Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የመንግሥት ድርጅቶች የሙስና መፈልፈያዎች ናቸው ብለን እናምናለን››

ሮበርትስ ኤም. ጀምስ፣ የሔሪቴጅ ፋውንዴሽን የኢኮኖሚ ባለሙያና ተመራማሪ

ጀምስ ኤም. ሮበርትስ ከአርባ ዓመታት በላይ ባስቆጠረውና በአሜሪካ በሚገኘው ሔሪቴጅ ፋውንዴሽን የኢኮኖሚ ባለሙያ በመሆን በምርምር ሥራዎች እያገለገሉ የሚገኙ ምሁር ናቸው፡፡ ሔሪቴጅ ፋንዴሽንን ከመቀላቀላቸው ቀድሞ ከ25 ዓመታት በላይ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አገልግለዋል፡፡ ሔሪቴጅ ፋውንዴሽን ቀኝ ዘመም ሲሆን፣ የሪፐብሊካን ፓርቲን በመደገፍና ጽንፈኛ የሊበራሊዝም መርሆዎች በማራመድም ይታወቃል፡፡ ሔሪቴጅ ፋውንዴሽን በየዓመቱ የአገሮችን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመተንተን፣ የሚከተሉት ፖሊሲ በገበያ የሚመራ መሆን አለመሆኑን ያጠናል፡፡ በዚህም መሠረት አገሮች በነፃ ገበያ መርህ መሠረት ኢኮኖሚያቸው የሚመራበት ፖሊሲ ምን ያህል የካፒታሊስት ሥርዓትን በመከተል ውጤታማ መሆን እንደቻለና ምን ያህል ዝግ እንደሆነ በመፈረጅ ለአገሮች ደረጃ ያወጣል፡፡ ሔሪቴጅ ፋውንዴሽን በየዓመቱ የሚያወጣው ሪፖርት የኢኮኖሚ ነፃነት መመዘኛ ወይም ኢኮኖሚክ ፍሪደም ኢንዴክስ የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን፣ በዚህ ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ በአብዛኛው የኢኮኖሚ ነፃነት ካልሰፈነባቸው አገሮች ተርታ ተፈርጃለች፡፡ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት ሮበርትስ፣ መመዘኛው እንዴት አገሮችን እንደሚፈርጅ አብራርተዋል፡፡ ከሙስና፣ ከፍርድ ቤቶች ነፃነት፣ ከንብረት ባለቤትነት መብት መከበር አኳያ አገሮች የሕግ የበላይነትን የሚያሰፍኑበት፣ የመንግሥት የፊሲካል ነፃነትንና ወጪን በሚመለከተው የመንግሥት አቅም ላይ የተመሠረቱ መመዘኛ መሥፈርቶችን በማስቀመጥ አገሮችን ነፃነት የሰፈነባቸው መሆን አለመሆናቸውን እየተነተነ ይተቻል፡፡ ሌሎችም መመዘኛዎችን ያካተተው የሔሪቴጅ ፋውንዴሽን ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን በአብዛኛው የኢኮኖሚ ነፃነት ከሌላቸው አገሮች ተርታ አስቀምጧታል፡፡ ከ100 ነጥብ 51.5 በመቶ ያገኘችው ኢትዮጵያ፣ በመንግሥት ጫናና ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ተቋማት ያስከተሉትን ተፅዕኖ፣ መንግሥት ወሳኝ የሚላቸው የኢኮኖሚ አውታሮች ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት አለመደረጋቸውና ሌሎችም ተመዝነው አገሪቱ ነፃነት የሌላት እንድትባል ማድረጉን ሮበርትስ ይተነትናሉ፡፡ ብርሃኑ ፈቃደ ከኢኮኖሚ ባለሙያውና ተመራማሪው ጀምስ ሮበርትስ ጋር ያደረው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ለመጀመር ያህል ወደ አዲስ አበባ ያመጣዎ ምክንያት ምን ነበር?

ሮበርትስ፡- ሔሪቴጅ ፋውንዴሽን አልፎ አልፎ በሚሰጠው ዕድል ወደ ተወሰኑ አገሮች በመሄድ ዓመታዊውን የኢኮኖሚ ነፃነት መመዘኛ ሪፖርት እናስተዋውቃለን፡፡ እዚህ የመጣሁትም ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የገበያ መር ሪፎርሞችንና ለውጦችን የሚደግፉ ሰዎች ሲኖሩ ስለምናራምዳቸው አስተሳሰቦች ለማካፈልና የገበያ መር አስተሳሰቦችን እንዲገነዘቡ ለመደገፍ እንጥራለን፡፡ ዓመታዊው የኢኮኖሚ ነፃነት መመዘኛ ጠቋሚዎችን የሚያብራራው ሪፖርት በየዓመቱ ከዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ጋር በመሆን የሚዘጋጅ ሲሆን፣ በአብዛኛው ነፃ ገበያን ማዕከል ያደረጉ እሴቶቻችንንና ዴሞክራሲን የምናንፀባርቅበት ሪፖርት ነው፡፡ ይህ ሲባልም አገሮችን አስቀድመን አንፈርጅበትም፡፡ ይሁንና ከኮሙዩኒዝም ውድቀት በኋላ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ስምምነት የተደረሰበት ይኸው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መርህ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ይህ ጉዳይ ወደዚህ የመጡበት ተልዕኮ አካል ነው ማለት ነው?

ሮበርትስ፡- ወደ አፍሪካ አገሮች በማደርገው ጉዞ መካከል እግረ መንገዴን በአዲስ አበባ ለማለፍ ነው የመጣሁት፡፡ እንደ አዲስ የተቋቋመው የአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት ሰዎችን ለማነጋገር በማሰብ ነበር የመጣሁት፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ኢትዮጵያውያንና አሜሪካውያን አባላትን ያቀፈ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከተቋሙ ሰዎች ጋር እነጋገራለሁ፡፡ በኢኮኖሚክስ መስክ ፍላጎቱ ያላቸው የሲቪል ማኅበራት ካሉም እነሱንም ለማነጋገር እፈልጋለሁ፡፡ ይኸው ነው፡፡ የምናወጣው ሪፖርት ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለውና በጥሩ መረጃዎች የተደራጀና ለዓመታት የቆየ ነው፡፡ በመሆኑም የመጣሁት ይህ ሪፖርት በየጊዜው እየወጣ እንደሚገኝ ለማሳወቅ ጭምር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢኮኖሚ ነፃነት ሪፖርቱ የሚጠቅሳቸው ምዘናዎችን ከማየታችን በፊት፣ የኢኮኖሚ ነፃነት የሚገለጽባቸው ዋና ዋና መርሆዎችን ምን እንደሆኑ ቢገልጹልን?

ሮበርትስ፡- በአራት ዋና ዋና የመመዘኛ ነጥቦች ላይ የሚመረኮዙ ናቸው፡፡ አንደኛው የሕግ የበላይነት ሲሆን ይህም የፍትሕ ሥርዓቱን፣ የንብረት ባለቤትነት መብት መከበርን፣ የመንግሥት ሙስናን የመዋጋት አቅምን የሚመለለከቱ ናቸው፡፡ በሪፖርታችን መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት ያለው አቅም ምን ያህን እንደሆነ እንዳስሳለን፡፡ ሁለተኛው መሠረታዊ መመዘኛ የመንግሥትን የፊስካልና የወጪ አቅም የሚመለከተው ነው፡፡ መንግሥት ምን ያህል ታክስ ይሰበስባል? ምን ያህል ወጪ ያደርጋል? የሚሉት ጉዳዮች በዚህ መመዘኛ መሠረት የሚቃኙ ናቸው፡፡ ሦስተኛው መመዘኛ ኢኮኖሚው እንዴት እንደሚተዳደር ለማሳየት የሚሞክር ሲሆን፣ በአራተኛነት የሚቀመጠው ደግሞ የኢኮኖሚው ለዓለም ገበያ ክፍት መሆን፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እንዲሁም ባንኮች ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ እነዚህን መመዘኛዎች ለመተንተን ዓለም አቀፍ አኃዛዊ መረጃዎችን እንጠቀማለን፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥታት በገዛ ፈቃዳቸው የሚያካሂዷቸው ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እያሉ፣ ሪፖርቱ የሚያቀርባቸው የኢኮኖሚ ነፃነት መለኪያዎች መቀመጣቸው ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ሮበርትስ፡- እርግጥ የሪፎርም ሥራዎችን ማካሄድ የመንግሥታት የግል ፍላጎት ላይ የሚወሰን ነው፡፡ ሪፎርም ማካሄድ ካልፈለጉም መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን የበለፀገች፣ ነፃና የተረጋጋች ዓለምን ማየት የአሜሪካ ፍላጎት በመሆኑ አንዱም እንዲህ ያለው ገበያ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ሪፎርም እንዲኖር ስለሚፈለግ ነው ሪፖርቱ የሚዘጋጀው፡፡ እኛ የምናከናውናቸው ነገሮችም ሁኔታዎች ይበልጥ የተሻለ ለማድረግ የታለሙ ናቸው፡፡ እንደ አሜሪካ ምሁራን ስብስብ ለምናከናውናቸው ተግባራት እገዛ የሚያደርጉልን አካላት አሉ፡፡ ከመንግሥት ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ ሳይደረግልን ገለልተኛ ተቋም እየመራን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን በገንዘብ የሚደግፉን ሰዎች ደኅንነቷ የተጠበቀና ብልፅግና የሞላባት ዓለምን ማየት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ብሄራዊ ደኅንነትም እንዲሁ ጠንካራ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ እንዲህ ያለው ጥረትም የዚያ ፍላጎት አካል ነው፡፡ ይሁንና ሪፎርም ማካሄድም ሆነ ለውጥ ማምጣት የየአገሮቹ ተግባር ነው፡፡ እኛ የምናደርገው አገሮች የሚከተሏቸውን ፖሊሲዎች በመመልከት የት እንደሚያደርሷቸው ማጥናት ነው፡፡ በተለይም ከሶቪዬት ኅብረት መፈራረስ በኋላ አገሮች ያከናወኗቸው መልካም ለውጦች በጥሩ ጎን የሚታዩ ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከኢኮኖሚ ነፃነት መመዘኛዎቹ ጋር በተያያዘ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን እንመልከት፡፡ ምንም እንኳ ጥሩ የኢኮኖሚ ለውጥ ቢያሳዩም በእናንተ ሪፖርት መሠረት እንደ ኢትዮጵያ ያሉት አገሮች ያስመዘገቡት ውጤት እጅግ ደካማ ነው፡፡ ከዚህ ጎን የሠራተኛ መብቶች፣ የሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች በሪፖርቱ እንዴት ተቃኝተዋል?

ሮበርትስ፡- የሪፖርቱ ግብ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ማተኮር አይደለም፡፡ እርግጥ በሪፖርቱ በተወሰነ ደረጃ ይጠቃቀሳሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ፍሪደም ሐውስ ዴምክራሲ የተባሉ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን በተናጠል ይከታተላሉ፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናልም እንዲህ ያለውን ነገር በመከታተል ይታወቃል፡፡ በቅርቡም ሙስና የተስፋፋባቸውን አገሮች በሚመለከት በድረ ገጹ መግለጫዎችን አውጥቷል፡፡ ሙስና ከሰብዓዊ መብቶች ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ይሁንና የእኛ ዋናው መልዕክት ግን ይሄ አይደለም፡፡ ዋና መልዕክታችን አገሮች ሚዛናዊ ፖሊሲዎችን መከተላቸው በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መጥፎ ታሪክ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ይረዳቸዋል የሚል ነው፡፡ እያደገ ያለ ኢኮኖሚ አላችሁ፡፡ ብዙ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና ሰዎችን ደስተኛ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚዎች አሏችሁ፡፡ ሰዎች የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓትና ጥሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ሰዎች ይሻሉ፡፡ እነዚህ ላይ ነው ሪፖርቱም ትኩረቱን የሚያደርገው፡፡

ሪፖርተር፡- በሪፖርቱ በተቃኙት መመዘኛዎች መሠረት አገሮች እንዴት ነው የሚደለደሉት?

ሮበርትስ፡- ስድስት ምድቦች አሉን፡፡ በመጀመሪያውና በከፍተኛው ረድፍ የተቀመጡት ስድስት አገሮች ብቻ ሲሆኑ፣ እነዚህም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ነፃነት የሰፈነባቸው ናቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህ አገሮች በመመዘኛዎቹ አኃዞች መሠረት ከ100 ነጥብ ውስጥ ከ80 በላይ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ቀጥለው የሚቀመጡት በአብዛኛው ነፃ ኢኮኖሚ የገነቡ አገሮች ሲሆኑ፣ አሜሪካም ከእነዚህ አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ ወደዚህ ምድብ የወረደችው መንግሥት ከሚያገኘው ገቢ በላይ ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ የመንግሥት ወጪ በጉድለት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሌሎችም ጉዳዮች አገሪቱ ዝቅተኛ ውጤት ለማስመዝገቧ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው በተወሰነ ደረጃ የኢኮኖሚ ነፃነት የሚታይባቸው አገሮች የሚደለደሉበት ምድብ ነው፡፡ በአብዛኛው ነፃ ያልሆነ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች የሚገኙበት ድልድልና ከፍተኛ ቁጥጥር የሚያደርጉና የተጨቆነ ኢኮኖሚ የሚያራምዱ አገሮችም የመጨረሻው ረድፍ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ እያንዳንዱ ምድብ የራሱ የሆኑ ባህርያት ያሉት ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው በሚረዳው መንገድ የቀረቡ መመዘኛዎች ተቀምጠውላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በተጨቆኑ ኢኖሚዎች ተርታ የሚመደቡ አገሮች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ አገሮች በአንፃራዊነት የተሻለ ነፃነት ባለውና ከዚያም በሚሻለው ምድብ ውስጥ ለመቀመጥ በመሠረታዊነት ምን እንዲያደርጉ ይመከራሉ?

ሮበርትስ፡- እንደማስበው በሕግ የበላይነት ላይ ማተኮሩ ጠቃሚና የሚመከር ነው፡፡ ከፖለቲካ መረጋጋት ጋር የሚያያዝ በመሆኑም በዚህ መመዘኛ ላይ ማተኮሩ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ያልተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታ ባለበት ጥንካራ ኢኮኖሚ መፍጠር ከባድ ይሆናል፡፡ ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነቡ ነገር ግን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የሰፈነባቸው አገሮች አሉ፡፡ በዚህ ላይ መከራከር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን በተረጋጋ መንፈስ ማከናወን የሚችሉበትና ወጥተው የሚገቡበት ሁኔታ ካልተፈጠረ፣ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት አዳጋሽ ስለሚሆን የሕግ የበላይነት ቁጥር አንድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን የሚታው በዚህ አገር ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች የሚኖራቸው በራስ መተማመን ነው፡፡ ስለዚህም ይህ በተወሰነ መልኩ ለዓለም የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች በርን ክፍት ከማድረግ ጋርም ይያያዛል፡፡

ሪፖርተር፡- ሪፖርቱ ኢትዮጵያን በተመለከተ እንደሚያስቀምጠው እንደ ኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ነፃነት ባሉት ሁለት መስኮች አገሪቱ በእያንዳንዳቸው ከ100 ያስመዘገበችው 20 ነጥብ ብቻ ነው፡፡ ይህ ምንን ያመላክታል?

ሮበርትስ፡- የሚያመላክተው መንግሥት ከዓለም ሁኔታዎች በተቃረነ አኳኋን በእነዚህ መስኮች ላይ የራሱን ውሳኔ ማሳለፉን ነው፡፡ ለአጭር ጊዜም ቢሆን እነዚህ ዘርፎች ዝግ መደረግ እንዳለባቸው ወስነዋል፡፡ ይህንን ስላደረጉ ልወቅሳቸው አልችልም፡፡ ይሁንና አገሪቱ ያሳየቻቸው ውጤቶች ከተፎካካሪዎቿ አኳያ ሲታዩ ዝቅተኛ መሆናቸውን ለማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ በኢንቨስትመንት መስክ ስላለው የግልጽነት ጥያቄ፣ በመሬት ባለቤትነት፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በፍርድ ቤቶች የመዳኘት ብቃቷ በዓለም መድረክ ላይ አገሪቱ ጉድለቶችና ድክመቶች ያሉባት ሆና እንድትታይ ያደርጓታል፡፡ ስለባንክ ኢንዱስትሪውም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ የውጭ ባንኮች እዚህ የማይንቀሳቀሱ ከሆነ የካፒታል አቅርቦት ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የባንክ ኢንዱስትሪው ከተነሳ፣ ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ መንግሥት የአገር ውስጥ ባንኮችን አቅም ሳልገነባ የውጭ ባንኮችን አላስገባም ማለቱን እንዴት ይመለከቱታል? ተዓማኒነት ያለው መከራከሪያ ነው ሊባል ይችላል?

ሮበርትስ፡- ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ከሚለው አባባል ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ይህም የባንክ ሥራን የሚመለከቱ ሶፍትዌሮች፣ እንደ ካፒታል የሚቆጠር የሰው ኃይል እንዲሁም ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ዓለም አቀፍ ንብረቶችን የውጭ ባንኮች ይዘው ቢመጡ ምርጥ የዓለም ተሞክሯቸውን ጭምር ይዘው ስለሚመጡ የአገር ውስጥ ባንኮችንም ለማጎልበት ያስችላሉ፡፡ በመሆኑም የመንግሥትን አቋም ባከብርም አልስማማበትም፡፡ እዚህ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ከነበራቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች የሰማሁትም ተመሳሳይነት ያለው ነገር ነው፡፡ በአግሮ ኢንዱስትሪ መስክ ለመሰማራት ይፈልጉ የነበሩት ኩባንያዎች ሲመጡ መንግሥት ቀድማችሁ ኢንዱስትሪዎችን ገንቡ ብሏቸዋል፡፡ ኩባንያዎቹ በበኩላቸው ቀድመን ገበያውን እንፍጠር፣ ምርቶቻችንን ተፈላጊ ለማድረግ ብራንዶቻችንን ቀድመን ማስተዋወቅ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ ይሁንና መንግሥት ቀድማችሁ ኢንቨስት አድርጉና ገበያውን ኋላ ትፈጥሩታላችሁ በማለቱ ሊስማሙ አልቻሉም፡፡ በቀላሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ለመተካት ይፈልጉ ነበር፡፡ መንግሥት የአቅርቦት ሰንሰለትና ሥርጭት፣ እንዲሁም የማቀዝቀዣ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ማስጠበቅ አለበት፡፡ ይህ መሟላቱን ከተመለከቱ በኋላ ኩባንዎቹ የመምጣትና ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንደነበራቸው አስታውቀው ነበር፡፡ መንግሥት ግን ቀድሞ ገንዘቡ እንዲመጣ ፈለገ፡፡ ይህ እንግዲህ ፍላጎት ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ አስተሳሰብ ነው፡፡ ኢንቨስተሮቹ እንዲሁ ገንዘባቸውን ማውጣትና ሥጋት ላይ መውደቅ አይፈልጉም፡፡ በተጠና አካሄድ ገንዘባቸውን መልሰው ማግኘት በሚችሉባቸው መስኮች ላይ ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ደህና ልምድና አቅሙ ያላቸው የውጭ ባንኮች እዚህ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ የአገር ባንኮች እንዲዋጡ ማድረግ ነው የሚለው ምን ያህል የሚያሰጋ አገላለጽ ነው?

ሮበርትስ፡- እንደምገምተው ይህ በጣሙን የተሳሳተ አባባል ነው፡፡ እውነታው የአገር ውስጥ ባንኮች ደንበኞቻቸውን በሚገባ የሚያውቁ በመሆናቸው ከውጮቹ ይልቅ ከደንበኞቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር ችለዋል፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮች የሚንቀሳቀሱባቸው መስኮች ከውጮቹ የተለዩ ናቸው፡፡ የውጮቹ ለትልልቅና ለዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች ፋይናንስ ማቅረብ ላይ ያተኩራሉ፡፡ በአንፃሩ የአገር ውስጥ ባንኮች ደንበኞች በአብዛኛው በአገር ውስጥ የተወሰኑ ስለሚሆኑ ከውጭ ባንኮች የሚቃጣባቸው ውድድር ይኖራል ለማለት ይቸግረኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የመንግሥት ድርጅቶች ከግሎቹ ይልቅ ጠንካራ ሆነው ይታያሉ፡፡ የመንግሥት ድርጅቶች ከግሎቹ ይልቅ ባላቸው ሚና ላይ ሪፖርቱ የሚለው ነገር አለ?

ሮበርትስ፡- በመንግሥት የሚተዳደሩ ድርጅቶችን በሚመለከት የምናራምደው አቋም የተለየ ነው፡፡ የመንግሥት ድርጅቶች የሙስና መፈልፈያዎች፣ የብቃት ችግር የተንሰራፋባቸው፣ በሥልጣን በመጠቀም የግል ፍላጎትና ተጠቃሚነትን የሚያስፋፉ፣ እንዲሁም ከለላን የሚያበረታቱና ሌሎችም መጥፎ መገለጫዎች የሚታዩባቸው ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ እነዚህ ተቋማት የኤክስፖርት ብድርና ሌሎችንም የሚያስፋፉ ናቸው፡፡ የንግድ መዛባትን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ንግድን ከመፍጠር ይልቅ ፍሰቱን የሚቀለብሱ ተቋማት ናቸው፡፡ ቻይኖች በዚህ ረገድ በእጅጉ ተጠያቂ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የአሜሪካ ኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ (ኤግዚም ባንክ)ን በይፋ እንቃወማለን፡፡ በዚህ መንገድ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለን አናምንም፡፡ ሆኖም በርካታ አገሮች በዚህ አኳኋን እንደሚሠሩ እንገነዘባለን፡፡ በአሜሪካ በመንግሥት እጅ የሚተዳደሩ ድርጅቶች አሉን፡፡ የተወሰነ ዓላማን ለማሳካት ይጠቅሙ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ወደ ግል ይዞታነት ተዛውረው ይበልጥ መስፋፋት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ግን የግሉ ዘርፍ በሚያቅማማባቸው መስኮች እየገባና ኢንቨስት እያደረገ ቀስ በቀስ ለግሉ ዘርፍ አስረክቦ እንደሚወጣ ይገልጻል፡፡ ይህ ከኢኮኖሚ ነፃነት መመዘኛው አኳያ እንዴት ይታያል?

ሮበርትስ፡- በላቲን አሜሪካ በርካታ ሥራዎችን አከናውኛለሁ፡፡ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ መተካት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ብዙም የሚበረታታ አይደለም፡፡ እንደሚታሰበው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ እንዲያውም ለኢኮኖሚ ዕድገት መገታትና ለከለላ መስፋፋት መንስዔ ሆኗል፡፡ ዝቅተኛ የምርት ውጤት በዘላቂነት እንዲኖር አስገድዷል፡፡ በመሆኑም በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ ሰዎች ደግመው እንዲያስቡ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ከገጠማት አስከፊ ሁኔታ ያልተናነሰ ችግር ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ መንግሥት ለሕዝቡ ደመወዝ የሚከፍል ይመስለዋል፡፡ ሰዎች እየሠሩና ምርት እያመረቱ ያሉ ይመስላቸዋል፡፡ እውነታው ግን ማንም የማይፈልገውን ቀሽም ምርት ማምረታቸው ነው፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ እንተካለን የሚሉ መንግሥታት የተወሰኑ ዘርፎችን አጥረው ያስቀምጣሉ፡፡ ይህም የግሉን ዘርፍ ከጨዋታ ውጪ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮች የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰቦችን ከእስያ አገሮች በመቅዳት ለመንቀሳቀስ እየሞከሩ ነው፡፡ ይሁንና ግን ከእስያዎቹ ይልቅ አፍሪካውያኑ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ነፃነት እንደሚታይባቸው ሪፖርታችሁ ያሳያል፡፡ ስለልማታዊ መንግሥት ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

ሮበርትስ፡- በአፍሪካውያንና በእስያ አናብርት (ኤሽያን ታይገርስ) ሞዴል መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት በውጭ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ መሆን ነው፡፡ አፍሪካውያን በለጋሾች ድጋፍ ላይ ተመሥርተዋል፡፡ እስያውያኑ ግን ይህን ዓይነት ድጋፍ አላገኙም፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው ለማንሳት ችለዋል፡፡ ይህ በእስያና በአፍሪካ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት ይመስለኛል፡፡ ከሃምሳ ዓመት በፊት የነበረችው ኮሪያ ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ትገኝ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ከፍታው ላይ ትገኛለች፡፡ በገበያ የሚመራ፣ በግሉ ዘርፍ ባለቤትነት የሚተዳደርና ጥሩ ሲያመርትም ማበረታቻ የሚገኝበት ሥርዓት መፍጠር ችለዋል፡፡ የተከተሉት ሞዴል ላይ የማንስማማባቸው ነጥቦች ግን መኖራቸው አልቀረም፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመገንባት ለግሉ ዘርፍ እንደ ማበረታቻ ፓኬጅ እያዋለ ነው፡፡ በእነዚህ ፓርኮች አማካይነት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም እየሞከረ ነው፡፡

ሮበርትስ፡- ይህ በኢትዮጵያ ሁኔታ እንዴት እየተሠራበት እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔ ስላልተመለከትኩ ምናልባት ጥያቄው ለመንግሥት ቢቀርብ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ይሁንና  እንዲህ ያሉ ነገሮች ስላመጡት ውጤት የሚያሳየኝ ባገኝ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ከአሜሪካ ኩባንያዎች መረዳት እንደቻልኩት ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸውን አንስተዋል፡፡ አሜሪካን ጨምሮ ሁሉም መንግሥታት ማለት ይቻላል የታክስ ማበረታቻና ሌላም ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ እኛ ግን በጠቅላላው አንደግፈውም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ፒቪኤች ያሉ አሜሪካ ኩባንያዎች ግን እዚህ መጥው ለመሥራት እየተዘጋጁ ነው፡፡ ምንም እንኳ በእናንተ ሪፖርት ዝቅተኛ ነጥብ ቢያስመዘግብም፣ መንግሥት የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ የሚያስችል ማበረታቻ እየሰጠ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡

ሮበርትስ፡- እንደገለጽኩት እንዲህ ያለውን አካሄድ በውጤቱ መዳኘት እፈልጋለሁ፡፡ ሆን ተብሎ በመንግሥት የሚመራ የንግድ ዘርፍ ከተፈጠረ፣ የገበያ ድርሻን ለማግኘት ሲባል ከለላ የሚሰጥ ከሆነ፣ አብዛኛውን ኢኮኖሚ ክፍል ተጠቃሚ አያደርግም፡፡ እርግጥ ለኩባንያው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደምረዳው ከሆነ የአገራችሁ ቴሌኮም ኢንዱስትሪ በርካታ ተወዳዳሪዎች እንዲገቡበት ቢደረግ ብዙ ኢንቨስትመንት ባመጣ ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት ከእጁ እንዲወጣ አይፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ኢኮኖሚያቸው ለውጭ ውድድር ክፍት ሆኖ ገበያ እንዲመራው ለማድረግ፣ እ.ኤ.አ. በ2008 የተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ ፍርኃት ፈጥሮባቸዋል ቢባል ፍትሐዊ አይሆንም?

ሮበርትስ፡- በእኔ አመለካከት እንዲያውም ተቃራኒው ነው እውነቱ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ ስምምነት በተደረሰበትና የዋሽንግተን ʻኮንሰንሰስʼ እየተባለ በሚጠራው የሪፎርም ፕሮግራም መሠረት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ያካሄዱ አገሮች ካደጉት አገሮች ይልቅ የፋይናንስ ቀውሱን በተሻለ ሁኔታ ተቋቁመውታል፡፡ ቀውሱ ያደጉትን እንጂ በማደግ ላይ ያሉትን ያን ያህል አልጎዳቸውም፡፡ ይህ የግሌ አመለካከት ነው፡፡ ይሁንና ይህ ከድርጊት የራቀ መከራከሪያ ነው፡፡ እንደ ቶማስ ቤክሌ ያሉ የኒዮ ማርክሲስት አቀንቃኞች እንደሚሉት ሳይሆን የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ አልወደቀም፡፡ ነገር ግን በምልዓት ሳይተረጎምና ተግባር ላይ ሳይውል ቀርቷል፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚ መስክ በጥልቀት ሥራ ላይ አልዋሉም፡፡ ክፍያዎችን ማስተናገድ፣ ሒሳብ መዝጋት ላይ በማተኮር በፌዴራል መጠባበቂያ፣ በአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክና በመሳሰሉት ላይ ተገድበዋል፡፡ ይህ በቂ አልነበረም፡፡ ሁለተኛ ዙር የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ እንዲኖርና የሪፎርም ሥራዎችም በአግባቡ እንዲከናወኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የብሬተን ውድ ተቋማት እየተባሉ የሚጠቀሱት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት የመዋቅራዊ ለውጥ ማስተካከያ ፕሮግራም የሚባለውን የፖሊሲ አቅጣጫ አገሮች እንዲከተሉ ማድረጋቸውና እሱንም ተከትሎ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ሲተቹ ኖረዋል፡፡ ከአርባ ዓመታት በላይ ስትንቀሳቀሱ እንደ መቆየታችሁ የሚቀርቡባችሁ ትችቶች ምንድን ናቸው?

ሮበርትስ፡- የምናቀርባቸው የፖሊሲ ምክሮች ምናልባት በፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን አገዛዝ ወቅት ቢሆን ኑሮ የተሻሉ ይሆኑ ነበር የሚሉን ይኖራሉ፡፡ አሁን ግን ነገሮች ተቀያይረዋል፡፡ በፕሬዚዳንት ሬገን ዘመን የጀመረና ‹‹ዘ ግሬት ሞደሬሽን›› (ታላቁ የቁጥጥር ጊዜ ሊባል የሚችል) እስከ ፋይናንስ ቀውሱ የዘለቀ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ በዚህ ወቅት የአሜሪካ ኢኮኖሚ በመላው ዓለም በእጅጉ ሲስፋፋ ታዝበናል፡፡ ይህ ግን የምንቀበለው መከራከሪያ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የኢኮኖሚ ሕግጋት የሚያሳዩዋቸው ባህሪያት ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ሁለት ጊዜ በተከሰቱት የፋይናንስ ቀውሶች ምክንያት የዓለም የሸቀጥ ዋጋ ወድቋል፡፡ ቻይና ስትወድቅ አሜሪካ በአንፃሩ መጠነ ሰፊ የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ክምችት በማግኘቷ በነዳጅ አምራቾችና ላኪ አገሮች ድርጅት ውስጥ እየተሳተፈች የዓለም የነዳጅ ገበያውን ለመቆጣጠር ችላ ነበር፡፡ አሁን ግን እነዚህ አገሮች ከሸቀጥ የሚያገኙት ንፋስ አመጣሽ ትርፍ ቀንሶባቸዋል፡፡ ይሁንና ችግሩ አገሮቹ በመልካሙ ጊዜ ለውጥ ማምጣት የሚችሉባቸውን ዕድሎች በከባድ ፖለቲካዊ ወሳኔዎቻቸው ምክንያት ሊያጡ ችለዋል፡፡ በጊዜው ገንዘቡ ነበራቸው፡፡ አሁን ግን የላቸውም፡፡ ምናልባትም የካርታ መጫዎቻዎቻችንን መልሰን እንጣለን ይሉ ይሆናል፡፡ ሆኖም ካርታዎቹ ግን ከተጣሉ ቆይተዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...