Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉለውጥ መምራት ወይም በለውጥ መገፋትና መገለል?

ለውጥ መምራት ወይም በለውጥ መገፋትና መገለል?

ቀን:

ወቅቱ ለኢሕአዴግ ያቀረበለት ምርጫ ነው

በሞላ ዘገዬ

ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ አገራዊ ፈተና ገጥሞናል። በአገራችን በበርካታ አካባቢዎች የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የቀጠፉ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ግጭቶች ከመፈታት ይልቅ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡና የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ወደከፋ ደረጃ እየወሰዱት ነው፡፡ አገራችን የገባችበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ እከሌ ከከሌ ሳይባል ሁላችንም ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ ስለተረዱ ይመስላል፣ የቀድሞ የሕወሓት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ በመገናኛ ብዙኃን በመቅረብ የችግሮቹን መንስዔዎች ማንሳትና የመፍትሔ ሐሳብ የሚሉትን መጠቆም ጀምረዋል። እኔም በዛሬው ጽሑፌ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ ሪፖርተር ጋዜጣ (ሐምሌ 17 እና 24 ቀን 2008 ዓ.ም.) ላይ በሁለት ክፍል ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ ተንተርሼ፣ ለገጠሙን አገራዊ ፈተናዎች መንስዔ ናቸው የምላቸውን ጉዳዮች እገልጽና እነዚህን አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍታት ያስችላሉ የምላቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ለመጠቆም እሞክራለሁ።

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን በአገራችን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት “በሠለጠነ መንገድ ተወያይተን እንፍታው” ሲሉ በሥልጣን ላይ ለሚገኙት ወገኖች፣ ለተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና የአገራቸው ሁኔታ ለሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በእኔ አስተያየት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ አገራችን የገባችበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ አሳስቧቸው በሥልጣን ላይ ያሉት አካላት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሌሎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሰከነ መንገድ እንዲወያዩና መላ እንዲመቱ ጥሪ ማቅረባቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። እኔም የአገራቸው ሁኔታ ከሚያሳስባቸው ወገኖች አንዱ ነኝ ብዬ ስለማምን፣ የጀኔራሉን ጥሪ ተቀብዬ ይህን ጽሑፍ አቅርቤያለሁ፡፡  

ጽሑፉ ሁለት ክፍሎች ይኖሩታል። በመጀመርያው ክፍል ጄኔራል ፃድቃን ያለንበትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ በተመለከተ ያቀረቧቸውን ትንታኔዎች ተቀብለን፣ “አሁን ወዳለንበት ሁኔታ እንዴት ገባን?” በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር ባቀረቧቸው ነጥቦች ላይ ስለማልስማማ፣ የራሴን ምልከታ እገልጻለሁ። በሁለተኛው ክፍል ፃድቃን ያስቀመጧቸውን ቢሆኖች (Scenarios) ተቀብዬ፣ ነገር ግን የመፍትሔ ሐሳቦች ብለው ባቀረቧቸው አስተያየቶች ላይ የሚጎድል ነገር ያለ ስለሚመስለኝ፣ በሁለት ንዑስ ርዕሶች ከፍዬ መጨመር አለባቸው የምላቸውን ነጥቦች እሰነዝራለሁ።

የችግሩ ምንጭ ምንድነው? 

እኔም እንደ ጄኔራል ፃድቃን አገራችን ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው እላለሁ። በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚቀሰቀሱትና የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚቀጥፉት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ምላሽ ያስፈልጋቸዋል። በበኩሌ ለሕዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ የሆነና የጉዳዩን ባለቤት (ሕዝቡን) ያሳተፈ ምላሻ ካልተሰጠ በስተቀር አገራችን ወደከፋ ሁኔታ ልትገባ ትችላለች የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለኝ። ብሔረሰባዊና ሃይማኖታዊ መልክ ያላቸው የሕዝብ ልዩነቶች፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና በደሃውና በሀብታሙ መካከል ያለው የሀብት ክፍፍል መራራቅ፣ በወጣቱ አካባቢ የሚታየው ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነትና ተስፋ ማጣት፣ በአገራችን የሰፈነው መረን የለቀቀ ሙስናና ሕዝብ ያማረረ የመልካም አስተዳደር ችግር እርስ በርሳቸው እየተመጋገቡ፣ ችግሮች መፈታት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ እሰጋለሁ። በመንግሥት በኩል መሠረታዊ የሆነውን ችግር ወደ መልካም አስተዳደር ችግር ለማውረድ የሚደረገው የተለመደው አካሄድ ጨርሶ መፍትሔ እንደማይሆን እረዳለሁ፡፡ ሕዝብንና አገርን ውድ ዋጋ ያስከፍላል ብዬም አምናለሁ። በሚያሳዝን ሁኔታ ሕዝቡ የሚጠይቀው ሌላ፣ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉት ኃይሎች የሚሰጡት ምላሽ ሌላ እየሆነ፣ በሕዝቡና በመንግሥት መካከል ትልቅ ገደል እየተፈጠረ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያሉት አካላት በኩል አሁንም እንደተለመደው የሚበጅህን የምናውቅልህ እኛ ነን የሚል አደገኛ አካሄድ እየተራመደ ነው፡፡ ሕዝቡ የሚበጀውን እንደማያውቅ፣ ሁልጊዜም ሞግዚት እንደሚያስፈልገውና እኛ የምንልህን ብቻ ተቀበል እየተባለ ነው፡፡ ይህ ነው የበሽታው ሁሉ ምንጭ፡፡

በእኔ አስተያየት የችግሮች ሁሉ ምንጭ ከፖለቲካ ባሕላችን ጋር የተያያዘ ነው። ጄኔራል ፃድቃን ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣን እስኪይዝ ድረስ ዴሞክራሲያዊ እንደነበር ጠቅሰው ሲያበቁ፣ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ የድርጅቱን ዴሞክራሲያዊነት የሚፈታተኑ ሦስት ትልልቅ ክንዋኔዎች መፈጸማቸውን ይነግሩናል። ፃድቃን እንደሚሉት “ኢሕአዴግ አንደኛ ከኦነግ ጋር የነበረውን ልዩነት የፈታበትን መንገድ፣ ሁለተኛ በሕወሓት ውስጥ የተፈጠረው የውስጠ ፓርቲ ቀውስ የተፈታበት ሒደትና ሦስተኛ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረው ቀውስ የተፈታበት መንገድ የኢሕአዴግን ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ያጎሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ተቋማዊ እንዲሆን ያደረጉ ክንዋኔዎች ናቸው፤” እኔ በዚህ አልስማማም። በእኔ አስተያየት ችግሩ የሚያያዘው ከድርጅቱ ተፈጥሮ ጋር ነው። ላብራራው።

ችግሩ የሚጀምረው ከሕወሓት መንታ ማንነት ነው ብዬ አስባለሁ። ሕወሓት ሲመሠረት በአንድ በኩል ማርክሲስታዊ ሌኒኒስታዊ፣ በሌላ በኩል የትግራይ ብሔርተኛ ሆኖ ነው የጀመረው፡፡ እነዚህ ድምር ማንነቶች ዴሞክራሲያዊ ቁመና እንዲኖረው አይፈቅዱለትም።

ሕወሓት እንደ ሌሎች በኢትዮጵያ አብዮት ዘመን እንደተመሠረቱ ድርጅቶች፣ ሌኒኒስትና ስታሊኒስት በሆኑ አስተምህሮዎች የተገነባ በመሆኑ ቅራኔዎችንና የቅራኔዎችን አፈታት በዚሁ ርዕዮተ ዓለም መነጽር የሚያይና የሚፈታ ድርጅት ነው። በዚህ አስተምህሮ መሠረት አንድ ሁሉን አውቃለሁ የሚል፣ ወይም ለሁሉም ችግሮች መፍትሔው እኔ ነኝ የሚል ድርጅት እንዳለ ስለሚታመን፣ ከዚያ ውጪ ያለው ኃይል ሁሉ ወይ የዚህ ድርጅት ደጋፊ ይሆናል፣ ካልሆነ ደግሞ ጠላት ነውና መደምሰስ አለበት ይባላል። ልዩነት አይከበርም። ልዩነትን ለዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መገበር ያስፈልጋል። በፓርቲ አባላት መካከል ውይይትና ክርክር ይደረጋል ቢባልም፣ በአብዛኛው ውይይቶችና ክርክሮች የሚደረጉት ጥቂት የፖሊት ቢሮ አባላት ወይም የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ሲሆን፣ የተወያዮች ሚና የውሳኔ ሐሳቡን ወይም ሰነዱን ማፅደቅ ወይም ማዳበር ብቻ ነው። ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚደረጉ ድርድሮችም ቢሆኑ የችግር መፍቻና የዘላቂ ሰላም መፍጠሪያ መንገዶች ሳይሆኑ፣ ማዘናጊያና ጊዜ መግዣ ናቸው። እነዚህ ድርጀቶች መቶ በመቶ ማሸነፍን እንጂ፣ የዴሞክራሲ እሴቶች የሆኑትን ከልብ መወያየትን፣ መደራደርንና ሰጥቶ መቀበልን አይቀበሉም። ለምሳሌ ያህል ሕወሓት በረኻ በነበረበት ወቅት ዴሞክራሲያዊ ነበረ ቢባልም፣ በትግራይ ሕዝብ ስም ከተደራጁ ድርጅቶችና በአካባቢው ይንቀሳቀሱ ከነበሩ ኅብረ ብሔራዊ ንቅናቄዎች ጋር የነበረውን ቅራኔ የፈታበት መንገድም ሆነ፣ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ከኦነግና ከቅንጅት ጋር የነበረውን ቅራኔ እንዲሁም በራሱ በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል የፈታበት መንገድ ሁሉ ይህንን መቶ በመቶ አሸናፊ የመሆን ባሕርይ የሚያሳዩ ናቸው እንጂ፣ ዴሞክራሲያዊ ባሕሪውን የሚገልጹ አልነበሩም፣ አይደሉም፡፡

በመሠረቱ ሁሉም በበ1960ዎቹ ዘመን የተፈጠሩ ስታሊኒስትና ማኦይስት ድርጅቶች አንድ ብቸኛና ያለቀለት መፍትሔ እንዳላቸው አድርጎ የማቅረብ በሽታ ነበረባቸው፣ አለባቸው። እነሱ ከሚያቀርቡት የመፍትሔ ሐሳብ ውጪ የተለየ አስተያየትና የተለየ አቀራረብ ሊኖር አይችልም የሚለው፣ ወይም ደግሞ ከዚህ ውጪ አማራጭ የለም የሚለው አመለካከት ምርጫ የሚያሳጣ ብቻ ሳይሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ የአዕምሮ ነፃነትን የሚጋፋ አካሄድ መሆኑ ግልጽ ይመስለኛል። በማንኛውም ዘዴ ቢሆን ትልቅ ጫና የሚፈጥረውና ነፃነት ገፋፊ የሚሆነው አማራጮችን ዘግቶ ልክ አንድ ብቸኛ መፍትሔ እንዳለ አድርጎ የማቅረብ አካሄድ ነው ለማለት ይቻላል። ‹ወይ እኔን ትደግፍና የጥቅም ተካፋይ ትሆናለህ፣ ካልሆነ ግን በኅልውናዬ ላይ መጥተሃልና ትደመሰሳለህ› በሚል ፀረ አማራጭና ፀረ ነፃነት አስተሳሰብ መመራት ትልቅ መከራ ነው።

በሁለተኝነትና በሦስተኝነት፣ የድርጅቱ ኢዴሞክራሲያዊነት የሚገለጸው ሕወሓትዎች (ኢሕአዴግአውያን) በ1983 ዓ.ም. የመንግሥትን ሥልጣን ሲቆጣጠሩ ያዋቀሩት የሽግግር መንግሥት ሁሉንም ወገን ያላሳተፈ መሆኑ፣ ከዚያም በኋላ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅም አሁን የሚነገርለትን ያህል ሕዝቡን ያላሳተፈ መሆኑ ነው። ለዚህ ነው ጄኔራል ፃድቃን የዘረዘሯቸው ችግሮች የድርጅቱ ኢዴሞክራሲያዊነት ውጤቶች እንጂ መንስዔ ናቸው ብዬ የማልቀበላቸው፡፡

ፖለቲካችን ከተለመደው የሴራ ፖለቲካ ሊፈወስ ይገባል

ከፍ ብዬ እንደገለጽኩት ጄኔራል ፃድቃን  የኢሕአዴግን ዴሞክራሲያዊነት የተፈታተኑ ያሏቸው ክንዋኔዎች በሙሉ ከድርጅቱ ተፈጥሮ አንፃር የሚጠበቁ እንጂ ጨርሶ እንግዳ ነገሮች አይደሉም። አሁን የሚታየው ችግርም የዚህ አስተሳስበ ውጤት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከዴሞክራሲ ጋር የተጣላ መሆኑን ተቀብሎ በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና አሠራር እስካልተቀየረ ድረስ፣ ለይስሙላ ስለመድበለ ሐሳብ (Pluralism) እና መድበለ ፓርቲ ሥርዓት መስበኩ ችግር እንጂ በጎ ውጤት አያስገኝም። እስከዛሬም አላስገኘም፡፡ ውሳኔ ከወሰኑ በኋላ ሕዝብን ማወያየት፣ የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ወገኖች (አሁን እንደሚታየው) በፀረ ልማት፣ በፀረ ሰላምነትና በውጭ ኃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚነት መፈረጅም ቢሆን በችግር ላይ ችግር ይፈጥራል እንጂ፣ የሚጠቅም አካሄድ አይደለም።

ከገባንበት አሳሳቢ ሁኔታ እንድንወጣ ካስፈለገ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ዕጣ ፈንታ በአንድ ድርጅት፣ ከዚያም ውስጥ በጥቂት የፖሊት ቢሮ አባላት የሚወሰንበት ሒደት መለወጥ ይኖርበታል። ሌሎችም ስለአገራቸው እንደሚቆረቆሩ፣ የሌሎችም ሐሳብ ሊጠቅም እንደሚችል ከልብ መቀበል ያስፈልጋል። ለዚህ ነው ከሁሉ አስቀድሞ ከዚህ የሴራ ፖለቲካ በሽታ መፈወስ ያስፈልጋል የምለው። የእኛ ትውልድ (ኢሕአዴግን ጨምሮ) ራሱን ከዚህ ድርጅታዊ አሠራርና የሴራ ፖለቲካ መፈወስ ካልቻለ፣ ቢያንስ ይህን አጥፊ አካሄድ ለተተኪው ትውልድ ማውረስ የለበትም። ወጣቱ ትውልድ በዚህ አስተሳሰብ ያልተበከለ፣ ልዩነትን የሚያከብርና ለውይይት ዝግጁ የሆነ ኃይል እንዲሆን ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። አሁን እንደሚታየው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው ጽንፈኛ የጎሳ ብሔርተኝነት፣ ከነባሩ የሴራና የመጠፋፋት ፖለቲካ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሒደት የሚያስከትለው ጥፋት የትየለሌ ነው፡፡

እዚህ ላይ ለበርካታ ዓመታት አምኜበት ስታገልለት የኖርኩትን አስተሳሰብ በተመለከተ ያለኝን አስተያየት ግልጽ ላድርግ። ደጋግሜ ከሴራ ፖለቲካ እንፈወስ፣ ከሚስጥራዊ ድርጅታዊ አሠራር እንላቀቅ፣ ዜጎች የመሰላቸውን ነገር ሳይፈሩና ምን ይደርስብኛል ሳይሉ የሚናገሩበትና የሚከራከሩበት መንገድ ይዘርጋ፣ ወዘተ. እያልኩ ስከራከርና ለዚህ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ትልቅ መሰናክል የሆነውን ሌሊኒስት፣ ስታሊኒስትና ማኦይስት አስተምህሮ ስተች፣ በመድበለ ሐሳብና በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚያምኑ፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ የሚታገሉና ዝቅተኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል ወገንተኛ የሆኑ፣ ዴሞክራሲያዊ ሶሻሊስት ፓርቲዎች (Democratic Socialists) መኖር የለባቸውም ወይም አያስፈልጉም እያልኩ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ።

የእኔ ክርክር በተለምዶ ‹ያ ትውልድ› እየተባለ የሚጠራው የእኔ ትውልድ የተጠመቀበትን፣ ለብዙዎች ሞት ምክንያት የሆነውንና አስካሁንም ድረስ በሁሉም አቅጣጫ ማዕከላዊ ቦታ ይዞ የፖለቲካ ባሕላችን እንዳይሻሻል አንቆ የያዘውን አስተሳሰብ የተመለከተ ነው። ትናንትና ጥያቄዎችን በውይይትና በድርድር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ፋሽስት፣ አናርኪስት፣ ወንበዴ፣ የዓረብ ተላላኪ፣ ወዘተ እየተባባልን የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ወገኖች እየፈረጅን ምን ላይ እንደደረስን እናውቃለን። አሁንም ቢሆን ከታሪክ ትምህርት ቀስሞ ፍረጃውን ማቆምና ለውይይት መዘጋጀቱ ነው የሚበጀው። እንዲያውም በእኔ አስተያየት አገራችን አሁን ከገባችበት እጅግ አሳሳቢና ፈታኝ ሁኔታ እንድትወጣና ዘላቂ የሆነ ሰላምና ልማት እንዲመጣ ካስፈለገ፣ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉት የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ብቻ ሳይሆን የትጥቅ ትግል ከሚያደርጉት ድርጅቶችም ጋር ለመወያየት መዘጋጀት ይኖርበታል።

በመንግሥት በኩል የሕዝብን ጥያቄ ያለመቀበል፣ መሠረታዊ ምላሽ የሚያስፈልጋቸውን ጥያቄችን ወደ ተራ የመልካም አስተዳደር ጥያቄነት የማውረድና ጥያቄው የጥቂቶች እንጂ የሕዝብ ጥያቄ አይደለም እየተባለ ሌላ የቤት ሥራ የማስቀመጥ አካሄድ ይስተዋላል። ይኼ አካሄድ መታረም ይኖርበታል። የሕዝብ ጥያቄዎችን በጥይትና ወጣቶችን በገፍ በማሰር ለመመለስ የሚደረገው ሙከራም ጥያቄውን ለጊዜው ያዳፍነው እንደሆነ እንጂ ችግሩን ጨርሶ አይፈታውም። መፍትሔው ሀቁን መቀበል ነው፣ መፍትሔው የሕዝብን ብሶት ከምር ማዳመጥ ነው፣ መፍትሔው ሕዝብ የሚበጀውን መምረጥ እንደሚችል ከልብ ማመን ነው፣ መፍትሔው ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን መንገድ መቀየስ ነው፡፡

የሕገ መንግሥት ‘ሪፎርም’ እና ብሔራዊ መግባባት

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፣ “አገራችን አሁን ካለችበት ቀውስ እንድትወጣ፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡትን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ያለምንም መሸራረፍ ተግባር ላይ በማዋል ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ያለምንም ተፅዕኖ በሰላማዊ ፖለቲካዊ ውድድር የሚሳተፉበትን ሁኔታ ማመቻቸት መጀመር አለበት፤” ሲሉ ጽፈዋል። ተገቢ አስተያየት ነው። ስለኅብረተሰብ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ ስለመተማመን፣ ስለነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባነሷቸው ነጥቦች ላይም እስማማለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተሰጠውን ተልዕኮ ብቻ እንዲፈጽም እንጂ ከየትኛውም ድርጅት ጋር ወገንተኛ ሆኖ እንዳይቆም፣ ይልቁንም “የፀጥታ ኃይሎች እንደ ሌሎች የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካላት በማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከመግባት ሙሉ በሙሉ መቆጠብ ይኖርባቸዋል። ዋናው ሥራቸው የአገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ነው፤” ያሉት ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ ነው።

የገለልተኝነታቸው ሁኔታ ብዙ ጥያቄ ስለሚነሳበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የመንግሥት ሚዲያ ቦርድ ያቀረቡት አስተያየትም በጣም ጥሩ ነው። ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው ጠቃሚ ነጥቦች ተነስተዋል። በአጠቃላይ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች በሥራ ላይ መዋል አለባቸው የሚለው አስተያየት የሚደገፍ ነው።

ሕዝብ ነፃነቱ ተጠብቆ ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ የመሰለውን እንዲናገር ካስፈለገ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የደኅነት ተቋማትና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች በተግባር ገለልተኛነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን ያስፈልጋል። መገናኛ ብዙኃንና የፍትሕ አካላት (ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ማረሚያ ቤት) ገለልተኛነትም እንዲሁ ሕገ መንግሥቱ በሚለው መሠረት በተግባር መረጋገጥ አለበት። እስከዚህ ድረስ ከሌተና ጄኔራል ፃድቃን ጋር እስማማለሁ።

ሆኖም ሕገ መንግሥቱ የዜጎችን መብት ለመጠበቅና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያግዙ በርካታ ድንጋጌዎች ቢኖሩትም፣ ከብዙ አቅጣጫዎች ጥያቄ የሚነሳበትና ከፍተኛ የሆነ የቅቡልነት (Legitmacy) ችግር ያለበት ሰነድ መሆኑን መካድ አይቻልም። ራሳቸው ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ሕገ መንግሥቱን አስመልክተው ሲገልጹ፣ “ሕገ መንግሥቱ በሕዝባዊ የትጥቅ ትግሉ ውስጥ አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ መንፈስ የተላበሰ፣ ኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት እንዲኖር የሚፈለገውን የመንግሥት አሠራርና ባሕርይ መለኪያ (Standard) ይሆናል ብለን ያስቀመጥነው የትጥቅ ትግሉ ድሎች መቋጫ ነበር እላለሁ፤” ያሉት፣ ሰነዱ ሕዝቡ አስተያየቱን ያልሰጠበትና በበቂ ያልመከረበት መሆኑን የሚጠቁም ነው። “ሁኔታው በፈቀደው መጠን ሕዝብ እንዲመክርበትና አስተያየቱን እንዲሰጥበት ተደርጓል፤” የሚለው አስተያየት አሳማኝ አይመስለኝም። የማያከራክረው ሀቅ ሰነዱ ምንም ያህል ጠቃሚ ድንጋጌዎች ያካተተ ሕገ መንግሥት ቢሆንም፣ ከፍተኛ ሆነ የቅቡልነት ችግር ያለበት ሰነድ መሆኑ ነው። በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱ ክፍፍል የፈጠሩ አንቀጾች መኖራቸውም እውነት ነው። ስለሆነም ከሁሉ በፊት ይህን ሕገ መንግሥት አንድ በትጥቅ ትግል ያሸነፈ ኃይል የጫነው ሰነድ ነው ከመባል ለማዳን፣ ወዲያውም በእነዚህ የሕዝብ ክፍፍል በፈጠሩ አንቀጾች ላይ አስተያየት እንዲሰጥና በሰነዱ መካተት ሲገባቸው ሳይካተቱ የቀሩ ሌሎች አንቀጾችን ለማካተት፣ እንዲሁም የሕገ መንግሥቱን ተቀባይነቱን ለመጨመር፣ የሕገ መንግሥት ሪፎርም የተሻለ አማራጭ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ከዚህ ቀደም በውይይት መጽሔት (ከቁጥር 01 እስከ 03 በተከታታይ) ባቀርብኳቸው ጽሑፎች ለመጠቆም እንደሞከርኩት፣ የሕገ መንግሥት ‹ሪፎርም› ሒደት መንግሥትና  ሕዝብን ለማቀራረብ፣  በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ውይይት ለመክፈት፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ሕዝብ የአገሪቱን የበላይ ሕግ በማመንጨትና በማፅደቅ፣ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ሕገ መንግሥት ለመፍጠር ትልቅ ዕድል ይከፍታል። በሒደቱ በርካታ አገራዊ ጥያቄዎች እየተነሱ ውይይትና ክርክር ስለሚደረግባቸው፣  የሕዝቡ የፖለቲካ ተሳትፎ ይጨምራል፤ ዴሞክራሲ ይለማመዳል፣ በኅብረተሰቡ መካከል መቀራረብና መተማመን እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፣ ወዘተ።

በመጨረሻም ኢሕአዴግ ለውጥ የመምራትን አማራጭ ለመውሰድ ከፈለገ የሚከተሉትን ዕርምጃዎች ሳይውል ሳያድር ሳያድር ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል፡፡ አንደኛ በየወህኒ ቤቱ የታጎሩትን የፖለቲካ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ አክቲቪስቶች፣ ወዘተ. ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ሊፈታቸው ይገባል፡፡ ሁለተኛ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ታቅፈው እርስ በርስ የተጋደሉትና እስካሁን ድረስ በጠላትነት የሚፈላለጉት ሁሉ ኢሕአዴግን ጨምሮ ላለፉት የፖለቲካ ድርጊቶቻቸው ምሕረት የሚያደርግ የምሕረት አዋጅ (Blanket Amnesty) ሊውጅ ይገባል፡፡ ሦስተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሙያና የሲቪል ማኀበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወዘተ. የሚሳተፉበት ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ የንግግር ጉባዔ ሊጠራ ይገባል፡፡

ደጋግሜ እንዳልኩት ኢሕአዴግ ይህን ካደረገ አገሪቱን ከጥፋት፣ ራሱንና ደጋፊዎቹንም በአገራችን እንደተለመደው መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር ከሚደርስ የበቀል ዕርምጃ ይታደጋቸዋል፡፡ በአጭሩ የተለመደው የመፈራረጅና የመጠፋፋት ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዘግቶ በአዲስ ተስፋ መጓዝ እንድንጀምር መሠረት ይጥላል፡፡

ይህን ምርጫ ወደጎን ካለ ግን ለውጥን መምራት አንዳልፈለገ ተቆጥሮ በለውጡ ሊገፋና ሊገለል ይችላል፡፡ ስለዚህ ምርጫው አንድም ከፍ ሲል የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ዕርምጃዎችን ወስዶ የለውጥ መሪ መሆን፣ አንድም እነዚህን ዕርምጃዎች ባለመውሰዱ ምክንያት በለውጥ መገፋትና መገለል ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ጀምሮ በውትድርና፣ በፖለቲካና በአስተዳደር የመንግሥት ሥራ ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሕግ አማካሪና ጠበቃ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...