Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአዳማ የወርቅ ኢዮቤልዩ እየተከበረ ነው

የአዳማ የወርቅ ኢዮቤልዩ እየተከበረ ነው

ቀን:

–  አዘጋጆቹ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ተፅዕኖ አላሳደረብንም ብለዋል

አዳማ ከተማ የተቆረቆረችበት 100ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ እየተከበረ ሲሆን፣ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በዓሉ ላይ ተፅዕኖ አለማሳደሩን አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን በአዳማና አዲስ አበባ ከተማ እንደሚካዱም አሳውቀዋል፡፡ አዘጋጆቹ ዓርብ መስከረም 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል ማዕከል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋት በከተማዋ የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ላይ ተፅዕኖ የለውም ብለዋል፡፡

የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ችላ ብሎ የሕዝባዊው ተቃውሞ መነሻ ከሆኑ ቦታዎች አንዱ በሆነው አዳማ ላይ  በዓል ማክበር ተገቢ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ለአዘጋጆቹ ቢሰነዘርም፣ አዘጋጆቹ የበዓሉ መከበር ተፅዕኖ እንደማያሳድር ተናግረዋል፡፡

የአዳማ ከተማ 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል አከባበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ቱሉ፣ ከተማዋ የተመሠረተችበትን ታሪካዊ ጊዜ ከግምት በማስገባት በዓሉ በአሁኑ ወቅት ይከበራል ብለዋል፡፡ ኃላፊው፣ በዓሉን በማስመልከት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡

‹‹የከተማዋ የምሥረታ በዓል አካል የሆነ ባዛርና ኤግዚቢሽን በቅርቡ በአዳማ ተካሂዷል፡፡ በቀጣይ በሚኖሩ ዝግጀቶችም ወቅታዊው ሁኔታ ተፅዕኖ ያሳድራል ብዬ አላምንም፤›› ብለዋል አቶ ዓለማየሁ፡፡ ኤግዚቢሽኑ በየቀኑ በአማካይ በ800 ሰዎች ተጎብኝቶ በአጠቃላይ ወደ 120 ሺሕ ሰዎች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በተቃውሞ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች እያሉ የወርቅ ኢዮቤልዩ መከበሩ አግባብ ነው? በሚል ከጋዜጠኞች ለተሰነዘረላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በዓሉ የፌሽታ ሳይሆን ለከተማዋ ገቢ ማሰባሰቢያ ነው፤›› በማለት የተዘጋጁ መርሐ ግብሮች እንደማይሰርዙም ገልጸዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የወርቅ ኢዮቤልዩውን ምክንያት በማድረግ ለከተማዋ ወደ 100 ሚሊዮን ብር ለማስገኘት አቅደዋል፡፡ በበዓሉ ለከተማዋ ተወላጆችና ጎብኚዎች የተዘጋጀ ቴሌቶን እንዳለና ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ ለበዓሉ ዝግጅት አነስተኛ በጀት እንደመደቡም አሳውቀዋል፡፡ ‹‹የከተማዋን ልደት ስናከብር የምናገኘው ገቢ ነዋሪዎች የተሻለ ኑሮ እንዲመሩና ምቹ ከተማ ለመፍጠር ይውላል፤›› ብለዋል፡፡

ከተማዋ ለቱሪዝም ኮንፈረንስ ምቹ ከመሆኗ አንፃር ብዙ ስላለመሠራቱና ከተማዋ የወሲብ ቱሪዝም መዳረሻነቷ አሳሳቢ ስለመሆኑንም ኃላፊው ተጠይቀው ነበር፡፡ በከተማዋ ለነዋሪዎች በቂ መዝናኛ ካለመኖሩም በላይ የቱሪዝም እንቅስቃሴውም ውስን መሆኑም ተነስቷል፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሕዝቡ ላይ ያሳደረገው ተፅዕኖ ተጠቅሷል፡፡ ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ ሀብትና ለስብሰባ ምቹነቷን ከግምት በማስገባት የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነቷ ላይ ጠንካራ ሥራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ ከተማዋ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ማካሄጃ እንድትሆን ለማስቻል መሠረተ ልማቱን ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በወሲብ ቱሪዝም ረገድ፣ ከተማዋ የወሲብ ቱዝሪም መዳረሻ ስለመሆኗ ተጨባጭ ጥናት እንዳላዩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከተማችንን በወሲብ ቱሪምዝ የሚያስጠራ የጎላ ጥናት በጄ የለም፡፡ ከተማዋ ሰዎች ለመዝናናት የሚመርጧት እንደመሆኗ ካለው እንቅስቃሴ የተለየ ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡

የከተማዋ የወርቅ ኢዮቤልዩ መከበር የጀመረው ሚያዝያ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ እስከ ጥቅምት አጋማሽ ይቀጥላል፡፡ አዘጋጆቹ እንደገለጹት፣ በዓሉ የከተማዋን ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ ያለመም ነው፡፡ ለበዓሉ የከተማዋ አመሠራረትና የ100 ዓመት ታሪክ ላይ ያተኮረ ጥናት ተሠርቶ ለኅትመት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ የከተማዋን የ100 ዓመት ጉዞ የሚያትት መጽሐፍም ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ተሠርቷል፡፡ በከተማዋ ታሪካዊ አመጣጥ ላይ በአዳማና አዲስ አበባ የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱም አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

የሙዚቃና የባህላዊ አልባሳት ትርዒት፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ የቁንጅና ውድድር እንዲሁም ኤግዚቢሽንና ባዛር ይካሄዳል፡፡ በአዳማ ከተማ ከሚካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛር በተጨማሪ ከመስከረም 7 እስከ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በኦሮሞ ባህል ማዕከል የሚካሄደው ኤግዚቢሽን ይጠቀሳል፡፡ ኃላፊው እስከ 200 የሚደርሱ አምራቾች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡

የከተማዋን ነዋሪዎች ጥያቄ ለመመለስና ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የባህል ማዕከል፣ የከተማ ፓርክና ስቴዲየም ግንባታ እንደሚጀመር አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፓርክ የሌለው ከተማ መተንፈሻ ሳንባ እንደሌለው ሰው ነው፡፡ የባህል ማዕከልና ስታዲየምም አስፈላጊ ናቸው፡፡ የእነዚህ ተቋሞች ዲዛይን ሒደት ላይ ሲሆን፣ ግንባታቸው በቀጣይ ዓመታት ይጠናቀቃል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡  ከግንባታዎቹ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ከተማዋ የገጠማት የጎርፍ አደጋና የወሰፊት ሥጋቶችም የጋዜጠኞች ጥያቄ ነበሩ፡፡

ኃላፊው በምላሻቸው፣ ተቋሞቹ ሲገነቡ በቅርቡ በከተማዋ ተከስቶ የነበረውን የጎርፍ አደጋ ታሳቢ ባደረገ መንገድ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ የጎርፍ አደጋው መንስዔ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተጠና መሆኑንም አክለዋል፡፡

አዳማ በ1908 ዓ.ም. የጂቡቲ አዲስ አበባ የባቡር ሐዲድ መስመርን ተከትላ ነበር የተመሠረተችው፡፡ የከተማዋ መጠሪያ ‹‹አዳሚ›› ከተሰኘውና የዛፍ ዓይነትን ከሚገልጸው የኦሮምኛ ቃል የተገኘ ነው፡፡ የከተማዋ መጠሪያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናዝሬት ቢባልም፣ ወደ አዳማ ተመልሷል፡፡ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫም ነበረች፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ስብሰባዎች ማካሄጃ በመሆኗ ትታወቃለች፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...