Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጋዜጠኝነት ትምህርት የተተቸበት መድረክ

የጋዜጠኝነት ትምህርት የተተቸበት መድረክ

ቀን:

በትግራይ ክልል ምሥራቃዊ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ዓዲግራት ይገኛል። ‹‹ሦስተኛ ትውልድ›› ተብለው ከሚጠሩ 10 ከፍተኛ የትምርት ተቋማት አንዱ ነው፡፡

 ዩኒቨርሲቲው ሲመሠረት የኮሌጆች ቁጥር አራት፤ ትምርት ክፍሎቹም አሥራ ሦስት ነበሩ። ዩኒቨርሲቲው ሥራውን በይፋ የጀመረው፡፡ ኅዳር 26 ቀን 2004 ዓ.ም. በአንድ ሺሕ ገደማ ተማሪዎች፣ 94 መምህራንና 109 የአስተዳደር ሠራተኞች ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት፣ አንድ ሺሕ ገደማ መምህራንና 1,350 የአስተዳደር ሠራተኞች አሉት። 13,000 መደበኛ ተማሪዎች ሲኖሩት፣ የክረምት፣ የማታና የድህረ ምረቃን ጨምሮ በጠቅላላ ወደ 18,000 ተማሪዎች ያስተናግዳል፡፡ ሦስተኛ ትውልድ ከተባሉት 10 ዩኒቨርሲቲዎች በአምስት ዓመት ውስጥ ይህን ያህል የተማሪ ቁጥር ያስተናገደ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያው እንደሆነ  መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 ዩኒቨርሲቲው ኮሌጆቹን ከአራት ወደ ስድስት ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ ስድስት የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ከፍቶ እያስተማረ ይገኛል። የትምህርት ክፍሎቹንም ወደ 41 ማሳደጉን የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮሐንስ ከበደ ተናግረዋል፡፡

የጋዜጠኝነት ሥርዓተ ትምህርት

በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙት ‹‹የሦስተኛ ትውልድ›› ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሆነው አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ በጋዜጠኝነት ላይ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ቀርፆ አዲስ የትምህርት ክፍል ለመክፈት በቅርቡ ጉባኤ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በጉባኤው በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ካሪኩለም፣ ላይ ክርክር ተነስቷል፡፡

በነሐሴ 2008 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ የፓናል ውይይት፣ በርከት ያሉ በሙያው ላይ ፍላጎት ያላቸው ባለሙያዎች መምህራንና ጋዜጠኞች የታደሙበት ሲሆን፣ ጥልቅ ክርክር ያስነሳው ‹‹የልማታዊ ጋዜጠኝነት ወገንተኝነት ለማን ነው?›› የሚል ነበር፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና የአካዴሚክ ኃላፊ ዶ/ር ዓለም መብራህቱ በይፋ የከፈቱት ይኼው የፓናል ውይይት፣ እስከ ዛሬ በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመሰጠት ላይ የሚገኘው የጋዜጠኝነት ትምህርት ሥርዓተ ትምህርትና  በአገሪቱ ያለውን የጋዜጠኝነት ትግበራን ዳስሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ዲን ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) እንዲሁም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ዲፓርትመንት ኃላፊ ዶ/ር ጀማል መሐመድ ዳሰሳ ካደረጉ የዘርፉ ምሁራን ይገኙባቸዋል፡፡

ሁለቱም ጥናት አቅራቢዎች በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተሰጠ ያለው የጋዜጠኝነት ሥርዓተ ትምህርት የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ አለመሆኑ፣ በአብዛኛው የሚሰጠው ትምህርት የመርህና የጽንሰ ሐሳብ እንደሆነና የተግባር ትምህርት እንደሚጎድለው የጋራ ዕይታቸው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ በመንግሥት ሚዲያዎች የሚታየው የልማታዊ ጋዜጠኝነት አሠራር ከመርሁ ውጪ መሆኑንም ምሁራኑ የተስማሙ ሲሆን፣ በአገሪቱ ጽንሰ ሐሳቡ ከሚያስቀምጠው ውጪ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነም አሳይተዋል፡፡ ዶ/ር ጀማል እንዳሉት፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ጋዜጠኞች፣ በተግባር አቅማቸው ደካማ ሲሆኑ፣ ከፍተኛ የክህሎት ውስንነትም አለባቸው፡፡

ከአሜሪካ የመጡና ልምዳቸውን ያካፈሉ ዶ/ር ርእሶም መስፍን በበኩላቸው፣ ከኮሌጅ ጋዜጣ እስከ ትልቅ ሚዲያ ባገኙት ልምድ መሠረት፣ ጋዜጠኝነት ከጽንሰ ሐሳብ ትምህርት ይበልጥ፣ በተግባር የሚለምዱት ሙያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጥ የጋዜጠኝነት ሙያ ትምህርት በተግባር እንዲደገፍና አብዛኛው ተግባር ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ይመክራሉ፡፡

አብዛኛው የአስተያየቶች ይዘት የ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኝነት›› ምንነትና ወገንተኝነት ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ ቀድመው አስተያየት ከሰጡት መካከል የሰንደቅ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ፋኑኤል ክንፉ በዓለም ያሉት ታዋቂ ሚዲያዎችን ጨምሮ ማናቸውም የሚዲያ ተቋማት የሚወግኑለት አካል እንዳለ በመናገር፤ የኢትዮጵያ የመንግሥት ሚዲያም ውግንናው ለመንግሥትና መንግሥት ለሚያመጣቸው ፖሊሲዎች እንዲሁም አፈጻጸሞች ቅድሚያ መስጠቱ ትክክል እንደሆነ ገልጽዋል፡፡

ጋዜጠኛ ፀጋይ ሐዲሽ፣ በትግራይ መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ ደረጃዎች ለረዥም ጊዜ የሠራ ጋዜጠኛ ሲሆን፣ ጋዜጠኝነት ትምህርት በኒዮ ሊብራሊዝም ሥርዓተ ትምህርት ላይ ተመሥርቷል በማለት ተማሪዎች የተበላሸ አስተሳሰብ ይዘው እንደሚመጡና በመንግሥት ተቋማት (ሚዲያ) ከገቡ በኋላ የመንግሥት ፖሊሲና አስተሳሰብ ተረድተው የተሻለ ግንዛቤ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ በአብዛኛው ከጋዜጠኛ ፋኑኤል ጋር የሚስማማ አስተያየት የሰነዘረው ፀጋይ፣ የአንድ ልማታዊ ጋዜጠኛ ወገንተኝነት መንግሥት ለሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የልማት ተግባራት እንደሆነ ያምናል፡፡ ፀጋይ እንደሚለው፣ ጋዜጠኛ ከዩኒቨርሲቲ ይዞት የሚወጣው የተዛባ አስተሳሰብ እንጂ ለመንግሥት መወገኑ ስህተት የለውም፡፡

የሁለቱንም ጋዜጠኞች አስተያየቶች በመቃወም አንዳንድ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን፣ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ትግበራ ላይ የተዛባ አረዳድ አለ የሚል ሐሳብ ተሰንዝሯል፡፡ በተለይ በጋዜጠኛ ፀጋይ የቀረበው ‹‹የልማታዊ ጋዜጠኝነት ወገንተኝነት ለመንግሥት ነው›› ማለታቸው፣ የተሳሳተ እንደሆነ  የመድረኩ ተሳታፊ ተናግረዋል፡፡

ጋዜጠኛ ፋኑኤል በግል ሚዲያ የሚገኝ ጋዜጠኛ መንግሥትን የሚሰድብ ጽሑፍ ያቀረበው፣ በውጭ አገር ጥገኝነት ለመጠየቅ በማለም ነው በሚል ያቀረበው አስተያየትም ተተችቷል፡፡

‹‹የመንግሥት ጋዜጠኛ ደግሞ አውሮፓና አሜሪካ በመሄድ ሳይሆን እዚሁ የባለሥልጣናትና የኃላፊዎች አፈ ቀላጤ በመሆን፣ የመንግሥት ጥገኝነት ጠይቆ፣ ከመንግሥት በላይ መንግሥት ሆኖ የሚኖር ነው፤›› ተብሎ ተተችቷል፡፡

የመንግሥት ጋዜጠኞች በተለይ ደግሞ የትግራይ ቴቪ የዚሁ ችግር ሰለባ መሆኑ የተተቸ ሲሆን፣ ሕዝቡ የቴሌቪዥን ጣቢያው ላይ እምነት እንዳይጥልና እንዳይከታተል እያደረገው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ፡፡

‹‹እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉት የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሚከተሉት አገሮች፣ ልማታዊ ጋዜጠኝነትን የሚዲያ ፍልስፍና ማድረጋቸው አያጠያይቅም›› የሚለው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ በሪሁ ሊላይ፣ መንግሥት ይህንን የሚዲያ ፍልስፍና እየተከተልኩኝ ነው ቢልም ሳይንሱ በአግባቡ እየተተገበረ እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡     

‹‹የአገራችን ሚዲያዎች በተለይም የመንግሥት ሚዲያዎች ከአስፈጻሚው አካል ʻነፃ ናቸውʼ ለሚሉት አያስደፍርም፤›› ይላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ጋዜጠኛ የልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ ተከትሎ በአንድ አካባቢ ያለውን የሕዝብ ችግር ጎልጉሎ ወደ ሚዲያ በማቅረብ መፍትሔ ለማምጣት በሚታትርበት ጊዜ አስፈጻሚው አካል ወደ ሕዝብ እንዳይሠራጭ የሚያደርግበት አጋጣሚዎች እንዳሉም ጋዜጠኛው ያስረዳል፡፡

የሕዝብ እሮሮዎችን ይዞ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለቃለ መጠይቅ በተቀመጠበት አንዱ ወቅት ‹‹ለመሆኑ ከኢቢሲ ነው የመጣኸው?›› የተባለበት ቀንም እንዳለ ያስታውሳል፡፡

የውራይና መጽሔት (ትግርኛ) ባለቤት ጌታቸው አረጋዊ በበኩሉ፣ ተመሳሳይ ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን፣ በተለይ በትግራይ ክልል መረጃ የማግኘትና ሐሳብን በነፃነት የመጻፍ ነፃነቱ የሳሳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጋዜጠኛ ጌታቸው፣ በአንዳንድ ወሳኝ ክንውኖችና ስብሰባዎች ሆን ተብሎ እንዳይገኝ እንደሚደረግ፣ ከተገኘም ‹ሳይጋበዝ ለምን መጣ› ተብሎ ብዙ መንገላታት እንደሚደርስበት አስረድቷል፡፡ ጌታቸው፣ በተለይ በአገሪቱ በሥራ ላይ ያለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት በተዛባ ሁኔታ እየተተረጎመ እንደሆነ ገልፆ፣ ከጽንሰ ሐሳቡ ውጪና በተቃራኒ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚሁ ውይይት መነሻ የሆነው ሥርዓተ ትምህርት የቀረጹት የዩኒቨርሲቲው መምህራንም በቀረቡት ሐሳቦች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከመካከላቸው መምህር በረከት ይኼይስ በሥርዓተ ትምህርቱ ቀረጻ ላይ የቀረቡ አስተያየቶች ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውን ገልጸው፣ የ‹‹ሚዲያ ወገንተኝነት ለመንግሥት አይደለም፣ እንዲያውም ለሕዝብም አይደለም፤ ወገንተኝነቱ ለእውነት ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እንኳን መንግሥት ሕዝብም ሊሳሳት ይችላል፤›› በማለት እስከዛሬ በአገሪቱ የሚሠራበት የሚዲያ ሥርዓተ ትምህርት ችግር እንዳለባቸው በዚህም የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተነሳሽነቱን ወስዶ ይህንን ችግር ለማሻሻል ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው አክለዋል፡፡

አሁን መሬት ላይ ያለው አካሄድ በልማታዊ ጋዜጠኝነት ላይ ያለ የተዛባ አመለካከት ውጤት መሆኑን በመተንተን ከሕዝቡ ንቃተ ህሊና አንጻር መቃኘት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ መርሁ መንግሥት የልማት ሥራዎች በሚሠራበት ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችና ጉድለቶች ነቅሶ በማውጣት ማሳየት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

መምህር ገብሩ ካሕሳይ በበኩላቸው፣ በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ለቀረቡ አንዳንድ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ አስተያየቶቹ ተካተውበት በአገሪቱ የተሻለና የተለየ የሚዲያ ተቋም ለመገንባት ዓላማ ያለው ዩኒቨርሲቲ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ዶ/ር ነጋሪ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ስለልማታዊ ጋዜጠኝነት ያለው አመለካከት የተዛባ ነው፡፡ ገለልተኛ የሚባል ሚድያ እየቀረ ቢሆንም፣ ወገንተኝነቱ ለመንግሥት የሚሆንበት ምክንያት ግን የለም፤›› ይላሉ፡፡ የሚዲያው ወገንተኝነት ለሕዝብና ለሃቅ ብቻ መሆኑን በመግለጽ፣ ጋዜጠኝነት ከዚህ ውጪ ሲሆን አለመተማመን እየተፈጠረ እንደሚሄድ ያስረዳሉ፡፡

ጋዜጠኛ ተአምራት የማነ በጋዜጠኝነት ላይ ስፔሻላይዜሽን እንዲኖር ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ዶ/ር ጀማል በበኩላቸው፣ ጋዜጠኝነት ውስጥ ‹‹ስፔሻላይዝድ›› የማድረግ አስፈላጊነት ላይ አተኩረው የተናገሩ ሲሆን፣ ጠቅላላ ትምህርት ከሚሰጥ አንድ ጋዜጠኛ በአንድ ውስን ጉዳይ ላይ ጥልቅ ዕውቀት እነዲያገኝ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኝነት›› በኢትዮጵያ ሃይጃክ የተደረገ ጽንሰ ሐሳብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሌላ ስማቸው ያልተጠቀሰ የዩኒቨርሲቲው መምህር፣ ‹‹በዩኒቨርሲቲው ሊከፈት የታሰበው የሚዲያ ማዕከል፣ አሁን ያሉት የመንግሥት ጋዜጠኞች ዓይነት የሚያስመርቅ ከሆነ፣ ሳይከፈት ቢቀርስ›› የሚል ጠንካራ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ዓለም በማጠቃለያ ሐሳባቸው የአገሪቱን የሚዲያ ሁኔታ ለማሻሻል ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ተባብሮ እንደሚሠራና የ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኝነት›› የተዛባ አመለካከት ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ክፍተቱን ለመሙላት ዲፓርትመንቱ የራሱ አዎንታዊ ሚና ይጫወታልም ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ግልጽ ክርክርና ውይይት በማዘጋጀትም የጠራ አስተሳሰብ ለመፍጠር ዩኒቨርሲቲው አበክሮ ይሠራል ሲሉ አክለዋል፡፡

የትግራይ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብረ ሚካኤል መለስ፣ በማጠቃለያ ንግግራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት መኖሩን ገልጸው፣ ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኝነት ከልማት ዘጋቢነት በላይ ነው፡፡ የመንግሥት አጨብጫቢ ሳይሆን ተቺ እንዲሆን ነው የሚፈለገው፤›› በማለት የምርመራ ጋዜጠኝነት ተግባር ላይ እንዲውልም መንግሥት እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...