‹‹ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በሰላም ተቃውሞን መግለጽ ይቻላል ብለዋል፡፡ አዎ፡፡ መንግሥት በሚፈልገው መልኩ ወይም መንግሥትን ለመደገፍ ከሆነ የከተማ አውቶቡስ ሳይቀር ተመድቦ መሰለፍ ይቻላል፡፡ ፌዴራል ፖሊስም ያጅባል፡፡ ችግሩ ሕዝብ የራሱን ጥያቄ ይዞ ሲነሣ ነው፡፡››
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ መምህር፣ በኢትዮጵያ ባለፈው ሩብ ምታመት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት አስመልክቶ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተናገሩት ኃይለ ቃል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከል አዳራሽ መስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደውና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ካሳ ተክለብርሃን በመሩት መድረክ፣ ምሁራኑ ስለ አገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች በፍትሐዊ ሀብትና ሥልጣን ክፍፍል፣ ከንግግር ነፃነት፣ ከትምህርት ጥራትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡