Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከ20 የሚበልጡ የአርበኞችና የከፍተኛ ሹማምንት ሐውልቶች ፈረሱ

ከ20 የሚበልጡ የአርበኞችና የከፍተኛ ሹማምንት ሐውልቶች ፈረሱ

ቀን:

በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቅጥር ጊቢ ውስጥ ከሚገኘው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞችና አገራቸውን በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ደረጃ ያገለገሉ ሹማምንቶች መካነ መቃብር ላይ ከቆሙት የተለያዩ ሐውልቶች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት ፈራረሱ፡፡ የእነዚህ ሐውልቶች የፈራረሱት፣ በአቅራቢያቸው የሚገኝ ዕድሜ ጠገብ የግራር ዛፍ ከስሩ ተገርስሶ በላያቸው ላይ በመውደቁ ነው፡፡

በነሐሴ 2008 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ከፈረሱት የመታሰቢያ ሐውልቶችና መካነ መቃብሮች መካከል፣ የቢትወደድ መንገሻ ውቤ፣ የደጃዝማቾች መንገሻ ጀምበሬ፣ በቀለ ወያ፣ ወርቁ አየለ፣ ደስታ እሸቴ፣ ዘውዴ ዳመን፣ ገብረመስቀል ኃይለ ማርያም፣ ተሾመ ሸንቁጥ፣ ተፈራ በላቸው፣ ሀብተሥላሴ በላይነህ፣ ታደመ ዘለቀ፣ የለጥይበሉ ገብሬ ይገኙበታል፡፡

ከዚህም ሌላ የፊታውራሪዎች አባተ ደርሶ፣ ተሰማ ረታ፣ ወልደፃድቅ ዘውዱ፣ እንዲሁም የልጅ አጥናፉ ሽፈራው፣ የሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሌ (ሰውየው)፣ ከብርጋዴር ጄኔራሎች ቶላ በዳኔ፣ ኃይለማርያም ግዛቸው ዓለማየሁ ጎሹ፣ የልጅ አጥናፉ ሽፈራው፣ የሻለቃ ኃይለሥላሴ በላይነህ፣ የሻምበል ደረጀ ኃይለ ማርያም፣ ከንቲባ አበራ ኃይለሥላሴ፣ የአቶ መኮንን ሀብተወልድ፣ የአቶ ስዩም በቀለ፣ የአቶ አፈወርቅ አዳፍሬ ሐውልት ከፈረሱት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከእነዚህም መካከል የአቶ መኮንን ሀብተወልድ ቤተሰቦች የአባታቸውን ሐውልት እንደገና ለማስተካከል፣ አካባቢውን ለማፅዳት፣ እንዲሁም በዛፉ ኃይል ፈራርሰው የወዳደቁትን ሌሎች ሐውልቶችን በማንሳት በየመቃብሩ ላይ ለማኖር ጥረት ከማድረጋቸው ውጭ ማንም አካል ዞር ብሎ እንዳላየው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ካናዳ የሚኖሩት የብርጋዴር ጄኔራል ቶላ በዳኔ ልጅ ወይዘሮ እናት ቶላ የአባታቸው መቃብር ላይ ያለው ሐውልት መፍረሱን ማየታቸውን፣ ለማስጠገን ሐሳብ እንደነበራቸውና የተሰጣቸው የአጭር ጊዜ ፈቃድ በማለቁ ሐሳባቸውን ተግባራዊ ሳያደርጉ እንደተመለሱ፣ አሁንም ከሌሎች ወገኖች ጋር በመቀናጀት አካባቢውን ፅዱና ውብ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

መምህር ሰለሞን በቀለ የቅድስት ሥላሴ የካቴድራል ዋና ጸሐፊን ስለዚሁ ጉዳይ አነጋግረናቸው ነበር፡፡ እንደ ጸሐፊው ዛፎቹ ለካቴድራሉ ውበት፣ ፀሎት ለማድረስ እጅግ በጣም ተስማሚና ምቹ ናቸው፡፡ ዕድሜ ጠገብ እንደመሆናቸው መጠን እንክብካቤም ይፈልጋሉ፡፡ የቀብር ሒደት የሚፈጸመው ደግሞ አጠገባቸው ወይም በመካከላቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ስሮች እንደሚነካኩ፣ ሥራቸው የተነካካ ዛፎች ደግሞ ኃይለኛ ነፋስ በሚነፍስበት ጊዜ በተለይ በክረምት ወራት ራሳቸው ሊወድቁና በዚህም ሳቢያ በአቅራቢያቸው ያሉት ሐውልቶችን እንደሚያፈራርሱ አስረድተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት አደጋው የተከሰተው ካቴድራሉ ለራሱ ጥቅም ሲል ዛፉን ሲያስቆርጥ ከሆነ ለደረሰው ጉዳትም ሆነ ጥፋት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ‹‹የተከሰተው ግን ይህ ሳይሆን በተፈጥሮ ወይም በወቅቱ በተነሳው ኃይለኛ ነፋስ ሳቢያ የዛፉ ከስሩ ተገርስሶ መውደቅ ነው›› የሚሉት ጸሐፊው፣ ይህም ሆኖ ግን የሐውልቱ ባለቤቶችና ጉዳዩ የሚመለከተው አካላት የፈራረሱትን ሐውልቶች መልሶ ለመተካትና አካባቢውን ውብና ጽዱ ለማድረግ ከተንቀሳቀሱ ካቴድራሉ ደግሞ የአቅሙን ያህል አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ሰማዕታት የፈጸሙት ተጋድሎ ለትውልድም አስተማሪ ሆኖ እንዲቀጥል፣ የውጭ አገር ጎብኚዎችም እንዲያዩትና እንዲመለከቱት ለማድረግ ቦታው ፅዱ፣ አረንጓዴና ውበቱ የተጠበቀ ሊሆን እንደሚገባ፣ በየዓመቱ ቢያንስ ከሁለት ሺሕ በላይ የሚሆኑ የውጭ አገር ጎብኚዎች ካቴድራሉን እንደሚጎበኙ፣ አብዛኞቹም በውስጡ ያሉትን ቅርሶች እንደሚመለከቱ መቃብሮቹን የሚያዩት ግን እግረ መንገዳቸውንና አስጎብኚው ሲጋብዛቸው እንደሆነ መምህር ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ከሟች ቤተሰቦችና ከካቴድራሉ ጋር በመሆን የጥገናውንና የማስዋቡን ሥራ አቅም በፈቀደ መጠን ለማከናወን ማኅበሩ ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...