የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የኢሬቻ በዓል ያለምንም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንዲከበር ጠየቀ፡፡ ኦፌኮ መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በተለይ የክረምቱ ዝናብ ወቅት አልፎ ወደ ብራ ሽግግር ሲደረግ፣ በአጠቃላይ በኩሽ ሕዝቦች በተለይ ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ዋቃ የሚመሰገንበት የኢሬቻ በዓል፣ ያለምንም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲከበር አበክሮ ጠይቋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ እምነት፣ ባህልና ታሪክ ለረዥም ዓመታት በተፅዕኖ ሥር ከቆየ በኋላ ዛሬም አስተማማኝነቱ ባይረጋገጥም በሕዝብ ልጆች መስዋዕትነት ወደነበረበት እየተመለሰ መሆኑን የኦፌኮ መግለጫ ያስረዳል፡፡
‹‹የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ አንድም ሃይማኖታዊ ነው፣ ሁለትም ባህላዊ ነው፡፡ ሃይማኖታዊውም ሆነ ባህላዊ አከባበሩ የዚያ የሚያራምደው ሕዝብ ታሪካዊ አንጡራ ሀብትና መገለጫ ነው፤›› ሲል ፓርቲው አስታውቋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ወደ መልካ (ወንዝ) ወርዶ፣ ወደ ቱሉ (ተራራ ወይም ኮረብታማ ቦታ) ወጥቶ ዋቃን እያመሰገነ የኢሬቻ በዓልን እንደሚያከብር፣ በአሁኑ ወቅት በተለይም የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ከስሙ ውጪ ባዕድ ስም እየተሰጠው ሲጣጣል ከቆየ በኋላ የበዓሉን ወግና ሥርዓት በያዘ ሁኔታ መከበር ቢጀምርም፣ ዛሬም ድረስ ራሳቸውን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በተለያየ ስም የጫኑና ለመጫን የሚፈልጉ ኃይሎች የበዓሉ አከባበር ከሚጠይቀው አግባብ ውጪ የተለያየ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ኦፌኮ ገልጿል፡፡
‹‹የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ፣ እንደዚያ ዓይነት ልብስ ልበሱ፣ እንደዚያ ዓይነት ጨርቅ ያዙ፣ እንደዚያ ዓይነት ምልክት አትያዙ እየተባለ የፖለቲካም ሆነ የግል ፍላጎታቸውን በሕዝብ ላይ ለመጫን እየሞከሩ ከመሆናቸውም በላይ፣ በሌላ በኩል እየቀጨጨ የነበረውን የዴሞክራሲ መካነ መቃብር ለመፈጸም እየተሞከረ ይገኛል፤›› ሲል ኦፌኮ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ከስሙ ውጪ ባዕድ ስም እየተሰጠው ሲጣጣል ከቆየ በኋላ የበዓሉን ወግና ሥርዓት በያዘ ሁኔታ መከበር ቢጀምርም፣ ዛሬም ድረስ ራሳቸውን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተለያየ ስም የጫኑና ለመጫን የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ፡፡ ኢሬቻ የባህልና የምሥጋና ቀን መሆኑ እየታወቀ የበዓሉ አከባበር ከሚጠይቀው ሥርዓት ውጪ በወንዝ መውረጃው መንገድ ላይ ኪነት ማስጨፈር፣ የፖለቲካ ንግግር ማድረግ፣ ያልተገቡ ድርጊቶች ናቸው፤›› በማለት ኦፌኮ በመግለጫው ይኮንናል፡፡
የ2009 ዓ.ም. የኢሬቻ በዓል ከምንጊዜው በላይ ሰላማዊና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት እንዲሆን ኦፌኮ ምኞቱን ገልጿል፡፡ ‹‹በ2008 ዓ.ም. እና ከዚያም ቀደም ባሉት ጊዜያት በኦሮሞ፣ በወልቃይት፣ በቅማንት፣ በኮንሶ፣ በጋምቤላ በተነሳው የመብትና የማንነት ጥያቄ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕዝብ ልጆች ሕይወት አልፏል፣ ታስረዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ተሰደዋል፤›› በማለት ኦፌኮ አስታውቋል፡፡
‹‹በዓሉን ለማክበር ከመላ አገሪቱ የሚመጡ ሰዎች በፀሎት፣ በመዝሙርና በዝምታ (ፅሞና) ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፤›› በማለት የሚገልጸው ኦፌኮ፣ ‹‹ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በስተቀር ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሊካሄዱ አይገባም፤›› ብሏል፡፡
የኢሬቻ በዓል የሕዝብ ባህልና ሃይማኖት በጣምራ የሚከበሩበት በመሆኑ፣ ማናቸውም የፖለቲካ ኃይሎች ከዋዜማው ጀምሮ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ ኦፌኮ በመግለጫው ጠይቋል፡፡