ ሳምንት፣ ቡናን ከማብቀል ጀምሮ ወደ ውጭ እስከ መላክ ድረስ ባለው የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን፣ በቡና ዘርፍ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎችንና የውጭ ገዥዎችን በአንድ መድረክ እንደሚያገናኝ ወይዘሪት ቤዛዊት ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቡና አብቃዮች፣ ላኪዎች፣ አቅራቢዎች፣ የቡና ማሸጊያ አምራቾች፣ አቀነባባሪዎችና የውጭ ገዥዎች እንደሚታደሙበት ይጠበቃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን የቡና አፈላል ሥርዓት የሚያሳይ ትዕይንት ማካተቱም ዓውደ ርዕዩን የፌስቲቫል ገፅታ እንደሚያላብሰው  ተናግረዋል፡፡

በቡና አምራችነት እምብዛም የማትታወቀው ቱርክ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢነት ያለውን የቡና አፈላል ባህላዊ ሥርዓቷን እ.ኤ.አ. በ2003 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባህል፣ የትምህርትና የሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) ማስመዝገቧን ወይዘሪት ቤዛዊት ይጠቅሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የተለያየና አስደናቂ የቡና አፈላል ሥርዓት እንዲሁም ከቡና ጋር የተያያዘ አገር በቀል ዕውቀት ቢኖራቸውም፣ ይህንን በተገቢው ደረጃ ማስተዋወቅ ባለመቻሉ ተጠቃሚነትን እንዳላስገኘ ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም ይህንን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባህልና አገር በቀል ዕውቀት በማስተዋወቅ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል፣ የኢትዮጵያን የቡና አፈላልና የአገር በቀል ዕውቀት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለማድረግ ዓውደ ርዕዩ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሒደት ከጀርመን፣ ከአሜሪካ፣ ከጃፓንና ከእንግሊዝ የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት የሚታወቁ ኩባንያዎች በዓውደ ርዕዩ ለመሳተፍ መመዝገባቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ቆንስላዎቹንና ኤምባሲዎቹን በመጠቀም ዓውደ ርዕዩን እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ ተሳታፊ ለሚሆኑ ኩባንያዎች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁባቸው 200 ማሳያዎች እንደተዘጋጁና እስካሁንም ከግማሽ በላይ ቦታ በተሳታፊዎች መያዙ ተገልጿል፡፡ ከዓውደ ርዕዩ ጎን ለጎን በቡና ላይ ምርምር ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ አገር ተመራማሪዎች የጥናት ግኝቶቻቸውን የሚያቀርቡ በመሆኑ፣ የጥናት ውጤቶቹ በዘርፉ ከሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተደርጎባቸው ውጤት እንዲመጣ የሚያስችሉ መንገዶችን ለማመቻቸት ይረዳል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች