Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትበቁሳዊ ልማት ጋጋታ ብቻ የሕዝብ ፍቅር አይታፈስም

በቁሳዊ ልማት ጋጋታ ብቻ የሕዝብ ፍቅር አይታፈስም

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ለድጋፍ ሸመታ አለኝታ የተደረገውና ስንት የሚወራለት ልማት በራሱ፣ ውስጡን ለቄስነት የማያጣው ነው፡፡ ይህንን ነጥብ ትንሽ እንዘርጋው፡፡

1) በደርግ ዘመን የተስፋፉትን ለምዝበራ የሚመቹትን የንብረትና የገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ብልሽቶች በዛሬው ‹‹የተሃድሶ›› ዘመንም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በልማት ድርጅቶች ውስጥ እናገኛቸዋለን፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የተወሰኑ ናሙና መሥሪያ ቤቶችን ክንዋኔ እየመረመረ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች ከዓመት ዓመት የሚያስገርም ነገር አያጣቸውም፡፡ ከደንብና ከመመርያ ውጪ ለትርፍ ሰዓት ሥራ፣ ለአበል፣ ለደመወዝና ለማበረታቻ፣ ወዘተ መክፈልን፣ መስክ ሳይወጡ ውሎ አበል መክፈልን፣ ምግብና መኝታ ችሎ እንደገና ውሎ አበል መክፈልንና መሥሪያ ቤት ለለቀቁና ለትምህርት ወደ ውጭ ሄደው ለቀሩ ደመወዝ መክፈልን ተሃድሷችን አልጠራረጋቸውም፡፡

ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረቡ እያሉ ያለ በቂ ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ ካቀረቡ ላይ መግዛት፣ ያለጨረታ መግዛት፣ ዋጋ ማቅረቢያ ሳይሰበስቡና ሳያወዳድሩ መግዛት፣ ከአንድ አቅራቢ ብቻ መግዛት፣ ያለ ውል ስምምነት ክፍያ መፈጸም፣ ለታቀደላቸው ዓላማ መዋላቸውን የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ማስረጃ ያልቀረበባቸው ወጪዎች (ደመወዝና አበልን ጨምሮ) ዛሬም አሉ፡፡

ስለአሠራር ለውጥ ስንቱን የሰማ ጆሯችን በዓመታዊ ቆጠራ ንብረትን አጣርቶ አለማወቅ ዛሬም መኖሩን ሰምቷል፡፡ ምን ይህ ብቻ! አገልግሎት መስጠት እየቻሉ ያላግባብ የተቀመጡ፣ በአያያዝ ጉድለት ብልሽት የደረሰባቸው፣ ከለቀቁ ሠራተኞች ያልተመሰሉ ንብረቶች፣ የሰሌዳ ቁጥር ወይም የበላለቤትነት መታወቂያ/ሊብሬ የሌላቸው መኪኖች ማጋጠማቸውን፣ የሻንሲ ቁጥርና የባለቤትነት መታወቂያቸው ያልተጣጠመ መኪኖች፣ ጭራሽ በአካል ለሌሉ መኪኖች ሊብሬዎች መገኘታቸውን አንብበናል፡፡ በናሙና ከታዩ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ ‹‹በአዲስ መልክ›› በተቋቋሙ ጊዜ የነበራቸውን የመነሻ ሒሳብ በአግባቡ የሚያሳይ መረጃ የሌላቸው መገኘትም (የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት፣ 2008 ገጽ 43-4) የሚያስተዛዝብና የሚያሳስብ ነው፡፡ በዛሬው ጊዜ ወጪ ምርት፣ ጥራትና ደኅንነቱ በአግባቡ ሳይረጋገጥ የሚሾልክበት ቀዳዳ መኖር፣ እንዲያውም ደረጃ አያሟላም የተባለ ምርት በደብዳቤ እንዲለቀቅ ማድረግ፣ ገቢ ዕቃዎችን በተመለከተም በኢትዮጵያ ተቀባይነት ያለውን የጥራት ደረጃ ማሟላታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ሳያቀርቡ የሚሾልኩበትና ገበያ ውስጥ የሚገቡበት ክፍተት መኖሩ፣ የመለኪያ መሣሪዎችም ደረጃና ትክክለኛነታቸው ሳይረጋገጥ ገበያ የሚገቡበት ዕድል መኖሩ፣ እነዚህን የመሳሰሉት ችግሮች ስለጓዳ ጎድጓዳችን ብዙ ፍንጭ ይሰጣሉ፡፡

የኦዲት ሥራ የሚታገለው እነዚህን ከመሳሳሉ ችግሮች ጋር ስለሆነ ችግሮችን ብቻ መጠቃቀስ አይበቃም፣ ችግሮቹ እየተባዙ ወይም እየተቃለሉ መምጣታቸውን ማሳየት ያስፈልጋል ሊባል ይችላል፡፡ ተገቢ ነው፡፡ ችግሮቹን ለማዳከም ጥረት ስለመደረጉና በየጊዜው መሻሻልም ስለመኖሩ ህዳሴያች ይነግረናል፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴራል ኦዲት የሶስት ዓመት (ከ2006-2008) ሪፖርትን ስናገናዝብ ከታዩት ውስን መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የጎላ ችግር ኖሮባቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጣቸው የ2005 ዓ.ም. ክንዋኔ በተመለከተው የ2006 ሪፖርት ላይ 15 ነበሩ፡፡ የ2006 ዓ.ም. ክንዋኔ በተመለከተው የ2007 ዓ.ም. ሪፖርት ላይ 20 መሥሪያ ቤቶች፤ የ2007 ዓ.ም. በተመለከተው የ2008 ዓ.ም. ሪፖርት ላይ ደግሞ 37 ነበሩ፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ2008 ዓ.ም. ምርመራው ከባድ ችግር ያገኘውም፣ የአቅም ግንባታ ኃይልና መፍለቂያ ይሆናሉ በተባሉ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ መሆኑ ግርምት የፈጠረ ነበር፡፡ በመልካም አስተዳደር ብልሽት አሳሳቢነት ረገድ የሕዝብ ሮሮ ንሮ መሰማቱና በዚህ ዓመት ችግሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ደረጃ ታምኖ፣ የሰው ምንጣሮ በፌዴራልና በክልሎች መጀመሩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ስለሥራ ልሽቀትና ስለንቅዘትም የሚናገር ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባካሄደው የጋራ ቤቶች ቆጠራ ለተጠቃሚ ያልተላላፉ፣ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ፣ ያላግባብ የተላላፉ፣ ወዘተ. መገኘታቸውም የቀልጣፋ ንብረት አያያዝና የፀዳ አሠራር ምን ያህል ሥር የሰደደ ችግር እንደሆነ የጠቆመ ነበር፡፡ ደንብ የተከተሉት የገንዘብ ወጪዎች ሁሉ በአዋዋላቸው አግባብነት ይለኩ ቢባልማ ክብረ በዓላት፣ ሴሚናሮች፣ ስብሰባቸው ከመብዛታቸው አልፎ ድግስ፣ ባለዓርማ ካኔቴራ/ኮፊያ ወይም ሻርፕ መውደዳቸው ብዙ በተባለለት ነበር፡፡ በቅርቡ ‹‹ኢቢሲ›› የሚባል ስም የያዘው የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ለ50ኛ ዓመት በዓሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ማውጣቱ (አዲስ አድማስ በታኅሳስ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዳወራን፣ ያውም በስንት ትችት ከሰባት ሚሊዮን ብር ወደ ሦስት ሚሊዮን ግድም ተቀንሶ) ህዳሴ ምን ያህል እንደዘለቀው ያሳየና በህዳሴ ‹‹አብሳሪነቱ›› ላይ የተሳለቀ ነበር፡፡ በዚሁ በ2008 ዓ.ም. ለሾፌሮቹ ለአንድ ጥንድ ጫማ ሁለት ሺሕ ብር እስከ ማውጣት የባጠጠ መሥሪያ ቤትም ነበር ብትባሉ ጆሯችሁ ያምናል?

2) እስካሁን ያወራነው ንቃቃት ንቃቃቱን ነው፡፡ የጉልህ ጥፋቶች ቤት ወደነበረው የስኳር ኮርፖሬሽን እንምጣ፡፡ የስኳር ልማት እጅግ ሰፋፊ የሸንኮራ እርሻ ዝግጅቶችንና አዋጪ ርቀት ላይ የተተከሉ ፋብሪካዎችን በብዙ ሺዎች ከሚቆጠሩ ሠራተኞች ጋር ማገጣጠምን የሚጠይቅ የመሆኑ ቅድመ ዕውቀት ለዛሬዋ ኢትዮጵያ እንግዳ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የስኳር ልማት ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ የዘለቀ ስለነበር፡፡ የእርሻ ልማትን፣ ፋብሪካዎችንና አያሌ ሠራተኞችን ወቅት ከወቅት የማገናኘቱ ነገር በጠንቃቃነት እየተገናዘበ ተያይዞ ካልሄደ ኪሳራ ውስጥ እንደሚጥል (ሸንኮራ ደርሶ ፋብሪካ ወደኋላ ቢቀር ሽንኮራ ስኳር ሳይሆን እንደሚበላሽ፣ ወዘተ) በሥራውና በሙያው ውስጥ በኖሩ ሰዎች ዘንድ እውቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የስኳር ኮርፖሬሽን ነባር ፋብሪካዎችን የማስፋፋትና አዲሶችን የመገንባት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይህንን መሰረታዊ ዕውቀት ተቆናጠው፣ በውጭ ምንዛሪና በሙያ አቅም ልክ ተመጥነው፣ ነባሮቹ እንቅስቃሴያቸው ሳይስተጓጎል ለአዲስ ተገንቢዎቹ የገንዘብ ምንጭ እየሆኑ፣ አዲሶቹም ለነባሮቹ ውጥረት አቅላይ እየሆኑ በሚደጋገፉበት ቅንብር ባለመመራታቸው ከስኳር ልማት ነባር ልምዳችን አኳያ መሠራት የማይገባው ጥፋት ተፈጽሟል፡፡

የዚህ ጥፋት ዋና ምንጩ በሩጫ አስገራሚ የልማት ክንዋኔ አሳይቶ የሕዝብ ድጋፍ የመሸመት ጥማት ነው፡፡ በአንድ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን (በአምስት ዓመት) ውስጥ ከአሥር የስኳር ፋብሪካዎች ሰባቱን ለመገንባት ማለም የዚህ አብነት ነው፡፡ ‹‹የተለጠጠ ዕቅድ›› ይባላል በኢሕአዴግ ቋንቋ፡፡ የሩጫ ሥራ ታላቅ ጥፋት ነው፡፡ እሱ ደግሞ ሌሎች ልጆች አሉት፡- ‹‹ይጀመርና በሒደት ይሟላል››፣ ‹‹እያጠፉ መማር›› የሚባሉ፡፡ እነዚህ ጥፋቶች ደግሞ ሌሎች ጥፋቶችን ይወልዳሉ፡፡ የገንዘብ አቅም በአንዴ ብዙ ቦታ ይበታተንና አንዱንም የማያጠግብ ይሆናል፡፡ አቅሙን ያላወቀ ‹‹እንችለዋለን›› ባይነት ወይም ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን፣ ባለመክሰር ጥንቁቅነት ያልተመራ (ከአስተማማኝ የሥራ ድርጅት/ኩባንያ ጋር ሥራውን ያልተዋዋለ፣ አስተማማኝ አማካሪና ተቆጣጣሪ ያልያዘና የሥራ ጥራት እየፈተሸ በሥራ ልክ ገንዘብ የማይከፍል) የሥራ ባለቤትነት ዝርክርኩ ይወጣል፡፡ የሥራ ተጀምሮ መገተር፣ የአንዱ ሥራ መዘግየት የሌላውን ሥራ ከንቱ ማስቀረት፣ የጥራት ጉድለት፣ ብክነት፣ ምዝበራ፣ የሚያዳግምና አክሳሪ የሥራ ክንዋኔ… ይህ ሁሉ በስኳር ልማት ውስጥ ደርሷል፡፡ ይህንኑ ለማሳየት የስኳር ኮርፖሬሽን በ2008 ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤት ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ካቀረበው የሥራ ክንዋኔ ዘገባ ውስጥ የተወሰኑትን  እንነካካ፡፡

አሠሪው ስኳር ኮርፖሬሽን በብቃት አወዳድሮና መርጦ ሥራ ተቋራጭነቱን አልሰጠም፡፡ ሥራው የተሰጠው በመንግሥት ትእዛዝ ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) ነው፡፡ ማለትም በንግድ ሥራ ዓለም አሠሪ ራሱን ከኪሳራ የሚጠብቅበትን ዘልማድ ራሱ መንግሥት ጣሰ፡፡ ውል የያዘ የሥራ ተቋራጭነት ኖሮ ቢሆን፣ አሠሪ ጥራት የለሽ ነገር ቢመጣበት ወይም ሥራ ቢዘግይበት በውሉ መሠረት ኪሳራ የማስተፋት፣ የገንዘብ ክፍያንም ሆነ የሥራ ዕርምጃን እያስፈተሸ የመክፈል አቅም ይኖረዋል፣ ሙስና ኃላፊነቱን እስካላሳተው ድረስ፡፡

ይህን ዓይነት ዋስትና ያለበትን የሥራ ተቋራጭ አመራረጥ ታዲያ መንግሥት ለምን ጣሰ? ያውም ሌሎች መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ሳያወዳድሩ ሥራ ቢሰጡ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጥፋት ጋር የሚያያዝ ሆኖ ሳለ! ብኢኮ ልምድ እንዲያካብት? ይህ እንኳን በግዙፍ ፕሮጀክት በትንንሽ ሥራዎችም ኪሳራ መድረስ የሌለበት ነው፡፡ ትምህርትና ልምምድ በራስ ኪሳራ እንጂ በሌላው ኪሳራ ሊሆን አይገባም፡፡ አገሪቱ የፈጠራ አቅም እንድታበጅ ተብሎ ከሆነ ይህ ዓይነቱ አቅም የሚገነባው አንድ ኮርፖሬሽንን እያጠፋ እንዲማር በማድረግ አይደለም፡፡ ለዚህ የተቋቋመ የአሠራር ዘዴ አለው፡፡ ከሙያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት እስከ ምሕንድስና ያለው የአገሪቱ ትምህርትና ሥልጠና እየለኩ እየቆረጡ፣ እየሞከሩ፣ እየሞረዱ፣ ደግሞ እንደገና ለጥፎ/ገጥሞ እያዩ የመሥራት ባህልን አጥብቦ፣ በወረቀት ላይ የተዘጋጁ እቅጭ ልኬቶችን ወደ መሥሪያ ቁሶች እቅጭ በእቅጭ ማስተላለፍን ሲያስጨብጠው፣ ከውጭ የመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተገልጋይ ከመሆን አዘልሎ ጥበባቸውን ከራስ ዕውቀት ጋር አዋህዶ ለሌላ ፈጠራ ስንቅ ማድረግን በየሥራ ቤቶች (በየጋራዦች፣ በየእንጨትና በብረታ ብረት ቤቶች፣ በየኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ማደሻ/መገጣጠሚያ ወዘተ. ወዘተ. ሥራ ቤቶች) ውስጥ ለማባዛት አቅም ሲኖረው ነው፡፡ ይህን የመሰለው የፈጠራና የጥበበኛነት ንጣፍ ገና ምኑ ተይዞ የሚባል ተግባር ነው፡፡

የእቅጭ ሥራ አጠቃላይ ንጣፍ ቢጓደልም ብኢኮን በብቃቱ መንግሥት ተማምኖበት ይሆን? ይህ ሆኖ ከነበረም ግምት እንደጠበቁት ሳይሆን ሲቀር ፈጣን እርማት ሊወሰድ በተገባ ነበር፡፡ መንግሥት ይህንን አላደረገም፡፡ መለዋወጫዎችን በብኢኮ ማሠራት እንኳ ከውጭ ከማስመጣት ይልቅ በአገር ውስጥ ማሠራት ይረክሳል የሚል ግምትን ያናጋ ገጽ ነበረው፡፡ ባነሰ ዋጋ ከውጭ ሊገኝ የሚችልን መለዋወጫ በተወደደ ዋጋ ከብኢኮ ስለማሠራታቸው ሪፖርት አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡ እውነተኛው ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ችግር ይሆን? ይሆን ይሆናል፡፡ ግን ጥራት በጎደለው የመለዋወጫ ሥራ ምክንያት በቀላሉ የማይሰበር/የማይሰናከል ሌላ አካል ተጎድቶ የስኳር ምርት ሥራ የተስተጓጎለበት፣ የበለጠ የምንዛሪ ወጪም በመለዋወጫ ብቻ ሳይሆን፣ የማምረት መሰናክል በገበያ ውስጥ ያስከተለውን የስኳር እጥረት ለማቃለል ስኳር ከውጭ ለማስመጣትም ይውል እንደነበር ተነግሯል፡፡

3) የስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎችም በቶሎ ለችግሮች መፍትሔ መፈለግ ተግባራቸው ነበር፡፡ እንዲህ ማለት ቀላል ነው፡፡ ግን ሥራ ተቋራጩ ለአሠሪው የጌታ ያህል ሲሆን ግን ከባድ ፈተና ነው፡፡ ብኢኮ በኢሕአዴጋዊ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የሚመራ መንግሥት የማለት ያህል እንደመሆኑ አይቆጡት፣ ሥራ ካንተ ጋር አቋርጫለሁ አይሉት፣ የቸገረ ነገር፡፡ አንበሳን እንደመደፋር ያለ ነው፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽን ሪፖርት አቅራቢዎች የጌታ መሰል ግልምጫንም እንደቀመሱ ጠቆም ከማድረግ አልተቆጠቡብም፡፡ እጅግ እቅጩነትን የሚጠይቁ ዕቃዎችን ለወንጂም ለፊንጫም ብኢኮዎች እንሠራለን ሲሉ አትችሉም ሲሉ የተሰጣቸውን ምላሽ አንደኛቸው ሲገልጡት፣ ‹‹አለሳልሰን ስንናገረው ቀላል ይመስላል… የሚያም ማሸማቀቅ ነበር፤›› ያሉት በምሬት ነበር፡፡ ከየትንንሹ ሹም የምትወረወር ማገጣበርን የሚያውቅ ሰው የ‹‹ማሸማቀቅ›› ንግግርን መገመት አይከብደውም፡፡ ቢያንስ ‹‹የጥገኛ አመለካከት የያዛችሁ! ልማቱ የውስጥ አቅም እንዳይገነባ የምታደናቅፋ…›› ምናንም የምትል ዓይነት ኃይለ ቃል ድቅን ትልበታለች፡፡

የዕቃዎች የጥራት ችግር በአገር ልጅ ሥራ ውስጥ ብቻ የሚያጋጥም  አይደለም፡፡ ከውጭ ኮሾ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች ገብተው በቶሎ እየተበላሹ ሥራ አስተጓጉለዋል፡፡ ጥራት የለሽ ዕቃ አምልጦ ቢገባም አስተማማኝ የጥራት ክትትልና የውል ጊዜ ሳያልፍ እንከናም ዕቃን የማወቁ ንቁነት ካለ ባለውሉን ተቋራጭ ማስከፈል እንደሚቻል፣ ሪፖርት አቅራቢዎቹ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሥራ ተቋራጭን ማስከፈላቸውን በምሳሌነት ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡

ጥራት የለሽ መለዋወጫ ከራሱ ጋር ደኅነኛውንም ዕቃ እያጠፋ ተጨማሪ ወጪ (በተለይ በማያወላዳው የውጭ ምንዛሪያችን ላይ) እንደሚያስከትል ሁሉ፣ ለአዲስ ዓይነት የቴክኖሎጂ ውጤት የሚመጥን የቴክኒክ ሥልጠና ማነስም መሰል ጥፋት የሚያደርስ መሆኑም አልተካደም፡፡ ብዙ ቦታ ላይ የተዘረጉ ብዙ ዓይነት የግንባታ ጅምሮች የውጭ ምንዛሪ ጥሪትን እንደመሻማታቸው፣ የውጭ ምንዛሪ ማነስ ለስኳር ኮርፖሬሽንም የማይለቅ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚሁ ምክንያት በቂ (የአንድ ሁለት ዓመት) የመለዋወጫ ስንቅ ይዞ በብልሽት ጊዜ ሥራ ሳይቋረጥ ለመዝለቅና ዓመታዊ የእድሳት ጊዜ ከመድረሱ አስቀድሞ አስፈላጊ መለዋወጫዎችን አዘጋጅቶ በሰዓቱ እድሳት ለማድረግ ፈተና ታይቷል፡፡ መለዋወጫ ለማሟላት ምንዛሪ የሚገኘው እድሳት በሚጀመርበት ጊዜ እየሆነ የጥፍዲያና የውጥረት ሥራ ደጋግሞ አጋጥሟል፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ ፋብሪካዎች አለመድረስ ወይም እያመረቱ በነበሩ ፋብሪካዎች መስተጓጎል ደርሶ በተወሰኑ ደኅነኛ ፋብሪካዎች ላይ የሚፈጠር የሥራ ጫና ለእድሳት እንኳ ትንፋሽ የሚከለክልበት ጊዜ ነበር፡፡

አዳዲስ ግንባታዎችንና ነባር የስኳር ልማቶችን በማስፋፋት ረገድ ከታዩ ጉልህ ችግሮ አንዱ ሳይጠናቀቁ ሥራ ማስጀምር ነው፡፡ አዲስ ፋብሪካዎች ተገቢውን የዕቃዎች ጥራት መያዛቸውና በደንብ መሥራታቸው ሳይፈተሽና ርክክብ ሳይደረግ ሥራ መጀመራቸው፣ ያልተሟሉና እንከናም ነገሮችን ከሚመለከተው ተቋራጭ በውል መሠረት ለመጠየቅ አያስችልም፡፡ መምጣት የሌለበት ኪሳራ ይመጣል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል የፋብሪካ ግንባታ በዚህ ጊዜ ለሥራ ዝግጁ ይሆናል ተብሎ ሲታቀድ፣ ከፋብሪካ የመድረሻ ጊዜ ጋር መርሐ ግብርን በማስተካከል የሸንኮራ አገዳ ልማቱን የማድረስ፣ የሠራተኛ ኃይሉን የማሰባሰብና ከተማ ቀረሽ የሠራተኛ መኖሪያን የማሟላት ሥራ ይካሄዳሉ፡፡ እንግዲህ ቃል በተገባው ጊዜ መሠረት መድረስ በነበረባቸው ፋብሪካዎች አልደረሱም ሲባል ጉድ ፍጥጥ ማለቱን ልብ በሉ፡፡ ከስኳር ኮርፖሬሽን ሪፖርት እንደተረዳነው፣ የኩራዝ አንድና የጣና በለስ ግንባታን ያካሄደው ብኢኮ የገንዘብ እጥረት አለብኝ ባለው መሠረት በልዩ ሁኔታ ከአገር ውስጥ ባንክ ብድር ተመቻችቶ በስኳር ኮርፖሬሽን ስም ቅድመ ክፍያ ተደርጎለትም ግንባታው በመዘግየቱ ምክንያት፣ ኩራዝ አንድ የስኳር ልማት ላይ ሠራተኛ ተቀጥሮ ወደ ሃያ ሚሊዮን በዓመት ያለ ሥራ የመክፈል ቀውስ ውስጥ መገባቱ፣ በ870 ሔክታር ላይ የለማ ሸንኮራ ዕድገቱንም ስኳሩንም ጨርሶ እንዳቆመና መወገዱ እንደማይቀር፣ ጣና በለስ ላይ 300 ሔክታር አገዳ እንደተወገደ በሪፖርቱ ጊዜ ተነግሯል፡፡

የዲዛይን ችግር ሌላው ጣጣ ነው፡፡ በተንዳሆ ልማት፣ በፋብሪካና በአገዳ እርሻ የመጨረሻ ጠርዝ መሀል እስከ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚደርስ መኖሩ ከፍተኛ የማጓጓዣ ወጪ የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ በሠራተኛ ቤቶች ግንባታ በኩልም ጥራታቸው የተጓደለና ለአካባቢው አየር ፀባይ የሚስማማ የዲዛይን ለውጥና ድጋሚ ሥራ የሚጠይቁ ግንባታዎች አጋጥመዋል፡፡ መጠለያ የለሽ የዕቃዎች አቀማመጥን  እንተወውና እላፊ ቅድመ ክፍያ አከናውኖ ውልን ለማቋረጥ መቸገር እንደታየ ሁሉ፣ ግንባታ ሳይጠናቀቅ እንዲያቋርጡ የተደረጉ የሥራ ተቋራጭንና አማካሪን ያለዝርዝር ርክክብ የማሰናበት ዝርክርክነትም ተፈጽሟል፡፡ እነዚህን በመሳሰሉት የጥፋት ሥራዎች ውስጥ የመቦጥቦጥና የማስቦጥበጥ አባዜ እንደሚኖር ማስተዋል አይሳንም፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን ሪፖርት ሌላም የማይታመን ጉድ አሰምቶናል፡፡ ቅሌት በማያልቅበት ተንዳሆ ውስጥ የስኳር ልማቱ ሠራተኞች ያልሆኑ ሰዎች (ካድሬ፣ አዛውንትና ሕፃናት) ደመወዝ የሚበሉበትም ሁኔታ ነበር፡፡ እንዲያውም የስኳር ልማቱ በጥቅሉ ብዙ ቢሊዮን ብር የተሰማራበት መሆኑና ሪፖርት አቅራቢዎቹ እንደጠቆሙን ኮርፖሬሽኑ የአገሪቱን ብር ያሰባሰበ የብር ጎተራ ተደርጎ መታየቱን፣ ኮርፖሬሽኑ ውስጥ ከተከሰቱ ለዘረፋ የተመቹ ብልሽቶና ከሌሎች ወገኖች ጋር ኮርፖሬሽኑ ከነበሩበት ውጣ ውረዶች ጋር ስናገናዝበው፣ ከማያልቅ የብር ጎተራ ውስጥ የድርሻን ከመዝገን ፍላጎት ጋር ብዙ ግጥሚያ የነበረም ይመስላል፡፡ ያለውድድርና እንደ ኩባንያ የኪሳራ ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ እንዲሳተፉ በተደረጉት ብኢኮና ክልላዊ የውኃ ሥራዎች ውስጥ አቅምን በማጎልበትም ሆነ በሌላ መልክ የሚገለጽ የድርሻ አዚም አይኖርም ብሎ ማሰብ በዝናብ ውስጥ ከዛፍ ላይ ያልረጠበ ቅጠል ለማግኘት እንደመሞከር ይሆናል፡፡ ጭቃማ ውኃን ለማጣራት (በተንዳሆ) መሬት ለማግኘት ከአስተዳደሩ ጋር በታየው ትንንቅና በተነሺዎች በኩል በነበረው ወፍራም የካሳ ፍላጎት ውስጥ ሁሉ ሌላው ከሚጎምደው ሲሳይ ውስጥ፣ እኛም ይርከፍከፍብን የሚል እስትንፋስ ሳይኖር አልቀረም፡፡

4) በአጠቃላይ በብዙ መንግሥታዊ የኢኮኖሚ ልማትና የሕዝብ አገልግሎቶች ውስጥ የምናገኛቸውን ችግሮች በስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ አላጣናቸውም፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽን ልምድ አብነት ሆኖ በአገራችን ልማት ውስጥ ነቀርሳ የሆኑ ችግሮችን (ከጉንጭ በላይ ለመጉረስ እንደመጣጣር ያለ፣ አቅምና ችሎታን ያላገናዘበ አቃጅነትን፣ የቅንጅት ጉድለትን፣ የተንከወከወ ሥራን፣ ዝርክርክ አያያዝንና አሠራርን፣ ፖለቲካዊ አሸማቃቂነትን፣ አፍ ጠለፋንና ስም ልጠፋን፣ ጥፋትና ድክመት መደባበቅን) አጉልቶ አሳይቶናል፡፡ የኢሕአዴግ ልማቱ ያለ እኔ አይሳካም ባይነት ይህን መሳይ ጉድ ያለበት ነው፡፡ የአንድ ኢሕአዴግ ፓርቲና የካድሬዎቹ ጥርነፋዊ አነቃናቂነት ለኢትዮጵያ እንደሚያንስ፣ አንድ የእሱ መሪነትና ክትትል ልማቱን በጥራት ማስኬድ እንደማያስችል ከዚህ በላይ ምን ማረጋገጫ ያሻል!?

እንዲህ ያለው ገመና ከተገለጠም በኋላ ኢሕአዴግ አለኝ የሚለው መፍትሔ የ‹‹ካይዘን››ን አሠራር አሰፍናለሁ፣ ኦዲተሮች በነፃነት እንዲሠሩ አደርጋለሁ፣ ሥራዎችን ከሥር ከሥር የመቆጣጠሪያና የመገምገሚያ ሥልት እዘረጋለሁ፣ ወዘተ. የሚል ነው፡፡ የአገሪቱ እውነታ የሚለው ደግሞ የአንድ ፓርቲና የመንግሥታዊ ቢሮክራሲ ዓይን አይበቃኝም ነው፡፡ እስከዛሬ ስንቱ ማሻሻያ እየተሞከረ እንደተውሸለሸለ ሁሉ፣ የአሁኑም መፍትሔ የማይውሸለሸለው በየትኛው ዋስትና? መፍትሔ እንደይውሸለሸልና እየተጣራ እንዲሄድ፣ ችግሮችም ውለው እያደሩ ጉዳት እንዳያደርሱ ዋስትናው ከመንግሥት ቢሮክራሲ ውጪ የሆነ ትልቅ ማይክሮስኮፕ የሕዝብና የነፃ ሚዲያ ማይክሮስኮፕ ነው፡፡ ልማቱ የዚህ ዓይነት ዓይን ይሻል፡፡ የኅብረተሰቡን የእኔ ባይ ተቆርቋሪነት ይሻል፡፡

የልማት ፕሮጀክት የዘረፋ ዋሻና ለአካባቢው ኅብረተሰብ የማይተርፍ የሌሎች/የጥቂቶች መክበሪያ፣ የአካባቢን ድንግል ሀብት ማራቆቻ ተደርጎ ሲታይ ትልቅ የተቀባይነት ምች አግኝቶታል ማለት ነው፡፡ ተቀባይነትን የማጣት ውድቀት አጥር የለሽ መሆን ነው፡፡ የተቀባይነት አጥር ባለሦስት ዙር ነው፡፡ ሙስናና ዝርክርክነትን አሸንፎ ስም ማግኘትና ለሌላው አርዓያ መሆን የመጀመሪያው የውስጥ አጥር ነው፡፡ በአካባቢ ኅብረተሰብ ዘንድ ጥቅሜ/አለኝታዬ ለመባል መብቃት ሁለተኛው የደኅንነት መጠበቂያ አጥር ነው፡፡ በተንዳሆ የአገዳ እርሻ ላይ ከብት የመልቀቅ ችግር የደረሰው የኮርፖሬሽኑ እርሻ በአካባቢው ሰዎች የአገዳ እርሻ የተሠራ አጥር ስላላበጀ ነበር፡፡ ሦስተኛውና ትልቁ አጥር፣ የክልልና የፌዴራል አስተዳደሮች ‹‹የእኔ›› ለመባል ያበቃ የፖለቲካ ተቀባይነት ማግኘት መቻላቸው ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱን የደኅንነት አጥር አለመሟላት የጠመንጃና የሽቦ አጥር ጥበቃ አይተካውም፡፡ ዛሬ ባይደርስ ነገ የሚደርስ የጥቃት ተጋላጭነት አብሮት ይኖራል፡፡ በቁጡው ቅዋሜ ጊዜ በመተሃራ፣ በወንጂና በፊንጫም ሆነ በሌሎች የልማት ተቋማት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት የዚሁ ማሳያ ነው፡፡

በልማት ተቋማት ላይ እልህ የሚወጣ ቅዋሜ አቅም ሲያገኝ ገዥዎችንም ለመሰልቀጥ አይመለስም፡፡ ሕዝብ ለገዥዎቹ መሬት የሚሆነው ኑሮው በቁሳዊና በመንፈሳዊ ፈርጆቹ የመሻሻል ጉዞ ውስጥ ከገባ ነው፡፡ ማለትም ከእህል ውኃና ምናምን ባሻገር ሰው በድንፋታና በሸር ከመሸማቀቅና በበደል ከመቁሰል ወጥቶ ነፃነቶችን ማጣጣምና በሰውነቱ መከበርን ይሻል፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱን የባለመብትነት ኑሮ መጎናፀፍ ይቅርና የሆድና የመጠለያ ፍላጎትን ማሟላት እንኳ ለተራው ዜጋ እየከበደ ነው፡፡ አሥራ ሦስት ዓመታት ያስቆጠረው የልማት ሩጫ ለገዥው ክፍል የተወሰነ ድጋፍ ቢያስገኝም የቅዋሜን፣ የጥላቻንና የግጭትን የማደግ አዝማሚያ አልቀየረም፡፡ ከዜና ምንጭነት እስከ አሠራጭነት ድረስ የሚዲያ አውታራትን አንሰራፍቶ የሚካሄደው የመረጃ አፈናና አወድሱኝ ባይ (ገመናን መግለጽ የማይወድ) የልማት ‹‹ስኬቶች›› ባዘቶ፣ የትኛውንም ዓይነት የሹክሽክታ ግባሶና ክፉ ወሬ ሁሉ ለመዋጥ ሕዝብን ማጋለጡ እንደቀጠለ ነው፡፡ ውሎ እያደረ ለቄስ የተተወውን ገመና ሕዝብ ባወቀ ጊዜ ደግሞ ያንኑ ያህል የመንግሥት ተቀባይነትና ተከባሪነት ፀሐይ እንዳደረቀው የጅብ ጥላ ይቀላል፡፡

የቱንም ያህል ልማት ቢካሄድ አገዛዙ ምሬትና ጥላቻ የሚያበዛና ቁጣ የሚጭር ጥፋት የማያልቅበት መሆኑም ሌላ የድጋፍ ፀር ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ ማቆሚያ ማቅለያ ማጣቱ፣ አንዱ ክፍል ሲፎክትና በዓይን ሲቀላውጥ በአንድ ጀምበር ሰማይ የሚወጡ ምንሽንሾች መፈጠራቸው፣ አስተዳደራዊ በደሉ፣ የፕሮፓጋንዳው ዓይነ ደረቅነት፣ እነዚህን የመሳሰሉት ሁሉ ልማቱ የሚያስገኘውን ጎሽታ መልሰው ሲያጥቡና ምሬት ሲያከማቹ ኖረዋል፡፡ የቅርቡን ብናስታውስ ከፍተኛ የመጠለያ ችግርና ውድነት ባለበት አዲስ አበባ ውስጥ፣ ችግር በማጠራቀምና የጨረቃ ቤትን ሕጋዊ እያደረጉ ሕገወጥነትን በማደፋፈር ራሱ አገዛዙ ተጠያቂ ሆኖ ሳለ፣ ያላንዳች ቶሎ ደራሽ መፍትሔ (ያውም በክረምት) በቦሌ ወረገኑና ላፍቶ ሠፈሮች ውስጥ በአንድ ጊዜ ብዙ ሺዎችን ቤት የለሽ ያደረገ የማፍረስ ዘመቻ ብዙ ቆሽት አሳርሯል፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ቅዋሜዎችንና ጥያቄዎችን ወደ ንግግር መድረክ አቅርቦ መፍትሔ በመፈለግ ፈንታ፣ ‹‹ሕገወጥ ሠልፍ››፣ ‹‹የአመፅ ተግባር›› እያሉ በኃይል ለመቅጣትና በስብከት ለማቀዝቀዝ መሞከር፣ ይኸው አሁን እንደምናየው የተዳፈኑ ብሶቶች ደጅ ወጥተው የተስፋፋ ቅዋሜ እንዲፈጥሩ አግዟል፡፡ ልማትን ቶሎ በቶሎ አግተልትሎ በሕዝብ ድጋፍና ውዳሴ የመንፈላሰሱ ሥሌትም እጅግ የተሳሳተ መሆኑ በዚሁ አስገምጋሚ ቅዋሜ አማካይነት ወለል ብሏል፡፡

እናም ካለኔ በቀር ልማታዊ የለምና በሥልጣን መቆየት ያለብኝ እኔ ብቻ ነኝ እያሉ ሌላውን አላስቀርብ ከማለት መውጣትና እጅ ለእጅ ተያይዞ ዴሞክራሲ ውስጥ መግባት፣ ለገዥው ፓርቲም ለልማቱም ለሕዝቡም እጅግ የሚበጅ ነው፡፡ የልማቱ ከውትፍትፍ ሥራ፣ ከምዝበራ፣ በድንገተኛ የቅዋሜ ደምAnchor ፍላት ከመጠቃት የመላቀቁ ዕድል፤ ትምህርትና ሥልጠናው የፈጠራ ችሎታን እያስታጠቀ ለአገሪቱ የጥበብ ንጣፍ የመሆኑ ነገር፣ የመንግሥት መሪነትና የሕዝብ ተቀባይነት የመገናኘታቸው ዕድል ሁሉ ያለው በዴሞክራሲ ጎዳና ውስጥ ነው፡፡ እውነታው ይህን ያህል ቁልጭ ያለ ሆኖ ሳለ፣ በፀጥታ በፓርቲያዊ ፕሮፓጋንዳ ጥርነፋ ጠምዶ የመግዛት ዘይቤ የፈለፈላቸው ችግሮች የአገዛዝ ዘይቤውንም አገርንም ሊበሉ በደረሱበት በዚህ ምዕራፍ እንኳ፣ ኢሕአዴግ ለራሱም ለሕዝብም ብሎ የዴሞክራሲን ጎዳና ከተቃዋሚዎቹ ጋር የመጥረግ አንጀት አላሳየም፡፡ የጥንትም ቄስ ሆነ የዛሬ ቄስ ወደ እግዜር ቅረቡ፣ ፆሙ፣ ፀልዩ ብሎ ከማለት አይርቅም፡፡ ጭላንጭል ነገር አናጣበትም ተብሎ ተስፋ የተደረገበት የነሐሴ 2008 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባም እንደ ሁልጊዜው ከእኔ ጋር ከሆናችሁ የማይገፋ ዳገት አይኖርም ከማለት ያለፈ የሰጠን የለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...