Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበበቆጂ ከተማ አትሌቶች ግንባታ አለመጀመራቸው እያነጋገረ ነው

በበቆጂ ከተማ አትሌቶች ግንባታ አለመጀመራቸው እያነጋገረ ነው

ቀን:

በኢትዮጵያ የብርቅዬ አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው በቆጂ ከተማ አትሌቶች ለግንባታ እንዲያውሉት ከከተማ አስተዳደሩ ያገኙት ቦታ ላይ ወደ ሥራ አለመግባታቸው እያነጋገረ ነው፡፡

የበቆጂ ከተማ ተወላጅ አትሌቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍም ለመሳተፍ ግንባታ ለማከናወን ከከተማ አስተዳደሩ ቦታ ያገኙ ቢሆንም፣ በተቀመጠላቸው ቀን ገደብ ውስጥ ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ዕገዳ እንደተጣለባቸው የበቆጂ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከበበው አዱኛ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹በአትሌት ቀነኒሳ ጠያቂነት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተገኝቶ የነበረ ቢሆንም በሥራ መደራረብ ለሁለት ዓመት ዘግይቶ ቆይቷል፤›› ብለዋል፡፡ ግንባታው የዘገየበትን ምክንያት አስመልክቶ የተጠየቁት የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ታላቅ ወንድም አቶ ታምራት በቀለ፣ በድጋሚ ወደ ግንባታ ለመግባት ቀነኒሳን ጨምሮ አትሌቶች ጥያቄ ቢያቀርቡም በከተማው አስተዳደር ይሁንታ አለማግኘቱን ተናግረዋል፡፡  

ቀነኒሳ በ2002 ዓ.ም. የነዳጅ ማደያ ለመገንባት 1,295 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ሆኖም በ2005 ዓ.ም. የዕገዳ ደብዳቤ ከተሰጠው በኋላ ግን በቦታው ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ ማከናወን እንዳልቻለ አቶ ታምራት ይናገራሉ፡፡  

አትሌቱ ቀደም ብሎ በተደጋጋሚ ወደ ከተማ አስተዳደሩ በማምራት የኢንቨስትመንት ጥያቄ ሲያቀርብና ሲከታተል የነበረ መሆኑንና የሚናገሩት አቶ ታምራት ጉዳዩን እንዲከታተሉ በቀነኒሳ ተወክለው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

አቶ ታምራት፣ ለኢንቨስትመንት የቀረበው ቦታ ላይ ግንባታ ለመጀመር ቀድሞ ስትኖርበት ለነበረችው የከተማዋ ነዋሪ 52 ሺሕ ብር ካሳ መከፈሉን ጭምር አብራርተዋል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ ወደ ሥራው ለመግባት ዝግጁ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ታምራት፣ የከተማ አስተዳደሩ ጉዳዩን እንደገና ተመልክቶ ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡  

‹‹ቦታው ለአንቨስትመንት ተብሎ ከተሰጣቸው አሥር ዓመት አልፎታል፡፡ በመሆኑም ወደ ግንባታ ባለመግባታቸው ምክንያት ቦታው ለሌሎች ባለሀብቶች ለመስጠት የጨረታ ፕሮግራም አውጥተናል፤›› በማለት የበቆጂ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከበበው አዱኛ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በሆቴልና በተለያዩ የንግድ ዘርፍ ላይ ለመሥራት የግንባታ ቦታ ጥያቄ ያቀረቡት አትሌቶቹ ወደ ሥራ ያለመግባታቸው ጉዳይ ከሕዝቡ ጥያቄ እያስነሳ ስለመሆኑም ከንቲባው አክለዋል፡፡

በበቆጂ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርና የከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ ኃይሉ ደሳለኝ፣ ‹‹በቆጂ ከተማ ያፈራቻቸው አትሌቶች ለከተማዋ ዕድገት የድርሻቸውን እንዳይወጡ የመልካም አስተዳደር ችግር አንዱ መንስኤ ነው፡፡ አትሌቶቹም ተወልደው ያደጉበትን ከተማ ስለረሱ በቆጂ የወላድ መካን ሆና ቆይታለች፤›› በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ለአትሌቶቹ የተሰጠውን ባዶ መሬት መመልከት ለከተማው ነዋሪ ‹‹አሳዛኝ ነው፤›› በማለት ቁጭታቸውን ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ለኢንቨስትመንት መሬት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ትጠቀሳለች፡፡ አትሌቷ ከአንድ ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት እንደወሰደች፣ ከእሷ በተጨማሪ ሌላዋ በቆጂ ያፈራቻት ጥሩነሽ ዲባባም በተመሳሳይ ከአንድ ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ ቦታ መውሰዳቸውን የከተማዋ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በበቆጂ ከተማ ተወልደውና አድገው በአትሌቲክሱ ከአገራቸውም አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ አገሪቱን ማስጠራት የቻሉት አትሌቶቹ፣ በትውልድ ከተማቸው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ለማድረግ የከተማዋ አስተዳደር ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ የከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ ታዬ ደስታ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በመጨረሻም የከተማ አስተዳደሩ አትሌቶዎቹ ወደ ግንባታ መግባት ከፈለጉ የከተማው አስተዳደር ፈቃደኛ መሆኑንና እስከ ጥቅምት 2009 ዓ.ም. ድረስ ወደ ግንባታ ካልገቡ ቀደም ሲል በተገለጸው መሠረት ለጨረታ ሊያቀርበው እንደሚችል አስታውቋል፡፡

17 ሺሕ ሕዝብ እንዳላት የሚነገርላት የበቆጂ ከተማ ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ እጅጋየሁ ዲባባ፣ እንዲሁም ገንዘቤ ዲባባን ካፈራቻቸው አትሌቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...