Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከ37 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚጠይቁ አዳዲስ መርሐ ግብሮችን ማዘጋጀቱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአሜሪካው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የሚሠራው ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ በኢትዮጵያ ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ድኅረ ምረቃ ባሉት ዕርከኖች የትምህርት አገልግሎት የሚሰጥባቸውን መርሐ ግብሮች ነድፎ ወደ ተግባር ለመግባት እየተዘጋጀ እንደሚገኝና ለዚህም የ37.5 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቅዳሜ፣ ታኅሳስ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሰባተኛ ጊዜ ተማሪዎችን ባስመረቀበት ፕሮግራም ወቅት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የትምህርት  አገልግሎቱን ለማስፋፋት የቀረፀውን ፕሮግራም በአዲስ አበባና በባህርዳር በሙከራ ደረጃ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡ ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ድኅረ ምረቃ ድረስ የሚዘልቀውን ፕሮጀክት ለመተግበር በዋና ዋና ከተሞች ግንባታ ለማካሄድ የመሬት ጥያቄ ማቅረቡን የገለጹት የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት አቶ አቤቱ መላኩ፣ ለዚህ ፕሮጀክት የሚውለውን ገንዘብ ለማግኘት ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ አቤቱ ገለጻ፣ ተቋሙ አገልግሎቱን ለማስፋትና ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆነውን ፋይናንስ ኦቨርሲስ ፕሮጀክት ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን (ኦፒክ) ከተባለ ተቋም በሚገኝ ብድር ፕሮጀክቱን ለመተግበር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ግለሰቦች ለመደገፍ ጭምር ይንቀሳቀሳል የተባለው ይህ የትምህርት ተቋም፣ የአሜሪካ ዜጎች በተለያዩ አገሮች ውስጥ በትምህርት፣ በእርሻ፣ በጤናና በመሳሰሉት መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉም በዝቅተኛ ወለድ ብድር የማመቻቸት ሥራ የሚሠራ ተቋም እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በካሊፎርኒያ ከሚገኘው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እየሠራ በመሆኑ፣ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቡን  አመልክተዋል፡፡ የብድር ጥያቄው አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንደሚያገኝና ፕሮጀክቱንም በአፋጣኝ ወደ ሥራ ያስገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ፡፡

ይህ ካልተሳካም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ፕሮጀክቱን ተግባራዊ እናደርጋለን ያሉት አቶ አቤቱ፣ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ጥራት ላይ የተመሠረተ አገልግሎቱን በሌሎች ዘርፎችም መስጠቱን እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሰባተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ሥርዓተ ትምህርቱ በሊንከን ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ያገናዘበ የትምህርት አሰጣጥ እንደሚከተል ተጠቅሷል፡፡

የማስተማሪያ መርጃ መሣሪያዎችና የመማርያ መጻሕፍት በሊንከን ዩኒቨርሲቲ የሚቀርቡለት ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲው ቤተ መጻሕፍት አማካይነት ከ150 ሺሕ በላይ መጻሕፍትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አጋዥ ማቴሪያሎችን ለማንበብም በሚያስችል ደረጃ የሚቀርቡበት ሲሆን፣ በአዲሱ ፕሮጀክት መሠረት ጥራት ላይ ያተኮረ ትምህርት ለመስጠት የሚረዱ ሥራዎችም እንደተካተቱ ተገልጿል፡፡

የትምህርት ተቋሙ ተልዕኮ በሥራ ጫና ምክንያት የመማር ዕድል ማግኘት ላልቻሉ ሆኖም የትምህርት ሚኒስቴርን መመዘኛዎች ለሚያሟሉ ዕጩ ተማሪዎች ልዩ የማስተማሪያ መርሐ ግብር መንደፉም ተብራርቷል፡፡

ተቋሙ ተማሪዎቹን የኢንተርፕሪነርሺፕ አስተሳሰብና ክህሎትን እንዲላበሱ ከማድረግ ጀምሮ የሚሠሯቸው ጥናታዊ ጽሑፎችም በኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭብጦች ላይ ያተኮሩ፣ በተግባር የሚተረጎም መፍትሔ ጠቋሚ ሐሳቦችን እንዲያቀርቡ ማበረታታት ዓላማው እንደሆነ ተቋሙ ይገልጻል፡፡ ዕጩ ተማሪዎቹን ከጥናት እስከ ተግባር ባለው ሒደት ውስጥ ድረስ የቢዝነስ ዕቅድ በመቅረፅ የሚሳታፉበትን አሠራር ዘርግቷል፡፡ በተጨማሪም ምሩቃን ተማሪዎች በወደፊቱ ሕይወታቸው በትምህርት ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በተግባር የሚያሳዩበት መሠረት እንዲኖራቸው የሚያግዝ አካሄድ መቅረፁን አስታውቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በማስትሬት ዲግሪ ሥልጠና የሚሳተፉ ተማሪዎችን መቀበል የጀመረ ሲሆን፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ለመጀመርያ ዲግሪ የሚያስፈልገውን ሥርዓተ ትምህርት ከሊንከን ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ትምህርት ጋር በማጣጣም የቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት ፀድቆ ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

 በ2004 ዓ.ም. ተቋቁሞ ከሊንክን ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሠራ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አገልግሎት በማስፋት በቅርቡ በጤና ሳይንስ መስክ (ዲያግኖስቲክ ኢሜጂንግ) የመጀመርያ ዲግሪ ሥልጠና ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከሊንክን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ላለፉት ተከታታይ ስድስት ዙሮች በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን መስክ በማትሬት ደረጃ 172 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተከናወነው ምረቃም 23 ተማሪዎችን በዚሁ መስክ፣ 14 ተማሪዎችን በመጀመርያ ዲግሪ ለማስመረቅ በቅቷል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚካኤል አርተር ሬይነር፣ የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሊቀመንበር ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል (ዶ/ር) ለተመራቂ ተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን አከናውነዋል፡፡ ዘንድሮ ከተመረቁት መካከል የቀድሞው የፍትሕ ሚኒስትር አቶ ብርሃን ኃይሉ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት የሊንክን ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ባለቤት ለአቶ ብዙዓየሁ ታደለ የመጀመርያውን የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል፡፡     

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች