ኢትዮጵያውያኑ መኳንንት አየነውና መሠረት መንግሥቱ 36ኛውን የቤጂንግ ማራቶን በወንዶችና በሴቶች ምድብ አሸነፉ፡፡
ቅዳሜ መስከረም 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደውና በኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የወርቅ ደረጃ ባለው የሩጫ ውድድር፣ በሴቶች የ26 ዓመቷ መሠረት የፈጸመችበት 2፡25፡56 ፈጣኗ ሯጭ አሰኝቷታል፡፡ መሠረትና ተከትላ ሁለተኛ የወጣችው መልካም ግዛው ስትሆን፣ ሰሜን ኮርያዊቷ ጆ ኡን ኦኬ ሦስተኛ ሆናለች፡፡
መሠረት በዓምናው የፓሪስ ማራቶን የራሷን ጊዜ በስድስት ደቂቃዎች በማሻሻል 2፡23፡26 መግባቷ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፈው ቅዳሜ የገባችበት ሰዓት ሁለተኛዋ ምርጥ ጊዜዋ መሆኑን የዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡
በወንዶች ምድብ የተወዳደረው መኳንንት በአራት ዓመት የማራቶን ተወዳዳሪነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በቤጂንግ ድል የተቀዳጀበት ነው፡፡ የ24 ዓመቱ መኳንንት ባሸናፊነት የፈጸመበት 2፡11፡09 ባንፃራዊ መልኩ ከሴቶቹ ዝግ ያለ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ፈየራ ገመዳ (2፡11፡30) እና መስፍን ተሾመ (2፡11፡56) ሁለተኛና ሦስተኛ ወጥተዋል፡፡ ሦስቱም ኢትዮጵያውያን የሽልማት ሠገነቱን ተቆጣጥረውታል፡፡ በቤጂንግ ማራቶን 30,000 ሯጮች መወዳደራቸው ታውቋል፡፡