Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየፌዴራል ፍርድ ቤቶች የአቤቱታ መርሐ ግብርና ተደራሽነት በአዲስ አበባ የፈጠረው ጫና

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የአቤቱታ መርሐ ግብርና ተደራሽነት በአዲስ አበባ የፈጠረው ጫና

ቀን:

በስመኘው አራጌ ይትባረክ

አዲስ አበባ ከተማ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ተዋልደውና ተቀላቅለው የሚኖሩበት የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ በመሆኗ፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያለመፈራረጅ በእኩልነት የሚኖሩባት የመቻቻል ከተማ ናት ለማለት ይቻላል፡፡ በዚያው አንፃር የሕግ የበላይነት ካልተረጋገጠ፣ ሥርዓትና ደንብ ካልተከበረባት፣ ዜጎች በእኩልነትና በፍትሐዊነት የማይስተናገዱባት ሁኔታ ከተፈጠረ የዚያኑ ያህል አስፈሪ ከተማ ነች፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ እንዳይናጋና ፍትሕ እንዳይጓደል፣ ዜጎች በየአካባቢያቸው ፍትሕ ማግኘት እንዲችሉ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ሥራዎችን በትጋት ለመሥራት ጥረት ማድረጋቸው የግድ ነው፡፡ በከተማዋ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ሄዶ ጉዳይ ለማስፈጸምና ሥራ ለመሥራት የትራንሰፖርት እጥረትና የኢኮኖሚ አቅም ውሱንነት ዜጎችን የሚፈታተኑ ጉዳዮች መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም ይቻል ዘንድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሥር ክፍላተ ከተሞች ተዋቅሮ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አስተዳደራዊና ሕጋዊ አገልግሎቶችን ዜጎች በየአካባቢያቸው እንዲያገኙ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሁሉንም የአገልግሎት ዓይነቶችና የአገልግሎት አሰጣጥን ለመገምገም ወይም አስተያየት ለመስጠት አይደለም፡፡ ዜጎች ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የተዋቀሩትን ፍርድ ቤቶች ለመመልከት ነው፡፡

በዚህ የፍርድ ቤቶች አወቃቀር በፌዴራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የአቤቱታ መስተንግዶ አሰጣጥና የተደራሽነት ጉዳይ ላይ ይህንን መጣጥፍ ለማቅረብ ወድጃለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ፍርድ ቤቶች ዕረፍት ላይ ስለሆኑ ያለፈውን ዓመት ሥራቸውን የሚገመግሙበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ጽሑፍም በአብዛኛው የሚያተኩረው ያለፈውን ዓመት አሠራር ነው፡፡

የአቤቱታ መርሐ ግብር

በፍርድ ቤቶች አሠራር ዜጎች መብታቸውን ከሚያስከብሩባቸውና የክርክር ሒደቱን ለማሳካት ወይም ለማስቆም ከሚጠይቋቸው አገልግሎቶች አንዱ አቤቱታ  ነው፡፡ አቤቱታ ከመደበኛው ክርክር ውጪ ተከራካሪ ወገኖች አስቸኳይ ጉዳይ ሲያጋጥማቸው  ለፍርድ ቤት በማቅረብ ሕጋዊ መፍትሔ የሚገኙበት ሕጋዊ አሠራር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች አስተዳደራዊ ሥራቸውን፣ የሚሠሯቸውንና አቤቱታ ለመቀበል መርሐ ግብራቸው የሚቀርፀው በፕሬዚዳንቶች በሚመራው መዋቅር እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች አቤቱታ የሚቀበሉበትንና የሚያስተናግዱበትን ቀን መርሐ ግብር በመንደፍ ለፍትሕ አካል አጋዥ ለሆኑት ዓቃቤ ሕግ፣ ጠበቆች፣ የሕግ ሙያ አገልግሎት በነፃ ወይም በክፍያ ለመስጠት ፈቃድ ላላቸው አካላት አመቺ ሁኔታ መፈጠሩን ማረጋገጥ አለበት፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ማስቻያ ሥፍራዎቸን ስንመለከት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ምድብ፣ የቀድሞው ጳውሎስ ምድብ፣ አውቶብስ ተራ አዲሱ ሚካኤል ፊት ለፊት በግምት ወደ ውስጥ 200 ሜትር ገባ ብሎ ይገኛል፡፡ የጉለሌ ክፍለ ከተማ አምስት ኪሎ ብሔራዊ ሙዚየም ፊት ለፊት የድሮ መናገሻ አውራጃ ግቢ ውስጥ መናገሻ ምድብ ችሎት በመባል በሚታወቅ ግቢ ያስችላል፡፡ የየካ ክፍለ ከተማ ደግሞ ሾላ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በራሱ ሕንፃ ላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ምድብ ችሎት ሲኤምሲ ሰሚት መንገድ ማና ሕንፃ አለፍ ብሎ ራሱ ባስገነባው ሥፍራ አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቂርቆስ ምድብ ቄራ ራሱ ባሠራው ሕንፃ በማስቻል ላይ ይገኛል፡፡ ልደታ በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ራሱ ባሠራው ሕንፃ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ኮልፌ ቀራኒዮ ጦር ኃይሎች አካባቢ በቅርቡ በተከራየው ሕንፃ ላይ ያስችላል፡፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ጎፋ ገብርኤል ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለ የኪራይ ሕንፃ ላይ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ አቃቂ ቃሊቲ መናኸሪያ አለፍ ብሎ ራሱ ባሠራው ሕንፃ ላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የአሥሩንም ክፍላተ ከተሞች የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ማስቻያ ሥፍራ ያለምክንያት አልተጠቀሱም፡፡ የሁሉም ችሎቶች የአቤቱታ ማስተናገጃ ቀን በአብዛኛው አንድ ቀን በሚሆንብት ጊዜ ለፍትሕ አጋዥ የሆኑ ከላይ የጠቀስኳቸው አካላት እንዴት እንደሚቸገሩ ልብ በሉ፡፡ በተግባርም እንደሚታየው ባለፈው ዓመት የአብዛኞቹ ችሎቶች የአቤቱታ ቀን መቀበያ ረቡዕ እንደነበረ የዚህ መጣጥፍ ጸሐፊ መረዳት ችሏል፡፡ ስለዚህ ከላይ የፍትሕ አካላቱን ያግዛሉ ተብለው የተቋቋሙ አካላትንና የፍርድ ቤት ተገልጋዮች በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ጉዳይ ሲኖራቸው ከየትኛው ሊሆኑ ይችላሉ? ይህንን የአቤቱታ ቀን በአንድ ቀን ሁሉም ችሎቶች እንዲያስተናግዱ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በሚወጣ መርሐ ግብር ሊተዳደር ይገባል፡፡

በዚህ የአቤቱታ ቀን መደራረብ ምክንያት ዜጎች መብታቸውን ሊያጡባቸው የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የጥሬ ገንዘብ ወጪ የሚደረግበት ባለ ጉዳይ የዕግድ አቤቱታ በማቅረብ የሚሸሸውን ይህንን ገንዘብ ወይም ሌላ ንብረትን ለማስቆም ረቡዕ መጠበቅ ካለበት፣ በሁለት ችሎቶች አስቸኳይ አቤቱታዎች ቢኖሩት አንዱን የማጣት ችግር ያጋጥመዋል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ለእነዚህ ችሎቶች በአንድ ከተማ ውስጥ ያሉት ቢያንስ በሳምንት ያሉትን አምስት ቀናት ሊደለደሉባቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የተደራሽነት ጉዳይ

ፍርድ ቤቶች በሥረ ነገርና በክልል የዳኝነት ሥልጣን የሚከፋፈሉበት ዋና ዓላማ ለኅብረተሰቡ ፍትሕ ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ዜጎች በአካባቢያቸው ፍትሕ እንዲያገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሥር ክፍላተ ከተሞች የተዋቀሩት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሁሉንም የችሎት ዓይነቶች አሟልተው ሊይዙ ይገባል፡፡ በተግባር እንደሚታየው ግን ሁሉም ችሎቶች ሁሉንም የክርክር ጉዳዮች አሟልተው ሲሰጡ አይታይም፡፡ ይህም ሲባል አሁን ባለው የፍርድ ቤቶች አወቃቀር የፍትሐ ብሔር፣ የቤተሰብ፣ የሥራ ክርክር፣ የወንጀል ችሎቶችና የአፈጻጸም ችሎቶች በአንድ ፍርድ ቤት ተሟልተው አይገኝም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የአቃቂ ቃሊቲ ምድብ ችሎት ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ፍርድ ለማስፈጸም ቂርቆስ ምድብ ችሎት የአፈጻጸም ፋይል መክፈት አለባቸው፡፡ ይህ ፍርድ ቤት የሚገኘው ቄራ አካባቢ ሲሆን፣ ይህ ከመደበኛው ክርክር ባልተናነሰ ጊዜና ገንዘብ የሚጠይቀው አፈጻጸም ችሎት በአቃቂ ቃሊቲ አለመከፈቱ፣ በተከራካሪ ወገኖች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ተገልጋዮች ሊገምቱ ይችላሉ፡፡ ከተደራሽነት አንፃር ይህ ተገቢ አይመስልም፡፡

በተመሳሳይ መንገድ የቦሌና የየካ ምድብ ችሎቶች የሰጧቸውን ፍርዶች አፈጻጸም የሚከፍተው በአራዳ ምድብ ችሎት ነው፡፡ ይህም በተመሳሳይ መንገድ ተገልጋዮችን ለእንግልት የሚዳርግ አሠራር ሆኖ ይታያል፡፡ የአራዳው አፈጻጸም ችሎት፣ የየካ፣ የአራዳ፣ የመናገሻ፣ የቦሌ የሰጧቸውን ፍርዶች ለማስፈጸም በአንድ ዳኛ ላይ የሚፈጠረውን የሥራ ጫናም ልብ ይሏል፡፡ በዚህ ምክንያት በአፈጻጸም ላይ የሚመደቡ ዳኞች የመሰላቸትና ከሥራው ጫና አንፃር ባለጉዳዮችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ ሲቸገሩ ይታያል፡፡

በአፈጻጸም ችሎት ሌላ መደበኛ ክርክር የማያስተናግዱ ችሎቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ የቦሌ ምድብ ችሎት ከቤተሰብና ከሥራ ክርክር ውጪ ያሉትን የውል፣ የውርስ፣ የንግድ፣ የሁከት ይወገድልኝ ክርክሮች አያስተናግድም፡፡ መንግሥት በከፍተኛ ወጪ አዳዲስ ሕንፃዎችን የገነባው የፍትሕን ተደራሽነት በማረጋገጥ ዜጎች ሁሉንም የሕግ ጉዳዮች በአቅራቢቸው ማግኘት እንዲችሉ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ደረጃ ሁሉንም አገልግሎቶች አንድ ዕርምጃ በተራመዱ ቁጥር ገንዘብ ወሳኝ በሆነበት ክልል፣ ዜጎች ፍትሕን በአቅራቢያቸው እንዲገኙ ማመቻቸት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም የሁሉም ፍርድ ቤቶች ችሎቶች ሁሉንም የክርክር ዓይነቶች አሟልተው ሊሰጡ ይገባል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችም ያለው የተደራሽነት ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በአራት ማስቻያ ሥፍራዎች ተዋቅረዋል፡፡ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ልደታ፣ ቂርቆስና ንፋስ ስልክ ላፍቶ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚስተናገዱ ሲሆን፣ የአዲስ ከተማና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች በአራዳ ሰባራ ባቡር አካባቢ የማስቻያ ሥፍራ ይስተናገዳሉ፡፡ የካና የቦሌ ክፍላተ ከተሞች ደግሞ በቦሌ ምድብ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አገልግሎቱን እንዲሰጡ ተዋቅረዋል፡፡ አቃቂ ቃሊቲ ደግሞ በአቃቂ ቃሊቲ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ ቀጥታ ክስ የሚባለውን ችሎት ከልደታ ፍርድ ቤት ውጪ ሌሎች አይሰጡም፡፡ ይህም አንደኛው የተደራሽነት ችግር ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በአንድ ማስቻያ ሥፍራ መከማቸታቸው በራሱ የሚያመጣውን ችግርም ልብ ይሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ይቀጥር እንደነበር ሁላችንም የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንድ የቼክ ጉዳይ ከሁለት ዓመት በላይ መውሰዱን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በግሉ ምስክር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የዘገየ ፍትሕ ሊከሰት የሚችለው ከመዝገቦች መብዛት፣ ሌሎች የተቋቋሙ ችሎቶች ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት ባለመቻላቸውና በአንድ ችሎት በርካታ ጉዳዮች በመከማቸታቸው ነው፡፡ ስለሆነም ተደራሽነት ዜጎች ከሚማረሩባቸው ጉዳዮች አንዱ ስለሆነ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ሆነ፣  በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙት ችሎቶች ሁሉንም የችሎት ዓይነቶች አሟልተው ሊሰጡ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፌዴራል ማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...