Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዩኒቨርሲቲ ደኅንነት እስከ ምን?

የዩኒቨርሲቲ ደኅንነት እስከ ምን?

ቀን:

ዩኒቨርሲቲዎች ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (1923-1967) ዘመን ጀምሮ የለውጥ ጥያቄ መነሻ ናቸው፡፡ በግቢው ያሉ ተማሪዎችም የኅብረተሰቡ ነፀብራቅ በመሆናቸው፣ በማኅበረሰባቸው ውስጥ ያሉ ብሶቶችን ለማውጣት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ይህ ብሶት ሲገለጽ በየጊዜው የነበሩ መንግሥታት የየራሳቸው የሆነ ጥያቄዎችን የሚያስተናግዱበት አግባብ ነበራቸው፡፡ በንጉሡ ዘመን ዩኒቨርሲቲዎችም በጣት የሚቆጠሩ፣ ተማሪዎችም ብዙ ያልነበሩ ቢሆንም፣ ተማሪው ጥያቄ ሲያነሳ ከግቢ ሳይወጣ ተቃውሞን የሚያካሂድበት በተቃራኒውም ጠባቂ ዘቦች ገብተው ተማሪን በመማታታቸው ‹‹ሕግ ባጠና›› የሚል ውስጠ ወይራ ግጥም የተነገረበት እንደነበርም ይነገራል፡፡ በደርግ ዘመንም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው በኃይል የነበረ ሲሆን፣ በኢሕአዴግ ዘመንም ተመሳሳይ አካሄድ ታይቷል፡፡ ተማሪዎች ማናቸውንም የመልካም አስተዳደርም ሆነ የፖለቲካ ጥያቄ ባነሱ ቁጥር፣ ሰብስቦ ከማወያየት ይልቅ የፀጥታ ኃይሉ  በዩኒቨርሲቲ አካባቢዎች እንዲከብ፣ አንዳንዴ ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ይኽም በቀላሉ ሊፈታ ይችል የነበረን ጥያቄ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ ተማሪዎች ይጎዳሉ፣ ንብረትም ይወድማል፡፡

በቅርቡ በ2008 ዓ.ም. በተለይ በአምቦና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የነበሩ ግጭቶች ሲታዩ እንኳን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ችገሮች ጭምር ቀድሞ በውይይት መፍታት ባለመቻሉ በሰው ላይ ጉዳት፣ በንብረት ላይ ውድመት አስከትሏል፡፡

ይኽም የ2009 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የከፋ ጊዜ ይዞ ይመጣ ይሆን? በሚል ወላጆች፣ መምህራንና ተማሪዎች ሥጋታቸውን እንዲገልጹ አድርጓል፡፡ በተለይ ከዚህ ቀደም ጥያቄዎችን ከምክክር ባለፈ የፀጥታ ኃይል በመጠቀም፣ ፀጥ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች፣ ተማሪዎች የተዳፈነ ስሜት ይዘው እንዲመጡ ሊያደርግ ይችላል የሚል ሥጋት አስከትሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ሚኒስቴር ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ስንሠራ እንደቆየነው ሁሉ አሁንም እንሠራለን፣ መምህራንን፣ ወላጆችንና ተማሪዎችን አወያይተን ችግሮች ቢከሰቱ በውይይት እንዴት እንደሚፈቱ የመፍትሔ አቅጣጫ እናስቀምጣለን፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችንም ፈትተናል ቢሉም፣ በተለይ ወላጆች በሥጋት ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን ወስዳ 515 ውጤት ያመጣች ልጃቸውን ምደባ (ዘገባው ሲጠናቀር አዲስ ተማሪዎች አልተመደቡም) እየተጠባበቁ የሚገኙት አባት፣ ልጃቸው እሳቸው ከሚኖሩበት አካባቢ ውጭ የመመደብ ዕድሏ እንደማንኛውም ተማሪ ሰፊ ከመሆኑ አንፃር፣ እንቅልፍ ማጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው እሳቸው በተማሩበት የደርግ ዘመንም ሆነ አሁን ባለው ሥርዓት የሚያዩት የሕዝብ ጥያቄን የመፍታት አካሄድ ከኃይል ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡

የአራት ኪሎ ካምፓስ ተማሪ በነበሩባቸው አራት ዓመታት ብዙ ጊዜ ለተቃውሞ ወጥተዋል፡፡ በተለይ ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ሲደረግ፣ መፈንቅለ መንግሥቱን ደግፈው፣ በኋላም መፈንቅለ መንግሥቱን የሞከሩ ጄኔራሎች ሲገደሉ፣ ተቃውመው ወጥተዋል፡፡ ‹‹በእነዚህ ጊዜያት ከዩኒቨርሲቲ ግቢ ውጭ የተገኘ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በፖሊስ እንደ እባብ ይቀጠቀጥ ነበር›› የሚሉት እኝህ አባት፣ በአሁኑ ሥርዓትም ጥያቄዎችን በኃይል የመፍታት አካሄድ በመኖሩ፣ ልጃቸው ከሳቸው ተነጥላ ሌላ ሥፍራ ብትመደብ፣ ምን እንደሚወስኑ መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡

18 ዓመቷን በዚህ ዓመት አጋማሽ ለምታከብረው ልጃቸው፣ ትምህርቱን አትማሪ ብሎ መወሰን ወይም ልጃቸውን ማሳመን ከባድ ነው፡፡ ትምህርት የወደፊት የሕይወት መሠረት ከመሆኑ አንፃር ‹‹አትማሪም/ክልል አትሄጅም ማለቱም፣ አስቸጋሪ ነው፡፡ ትልቅ ፈተና ሆኖብኛል፤›› ይላሉ፡፡

በሳቸው ጊዜ የምግብ ጥያቄ እንኳን አንስተው፣ ችግሩን በኃይል ለመፍታት ይሞከር እንደነበር በማስታወስ፣ አሁንም የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በኃይል የሚፈታበት አካሄድ፣ ለሳቸው ብቻ ሳይሆን፣ እንደ እሳቸው ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚልኩ ወላጆች ሥጋት እንደሆነ ያምናሉ፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ችግሮች በውይይት የሚፈቱበት አሠራር በመዘርጋቱ አስጊ ነገር እንደማይኖርና ለዚህም ኃላፊነት እንደሚወስድ ቢያሳውቅም፣ ‹‹እኔ በማንኛውም እንቅስቃሴ፣ በፖለቲካም ይሁን በግቢው አስተዳደር ጉዳዮች ልጄ ድንጋይ አንስታ መስታወት እንደማትሰብር፣ ንብረት እንደማታወድም እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሕይወቴን እስከመስጠትም ዋስ ሆኜ እፈርማለሁ፡፡ መንግሥት ወይም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ግን ችግር ቢፈጠር ልጄ ጉዳት እንዳይደርስባት ዋስትና ይሆነኛል ብዬ አላምንም፤›› ሲሉም ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

በተለይ በ2008 ዓ.ም.  በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተነሱ ጥያቄዎች፣ ከኅብረተሰቡ ጋር የተደረጉ ውይይቶች እንዳሉ ሆነው፣ ለመመለስ የተሞከረባቸው የኃይል አግባብ ዩኒቨርሲቲዎች ሲከፈቱ ሊባባስ ይችላል የሚለው ሥጋት እንደ ወላጅ ብዙዎች ላይ ቢንፀባረቅም፣ ዩኒቨርሲቲዎች ነባር ተማሪዎች ወደየተቋማቸው እንዲገቡ የጊዜ ሰሌዳ አውጥተው (ከመስከረም 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በኋላ) ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ከዚህ ቀድሞ ከመምህራን፣ ከተማሪዎችና ከወላጆች (የመምህራን ተደርጓል) ከመማር ማስተማሩ ውጪ ደግሞ በማኅበረሰቡ ዘንድ ውይይት ተደርጎ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ ካልተሰጠ፣ መንግሥት በዩኒቨርሰቲዎች ማናቸውም ጥያቄ ቢነሳ በኃይል ሳይሆን በንግግር ለመፍታት ካልሠራ አስከፊ ውጤት ይገጥመናል የሚሉት ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡ ‹‹ሥጋቱ የተማሪ ወይም የወላጅ ብቻ ሳይሆን የእኛ የመምህራንም ነው፤›› የሚሉት መምህር፣ መንግሥት የፀጥታ ኃይል የመጠቀም አካሄዱን ማቆም አለበት፣ ችግሮች ከተከሰቱም በዩኒቨርሲቲው ማኅብረሰብ መፈታት ይችላሉ፣ ካለኝ ልምድ ችግሮች የሚባባሱት፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም፣ ወላጆችም ሆኑ መንግሥት ውጥረት ውስጥ የሚገቡት እዛው በጊቢው ሊያልቁ የሚችሉ ጉዳዮችን በፀጥታ ኃይል ለማርገብ ሲሞከር ነው፤›› ይላሉ፡፡

የተማሪ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ወይም ጥያቄ መጠየቅ ሳይሆን፣ የፀጥታ ኃይል ጣልቃ መግባት ግጭቶችን ያባብሳል፣ ጉዳዩ የማይመለከተው ሁሉ የችግሩ ሰለባ ይሆናል ሲሉም በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት ወቅት የገጠማቸውን ያስታውሳሉ፡፡

ወቅቱ ጾም ነበርና የሚጾሙ ተማሪዎች ቁርስና ምሳቸውን ውጭ ለተቸገሩ ተማሪዎች ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡ ይህ በዩኒቨርሲቲው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በመሆኑም ጥያቄ ያላቸው ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አካላት ጋር መወያየት ይጀምራሉ፡፡ በመሀል ግን የፀጥታ ኃይሎች ግቢ ደርሰዋል፡፡ ይህ ሲሆን ተማሪው ተቆጣ፡፡ በዚህም የፀጥታ ኃይሎች መማታት ጀመሩ፡፡ ከላይብረሪ ወጥተው ወደ ዶርም እየሄዱ የነበሩት የአሁኑ መምህርም በፀጥታ ኃይል መመታታቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጉዳዩ አይመለከተኝም ጥያቄ አቅራቢም አልነበርኩም፡፡ ጥያቄ ያቀረቡት መመታት አለባቸው የሚል አቋም ባይኖረኝም፣ ይህ የሚያሳየው በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ጥያቄ በፀጥታ ኃይል ከታጀበ፣ መምህር ሆነ ተማሪ፣ ጥፋት ያጠፉ ይሁን ያላጠፋ የሚለይበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ የተገኘው ሁሉ ተጎጂ ይሆናል፤›› ይላሉ፡፡

በዚሁ ዩኒቨርሲቲ መምህር ከሆኑ በኋላ፣ ግጭቶች ገጥሟቸው ባያውቅም በአምቦና በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በ2008 ዓ.ም. የተከሰተው እንደሚያበሳጫቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአካል ጉዳት ባያደርስብኝም ተማሪ ሲመታ፣ ሲሰቃይ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ከትምህርቱ ሲስተጓጎል መስማቱ የሥነ ልቦና ቀውስ አስከትሎብኛል፤›› ብለዋል፡፡

ሰሞኑን በአገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተካሄዱ የመምህራንና የመንግሥት ባለሥልጣናት ውይይት ላይ የተነሱ ሐሳቦች፣ ጠቃሚና ችግሮችን ለመፍታት፣ ሰላም ለማምጣት የጎላ ሚና እንዳላቸው አንዳንድ ምሁራን ሲገልጹ፣ አንዳንዶች ደግሞ ግዴታ ስለሆነባቸው ብቻ መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያነጋገርናቸው ምሁራንም፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ብጥብጥ ተነስቶ ብቻ ሳይሆን ምንም ነገር በሌለበት እንኳን በፖለቲካ አመለካከታቸው ወይም ጠያቂ በመሆናቸው ብቻ ሥጋት እንደሚያድርባቸው ነግረውናል፡፡ በተካሄደው የመምህራንና የመንግሥት ባለሥልጣናት ውይይት ላይ የተገኙትም፣ ከመንግሥት የሚደርስባቸውን አሉታዊ ጫና ለማስቀረት እንጂ፣ ፍላጎቱ ኖሯቸውና በሚሰነዘሩ አስተያየቶች ላይ መንግሥት አዎንታዊ ለውጥ ያመጣል ብለው አምነው እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

በየትኛውም የትምህርት እርከን በመማር ማስተማሩ ሒደት ውስጥ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪውና የመምህሩ፣ የተማሪው የመምህሩና የአስተዳደሩ ብሎም የመንግሥት የፖለቲካ አመለካከት አንድ የሚሆንባቸው ብሎም የሚለያይባቸው ጊዜያቶች አሉ፡፡ ልዩነት በሚኖርበት ጊዜ ልዩነትን ኃያሉ ሌላውን በማሸማቀቅ የሚፈታበት አካሄድ በአጠቃላይ የሚያሽመደምደው ማኅበረሰቡን ሲሆን፣ ወላጆችም በተቋማት ላይ አመኔታ፣ መምህራንና ተማሪዎችም መፈናፈኛ እንዲያጡ ያደርጋል፡፡

ከተወለደችበት ክልል ውጭ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት የምትከታተል ልጅ እንዳለቻቸው የሚገልጹት እናት፣ ልጃቸው ትምህርቱን መከታተሏን የማታቋርጥ ቢሆንም፣ በግላቸው በከተማው ፀጥታ ኃይሎች መግባታቸው ሥጋት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ማስተማር ግድ ነው ምርጫ የለም፡፡ የአገሪቷ ሰላም መጠበቅም ግድ ነው፤›› የሚሉ እናት፣ መንግሥት ጥያቄዎችን በውይይት መፍታት፣ መፍትሔዎቹን ወደ መሬት ማውረድ፣ አለበት፣ ቁልፉም ያለው መንግሥት ጋር ነው ይላሉ፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት በመከታተል ላይ የምትገኘው ተማሪ፣ በባህር ዳር አለመረጋጋትና አድማ በነበረበት በ2008 ዓ.ም. መገባደጃ፣ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የደረሰባቸው ጉዳት እንደሌለ፣ በከተማው ላይ ችግር ቢኖርም በግቢ ምግብ ከማጣትና የቢሮ ሠራተኞችን ካለማግኘት ባለፈ የጎላ ችግር እንዳልነበር በመግለጽ፣ ከመስከረም 18 በኋላ ለሚጀመረው ትምህርት ወደ ባህር ዳር ለመጓዝ መዘጋጀቷን ትገልጻለች፡፡ አባቷ ትምህርቱን እንድትተወው የመከራት ቢሆንም ግቢ ውስጥ የደኅንነት ሥጋት አይገጥመኝም የሚል እምነት እንዳላትና ችግር ከተፈጠረም ተማሪውም ሆነ ኅብረተሰቡ የሚደርስበትን ችግር አብራ እንደምትካፈል፣ ሆኖም ችግር ይፈጠራል የሚል ሥጋት ልቧ እንዳልገባ ትናገራለች፡፡

ምንም እንኳ በ2008 ዓ.ም. በአገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርቲዎች ችግር ባይከሰትም፣ በተከሰተባቸው ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች የነበረው ጥያቄን የመመለስ አግባብ አዎንታዊ አልነበረም፡፡ ዓመቱ ከሌሎቹ ሲነፃፀርም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተቃውሞ የነበረበት በመሆኑ ሥጋቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ተማሪዎችም የኅብረተቡ ነፀብራቅ ከመሆናቸው አንፃር፣ በማንኛውም ጊዜ የመልካም አስተዳደርም ሆነ የፖለቲካ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፡፡ ይህንን ያገናዘበ ምን ዓይነት ሥራ ተሠርቷል? የሚሉ ጥያቄዎችም ይነሳሉ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የጎላ ሥጋት እንደማይኖር፣ የመማር ማስተማሩ ሒደት ሰላማዊ እንዲሆንም ከዚህ ቀደም የነበረውን ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር የመወያያት ልምድ፣ አሁን ላይ ወላጆችን ጨምሮ እየሠራና በቀጣይም እንደሚሠራበት ይገልጻል፡፡

የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ጣፋ እንደሚሉት፣ የ2009 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተመለከተ ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሰላማዊና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ዋነኛው በመሆኑ፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሒደት እንዲረጋገጥ የተጀመሩና የተሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በአገሪቱ ከመልካም አስተዳደርና ከኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ጋር ተያይዞ እዛም እዚም የተፈጠሩ ችግሮች የተማሪው ቤተሰብ ላይ ሥጋትን እንደፈጠሩ መገንዘብ ይቻላል የሚሉት አቶ ወርቅነህ፣ ይህ ማለት ግን በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት  ተቋማት ችግር አለ ለማለት እንደማያስደፍር፣ ለችግሩ ሰለባ የሆኑት በጣት ከሚቆጠሩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም ቢሆን፣ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙና የባከኑ ጊዜያቶች ተካክሰው ትምህርቱ እንዲጠናቀቅ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

ተማሪ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲያነሳ ችግሮችን በውይይት መፍታት እየተቻለ ከዚሁ ጐን ለጐን የፀጥታ ኃይሎች እንዲገቡ ይደረጋል በማለት አስተያየት የሚሰጡ መኖራቸውን ተከትሎ፣ ለአቶ ወርቅነህ ላነሳነው ጥያቄ፣ ከመልካም አስተዳደር ችግሮች አንፃር በተለይ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር፣ ተማሪዎችም ጥያቄ አንስተው ወዳለመግባባትና ወደ አመፅ የተሸጋገሩበት ጊዜ አለመኖሩን ይናገራሉ፡፡ የሚፈለገውም ችግሮች በመግባባት እንዲፈቱ፣ ከምንም በላይ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበረሰብ ስለሰላም አስፈላጊነት መስማማት አለበት ብለዋል፡፡

የሚነሱ ጥያቄች፣ የፖለቲካ ልዩነትም ቢኖር አፋጣኝ የሆነ ምላሽ ከመስጠት አንፃር የሚሠራበት አካሄድ እንዳለ ሁሉ፣ በረዥምና በአጭር ጊዜ የሚፈቱ ጥያቄዎችም አሉ፡፡ የማይፈቱ ጥያቄዎች ቢኖሩ ተማሪዎችም፣ መምህሩና ሁሉም አካላት ስሜታዊ በመሆን ለውጥ እንደማይመጣ መስማማት  አለባቸው የሚሉት አቶ ወርቅነህ፣ የመማር ማስተማሩ ሒደት ሲናጋ መንግሥት ሕገ መንግሥት የማስከበር ሥልጣኑን እንደሚተገብር፣ የፀጥታ ኃይሎችም ትምህርት ተቋማት የሚገቡት ከተቋሙና ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ ችግር ሲኖር፣ በተቋማቱና በክልሉ ይሁኝታና ፈቃድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዙኃኑ ተማሪና መምህር ሳይሆን ጥቂት የመማር ማስተማሩን ሒደት የሚያደናቅፉ መኖራቸውን፣ እነዚህ ተነጥለው የሚወጡትም በማኅበረሰቡ ጭምር መሆኑንም ያክላሉ፡፡

ተማሪዎች ከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ወይም ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ ጥያቄ አንስተው ያውቃሉ? የሚል ጥያቄም አንስተን ነበር፡፡ እንደ አቶ ወርቅነህ፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር አልተፈጠረም፡፡ በ2008 ዓ.ም. ላይ በጣት የሚቆጠሩ ተቋማት ላይ ችግሮች ተከስተው፣ ከተማሪው፣ ከወላጅና ከማኅበረሰቡ ጋር በተደረገ ውይይት ተፈትተዋል፡፡ እንደ ትምህርት ሚኒስቴርም ችግሮች በውይይት የሚረግቡበት ላይ እየተሠራ ሲሆን፣ ከዚህ አልፎ ችግሮች መማር ማስተማሩን ካወኩ፣ የፌዴራል ወይም ክልል መንግሥታት ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ሰላማዊ መማር ማስተማሩን ከማረጋገጥ አንፃር ተማሪው በስሜት ሳይሆን በውይይት ተማምኖ ችግሮች እንዲፈቱ ከማድረግ አንፃር፣  ሰላማዊ የትግል ሥልት ላይ በየዓመቱ ሥልጠና እንደሚሰጥ፣ ሰላምን ለማረጋገጥም ዘንድሮ ላይ ወላጆች መካተታቸውን፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ውይይቶችም ለዘርፉ ሰላም አዎንታዊ ሚና እንደነበራቸውና ከዚህ  በኋላም ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

መምህራን በፖለቲካ አመለካከታቸው እንደሚፈረጁ በየዩኒቨርሲቲ የውይይት መድረኮች መንፀባረቃቸውን፣ ይህም ለመምህሩ ሥጋት መሆኑን በመጥቀስ፣ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ውስጥ ተማሪውም ሆነ መምህሩ የተለየ አቋምና የፖለቲካ አመለካከትን በማንፀባረቁ የማይገለልበት፣ መምህሩ የተለየ አቋሙን በማንፀባረቁ ከማስተማር የማይታጎልበት አጫዋች ሜዳ በዩኒቨርሲቲው ተፈጥሯል ወይ? የሚለውን በተመለከተም፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ውይይቶች የሚደረጉትም ነፃ ሐሳብን ለማንሸራሸር፣ ሕግ ካልተጣሰ በስተቀር ሰው በመናገሩና ሐሳቡን በመግለጹ የተወሰደበት ዕርምጃ እንደ እሳቸው አለመኖሩን ያምናሉ፡፡

ነገር ግን ሕጉን አጣመው የሚረዱና ከአፈጻጸም አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮች ሊስተዋሉ እንደሚችሉ፣ ይህ ግን አጠቃላይ ሥርዓቱን እንደማይወክል ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሰው ስለተናገረ፣ የተለየ አቋም ስላራመደ ብቻ ችግር ከደረሰበት እኛም የምንቃወመውና የምንታገለው ነው፤ እንዲህ ዓይነት ችግር ካለም ትምህርት ሚኒስቴር ያወግዘዋል፤ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚጋፋ፣ ሰላም የሚያደፈርስ ካልሆነ፣ መድረኮቹ የነፃ ሐሳብ ማንሸራሸሪያ ናቸው›› ብለዋል፡፡

በወላጆች፣ በመምህራንና በተማሪዎች ሥጋት አለ የሚለውን እንደ ትምህርት ሚኒስቴር አንቀበልም የሚሉት አቶ ወርቅነህ፣ ችግሮች በውይይት እየተፈቱ፣ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ስላልሆኑ፣ የተማሪዎች ደኅንነት እንዲጠበቅ እየተሠራ በመሆኑ፣ ወላጆችም ሆኑ ተማሪዎች ይህን ተገንዝበው ተማሪዎች በተሰጠው ጊዜ ሰሌዳ መሠረት ወደየዩኒቨርሲቲዎቻቸው እንዲገቡ መክረዋል፡፡

የ2008 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱት 246 ሺሕ 570 ተፈታኞች ውስጥ 50 በመቶዎቹ 350 እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ተማሪዎች ከ100 ሺሕ በላይ የሚሆኑት በመላ አገሪቱ የሚገኙ 35 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚመደቡ ናቸው፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...