አንድ ሰኞ በማለዳ ከመገናኛ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ የሚያመራው ሐይገር ባስ ውስጥ ተሳፈርኩ፡፡ የመጨረሻው መቀመጫ ላይ በስተቀኝ በኩል ያለው መስኮት አጠገብ ከመቀመጤ፣ አንዲት ሴት አራስ ሕፃን ታቅፋ አጠገቤ ቁጭ አለች፡፡ ሴቲቷን ዞር ብዬ ሳያት በጣም ለጋ ወጣት ናት፡፡ ከ16 ዓመት አይበልጣትም፡፡ ተመቻችታ ከተቀመጠች በኋላ፣ ‹‹ተመስገን!›› የሚል የምሥጋና ቃል አሰማች፡፡ አሁንም ዞር ብዬ ሳያት ያቺ ለጋ ወጣት ፊቷ ከመገርጣቱም በላይ ድካም ይታይባታል፡፡ ሕፃኗ እናቷ እቅፍ ውስጥ ሆና ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ውስጥ ናት፡፡ እናቲቱ በእጇ ይዛ የነበረውን የተቋጠረ ኩርቱ ፌስታል እግሮቿ መሀል ካሳረፈች በኋላ አሁንም ‹‹ተመስገን!›› አለች፡፡
እንደምንም ብዬ ትንፋሼን ከሰበሰብኩ በኋላ፣ ‹‹ምነው ተመስገን አበዛሽ?›› በማለት ጅላጅል ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ የገረጣ ፊቷን በድርበቡ መለስ አድርጋ፣ ‹‹ፈጣሪ አምላኬን ነው ተመስገን የምለው፡፡ እሱን ለማመስገን ደግሞ ማንንም ማስፈቀድ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ ተግባባን?›› ስትለኝ ደንገጥ አልኩ፡፡ ‹‹አየሽ የእኔ እህት፣ ለምን ተመስገን አልሽ ማለቴ ሳይሆን ስትደጋግሚው ገርሞኝ ነው…›› ብዬ ተንተባተብኩ፡፡ እሷ ግን ዋዘኛ አይደለችም፡፡ ‹‹ፈጣሪዬን ደጋግሜ ተመስገን በማለቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ እሱ እኮ እንደ ሰው ይኼን አደረግኩላችሁ፣ አሳካሁላችሁ፣ ውለታ ዋልኩላችሁ… እያለ ባያስቸግረንም ተመስገን ማለት ተገቢ ነው፡፡ ለእኔ ያደረገውን እኔ ስለማውቅ ደጋግሜ አመሰግነዋለሁ፤›› አለችኝ፡፡
እስቲ ስለግል ሕይወቷ አውቄ የበለጠ ብንነጋገር መልካም ይሆናል ብዬ ላነጋግራት ስዘጋጅ አንድ አብሮን የተሳፈረ መንገደኛ፣ ‹‹ወንድሞቼ እህቶቼ በጎች ሸጬ ያገኘሁትን 30 ሺሕ ብር ተዘርፌ አገሬ መግቢያ ስላጠሁ የቻላችሁትን ዕርዱኝ…›› ብሎ ሐይገር ባሱን በድምፁ ተቆጣጠረ፡፡ ደጉ የአዲስ አበባ ሰው ከዳር እስከ ዳር ኪሱን እየዳበሰ ሰውየውን በዕርዳታ ሲዳብሰው፣ ሰውየው ከእያንዳንዱ ሰው በተቀበለ ቁጥር፣ ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ እናንተንም ከእኔ ዓይነቱ መከራ ይጠብቃችሁ…›› እያለ መረቀ፡፡ አጠገቤ የተቀመጠችው የጨቅላ ሕፃን እናት ከአነስተኛ የእጅ ቦርሳዋ ውስጥ ድፍን አምስት ብር እየሰጠችው፣ ‹‹አይዞዎት አባት ሁሉን ቻይ ቸሩ አምላክ የጠፋብዎትን ይተካልዎታል…›› እያለች አፅናናችው፡፡
ሐይገር ባሱ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን አደባባዩን ሲያቋርጥ የሰውየው ስልክ ሲጮህ ሰማን፡፡ ሰውየው ከኮቱ የውስጥ ደረት ኪስ ውስጥ አውጥቶ በሚያስገመግም ድምፅ፣ ‹‹ሃሎ! ሃሎ! ማን ልበል….›› እያለ ከጠያየቀ በኋላ ከደዋዩ ምን እንደተባለ አይታወቅም፣ ‹‹ዕልልል…. ዕልልል…. የዘረፉኝ ሰዎች ከእነ ገንዘቡ ተይዘዋል….›› ሲል ተሳፋሪዎች በሙሉ ማለት ይቻላል በጭብጨባ አጀቡት፡፡ ሰውየው ባምቢስ አጠገብ ሐይገር ባሱ ቆሞለት በታላቅ አክብሮት ሁላችንንም ካመሰገነ በኋላ ወደተደወለለት ፖሊስ ጣቢያ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ አጠገቤ የተቀመጠችው የልጅ እናት፣ ‹‹ወንድሜ አየህ የፈጣሪን ሥራ? እኚህ አዛውንት ላባቸውን ጠብ አድርገው ለፍተው ያገኙትን ወንበዴ ዘረፋቸው፡፡ የማያንቀላፋው አምላክ ደግሞ አስገኘላቸው፡፡ ቅንጣት እምነት ካለን መሆን የማይችል ነገር የለም፤›› ስትለኝ ልጅነቷ አጠራጠረኝ፡፡
‹‹ለመሆኑ አንቺ ማነሽ? በዚህ ዕድሜሽ እንዴት የልጅ እናት ሆንሽ? ፈጣሪ ምን አድርጎልሽ ነው እንዲህ በምሥጋና ስሙን ደጋግመሽ የምትጠሪው?….›› በማለት ጠንከር ብዬ ጠየቅኳት፡፡ ከት ብላ ሳቀች፡፡ ‹‹ምን አሳቀሽ?›› ስላት፣ ‹‹ገርመኸኝ ነው፤›› አለችኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከማያውቁት ሰው ጋር መነጋገር ጥሩ እንዳልሆነ ባውቅም፣ ‹‹ምኑ ነው የሚያስገርምሽ?›› አልኳት፡፡ አሁን በመጠኑ ፈገግ ብላ፣ ‹‹ስሜን ባልነግርህም እንደምታየኝ የልጅ እናት ነኝ፡፡ የምኖረው ደግሞ ዓለም ገና ነው፡፡ ከሰበታ ወዲህ፡፡ በልጅነቴ መውለዴ ደግሞ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ የአባት ያህል የሚያስብልኝ ባልም አለኝ፤›› ብላ ዝም አለች፡፡
‹‹ታዲያ ምነው ፊትሽ ገረጣ? ድካምስ ለምን ይታይብሻል? ለሚያይሽ እኮ ደስተኛ ሳይሆን አሳዛኝ ትመስያለሽ…›› በማለት ወግ መጠረቅ ስጀምር፣ ‹‹ተሳስተሃል፡፡ ፊቴ ገርጥቶ ከመሰለህ እንደሱ አይደለም፡፡ እኔ ሁሌም እንዲሁ ነኝ፡፡ ትናንት እህቴ ዘንድ ለእረፍት መጥቼ ከእሷ ጋር ውዬ ካደርኩ በኋላ ሸኝታኝ ወደ ቤቴ እየተመለስኩ ነው፡፡ ፈጣሪ የተመሠገነ ይሁን በኑሮዬም ደስተኛ ነኝ፡፡ ያውም አርሶ አደር፡፡ በዕድሜዬ ደግሞ በጣም ልጅ እንዳልመስልህ 19 ዓመቴ ነው፡፡ አየህ ፈጣሪ ይመሥገን እኛ አርሶ አደሮች ጠምዘዝ ያልን ነን፡፡ እንደ ከተማ ሰው አይተኸኝ ከሳች ገረጣች ብለህ እንደምታስብ ይገባኛል፡፡ አሁንስ ተግባባን?›› ስትለኝ የገዛ ሳቄ አመለጠኝ፡፡ እሷ እንደምትለው ከባሏ ጋር የተለያዩ አትክልቶችና ጥራጥሬዎች እያመረቱ ይሸጣሉ፡፡ ከከተማ ወጣ ብሎ ቤት ሠርተዋል፡፡ ከተማም ንግድ እየጀመሩ ነው፡፡ ለካ የእኔ ዓይን ነው እንጂ የቃዥው ልጅቷም ሆነች ሕፃኗ የለበሱት ንፁህ፣ አካኋናቸውም ጥሩ የሚባል ነው፡፡
አንድ ነገር ግን ከነከነኝ፡፡ በተናገረች ቁጥር የፈጣሪ ቃል ከአፏ አይጠፋም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ተለሳልሼ ጠየቅኳት፡፡ ‹‹የእኔ ወንድም ፈጣሪ ያዘዘንን መፈጸም ብንችል እኮ አገር ሰላም፣ ሕዝብም ደስተኛ ይሆናል፡፡ ከራሳችን ጋር ስንጣላ ከፈጣሪ እንራራቃለን፡፡ ፈጣሪ የሰበከው ሰላም፣ ፍቅር፣ መከባበር፣ መተሳሰብ፣ … ነው፡፡ እኛ ግን በገዛ እጃችን ሰላም እናደፈርሳለን፡፡ ፍቅርን ለጠብ እንለውጣለን፡፡ በመተሳሰብና በመከባበር ፋንታ እንተማማለን፡፡ እንዘራረፋለን፡፡ ለአገራችንና ለወገኖቻችን በመጨነቅ ፋንታ በዘርና በሃይማኖት እንከፋፈላለን፡፡ ለሚለያየን ሰይጣን ዕድል እንሰጣለን፡፡ አየህ ወንድሜ የፈጣሪን መንገድ ብንከተል አንጎዳም፡፡ ፈሪኃ እግዚአብሔር ማለት እኮ በቀና ጎዳና እየተጓዝክ ወገንህን ማክበር፣ ማስደሰትና ለአገር በጎ ነገር መፈጸም ማለት ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ብትማር ፈሪኃ እግዚአብሔር ከሌለህ ማስተዋል አይኖርህም፡፡ ትምህርት ለጠቃሚ ዓላማ ካልዋለ መማር ጥቅሙ ምንድነው? ማስተዋል የጎደለው ትምህርትስ ምን ይጠቅማል? በእያንዳንዱ የግልም ሆነ የአገር ጉዳይ ፈጣሪን ካልያዝክ የት ትደርሳለህ?….›› እያለች ያቺ አርሶ አደር ወጣት ማብራሪያ ስትሰጠኝ፣ እዚህ አገር ውስጥ በመማርና ባለመማር መካከል ያለው ልዩነት አልታይህ አለኝ፡፡ (ደጀኔ ለገሠ፣ ከጉርድ ሾላ)