Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አገር ታሟል ሐኪም ይሻል

 የአገራችን የፖለቲካ ትኩሳት ብዙ እየተባለለት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ አኳኋን ለተፈጠረው ችግር መንስዔው ምንም ይሁን፣ የሰው ሕይወት እየጠፋበት መሆኑ ከምንም በላይ ያሳዝናል፡፡ እጅግ ያማል፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ በግጭቱም የጠፋው የሰው ሕይወት፣ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በብርቱ እንዲታይ የሚያስገድድ ሲሆን፣ ዘግናኙ ግጭት ለምንና እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ማወቅን፣ ዳግም እንዳይከሰት የሚረዳ ዘላቂ መፍትሔንም ይጠይቃል፡፡

የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልብ የሰበረ ድርጊት ሳቢያ የሰው ሕይወት ተቀጥፏል፡፡  አያሌ ንብረት ወድሟል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በሚያያዝ አኳኋን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጠረ የተባለው ችግር፣ ክቡሩን የሰው ሕይወት መገበሩ መሆኑም ወዴት እየተጓዝን ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ ከእነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚነሱትን ጥያቄዎችም በአግባቡ ማስተናገድ የግድ ይላል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታዩትን ችግሮችና እየተነሱ ያሉትን ጥያቄዎችን በአጥጋቢነት ለመመለስ የሚረዳ መፍትሔ እየተፈለገለት ነው ቢባልም ቅሉ፣ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ብዙዎችን እያሳሰበ ከመሆኑ አንፃር አስቸኳይ እልባት ካልተቀመጠለት ሁኔታው ሊባባስ እንደሚችል እየታየ ነው፡፡ ግጭቶችና አለመግባባቶች ከመርገብ ይልቅ እያሰለሱ መባባሳቸው ጉዳዩን በጥንቃቄ ተመልክቶ አግባብነት ያለው ምላሽ መስጠትን እንደሚሻ አያጠያይቅም፡፡ በተለይ የሰዎች ሕይወት እየጠፋና ከየኖሩበት ቀዬ እየተፈናቀሉ ነውና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት መጓተቱ ተገቢ አይሆንም፡፡  

እዚህም እዚያም የሚሰሙት ብሶቶች ስለአገራችን ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንድናስብ የሚያስገድዱ ከመሆናቸውም በላይ፣ የችግሮቹን ትክክለኛ ምንጭ መለየት፣ ለመፍትሔው የሕዝብን ጥያቄ ባገናዘበ መልኩ መንቀሳቀስንም ይጠይቃሉ፡፡

ችግሩ የአገር ህልውናን የሚፈታተን፣ የዜጎችን ሰላም የሚያናጋ እንዲሁም የዕለት ሥራቸውን ከማከናወን ተገድበው ይልቁንም በሥጋት እንዲሸበሩ የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት የበኩሉን ማድረግ ይጠበቅታል፡፡  እየተፈጠረ ካለው አደጋ አንፃር በመደማመጥ መፍትሔ ለማምጣት ቁርጠኛ መሆንም ይገባል፡፡

ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ እስከዛሬ ባልተለመደ አኳኋን ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ማብራሪያ ይስጡን ማለታቸው የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ለችግሩ መፍትሔ የመፈለግና መፍትሔ የሚያመጣ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ቢሆንም፣ ሁሉም ወገን ለዚህ መተባበር ይኖርበታል፡፡

የሕዝብን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ዕርምጃ በመውሰድና ከገባንበት አዙሪት እንድንወጣ  ካስፈለገም አገርን በማስቀደም ቡድንተኝነትን ማክሰም ያስፈልጋል፡፡ እየታዩ ያሉት አሳዛኝ ድርጊቶች ከሚያሳርፉት ተፅዕኖ ባሻገር፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እየተፈጠረ የሚገኘው አሉታዊ ተፅዕኖም በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡ ዜጎች ተረጋግተው እንዳይሠሩ ሆነዋል፡፡ ውጥረትና ሥጋት በነገሠ ቁጥር የሚርደው የቢዝነስ እንቅስቃሴ አገርንም ዜጎቿንም ወደ ኋላ እንደሚጎትት የታወቀ ነው፡፡ ዛሬ ከሚታየው በመነሳት ነገ የሚሆነው አይታወቅ በሚል ሥጋት ገበያው ውስጥ የሚፈጠረው ውዥንብርና ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡

አጋጣሚ ሆኖ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱት ድርጊቶችና የሚዛመቱት አስደንጋጭ ወሬዎች መሠረታዊ እልባት ሳያገኙ፣ መንግሥት የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ማድረጉ ነገሩን አባብሷል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የተፈጠረውም አሉታዊ ተፅዕኖ ሳያንስ፣ አለመረጋጋቱ የንግዱ ኅብረተሰብ ተረጋግቶ ሥራውን እንዳይሠራ እያስገደደው እንደሚገኝ ከመንግሥት የተሰወረ አይደለም፡፡  

ባንኮች ብድር ከመስጠት እየተቀዛቀዙ ነው፡፡ ከባንኮች ብድር የወሰዱም በወቅቱ ላለመክፈል የሚያሳዩት ምልክትም ከአገሪቱ ወቅታዊ ትኩሳት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኩባንያዎች የንግድ ሥራቸው እየተቀዛቀዘ መምጣቱም መንግሥት ለወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት ምን ያህል ሸክም እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ሰላማዊ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴውም ያለ ሥጋት እንዲቀጥል የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው፡፡ አገር ወደ ኋላ እንዳትመለስ አላስፈላጊ የግብይት ሥርዓት ተንሰራፍቶ ሸማቹ የባሰ ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ፣ በዚህም የአገሪቱ ቀውስ እንዳይባባስ ለማድረግ ብስለት ባለው መንገድ ችግሮቹ መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ የተጎዱ ዜጎችን መርዳትና ለጉዳታቸው ካሳ መስጠትም ከመፍትሔዎቹ መካከል ይታሰብ፡፡

ለዚህ ትልቁን ኃላፊነት የሚወስደው መንግሥት ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ዜጋም የመፍትሔው አካል መሆን አለበት፡፡ በአገር ጉዳይ አያገባኝም ማለት ስለማይቻል፣ መንግሥት የሁሉንም ጥያቄ በማስተናገድ የፖለቲካው ትኩሳት በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረውን ግርዶሽ መግፈፍ ያስፈልጋል፡፡ ለደም መፋሰሱ ምክንያት የሆኑትንም በተገቢው መንገድ ተጠያቂ ማድረግና የሕዝብ ቁስል በመመልከት ዕርምጃ መውሰድ ለመንግሥት ተዓማኒነትና ተሰሚነት አስተዋጽኦ ያድርጋል፡፡ አበው ሲተርቱ ‹‹ሽበን አያሳጣን›› እንዲሉ፣ በአገር ወግና ልማድ መሠረት በዳይና ተበዳይ፣ ሕዝብና መንግሥት በአውጫጪኝ እርቅ ሊያወርዱ ይገባቸዋል፡፡

ኢኮኖሚውንም ለሕዝብ በሚጠቅም ፍጥነት ከዚህ ቀደም በተሻለ መንገድ ማራመድ ካስፈለገ አገር ሰላም መሆን ሊሆን ይገባልና፣ እዚህም እዚያም የሚያስተጋቡት ድምፆች በአግባቡ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የሚቀመጡት መፍትሔዎችም እንደከዚህ ቀደሙ እሳት ለማጥፋትና ለታይታ ወይም ነገር ለማለዘብ ተብሎ ሳይሆን፣ ለዘለቄታው፣ ለአብሮነታችን፣ ለህልውናችን ዋስትና ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለታመመ አካል ደህነኛ ሐኪም እንደሚሻው፣ ለታመችው አገራችንም ደህና ብልኃት የሚያውቅ፣ ውልቃታችንን የሚጠግን እንሻለን!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት