Wednesday, February 28, 2024

በሕግ ሳይሆን በፖለቲካ የሚፈቱት የማንነት ጥያቄዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በ1960ዎቹ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ተማሪዎች የፖለቲካ ንቅናቄ ማዕከል ያደረገው ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነ የፖለቲካዊ ሥርዓትን በክርክር አንጥሮ ለማውጣት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተጨፈለቁ ማንነቶችን ከጭቆና በማውጣት ሁሉንም የአገሪቱ ብሔረሰቦች ነፃነት የሚያጐናጽፍ ሥርዓትን ለማበጀት ያለመ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ የተማሪዎቹ ንቅናቄ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሶ ሊፈጥሩት የነበረው ፖለቲካዊ ሥርዓት በወታደራዊ ኃይል ተቀልብሶ ወታደራዊ መንግሥት ቢመሠረትም የወጣቶቹ እምነት አልሞተም፡፡ ይሁን እንጂ እንደ አጀማመራቸው በሰላማዊ ትግል ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ይህንኑ የተማሪዎችን መሠረታዊ ዓላማ በማንገብ ትጥቅ ትግል ከጀመሩት ድርጅቶች መካከልም ስኬትን የተቀዳጁት ሕወሓትና ኢሕዴን የመሠረቱት ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. ወታደራዊ አገዛዙን በማስወገድ አገሪቱን ሲቆጣጠርም፣ ይኸው መሠረታዊ የትግሉ መርህ አልሞተም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ከግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. በኋላ የመሠረተው የሽግግር መንግሥት ቋሚ መርህም ተጨፍልቀው ለዘመናት የኖሩ የብሔሮች ማንነትን ነፃነት ማጐናፀፍ ነበር፡፡

የሽግግር መንግሥቱ ቻርተር ፖለቲካዊ አስተዳደር ምሰሶ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መሠረት ያደረገ ያልተማከለ አስተዳደርን በወቅቱ ፈጥሯል፡፡ በዚሁ ቻርተር መሠረት በወቅቱ ተቋቁሞ የነበረው የሕዝቦች ምክር ቤት የደነገገው አዋጅ ቁጥር 7/1984 የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ የራሳቸውን አስተዳደር መመሥረት እንዲችሉ ፈቅዷል፡፡ በዚሁ መሠረት የራሳቸው ክልላዊ ወሰን ያላቸውን 63 ብሔር ብሔረሰቦችን እንደለየና ከእነዚህ ውስጥ 47ቱ የራሳቸውን አስተዳደር እንዲመሠርቱ ዕውቅና መስጠቱንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚሁ መሠረትም ብሔርን መሠረት ያደረጉ 14 ክልላዊ አስተዳደሮችና በርካታ ንዑስ የአካባቢ አስተዳደሮች ተመሥርተው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ብሔርን መሠረት በማድረግና በሽግግር መንግሥት ወቅት የተመሠረቱትን ክልላዊ አስተዳደሮች በመቀበል በ1987 ዓ.ም. የፀደቀውና በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ማንነትን መሠረት ያደረገ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን በኢትዮጵያ አወጀ፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት በሚል ንዑስ ሥር ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፤›› የሚል ድንጋጌን አስቀምጧል፡፡

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ሦስት ላይ ደግሞ ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ብሔር ብሔረሰቡ ሕዝቡ በሠፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋም የማቋቋም፣ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መበትን ያጠቃልላል፤›› የሚል ፖለቲካዊ መብቶችን ያዘለ ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊትም ሆነ በኋላ በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን የተጠቀሰውን ድንጋጌ ኢትዮጵያን ለመበታተን ያለመ እንደሆነ ሲተቹት የነበረ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ወደ ተግባር ከገባ 20ኛ ዓመቱ ቢያልፍም ራስን ከማስተዳደር ጋር በተያያዙ ጥያቄዎች አገሪቱ በየቦታው በግጭቶች እየታመሰች ትገኛለች፡፡ ሕገ መንግሥቱን ያመነጨውና አገሪቱን ላለፉት 25 ዓመታት እያስተዳደረ የሚገኘው ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ድንጋጌ አንቀጽ 39 መሠረት እያኖረ ነው? የሚለው ጥያቄ አሁንም ተደጋግሞ ይነሳል፡፡

ኮንሶ እንደ ማሳያ

በደቡብ ክልል የኮንሶ ብሔረሰብ ለዓመታት ያልተመለሰለትን ራስን በራስ የማስተዳደር ሰላማዊ ጥያቄው አሁን ወደ ግጭት ተቀይሯል፡፡ ሰሞኑን በተቀሰቀሰው አመፅም ከሰባት ሺሕ በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ከ12 ሺሕ በላይ ሰዎች ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎችም መሞታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል መምህር የሆኑት አቶ ናሁሰናይ በላይ በግጭቱ ወቅት በኮንሶ ለጥናታዊ ጉዞ ተዘጋጅተው የነበሩ ሲሆን፣ በግጭቱ ምክንያት ጉዟቸውን ለመሰረዝ ተገደዋል፡፡

‹‹የኮንሶ ጥናታዊ ጉዞዬን እንድሰርዝ ያስገደደኝን ግጭት ምንነት ለማወቅ የአካባቢው ሰዎችን አነጋግሬ ያገኘሁት መረጃ›› በማለት ባስነበቡት ጽሑፍ፣ ሁኔታው ከአሁኑ ካልተገታ ወደማያባራ ግጭትና መተራረድ ሊያመራ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የኮንሶ ሕዝብ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት እስከ 2004 ዓ.ም. በልዩ ወረዳ መዋቅር ራሱን ሲያስተዳድር ቆይቷል፡፡ ከመጋቢት ወር 2004 ዓ.ም. በኋላ ግን የኮንሶ ልዩ ወረዳ ከቡርጂ፣ ከአማሮ፣ ከአሌ እና ከደራሼ ሕዝቦችን በመጨመር የሰገን አካባቢ ዞን ተደርጐ ተዋቅሯል፡፡

አቶ ናሁስናይ የሰገን ዞን ምሥረታ በባህሪው ራስ ገዝ አስተዳደር የነበሩ ወረዳዎችን በማሰባሰብ የተዋቀረ ሲሆን፣ ሕዝቦች መክረውበትና ፈቅደው የተዋሀዱበት አለመሆኑን፣ ይልቁንም የክልሉ አመራሮች ባቀዱት መሠረት ብቻ የተመሠረተ ዞን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮንሶ ልዩ ወረዳ ፈርሶ የሰገን ሕዝቦች ዞን ምሥረታ ከተካሄደበት ማግሥት አንስቶ በተፈጠረው የዞን መዋቅር ደስተኛ አለመሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

ፍትሐዊ የበጀት፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና እንዲሁም ማኅበራዊ ጥቅሞች እንደተጓደሉበት እየገለጸ ይገኛል፡፡ ከዞኑ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኮንሶን ብሔረሰብ ተወላጆች መገለል እየደረሰባቸው መሆኑን እየገለጹ ናቸው፡፡

እነዚህንና ሌሎች ያልተገለጹ በደሎችን ምክንያት በማድረግ የኮንሶ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እንዲመለስና ራሱን ችሎ የብሔረሰብ ዞን ሆኖ እንዲደራጅ፣ እንዲሁም ያለ ኮንሶ ሕዝብ ዕውቅና ከኮንሶ ወረዳ የተቆረጡ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ እንዲመለሱለት ለክልሉም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይህ ባለመሆኑም ሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ የነበረው የኮንሶ ብሔር ጥያቄ ወደ ግጭት አምርቶ ደም እያፋሰሰ ይገኛል፡፡

‹‹የተጠየቀው ጥያቄ ሕጋዊነቱንና ሕገ መንግሥታዊ አካሄድን የጠበቀ እስከሆነ ድረስ ሕጋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ይህ ጥያቄ ለምን ተጠየቀ ተብሎ የኃይል ዕርምጃ መውሰድ ዘላቂና ተገቢ መፍትሔ ፈጽሞ አይሆንም፡፡ የአካባቢው አመራሮች እየፈጸሙት ያለው ወንጀል ልክ የለውም፡፡ በሰሞኑ ግርግርም ወደ ሦስት መንደር የሚሆኑ የሣር ጐጆዎች መቃጠላቸውንና ነፍሳቸውን ለማዳን ሲሉም በርከት ያሉ ኮንሶዎች ለመሰደድ መገደዳቸውን ለመረዳት ችያለሁ፤›› በማለት ሁኔታውን አቶ ናሁሰናይ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ከሌሎቹ ክልሎች በተለየ ሁኔታ ነገር ግን ከፌዴራል መንግሥቱ አወቃቀር ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ሁለት አወቃቀሮች አሉት፡፡ የደቡብ ክልል ምክር ቤትና የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት በሚል የተዋቀረ ነው፡፡ የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት በፌዴራል መንግሥቱ አወቃቀር መሠረት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

በመሆኑም የኮንሶን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የሚመልሰው የደቡብ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ነው፡፡ የኮንሶን ጉዳይ የተጠየቁት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ለማ ገዙሜ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ አወቃቀር የአስተዳደር ቅልጥፍናን አመቺነትንና የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ታሳቢ በማድረግ ነው የሚመለስ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም የኮንሶ ወረዳ በሰገን ሕዝቦች ዞን እንዲካተት የተደረገው ይህንን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አፈ ጉባዔው አቶ ለማ ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ጉዳዮችና አካባቢያዊ አስተዳደሮች ላይ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ዘመላክ አየለ አይተነው፣ የክልሉ መንግሥት ውሳኔ የኮንሶ ሕዝብን ሕገ መንግሥታዊ መብት የረገጠ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የአገሪቱ ሕገ መንግሥትም ሆነ የደቡብ ክልል ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት የኮንሶ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ ተከብሮለት ልዩ ወረዳ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ኮንሶ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት ከኮንሶ ጋር በመሆን የሰገን ዞንን የመሠረቱት አማሮ፣ ቡርጂና ደራሼ ልዩ ወረዳ እንደነበሩ የሚገልጹት ዶ/ር ዘመላክ፣ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ዴኢሕዴን በ2004 ዓ.ም. በወሰደው ፖለቲካዊ ዕርምጃ ሁሉንም ልዩ ወረዳዎች በማፍረስና እንዲዋሀዱ በማድረግ የሰገን ሕዝቦች ዞን ሆነው እንዲዋቀሩ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡

የሰገን ዞን የብሔረሰቦች ጥርቅም የሆነ የአስተዳደር አካል እንጂ ራስ ገዝ የሆነ የአካባቢያዊ መንግሥት መዋቅር አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ከልዩ ወረዳ ጋር ሲነፃፀር የዞን አወቃቀር እዚህ ግባ የማይባል አነስተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ብቻ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

ኮንሶን ጨምሮ አራቱ ልዩ ወረዳዎች ፈርሰው የሰገን ሕዝቦች ዞን ሆነው በአንድ እንዲዋቀሩ መደረጉ የኮንሶ ብሔረሰብን ራስን በራስ የማስተዳደር ፖለቲካዊ ሥልጣንን እንዳሳጣ ዶ/ር ዘመላክ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከአንቀጽ 39 ጋር የሚላተመው ኢሕአዴግ

በሥራ ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 የደነገገው የብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች መብት ጠቅላላ ድንጋጌ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ፖለቲካዊ መብት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሳይሆን ለብሔሮች የተሰጠ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

በዚህ ድንጋጌ መሠረት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ራስን ከማስተዳደር ሙሉ መብት ባለፈ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠልንም አጐናፅፏል፡፡

ይህ የብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ፖለቲካዊ መብት ተግባራዊ ይሆን ዘንድም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 50 (4) ላይ ክልሎች አስፈላጊ ሆኖ በሚያገኙት ሁኔታ መሠረት የራሳቸውን አስተዳደራዊ መዋቅሮች ሊያቋቁሙ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ማንኛውም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዳላቸው ቢገለጽም፣ የአስተዳደር መዋቅሩን ክልሎች በሚመቻቸው መሠረት እንዲፈቅዱ ደንግጓል፡፡

‹‹The Politics of Sub-national Constitutions and Local Government in Ethiopia›› በሚል ርዕስ የጥናት ጽሑፋቸውን ያሳተሙት ዶ/ር ዘመላክ፣ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ 670 ወረዳዎችና 98 የከተማ አስተዳደሮች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡     

ወረዳዎች በክልሎች ሕገ መንግሥት መሠረት የሚመሠረቱ መሆናቸውን የሚያስታውሱት ዶ/ር ዘመላክ፣ በልዩ ወረዳና በብሔረሰብ ዞን የሚዋቀሩ የአስተዳደር መዋቅሮች ደግሞ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 የሚሰጠውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተግባራዊ የሚሆንበት አወቃቀር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ልዩ ወረዳ የተባለው ከወረዳ የተለየ በመሆኑና ልዩነቱም የልዩ ወረዳ አስተዳደራዊ ክልል የሚወሰነው በብሔረሰቡ አሰፋፈር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የብሔረሰብ ዞን አወቃቀር ዓላማው ከልዩ ወረዳ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ክልላዊ ወሰኑ ወይም የቆዳ ሽፋኑ ሰፋ ያለ በመሆኑና በውስጡ ከሁለት በላይ ወረዳዎችን ሊይዝ የሚችል ስለሆነ ከልዩ ወረዳ የተለየ ስያሜ እንዲይዝ እንዳደረገው ይገልጻሉ፡፡

በዚህም መሠረት በአምስት ክልላዊ መንግሥቶች ውስጥ የልዩ ወረዳ አወቃቀር መኖሩን እነርሱም ደቡብ፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና አፋር ናቸው፡፡ በእነዚህ ክልላዊ መንግሥታት ውስጥም የብሔረሰብ ዞኖች አደረጃጀት መኖሩን ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት ያህል በአማራ ክልል የኦሮሞ፣ ሕምራና አዊ ብሔረሰብ ዞኖችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የመጀመሪያው የአካባቢ መንግሥት አወቃቀር የተጀመረው በሽግግር መንግሥት ወቅት መሆኑን በጥናታዊ ጽሑፋቸው የገለጹት ዶ/ር ዘመላክ፣ ክልሎች ሕገ መንግሥቶቻቸውን ካፀደቁ በኋላ የነበሩትን አካባቢያዊ አስተዳደሮች እንዳለ እንደተቀበሏቸው ያስረዳሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፀድቆ ተግባራዊ መሆን በጀመረባቸው ዓመታት አገሪቱን የሚያስተዳድረው ኢሕአዴግ ማንኛውንም የብሔረሰብ መብት ጥያቄ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር ረገድም ችግር እንዳልነበረበት ያስታውሳሉ፡፡

ኢሕአዴግ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ይህንን ያደርግ የነበረው የብሔረሰቦች ግጭትን ለማብረድ እንደሆነ በመጥቀስ፣ በማሳያነት በሰሜን ኦሞ የብሔረሰብ ዞን አወቃቀር ተነስቶ የነበረውን ግጭት ያስታውሳሉ፡፡ ለምሳሌ ወላይታ፣ ጋሞ ጐፋና ዳውሮ ብሔረሰቦችን በማጣመር የሰሜን ኦሞ የብሔረሰብ ዞን መፈጠሩን ይጠቅሳሉ፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ወላይታ ራሱን የቻለ የብሔረሰብ ዞን እንዲኖረውና ከሰሜን ኦሞ ዞን መለየት መፈለጉ በመሀላቸው ግጭትን እንደቀሰቀሰ፣ በመሆኑም የክልሉ መንግሥት በፍጥነት የወላይታን ጥያቄ መቀበሉን ይገልጻሉ፡፡

በዚህ የተነሳም የሰሜን ኦሞ ብሔረሰብ ዞን ለሦስት ራሳቸውን የቻሉ የብሔረሰብ ዞኖች (ዳውሮ፣ ጋሞጐፋና ወላይታ) እና ሁለት ልዩ ወረዳዎች (ባስኬቶና ኮንታ) አወቃቀሮች መፈጠራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. ከ2000 በኋላ ኢሕአዴግ የብሔረሰቦችን ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ የሕዝቦችን የአገልግሎት አቅርቦትና የልማት ጥያቄ ለመመለስ እንዳላስቻለው በመጥቀስ፣ የልዩ ወረዳና የብሔረሰብ ዞን አስተዳደራዊ መዋቅር ጥያቄዎችን መንፈግ መጀመሩን ያብራራሉ፡፡

እነዚህ የልዩ ወረዳና የብሔረሰብ ዞን ጥያቄዎች መቆሚያ ያጡት የማኅበረሰቡ ልሂቃን የሥልጣንና የሀብት ማስገኛ መንገድ አድርገው በመቁጠራቸው እንደሆነ በገዥው ፓርቲ መታመኑን ያስረዳሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ከገዥው ፓርቲ ማዕከል ወደታች የወረደ በሚመስል መልኩ ክልሎች ሕገ መንግሥቶቻቸውን በማሻሻል አስተዳደራዊ መዋቅር ብቻ ለሆኑት ወረዳዎች የተሻለ ሥልጣንና ሀብት በመልቀቅ፣ የልዩ ወረዳና የብሔረሰብ ዞን ጥያቄዎችን ማዳከም መጀመራቸውን ያስረዳሉ፡፡

ከላይ በወረዳው የኢሕአዴግ ትዕዛዝ ክልሎች ሕገ መንግሥታቸውን በማሻሻል ቀደም ሲል የክልል ፕሬዚዳንቶች በወረዳዎች ላይ የነበራቸውን ፍፁማዊ ሥልጣን እንዲያጡ መደረጋቸውን ያትታሉ፡፡ ለዚህ የሚሰጠው ሁለተኛው ምክንያት የመንግሥት የልማት ፖሊሲ አቅጣጫ የነበረው ዘላቂ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም መሠረት ያደረገው ወረዳዎች ላይ ነበር፡፡ መንግሥት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP) የተባለውን የልማት ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ደግሞ፣ ወረዳዎች መረሳታቸውንና ከተሞች ላይ ትኩረት ያደረገ የልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም ኢሕአዴግ በመጀመሪያ የብሔረሰቦችን ግጭት በማስወገድ መረጋጋትን ለመፍጠር ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን ብሔርን መሠረት ያደረገ አካባቢያዊ አስተዳደርን መፍቀድ ከጀመረ በኋላ፣ የልማትና ተመጣጣኝ የአገልግሎት አቅርቦትን ለሕዝቦች ለማድረስ በሚል ልማታዊ ምክንያት የብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ማፈኑን ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም በአንድ ወቅት ብሔር ተኮር የነበሩ ወረዳዎችን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ማዋሀድ ድረስ በመሄድ፣ በኋላ የልማት አቅጣጫው ከተማ ተኮር ሲሆን ወረዳዎችን በመርሳት ክልሎች ከራሳቸው ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚመልስ አካባቢያዊ የመንግሥት መዋቅር እንዳይፈጥሩ በማድረግ፣ ግጭቶች በየቦታው እንዲስፋፉ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡

አንድ ወጥ አካባቢያዊ የአስተዳደር መዋቅር በሁሉም ክልላዊ መንግሥቶች የሚሠራ ባለመሆኑ፣ ለክልሎቹ ነፃነት በመሰጠት ተገቢ የሆነውን አደረጃጀት በራሳቸው እንዲወስኑ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ

የአካባቢያዊ አስተዳደሮች በክልሎች ሕገ መንግሥትና ነባራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ መወሰኑ ቀርቶ፣ ከኢሕአዴግ በሚመጣ ውሳኔ የልማት አቅጣጫን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎችን ክልሎች እንዲከተሉ በመደረጉ በየቦታው ግጭት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ የግጭት ስፋቱ በዋናነት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ያይል እንጂ በአማራ ክልል የቅማንት ጥያቄ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል የወልቃይት ጥያቄ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ቢሆንም ማጠንጠኛቸው ራስን ማስተዳደር ነው፡፡

እነዚህን ጥያቄዎች በሕገ መንግሥታዊ መርህ መሠረት ከመመለስ ይልቅ ለማዳፈን መሞከር የግጭቱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የሰላምና ደኅንነት ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ ስለዚህ በሕግና በቴክኒክ መመለስ ሲገባው በፖለቲካ ነው እየተመለሰ ያለው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ለተመሳሳይ ጉዳይ የተለያዩ ምላሾችን መስጠት ያመጣል፡፡ ለአላባ የፈቀድከውን ለኮንሶ ትከለክላለህ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ወጥ የሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መስፈን አለበት የሚሉት እኚሁ ባለሙያ፣ ‹‹ሕዝብ አንቀሳቅሰህ መንግሥትን ስታስጨንቅ የሚሰጥ መብት እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብት በአገሪቱ ውስጥ ወጥ ሆኖ ሊተገበር አልቻለም፤›› ይላሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጣቸው መርሆዎች እያሉ ኢሕአዴግ ተግባራዊ እያደረገ ያለው በተለየ መንገድ መሆኑን ያስረዱት እኚሁ ባለሙያ፣ የሁለቱ ግጭት አገሪቱን እየበጠበጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ በሕገ መንግሥቱ ላይ እስከሆነ ድረስ፣ ለዚህ ሕገ መንግሥት ዜጐች ብቻ ሳይሆኑ ኢሕአዴግም ሊገዛ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የሕገ መንግሥቱን መርህ በመከተል እያንዳንዱን የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ መመለስ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የሚያምኑት ዶ/ር ዘመላክ፣ ጥያቄውን መከልከል ግን ፀረ ሕገ መንግሥት ከመሆንም ባሻገር የግጭት ምንጭ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ሁሉም የራስ ገዝ አስተዳደሮች የማኅበረሰብ ወይም የብሔረሰቡ ሙሉ ፍላጎት ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም፣ መከልከሉ ግን ሕገ መንግሥታዊ እንደማያደርገው ዶ/ር ዘመላክ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎቹን በጥብቅ ተግባራዊ ለማድረግ ባለ ችግርና በተለያዩ የብሔር ማኅበረሰቦች ሊቀጥል የሚችለው የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ውዝግብና የግጭት ምንጭ ሆኖ እንደሚቀጥል የዶ/ር ዘመላክ እምነት ነው፡፡

  

         

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -