Saturday, September 23, 2023

ስለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ዜጎች ምን ይላሉ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጤና ስለመታወኩ ጥርጣሬ ያላቸው ጥቂቶች ናቸው፡፡ መጀመርያ አካባቢ የተነሱትን ሕዝባዊ ተቃውሞዎችና አመፆች መነሻን ከራሱ አርቆ በውጭ በሚገኙና ውጫዊ በሆኑ ኃይሎች ላይ ጥሎ የነበረው ገዥው ፓርቲም፣ አሁን ጤናማ ላልሆኑት አዝማሚያዎችና ችግሮች ዋነኛ መነሻ ራሱ መሆኑን፣ በውስጡ ያሉ አጥፊ ኃይሎችን በመታገል በድጋሚ ራሱን አድሶ ወደ ቀደመው ማንነቱ እንደሚመለስ እየተናገረ ነው፡፡ የአገሪቱን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ግለሰቦች ግን ባሉት ችግሮች ስፋትና መጠን፣ በችግሮቹ መነሻና መፍትሔዎች ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን በማራመድ ላይ ናቸው፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በዜጎች መካከል የተፈጠረው መጠነኛ ግጭት ወደ ለየለት ብጥብጥና ግርግር በማምራት፣ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ማስከተሉ ይታወሳል፣ አሁንም እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡ በሒደትም ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በሕዝቡ ላይ ውጥረት ማንገሳቸውና ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንቅስቃሴ ማወኩ ተጠቃሽ ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ፓርቲዎችም ይፋ የወጣና በድብቅ የሚከናወን የፖለቲካ ትግል ይህን ውጥረት እንዳባባሰው ብዙዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚሁ ምክንያት ቀደም ሲል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የተገደደችው አገር፣ ችግሮቿን ቶሎ ካልፈታች የባሰ ነገር እንዳይገጥማት ብዙዎች በመሥጋት ላይ ናቸው፡፡ ታደሰ ገብረ ማርያም፣ ምህረተሥላሴ መኮንን፣ ውድነህ ዘነበ፣ ዳዊት ታዬ፣ ሔኖክ ያሬድና ሻሂዳ ሁሴን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያነጋገሯቸው ግለሰቦችም ይህንኑ ያንፀባርቃሉ፡፡

አገሪቱ የገባችበት ችግር ምን ያህል ከባድ ነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ (የኢንሹራንስ ባለሙያና ባለሀብት)

‹‹ሁኔታው ያስፈራል፡፡ የሰው ሕይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ በመሆኑ ሁላችንንም ያሠጋናል፡፡ ችግሩ ከፍተኛ ነው፡፡››  

አቶ አያልነህ ሙላት (ፀሐፊ ተውኔት)

‹‹በእኔ ዕድሜ ዘመን ውስጥ እንደ አሁኑ የከፋ ጊዜ አላየሁም፡፡ ሦስት መንግሥታት አሳልፌያለሁ፡፡ ቀድሞ የነበሩት ችግሮች በፓርቲዎች ወይም በመንግሥት የተፈጠሩ ናቸው፡፡ የአሁኑን ችግር የከፋና አሥጊ የሚያደርገው በሕዝቡ መካከል የተፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ ፓርቲ በፓርቲ ላይ ቢሆን ሕዝቡ አንዱን ወግኖ ሊያመልጥ ይችል ነበር፡፡ ሕዝቡ ራሱ ነገሮችን የማይሆን ደረጃ ላይ ካደረሰ በጣም አሥጊ ነው፡፡››

አቶ አበራ ሞልቶት (የቀድሞ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርና የረዥም ዕድሜ ባለፀጋ)

‹‹ዩኒቨርሲቲዎችን የማያቸው እንደ አንድ ትንሽ ኢትዮጵያ፣ ወይም እንደ አንድ ማኅበረሰብ ወይም እንደ አንድ ቤተሰብ ነው፡፡ እየተስተዋለ ያለው ግን የመከፋፈል፣ በጐሪጥ የመታየት፣ የጥላቻና የበቀል ስሜትን ያካተተ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ ከዚህ ግምገማ በመነሳት በዩኒቨርሲቲዎች የአመራር ቀውስና ድክመት አለ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡››

ዶ/ር ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (የአፍሪካ ፍልስፍና መምህር)

‹‹አሁን በተጨባጭ እየሆነ ያለውን ነገር ስመለከት፣ ‹‹ኦሮማይ›› እንድል አስገድዶኛል፡፡ ዳግም ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳንገባ ትልቅ ሥጋት አለኝ፡፡ እንደ አንድ ወጣት ዜጋ ግራ ገብቶኛል፡፡››

አቶ ያሬድ ሹመቴ (ፊልም ሠሪ)

‹‹ያለንበት ጊዜ የታሪክ እጥፋት ነው፡፡ አንድ የታሪክ ምዕራፍ ወደሌላ ሊቀየር ሲል ያለው እጥፋት ላይ እንደሆንን ይሰማኛል፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ደርግ የመጣንበት ወቅት አለ፡፡ በደርግ ከጄኔራሎች ወደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የመጣንበት እጥፋት አለ፡፡ እጥፋቱ የመንግሥት መቀየር ብቻ ሳይሆን፣ የታሪክ መልክ መየቀርም ነው፡፡ እኔን የሚያስጨንቁኝ ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ምንም ሥጋት የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ለወደፊት ትፈርሳለች ወይም የሚያፈርሳት ነገር ላይ ነች የሚል ሥጋት የለኝም፡፡ አሁን የተፈጠረውን ነገር ኅብረት የሚፈልግ በጣም ብዙ ሕዝብ እንዳለ አሳይቶናል፡፡ አንደኛ በዘር፣ በጎሳና በቋንቋ ተከፋፍሎ የብዙ ሕይወት እየጠፋ መምጣቱ ያሳስበኛል፡፡ ሁለተኛው ከአንድ ትውልድ በላይ ሊቀጥል የሚችል ጠባሳ የሚያስቀምጥ ቂምና በቀል ነው፡፡ ከሰው ሕይወት መጥፋት ባሻገር የወደፊት ታሪካችንን መልክ የሚቀይር ነው፡፡››

አቶ ፀጋዬ አበበ (ባለሀብት)

‹‹አሁን ተፈጠሩ የተባሉት ችግሮች በኢትዮጵያ ታሪክ ያልሰማናቸው ናቸው፡፡ አሁን ያለውን ኢኮኖሚ ዕድገት የበለጠ ማሳደግ እንጂ እንዲህ ያለ ነገር መፈጠር የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ በብሔር ግጭት አትታወቅም፡፡ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች አገር ነች፡፡ የብሔር ግጭት መፈጠሩ ለአገር ትልቅ ሥጋት ነው፡፡››

ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን (የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት)

‹‹አገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ የሚያስከፋ ነው፡፡ ነገር ግን ያስከፋል ተብሎ ደግሞ መደናገጥ አይገባም፡፡ ይህም ሆኖ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመንና ሊቢያ ያለው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ይከሰታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ለየት ያለ ባህል አላት፡፡ ሕዝቡ ባለፉት ግጭቶች ሳቢያ ቁርሾ ይዞ፣ ለልጅ ልጅ ያስተላለፈበት ጊዜ  የለም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ሁኔታው አስከፊ መሆኑን ከመግለጽ፣ ሕዝቡም ብሶቱን ከማሰማት ተቆጥቧል፡፡››  

አገሪቱን ወደዚህ ችግር በምን ምክንያት ገባች?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ

‹‹ችግሩ አሁን አይደለም የጀመረው፡፡ ቀስ በቀስ ሲብላላ ቆይቶ ነው አሁን የፈነዳው፡፡ ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ቅያሜ አላቸው፡፡ ይህንን የምትፈታው መድኃኒትህ ይኼ ነው ብለህ አንተ የምታስበውን መድኃኒት በማቅረብ አይደለም፡፡ ሕዝቡን ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡››

አቶ አያልነህ ሙላት

‹‹ዋናው ምክንያት ሕገ መንግሥት ለኢትዮጵያዊነት ቦታ የማይሰጥ መሆኑ ነው፡፡ በአብዛኛው ብሔር ብሔረሰቦች በሚል በብሔር ስሜት ላይ የተዋቀረ ነው፡፡ ይኼ ኢትዮጵያዊነትን ሸርሽሯል፡፡ ሁለተኛው መንግሥታት በራሳቸው አቋም ያቆየናል፣ ለአገዛዝ ያመቸናል ብለው የሚቀይሱት ከሕዝቡ የመነጨ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲዋቀር በኢትዮጵያዊ መንፈስና በአገር በቀል ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ቢገነባ ኖሮ ይኼ ሁሉ ችግር አይኖርም ነበር፡፡ ከአማራው፣ ከኦሮሞው የገዳ ሥርዓትና ከተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦቹ ቱባ ሕይወት ውስጥ ሕገ መንግሥቱን ብናመነጭ ኖሮ እንዲህ ውጥንቅጡ የወጣና ልንጨብጠው ያልቻልን ነገር አይፈጠርም ነበር፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱ ጀምሮ ሕገ መንግሥቶቻችን በሙሉ ከፈረንጅ የተገለበጡ ናቸው፡፡ ከፈረንጅ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ኢትዮጵያዊ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት ዳማትን የመሰለ መንግሥት አቋቁሞ ይመራ የነበረ ኢትዮጵያዊ፣ አሁን የሚተዳደረው ፈረንጅ በጻፈው ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ ከእንግሊዝ፣ የደርግ ከሶሻሊዝም፣ የአሁኑ ከአሜሪካ የተውጣጡ  ናቸው፡፡ እነዚህ በምንም ተዓምር የኢትዮጵያን ሕዝብ ቱባ ባህልና አስተሳሰብ የሚደግፉና የሚያራምዱ አይደለም፡፡ በውጭ የታነፀ ሕገ መንግሥት ይህንን ሕዝብ አንድ አድርጎ ይመራዋል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡››

ዶ/ር አግደው ረዴ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር)

‹‹አገሪቱ የተለያዩ የመሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት በዕድገት ጎዳና ትገኛለች፡፡ ዕድገት ደግሞ ያለ ግጭት አይሆንም፡፡ ፍላጎት በበዛ ቁጥር ግጭት አይቀሬ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ አልፎ አልፎ ግጭቶች እየታዩ ነው፡፡ ግጭቶቹም በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በብሔረሰቦች፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪዎች፣ በከተማና በገጠር ነዋሪዎች፣ ባላቸውና በሌላቸው፣ አዋቂ በሆኑና ባልሆኑ ሰዎች፣ እንዲሁም በሃይማኖቶች መካከል ሊሆን ይችላል፡፡››

አቶ ፀጋ አሳመረ (የነዳጅ ማመላለሻ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት)

‹‹አሁን ለተንሰራፋው ችግር መንስዔ የዘር ፖለቲካ ነው፡፡ አንድ ወዳጄ ተከሰሰና እሱን ለመዋስ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ ነበር፡፡ ዕድሜና የትምህርት ደረጃ ሁሉን ከነገርኩ በኋላ ዘርህ ምንድነው ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ አልኩት፡፡ በፍፁም ዘርህን ጥቀስ አለኝ፡፡ እኔ ከሁሉም ዘር የተነካካሁ ስለሆነ ይህ ነው ብዬ መናገር አልችልም፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ አልኩት፡፡ ዋስ መሆን አትችልም ተባልኩ፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? እነዚህ ቀላል የሚመስሉ ክስተቶች እየሰፉ ሄደው ዛሬ በየቦታው የወገኖቻችን ሕይወት እንዲጠፋ እያደረጉ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ወገኖቻችን አያት ቅድመ አያቶቻቸው ከነበረበት ቦታ ዘር እየተቆጠረ እየተፈናቀሉ እየሞቱ ነው፡፡ አንድ ክልል ላይ ሄደህ ዳኝነት ብትጠይቅ ፍትሕ አታገኝም፡፡ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ አገር መዓት መንግሥት ተፈጥሯል፡፡ የአንድ አገር መንግሥት አንድ ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ አንድ መለያ ነው ሊኖር የሚገባው፡፡ የብሔሮች ስም እየተጠራ ክልል ተደራጅቶ መንግሥት መባባል በራሱ ልክ አይደለም፡፡ የአማራ ክልል ሲባል አማራ ብቻ የሚኖርበት ተደርጎ ጭንቅላት ውስጥ ይሳላል፡፡ ከስም አወጣጡ ጀምሮ እኔ አልወደውም፡፡ የፌዴራሊዝም አተገባበሩ በድጋሚ ሊታይ ይገባል፡፡ ደብረ ብርሃን የሚኖር አማራ አጠገቡ መዳኘት እየቻለ ባህር ዳር ለምን ይሄዳል? በንጉሡ ዘመነ መንግሥት ለምሳሌ የሰላሌና የመራቤቴ አውራጃ ግዛት አንድ ነው፡፡ ፍቼ ሆኖ ኖራን፣ መራቤቴን፣ እንሳሮን፣ ሚዳን ያስተዳድራል፡፡ ያኔ ምን ችግር ተፈጥሯል? ተከሳሽ ኦሮሞ ቢሆን የኦሮሚኛ አስተርጓሚ፣ አማራ ከሆነ የአማራ አስተርጓሚ ይሰየማል፡፡ በኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት መጠላላትና መጠላለፍ አጋጥሞ አያውቅም፡፡ ይህ ዘር ላይ መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ከተተገበረ በኋላ በርካቶች ከሚኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል፡፡ በርካቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው አልፏል፡፡››

አቶ አበራ ሞልቶት

‹‹አገሪቱ አሁን ያለችበት አስከፊ ሁኔታ ላይ ልትደርስ የቻለችው አሳታፊ የሆነ ውይይት ወይም ንግግር ባለመካሄዱና የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት እኔ ነኝ አቅም ያለኝ ባይነት በመከሰቱ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱም ጥፋት ሁላችንም ከተጠያቂነት አናመልጥም፡፡ ሕገ መንግሥቱና ፌዴሬሽኑ ችግር አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ በትክክል ጥቅም ላይ ከዋሉ ወይም ተግባራዊ ከተደረጉ ሊያሠሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ፌዴሬሽኑ በትክክል ጥቅም ላይ ውሏል ወይም ተግባራዊ ሆኗል ለማለት አያስደፍርም፡፡››

ዶ/ር ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ

‹‹ኢሕአዴግ በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ነጋዴዎች ልማቱን ማፅዳት አልቻለም። ያላግባብ መበልፀግ (ሙስና) ባህል ሆኗል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሰፍኗል፣ የውሸት ባህል ነግሷል፣ ለሆዱና ለፍትወት ብቻ ያደረ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ አድሏዊነት፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነትና ጨቋኝነት ተንሰራፍቷል፡፡ ብሔርተኝነት ከመጠን በላይ ተለጥጧል፡፡ በሰላምና በፍቅር አንድ ላይ መኖር አልተቻለም፡፡ ሕዝብና መንግሥት የጥይት ጨዋታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ወጣቱ ተስፋ ቆርጧል፣ መግባባት፣ መደማመጥና መነጋገር ጠፍቶ መናናቅ ብቻ ሆኗል፡፡ የአብሮነት መንፈስ የሚባል ነገር ጠፍቷል፡፡ ለምዕራቡ ዓለም የአስገዳጅነት መንፈስ ሰፍኖ ሕዝቡ ስሜቱ ተሰልቧል፡፡ ደሃው በኃይልና በጉልበት ከተወለደበት ቀዬ ተፈናቅሏልወዘተ። በአጠቃላይ እንደገና ተመልሰን የቆንጨራ ጨዋታ ውስጥ ገብተናል፡፡ ይህ የማይካድ ነው። መንግሥት በሕዝብ ብሶትና እንባ ማትረፍ የሚሹትን ሰዎች አያውቅም ማለት አይቻልም። ስለዚህ በሕዝብ ስም የራሳቸውን ኑሮ ያመቻቹና የሕዝብን ገንዘብ በጆንያ የሚዘርፉ ግለሰቦችን ወደ ፍርድ ለምን እንደማያመጣቸው ፈጽሞ ግልጽ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ በሥርዓቱ ውስጥ ተሰግስገው ያሉ አብዛኞቹ ግለሰቦች (ሁሉም አይደሉም) ስለሆዳቸው እንጂ ስለሕዝቡ አሰቃቂ ሁኔታ የሚያስቡበት ሰዓትም የላቸውም፡፡ ባለፉት 44 ዓመታት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት አልተቻለም። የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖለቲካዊ ፍልስፍና ከጥይት ጨዋታ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ ሰላም እንዲወልዱ የሚያስችል ባህል የለንም፡፡››

አቶ ያሬድ ሹመቴ

‹‹የመጀመርያው የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ ሕዝቦች ብሎ ያመጣው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ በኅብረት እንደ አንድ ይታይ የነበረውን ሕዝብ ወደ ልዩነት እንዲመጣ ያደረገው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ካሉ በኋላ የተለያየ ማንነት እንዳላቸውና በማንነታቸው ውስጥ ልዩነታቸው እንዲሰፋ ተደርጓል፡፡ ያልነበረ ታርጋ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ አንድን ሰው በቤቱ፣ በንብረቱና በአገሩ ከእሱ ጋር የሚፋቀሩትና አብረውት የሚኖሩት እሱን በብሔር የሚመስሉ ሰዎች ብቻ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ አንዱ ከሌላው የሚለይበት ሰንደቅ ዓላማ ተሠርቶ፣ የተለያየ መሆኑን በአደባባይ እንዲዘክር ተደርጓል፡፡ ይኼ ሕዝቡ ከዚህ ቀደም ያልነበረውን በብሔር ጉዳይ የተጋ ተሳትፎ እንዲኖረው አድርጓል፡፡ አንድነትን የሚያፈርስ አንድምታ እንኳን ቢኖረው፣ እንዲያውም አንድነትን ያጠናክራል ቢሉም፣ ሚዲያው ትኩረት ሰጥቶ የሠራውና በመንግሥት ለረዥም ዘመናት ሲታወጅ የኖረው ልዩነት ነው፡፡ ልዩነት ላይ መሠረት ያደረገ፣ የኢትዮጵያን የቀደመ ታሪክ ያላገናዘበና በኅብረት የማያምንና ለአንድነት ቅድሚያ የማይሰጥ ሕገ መንግሥት መኖሩ የመጀመርያው ችግር ነው፡፡ ሁለተኛው የትምህርት ሥርዓቱ ነው፡፡ በመማር ማስተማር ሒደት ውስጥ የትምህርት ጥራት አለመኖር በአዕምሮው የበለፀገ፣ በአስተሳሰቡ ተራማጅ የሆነ፣ አገሩን የሚወድ፣ በአገሩ የሚኮራ፣ በአቋራጭ ለመበልፀግ የማይፈልግና የመጨረሻ ግቡ ለአገሩ መድረስ የሆነ ትውልድ እንዳይገኝ አድርጓል፡፡››

ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን

‹‹አገሪቱ አስከፊ ሁኔታ ላይ ልትደርስ የቻለችው ትንሽ እሳት ሲነሳ እሳቱን ለማጥፋት ያህል ብቻ ትንሽ ስለተነገረ ነው፡፡ የተነገረውም ፍፃሜ ላይ ሳይደርስ፣ ተመልሶ ስለሚመጣ ወይም ስለሚያገረሽ ነው፡፡››

አቶ ጥላሁን አበበ (የኢትዮጵያ ጡረተኞችና አረጋውያን ብሔራዊ ማኅበር መሥራችና የማኅበሩ አምባሳደር)

‹‹ከቆዩ መጻሕፍትና ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያ ዓለም ያፋጠጠባት አገር ናት፡፡ ያፈጠጠባትም ምክንያት በእምነቷ የፀናች፣ ሕዝቦቿ ደግሞ ፈሪኃ እግዚአብሔር ያደረባቸውና በቀላሉ ሊፋቱ ወይም ሊበረግጉ የማይችሉ መሆናቸውን በመገንዘብ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ይህ ዓይነቱን ሕዝብ ከአሁኑ ካልቀየርነውና አንገቱን እንዲደፋ ካላደረግነው በስተቀር፣ ዋል አደር ካለ ከቁጥጥራችን ውጭ ሆኖ የበላይነትን መንፈስ ሊላበስ ይችላል የሚል እምነት ያላቸው ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች እንዳሉና ዓላማቸውንም የሚያስፈጽሙ ቡድኖች መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ካለፈው ዓመት ጀምሮ እዚህም እዚያም የሚታዩት ግጭቶች የእነዚህ ኃይሎች ነፀብራቅ የሆኑ የውስጥና የውጭ እጆች አሉበት፡፡››

አገሪቱን ከገባችበት ችግር ለማውጣት ምን መደረግ አለበት?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ

‹‹ሕዝባዊና አገራዊ እርቅ ያስፍልገናል፡፡ ልዩነት በመካከላችን ይኖራል፡፡ ነገር ግን ሁላችንም የአንድ ኢትዮጵያ ልጆች ነን፡፡ ከፍቶኛል የሚል ሁሉ የሚተነፍስበት ሸንጎና የጥምረት ወይም የኅብረት መንግሥት ያስፈልገናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቻችን መጀመርያ በራሳቸው መካከል እርቅ ያድርጉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ሌሎችን ይቅር ለማለትም፣ ይቅርታ ለማለትም፣ ይቅርታ ለመጠየቅም ዝግጁ ይሆናሉ፡፡››

አቶ አያልነህ ሙላት

‹‹መንግሥት ይህንን ችግር የሚፈታ ሆኖ አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም የችግሩ ዋና ተዋናይ ነው፡፡ የእሱን ችግር እሱ ራሱ ይፈታል ብሎ ማሰብ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ልሂቃንም ይህንን ችግር ይፈታሉ ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም እንደ ሕገ መንግሥቱ ፈረንጅ አዘጋጅቶ በሰጠን ሥርዓተ ትምህርት ታንፀን የወጣን  ነን፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ የፈረንጅ ቱቦዎች አድርጎ ነው የፈጠረን፡፡ አሜሪካ የተማረ የአሜሪካን፣ ሩሲያ የተማረ የሩሲያን፣ ፈረንሣይ የተማረ የፈረንሣይን ሕይወት ያስተጋባል እንጂ ኢትዮጵያዊነትን የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በውስጡ የሌለና በኢትዮጵያ አገር በቀል ዕውቀት መሠረት የሌለው ምሁር አሁን የተፈጠውን ችግር ለመፍታት የሚችል አይመስለኝም፡፡ መፍትሔውን መፈለግ ያለብን ከኅብረተሰቡ ውስጥ ነው፡፡ ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ መፍትሔው መገኘት አለበት፡፡ ምሁሩ የቴክኒክ ድጋፍ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ኮንፈረንስ ተደርጎ፣ ኅብረተሰቡ የራሱ የሆነ አመራር ሰጥቶ፣ ሕዝባዊ ሥርዓት መዋቀር አለበት፡፡ መንግሥትና ምሁሩ ይፍታው ቢባልም ተመልሶ ጭቃ ይሆናል፡፡ ተልሶ ወደማያስፈልግ ችግር ውስጥ ያስገባናል፡፡ ሕዝቡ በሚመርጠውና በአካባቢው ቋንቋ እየተናገረ ችግሩን መፍታት ይኖርበታል፡፡››

ዶ/ር አግደው ረዴ

‹‹ግጭቶቹ ሊፈቱ የሚችሉት ግጭቶችን በፈጠሩ ወይም በግጭቶቹ በተጠቁ ሰዎች ወይም በፖለቲካ ሳይሆን በባህላዊ መንገድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግጭቶችን ለመፍታት ኃይል የምንጠቀም ከሆነ መፍትሔ ሳይሆን ሌላ ግጭት እንደምናመጣ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በባህላዊ ግጭት አፈታትም ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአካባቢው ታዋቂ ግለሰቦች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወዘተ የመሳሰሉ ገለልተኛ ወገኖች መሳተፍ አለባቸው፡፡ የገለልተኛ ወገኖች ተሳትፎ ያስፈለገበት ምክንያት እርስ በርስ ስለሚተዋወቁ፣ ጨቋኙንና ተጨቋኙን፣ ወይም ግጭት አነሳሹንና አቀጣጣዩንም ለይቶ የማወቅ ዕድል ስላላቸው ነው፡፡ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ለውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት በር ይከፍታሉ፡፡ አገሪቷ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ እያደገ ቢያንስ ቢያንስ ሰው በልቶ እንደሚያድር፣ የውጭ ባለሀብቶችም ወደ አገር ውስጥ እየገቡ መዋዕለ ንዋያቸውን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማፍሰስ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕድገት እንደ ውስጥ እግር እሳት ያንገበገባቸው ጠላቶች አለመረጋጋቶችን በመጠቀም አፍራሽ እጃቸውን ከመዘርጋት ወደኋላ እንደማይሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡››

ዶ/ር ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ

‹‹በብሔረሰቦች መካከል ፍርኃትና ጥርጣሬን የሚያጭር ማንኛውም ግለሰብ፣ ከቶ የሕዝብ መሪ ሊሆን አይችልም፡፡ አዕምሮውንና ራሱን ነፃ ያላወጣ ሰው፣ ስለሰው ልጅ ክብርና ተፈጥሯዊ መብት ምንም የሚያውቀው ነገር የለምና፡፡ መንግሥት/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በብሔርና በሃይማኖት አለያይተው እያጫረሱ ያሉትን ‹‹ወሮበላ ፖለቲከኞችን›› ወደ ፍርድ ማምጣት ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የዕብደት ሥራን የተያያዙትን ገዳዮችንና ዘራፊ ‹‹መሪዎችን›› ዘብጥያ ማውረድ አለበት፡፡ ልማቱን ከቆጫሚዎች [ከቀጣፊዎች] ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ ያልሆነ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሆነ ግለሰብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መወገዝ አለበት፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በብሔረሰቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር ሲሉ ‹‹የዋልሴ (ሾተል) ፍልስፍና›› ወይም ‹‹የጉዶ አስተሳሰብ›› እያቀነቀኑ ያሉትን አንዳንድ ሆዳም ካድሬዎችን የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓይነ ቁራኛ መከታተል ይኖርበታል፡፡መንግሥት ሙስና የሚሉት ካንሰር አገሪቷን ከመግደሉ በፍት አስቀድሞ መድኃኒቱን ካለፈላለገለት መዘዙ አደገኛ መሆኑ አጠያያቅ አይደለም። በሕዝብ ስም እየነገዱ ከፍተኛ ሀብት ያካበቱትን ግለሰቦች እያጣራ ፍርድ ፊት የማቅረብ ሞራላዊ ግዴታ አለበት፡፡ በሙስና ምክንያት 20 ሚሊዮን የናጠጠ ሀብታምና 80 ሚሊዮን መናጢ ደሃ ይዘን የሚንቀጥልበት ምንም ዓይነት መለኮታዊም ሆነ ምድራዊ ምክንያት ሊኖር አይገባም። ‹‹በቅርብ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንሠለፋለን›› የሚል ትንቢት ግቡን እንዲመታ ከተፈለገ፣ መንግሥት የሙሰኞች እጅ እንዴት መቀንጠስ እንዳለበት ከአሁኑ በደንብ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ይህ እስካልተደረገ ድረስ፣ ‹‹መጀመርያ ሙስና ነበር፣ ሙስናም በሥልጣን ዘንድ ነበር፣ ሙስናም ሥልጣን ነበር፤›› የሚል ‹‹የሙስና ወንጌል›› በኢትዮጵያ ምድር እየሰተበከና አየተተገበረ ይቀጥላል፡፡ ለነገሩ ሙስና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥም በእጅጉ አድማሱን እያሰፋ መጥቷል። ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ከባድ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል። በተለይ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሕዝቡ በቆንጨራ እየተጨራረሰ ዝም የሚሉ ከሆነ፣ በፈጣሪና በሕግ ፊት ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ እምነትና ፀሎት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ፍትሕ ሲጓደል እያዩ ዝም ማለት የለባቸውም፡፡ ከምሁራንና ከአገር ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ ተልዕኮ እንጠብቃለን፡፡ ተማርኩ ብሎ ጥሩንባ መንፋት በቂ አይደለም፡፡ ትልቁ ነገር ዕውቀትን ወደ ተግባር መቀየሩ ነው፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ሳይኖር ተማርኩ ብሎ መንጠራራት፣ በፍልስፍው ዓለም ምሁራዊ ውስልትና ይባላል፡፡ የአንድ ግለሰብ ዕውቀት (ሥልጠና) ብዙኃኑን ካልጠቀመ፣ የፕሮፈሰርነት ማዕረጉ ለሕዝቡ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ወይም ድንች ሊሆን አይችልም፡፡ በተግባር ያልተገለጠ ዕውቀትና ከመልካም ሥራ የተለየ እምነት አንድ ነው፡፡ ሰው መከበር ያለበት በተግባሩና በአስተሳሰቡ እንጂ በማዕረጉ አይደለም፡፡ ከባለጌ ክቡር የደሃ ሥልጡን ይሻላልና ጥሩንባ የሚነፉ ሰዎች አላጣንም፡፡ ጋንዲ ‹‹ከአንድ ኩንታል ወሬ አንድ ኪሎ ተግባር›› ብሎ  የለ? መንግሥትና ሕዝብ ከታረቁ ብሔራዊ እርቅ ላይ እንደርስ ይሆናል፡፡ ካልሆነ መበታተናችን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ከማንኛውም ዕልቂት ፈጣሪ እንዲጠብቀን ግን አጥብቀን መሥራት አለብን። ከሁሉም በላይ ለዚች አገር የሚያስፈልጋት ሰላም ነው፡፡ ሰላም! ሰላም! ሰላም! ዘላቂ ሰላም! ሮናልድ ሬገን ያለውን ግን እንዳንረሳ፣ ‹‹ሰላም የግጭት አለመኖር አይደለም፣ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅም ነው፤›› ስለዚህ ከራሷ ጋራ ሰላም የፈጠረች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በአንድነት እንሥራ፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ እንደሚለን፣ ‹‹ጦርነትን ማወጅ የለብንም ማለት ብቻ በቂ አይደለም፣ ሰላምን መውደድና መስዋዕትነት መክፈልም ይኖርብናል፤›› ስስታምነት ይብቃን፣ የንፁኃን ደም መፍሰስ የለበትም፣ አድሏዊነትን አጥብቀን እንዋጋ፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ እናከብር፣ የመጠላለፍ ፖለቲካ ይብቃን፣ በአጠቃላይ በባህልና በታሪክ በተሳሰሩ ሕዝቦች መካከል የቆንጨራ ፍልስፍናን ማቀንቀን፣ ለዚች አገር የሚበጅ አይመስለኝም።››  

አቶ ያሬድ ሹመቴ

‹‹መንግሥትና ሕዝብ በኢትዮጵያዊ አንድነት ማመን ይገባቸዋል፡፡ ሕዝብ እንዲያምን ሚዲያዎች ወደ ሕዝብ ቀርበው ሐሳብ የሚያቀርቡ የአገር ምሁራን፣ ሕዝብ በብዛት የሚገኝባቸው የማኅበራዊ መስተጋብር ተቋማትም ሊነገርላቸው ይገባል፡፡ አፄ ምኒልክ ሰውን ማስተማር ማለት ድንጋይ እንደ መውቀር ነው ይላሉ፡፡ ድንጋይ ሲወቀር በአንድ ጊዜ አይመታም፡፡ ቀስ እየተባለ ነው ቅርፅ የሚይዘው፡፡ በ27 ዓመታት ውስጥ ብሔር የሚለው ነገር ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ስለተነገረን ነው የተዋሀደን፡፡ ስለዚህ አንድነትና ኅብረትም ሊነገር ይገባል፡፡ መንግሥት ስለፓርቲ ህልውናና ስለብሔር ህልውና ሳይሆን ስለአገር ህልውና ሊጨነቅ ይገባዋል፡፡ ይኼ ፓርቲ ወይም ያ ፓርቲ፣ ይኼ ብሔር ወይም ያ ብሔር ሊቀጥል የሚችለው ኢትዮጵያ ስትቀጥል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያን አፍርሶ ፓርቲውን ወይም ብሔሩን ማንም ማስቀጠል አይችልም፡፡ እርስ በርሱ ይበላላል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ‹‹ተሳስተናልና ልንታረም ይገባል፣ መቅደም ያለባት አንዲቷ ኢትዮጵያ ነች›› መባል አለበት፡፡››

አቶ ፀጋዬ አበበ

‹‹አገራችን ሰላም ሆና የተጀመረው ልማት እንዲቀጥል የመንግሥትም የሕዝብ ፍላጎት ነው፡፡ ችግሮች ቢኖሩም አንድ ቤተሰብ ውስጥ እንደሚፈጠር ችግር ነው፡፡ ሁላችንም የምንገዛበት ሕገ መንግሥት አለና ሁላችንም በዚህ መተዳደር አለብን፡፡ በዚህ መሠረት የማይኖር መፍትሔና የማይፈታ ጥያቄ የለም የሚል እምነት የለኝም፡፡ የአንድ ቤተሰብ ችግር የሚፈታው በራሱ በቤተሰቡ አባልና በቅርብ ሽማግሌዎች ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥታችን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመደማመጥ ያሉትን ችግሮቻችንን መፍታት ይኖርበታል፡፡ አሁንም ወደፊትም ጠንካራ ሆኖ ለመቀጠል መደማመጥና መተባበር ያስፈልጋል፡፡ ለውጭ ጠላት በራችንን ሳንከፍት አንድ ሆነን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ነጩ ጥቁር ነው፣ ጥቁሩ ነጭ ነው ብሎ የሚከራከር አይኖርም፡፡ መደማመጥ አለብን፡፡ መነጋገሩ አስፈላጊ ነው፡፡ ችግሮቻችንን በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሚፈቱ ናቸው፡፡ከዚህ ውጭ የምንሄድ ከሆነ ሁሉም ወደራሱ አቅጣጫ ይሄድና ለአገር የሚበጅ ነገር አይፈጠርም፡፡ ለውጭ ጠላትም ራሳችንን እናጋልጣለን፡፡ ስለዚህ ጠንካራ መሠረት ያለው አገርና ጨዋ ሕዝብ ስላለን በመነጋገርና በመደማመጥ ወደ መፍትሔው መሄድ  አለብን፡፡›› 

አቶ ፀጋ አሳመረ

‹‹ግልጽ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ለምን በኦሮሞ ለምን በአማራ ሕዝቦች ተጠላሁ ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ለውጥ ከሚፈልጉ ሕዝቦች ጎን መቆም አለበት፡፡ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ግልጽ ውይይት ተደርጎ እርቅ መውረድ አለበት፡፡››

ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን

‹‹መንግሥት የሕዝቡን ችግር መረዳትና ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም የማይናቅ ጉዳይ እንደሆነ መታሰብ አለበት፡፡ እየተደረገም ነው፡፡ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ‘ጣናም የእኛ ነው’ ብለዋል፡፡ ይህ ትልቅ መልዕክት አለው፡፡  በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል እርስ በርስ የመረዳዳት ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ለሌላው በአርያነት የሚታይ ተግባር ነው፡፡ ሌሎቹም በራሳቸው ክልል ብቻ ሳይታጠሩ ከአጎራባቾቻቸው ጋር የትብብር ስምምነት ሊያደርጉ ይገባል፡፡››

አቶ ጥላሁን አበበ

‹‹የአገሪቱ ሕዝቦችና መንግሥት የውጭ እጅ እንዳለ ተገንዝበው ችግሩን ማክሸፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰይጣናዊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በመመካከርና በመግባባት ለመፍታት መሞከር እንጂ ኃይል መጠቀም የትም አያደርስም፡፡ በውጭም በውስጥም የሚቃጣውን ግጭትና አምባጓሮ ለመግታት ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰላምን ለመፍጠር ደግሞ የሕዝብ እምነትና ተሳትፎ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡››

አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ (የሴንተር ፎር አፍሪካ ሊደርሽፕ ስተዲስና የኤክስ ሀብ አዲስ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ)

‹‹በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ ጥሩም መጥፎም ጎን አለው፡፡ ለብዙዎቻችን መጥፎ የሚመስሉ ነገሮች በትክክል መጥፎ ናቸው ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ኢሕአዴግ ለ26 ዓመታት የለፋለት ዓላማ ፍሬ አፈራ ማለት ነው፡፡ በፊት ሐሳብን በነፃነት መግለጽ የማይታሰብ ነበር፡፡ አሁን ግን ሐሳቡን በነፃነት የሚገልጽ፣ መብቱን የሚጠይቅ፣ ጦርነት የማያውቅ፣ መንግሥትን የማይፈራ ትውልድ መፍጠር ተችሏል፡፡ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን መቋቋም የማይችል ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል ለ26 ዓመታት ሲተገበር በቆየው ፌዴራሊዝም በተግባር የተፈተነ ልምድ አገኘን ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ያጋጠሙን ጥሩም መጥፎም ችግሮች ልምድ ሰጥተውናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን መቀየርና መታደስ የሚገባን ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ አክራሪነት፣ ብሔርተኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ትልቅ አደጋ ውስጥ እየከተቱን ነው፡፡ ሰባ በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ወጣት ነው፡፡ ወጣት ደግሞ በሰከነ አዕምሮ ነገሮችን ማመዛዘን ላይ ብዙም አይደለም፡፡ ስለዚህም እንደ አገር ማሰብና መታደስ አለብን፡፡ ነገሮች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ እንደ ሌሎች አገሮች የምንፈረካከስበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም እንደ ሕዝብ መታደስ አለብን፡፡ ከፍ ያለ የሞራል ልህቀት ያላቸው ግለሰቦች መፈጠር አለባቸው፡፡ የፍርድ ቤቶች ነፃነት መከበርና ጥፋተኞችን በሕግ የመጠየቅ ባህል ሊዳብር ይገባል፡፡ የአሸናፊነትና የተሸናፊነት ስሜት ሳይኖር መነጋገርና መደማመጥ አለብን፡፡ ማኅበረሰቡ ሐሳቡን መግለጽ የሚችልባቸውን መድረኮች መፍጠር ግድ ይላል፡፡››

ሼክ ኡመር ኢማም (የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት)

‹‹በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት በኩል በሰጠነው መግለጫም ብሔር ተኮር ግጭት ሰላማችንን እየነሳ መሆኑን ገልጸናል፡፡ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ትክክል ናቸው፡፡ ነገር ግን የሰው ሕይወት እስከማስጠፋትና ንብረት እስከማውደም የሚያደርስ መሠረት የለም፡፡ ይህም አገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል ከበስተጀርባ መኖሩን የሚያሳይ ሲሆን፣ ጉዳዩ በጥልቀት መፈተሽ አለበት፡፡ አብሮ የኖረ ሕዝብ እየተነሱት ባሉት ጥያቄዎች ብቻ ይህን ያህል እንደማይጋጭ እርግጥ ነው፡፡ አንድነታችንን የሚጠላ አካል እንዳለ ይሰማኛል፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ እየታየ ላለው አለመረጋጋት ምክንያት ነው ብዬ የማስበው ብሔርተኝነት የኢትዮጵያዊነትን ያህል አለመስረፁ ነው፡፡ ይህች አገር ከፈረሰች ሁላችንም ተጎጂዎች ነን፡፡ ስለዚህም ችግሩን የፈጠርነው እኛ፣ መፍትሔውንም ማምጣት ያለብን እኛው ነን፡፡ ሁሉም ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ መንግሥትም ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቦ መወያየትና ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ የሃይማኖት መሪዎችም ትልቁን ሚና መጫወት መጫወትና ሕዝቡን ማረጋጋት አለባቸው፡፡››

 

     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -