ቀለበቱን ከወር በፊት ያገኘችው ዋናተኛ ጆሲ ኒስኰ (በግራ) ቀለበቱን ፎቶ አንስታና በቀለበቱ ላይ የተጠቀሰውን ቀን ገልጻ ፌስቡክ ላይ ለቀቀችው
***********
ቱ! በል
ቱፍ – በል! ማሙሽ ቱ!
አለችው እናቱ
እሷው ናት አባቱ
ወንድምና እህቱ
ነፍስና አካላቱ፡፡
ማሙሽ ብቻ – ብቻውን
እያዩ መምጫ – መምጫውን
ያለምንም ከልካይ
ከጐጆው በራፍ ላይ
አፈር አድበልብሎ
ሲቅም እንደቆሎ….
እናት በችኮላ
እንስራዋን አዝላ
ልጄ! … ልጄን! … ብላ
አሳብራ መንገዷን
ዘንግታ ድካሟን
ስትደርስ ከደጃፉ
ሆኖ ስታገኘው አፈር ቅሞ ባፉ
ብድግ አ‘ረገችው
ቱፍ – በል!!! እያለችው፡፡
ጭቃ ባፉ ሞልቶ …
መላ – አካሉ ቦክቶ … ሆኖ ስላየችው፤
መታ አ‘ረገችው
ቱፍ – በል! እያለችው፡፡
እንባውን ስታየው
ቱ – በል! እያለችው
እየዳበሰችው
እያባበለችው
አቅፋ እየሳመችው
አዝላ እያስተኛችው
እሷም እንደማሙሽ ጭቃውን ቃመችው፡፡
- አሰፋ ጉያ ‹‹የከንፈር ወዳጅ››(1984)
***********
‹‹በማር ጠብታ አገር ተመታ››
በ19ኛው ኦሊምፒያድ ላይ የአፓርታይድ ፖሊሲ የምትከተለዋ ደቡብ አፍሪካ እንድትካፈል የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቨሪ ብራንደጅ በመፍቀዳቸው ዜናው በየክፍለ ዓለማቱ እንደተሰራጨ ከፍተኛ ተቃውሞ ከአፍሪካ ተነስቶ በእስያ፣ በአውሮፓና በላቲን አሜሪካ አገሮች ድጋፍ በማስተጋባቱ በዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የአፍሪካዊው ተወካይ በሆኑት በፕሬዚዳንት ይድነቃቸው ተሰማና በሜክሲኮ ውትወታ ደቡብ አፍሪካን ከሜክሲኮው ጨዋታዎች አስወገዷት፡፡ ይህም ትልቅ የምሥራች ሆነ፡፡ የሜክሲኮ ሕዝብና ባለሥልጣኖችም ከፍ ያለ ደስታ ተሰማቸው፡፡
ነገር ግን ሜክሲኮ ሊቃዋ በዚህ አላበቃላትም ነበር፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከሜክሲኮው ኦሊምፒክ በመወገዷ የተሰማቸውን ደስታ ሳይጨርሱ ወዲያው የተማሪዎች ብጥብጥ ተነሳ፡፡ የተማሪዎቹ ረብሻ የተነሳው በአንዲት ልጃረገድ ምክንያት ነበር፡፡ አንድ የሙያ ትምህርት ቤት ተማሪና አንድ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አንዷን ልጃገረድ ለሁለት የከንፈር ወዳጅነት ይዘው ኖሮ ለኔ ለኔ በመባባል ስለተጣሉባት ገላጋይ ጠፍቶ ሁለቱ ሲደባደቡ፤ ሌሎች የሁለቱ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ፍልሚያውን ለማየት ከመጡ በኋላ አንዱ ሌላውን ሲያንጓጥጥ፤ ሲጐሽም ከፍልሚያነት አልፎ የተማሪዎች የእርስ በርስ ጦርነት ሆነ፡፡ በዚህ የተነሳ ‹‹በማር ጠብታ አገር ተመታ›› እንደሚባለው፤ በአገሪቱ ትልቅ ሽብር ተነስቶ የተማሪዎቹን ረብሻ ለማብረድ የመጡት ፖሊሶችና ወታደሮች ለሕይወታቸው አስጊ ሆኖ ስላገኙት በጥይት መጠቀም ግድ ሆነባቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የ49 ሰላማዊ ተማሪዎች ሕይወት አልፏል፡፡ በግርግሩ ከ150 ሺሕ የማያንሱ ተማሪዎችም ተካፋይ ነበሩ፡፡
- መጽሐፈ ሔኖክ ‹‹ቅምሻ›› በአዲስ ዘመን (ሐምሌ 30 ቀን 1975 ዓ.ም.)
********
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን እንኳን ከኳስ ከጥይትም እናመልጣለን››
ከዕለታት አንድ ቀን አፄ ኃይለሥላሴና የኬንያው ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ የአገሮቻቸው ብሔራዊ ቡድኖች የእግር ኳስ ግጥሚያ ሲያደርጉ ይመለከቱ ነበር፡፡ ታዲያ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ይጠናቀቃል፡፡ በመጨረሻም የጨዋታው ዳኛ ሁለቱ መሪዎች እንደ ግብ ጠባቂ ሆነው ጨዋታው ይዳኛል ብለው ወሰኑ፡፡
በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ጆሞ ኬንያታ ግብ ጠባቂ ሆነው የኢትዮጵያው ንጉሥ ፍፁም ቅጣት ምት በመምታት ጎል አስቆጠሩ፡፡
ቀጥሎ ፍፁም ቅጣት ምት መምታቱ የኬንያው ፕሬዝደንት ተራ ስለነበር የኢትዮጵያው ንጉሥ ጎል ጠባቂ ሆኑ፡፡
እናም የኬንያው መሪ ኳሱን ለመምታት ከሌላኛው የግብ ክልል ተነስተው ሜዳውን ሙሉ ሲንደረደሩ ባዩ ጊዜ የኢትዮጵያው ንጉሥ ግቡን ትተው ስለሸሹ የኬንያው መሪ ግብ ያስቆጥራሉ፡፡
ኃይለሥላሴም “ለምንድነው የሸሹት?” ተብለው ሲጠየቁ “እኛ ኢትዮጵያውያን እንኳን ከኳስ ከጥይትም እናመልጣለን፡፡” ብለው መለሱ ይባላል፡፡
- በዳንኤል ገሠሠ የተተረከ የአማራ ተረት
***********
ከ37 ዓመታት በኋላ የተገኘው የጋብቻ ቀለበት
ኦገስቲን አልያጋና ጁኒ ሳንቼዝ ከ37 ዓመታት በፊት ነበር በትዳር የተጣመሩት፡፡ የያኔዎቹ ወጣት ጥንዶች ትዳራችሁ የአብርሃምና የሳራ ይሁንላችሁ ተብለው በዘመድ አዝማድ ተመርቀው ጎጆ ወጡ፡፡ አዲስ ትዳራቸውን እያጣጣሙ ሳለ ኦገስቲን የጋብቻ ቀለበቱ ይጠፋበታል፡፡ የጋብቻቸው ቀንና ዓመተ ምሕረት እ.ኤ.አ. ፌብርዋሪ 17፣ 1979 የተቀረፀበት የጋብቻ ቀለበቱ ከጣቱ ላይ የጠፋው በሚዋኝበት ወቅት ነበር፡፡ ቃላቸውን ያሠሩበት ቀለበት ቢጠፋም ትዳራቸው እንደሞቀ ቀጠለ፡፡ ከሦስት አሠርታት በኋላ ግን ጥንዶቹ ያልጠበቁትን ዜና በፌስቡክ ገፅ አነበቡ፡፡ ከ37 ዓመታት በፊት የጠፋው የኦገስቲን ቀለበት በዕድሜ ብዛት በቆሻሻ ቢወረስም ይዋኝበት የነበረው ገንዳ ውስጥ ተገኘ፡፡ ቀለበቱን ከወር በፊት ያገኘችው ዋናተኛ ጆሲ ኒስኰ ቀለበቱን ፎቶ አንስታና በቀለበቱ ላይ የተጠቀሰውን ቀን ገልጻ ፌስቡክ ላይ ለቀቀችው፡፡ የቀለበቱን ባለቤቶች የሚያውቁ ሰዎች እንዲያፈላልጉትም ጠየቀች፡፡ መልዕክቱን ከ80,000 ሰዎች በላይ ተቀባብለውት ኦገስቲን ጋር ደረሰ፡፡ ሁኔታው ደስታና አግራሞት ያጫረባቸው ኦገስቲንና ባለቤቱ ቀለበቱን ከዋናተኛዋ ሲረከቡ በእንባ መታጠባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
********
መኪናውን ጣሪያ ላይ ያሳረፈው ሾፌር
ባለፈው ዓርብ በቻይና ኪንጋዶ በተሰኘ አካባቢ የተከሰተ ነው፡፡ ዳገት በመውጣት ላይ የነበረችው መኪና አሽከርካሪ መኪናዋ እንደፈለገው አልቆም ስትለው እንደምንም ከዋና መንገድ እንድትወጣ አድርጎ ጣሪያ ላይ እንድታርፍ ማድረጉን ዘሚረር ዘግቧል፡፡ በአደጋው አሽከርካሪውም ሆነ መኪናው ያረፈበት ቤት የነበረ ሰው አልተጎዳም፡፡ መኪናዋን ከሰው ቤት ጣሪያ ያሳረፈው ሾፌርም እንደዋዛ የመኪናዋን በር ከፍቶ ወጥቷል፡፡