Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሃያ ስድስት አሮጌ ዓመታት

ሃያ ስድስት አሮጌ ዓመታት

ቀን:

በመታሰቢያ መላከ ሕይወት ገብረ ክርስቶስ

በጣም እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ነገር ቢኖር ማንም ኢትዮጵያዊ አዲስ ዓመት ሲመጣ አንድ ሰው ወይም ከዚያ በላይ መልካም አዲስ ዓመት የምትለዋን መልካም ምኞት ሳይናገር ያልፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን ዓመት በተለወጠ ቁጥር አስደንጋጭ የኑሮ ውድነትና ለኑሮ የማይመቹ ዜናዎች መስማት በእጅጉ የተለመዱ ናቸው፡፡ የቤት ኪራይ መናር፣ የዋጋ ግሽበት፣ የሰላም መታጣት፣ ወዘተ አዲሱን ዓመት የደስታና የብልፅግና ከማድረግ ይልቅ ፍርኃት እንዲይዘንና እንድንሸማቀቅ የሚያደርግበት ሁኔታ መቆሚያ ማግኘት አልቻለም፡፡

በ2008 ዓ.ም. አገሪቷ ያስተናገደችው ሕዝባዊ አመፅ የብዙ ሺሕ ሰዎችን ሕይወት በእጅጉ ያናጋ ሆኖ አልፏል፡፡ ይህንን ችግር በእጅጉ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ተመልክተንና አጥንተን እውነተኛ ሰላምን ማግኘት እንድንችል መጣር፣ ከማንኛውም አገሩን ከሚወድ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ እዚህ ላይ ልንገነዘበው የሚገባ ተግባር እውነተኛ ሰላምን ምን እንደሆነ ማወቅ ስንችል ነው፡፡ በጠመንጃና አፈሙዝ የመጣ ሰላም ሰላም ሊባል አይችልም፡፡ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር፣ ከሰብዓዊ፣ ከቁሳዊ፣ ከዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ ወዘተ ጋር ሲመጣ ብቻ ነው እውነተኛ ሰላም ሊባል የሚቻለው፡፡

እንደሚታወቀው በአንድ መንግሥት ላይ የሚነሳ ተቃውሞ በአራት የሚከፈል ነው፡፡ በመጀመሪያ አንድ መንግሥት የተሳሳተ መንገድ ይዞ ሲጓዝ ድምፃቸውን የሚያሰሙት የአገሪቱ ምሁራን ናቸው፡፡ ከዚያም በመቀጠል ሚዲያው የተቃውሞ መንደር ይሆናል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ሥርዓቱ ውስጥ የነበሩ ሥርዓቱን ለማረምና ለማሻሻል ጥረት አድርገው አልሳካ ሲላቸው ከሥርዓቱ ወጥተው ተቃዋሚ የሚሆኑበት ሒደት ነው፡፡ በመጨረሻም ሥርዓቱ የሚያራምደው ትክክለኛ ያልሆነ መንገድ የእያንዳንዱን በር ማንኳኳት ሲጀምር ሰፊው ሕዝብ (በአብዛኛው ያልተማረው የኅብረተሰብ ክፍል) አንዲት ትንሽ ሰበብ ፈልጐ አደባባይ መውጣት ይጀምራል፡፡

በዚህን ወቅት ነው የሥርዓቱ መሪዎች ብቃት የሚለካው፡፡ በብዙ አገሮች እንደታየው ሕዝባዊ አመፅን በጠመንጃ አፈሙዝ ለማስቆም የሞከሩ ራሳቸውንም አገራቸውንም ለውድመት ነው የዳረጉት፡፡ መፍትሔ የሚሆነው ማንኛውንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊና ፖሊሲያዊ ፈጣን ለውጥ በማምጣት ብቻ ነው ያንን ሥርዓት ማዳን የሚቻለው፡፡ በዓለማችን የአመፆች ታሪክ ሚኒስትሮችንና ሌሎች ባለሥልጣናትን በመቀየር የተረፈ አንድም ብልሹ ሥርዓት የለም፡፡ ምክንያቱም እነዚያን ብልሹ ባለሥልጣናት የፈጠረው ብልሹ የሆነው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህን ሰዎች አምጦ የወለዳቸው ሥርዓቱ በመሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ እንደ አንድ ዜጋ በአገራችን ያለው ዋና ችግር ምንድነው የሚለውን ጉዳይ ብዕሬን ከማንሳቴ በፊት፣ ከብዙ ምሁራንና ከአንባቢያን ጋር ውይይት አድርጌ የደረስኩበት አንድ ድምዳሜ አለኝ፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው ሰፊ በመሆኗ በተለያዩ ቦታ የተለያየ የሁከት መጠን፣ ችግሮችና ተግዳሮቶች እንዳሉ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ (ከዚህ ቀደም በሪፖርተር ጋዜጣ ለማመልከት እንደሞከርኩት) የተለያየ የፌዴራል ሥርዓት መኖሩ አንዱ ክልል ለልማትና ለኢቨስትመንት አመቺ ሲሆን ሌላው ደግሞ መንደርተኝነት ጠባብነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ፣ ለልማትና ለኢንቨስትመንት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በአገራችን የታየው ጉርብጥብጥ ያለ ዕድገት በተለይ አሁን ላይ አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን ቀላዋጭ እያደረገ በመሆኑ፣ አሁን ላለው ብጥብጥና አለመረጋጋት እንደ ዋና ምክንያት አድርጐ መውሰድ ይቻላል፡፡

ሌላው ደግሞ መብትን በተመለከተ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች አንድ ዜጋ የቤት ባለቤት የመሆንና ቤቱን የማከራየት ከዚያም በላይ የመሸጥ መብት ሲኖረው፣ የገጠሩ ማኅበረሰብ ግን ያለው መብት መሬቱን ማረስና ማከራየት ብቻ ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል የሚል ሕግ ያወጣ መንግሥት እንዴት መሬት የመሸጥ መብት ይከለክላል? አንድ ገበሬ ዕድሜው በሚደክምበት ጊዜ መሬቱን ሸጦ ወደ ከተማ ሄዶ ቀለል ያለ ሥራ እየሠራ የመኖር መብቱን ሕገ መንግሥቱ አግዶታል፡፡

ለምሳሌ አንድ ገበሬ አሥር ልጆች ቢኖሩትና ሁለት ሔክታር መሬት ቢኖረው፣ ገበሬው ዕድሜው ሲገፋ መሬቱን ለልጆቹ ሲያከፋፍል በመሬት መጣበብ ሳቢያ ሁሉም ድሆች ነው የሚሆኑት፡፡ ነገር ግን ይህ ገበሬ መሬቱን ለባለ ሀብት ሸጦ የተወሰነ ገንዘብ ቢያገኝ፣ ባለሀብቱ መሬቱን አልምቶ ለገበሬው ልጆችና ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ በዚያ አካባቢ ያልነበሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ልማቶችን የሚያመጣ በመሆኑ፣ መንግሥት ወደ ሌሎች ጉዳዮች ፊቱን እንዲያዞር ይረዳዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ጐረቤቶችዋ በረሃማ የሚበዛባት አገር ሳትሆን አብዛኛው የአገሪቱ መሬት ሊታረስና ለተለያዩ ልማቶች ሊውል የሚችል በመሆኑ፣ ላለፉት ዓመታት ዋና ትኩረታችን በዚህ ዘርፍ ላይ አለማድረጋችን አሁን ለምናየው አለመረጋጋት ዋነኛው ችግር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሥልጣን የያዘው ኃይል በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ለሰፋፊ እርሻዎች (Commercial Farming) ቤተሰባዊ እርሻ (Substantial Farming) የሚሆነውን መሬት በካርታ ደረጃ በመለየት ሰፊ ሥራ መሥራት ቢገባውም፣ ይህንን አለማድረጉ ትልቅ ጉድለት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ተራራማ ቦታዎች ለቤተሰብ እርሻዎች፣ ሜዳማ ቦታዎች ለሰፋፊ እርሻዎች ተብሎ መለየቱ እጅግ ወሳኝ ሥራ ነው፡፡ ሌላው ትልቅ ችግር ነው ብዬ የማምነው በሕገ መንግሥቱ ላይ የመሬትን ባለቤትነት ለመንግሥት ብቻ ማድረግ የሚያስከፍለው ዋጋ አደገኛ መሆኑ ነው፡፡

በእኔ እምነት መሬት በአምስት ባለቤቶች ተከፍሎ መተዳደር አለበት፡፡

  1. የፌዴራል መንግሥት የሆነ የመሬት ይዞታ

ይህ ዓይነት ይዞታ የፌዴራል መንግሥት ለተለያዩ ተግባራት ማለትም እንደ ብሔራዊ ፓርኮች፣ ታላላቅ የባቡርና የመንገድ ልማቶች የሚገነቡባቸው መሬቶች፣ የዩኒቨርሲቲዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የወታደራዊ ተቋማት፣ የኤርፖርቶች፣ ወዘተ የመሳሰሉ የመሬት ይዞታዎች የፌዴራል መንግሥት ይዞታ ሆነው መያዛቸው በእጅጉ ተገቢ ነው፡፡   

  1.  የክልል መስተዳድሮች የሚያስተዳድሩት መሬት

ይህ ዓይነቱ መሬት ለትምህርት ቤቶች፣ ለስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ ለፓርኮች ወዘተ የሚያገለግሉ የሚሆኑ ይዞታዎች በክልል መስተዳደሮች በባለቤትነት ቢተዳደሩ በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ 

  1. በግለሰብ የሚያዙ መሬቶች  

ማንኛውም ዜጋ የከተማም ሆነ የገጠር ነዋሪ የእኔ የሚለውና በማንኛውም ጊዜ ሊያለማው፣ ሊያከራየው፣ ሊሸጠውና ሊለውጠው የሚችለው የመሬት ይዞታ ባለቤት ሊሆን ይገባል፡፡ የማንኛውም ዜጋ የዜግነት መብት ከመሆኑም በላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ መብት በመሆኑ ይህ መብት ያለ ምንም መሸራረፍ መከበር አለበት፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ ዕድገት በያዘው ይዞታ ላይ ተግቶ የሚሠራውና በራስ መተማመን የሚጨምረው፣ የባለቤትነት መብት ያለምንም መሸራረፍ ሲከበር ብቻ ነው፡፡ በእኔ እምነት አሁን ለሚታየው አለመረጋጋት ይህ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡   

  1. በማኅበረሰብ ተቋማት የሚያዝ መሬት

የሃይማኖት ተቋማት፣ እድሮች፣ አክስዮን ማኅበራት፣ ወዘተ የብዙኃን ንብረት የሆነ የመሬት ይዞታ ነው፡፡    

  1. በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያዝ መሬት 

ኤምባሲዎች፣ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አፍሪካ ኅብረት ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያዙ የመሬት ይዞታዎች ሲሆኑ፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው ይላል እንጂ፣ እነዚህ የመሬት ይዞታዎች መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ሊያዝባቸው የማይችሉ ይዞታዎች ናቸው፡፡

በዚህ መንገድ ሕገ መንግሥቱ ቢስተካከል ሁሉም የመሬት ባለቤት ኖሮት ተገቢውን እንክብካቤ የሚያገኝ በመሆኑ በአገሪቱ ውስጥ ፈጣን ዕድገትንና ሰላምን ማየት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ዜጋ ጊዜውን በሥራ ስለሚያሳልፍ ለፖለቲካ የሚሆን ጊዜ እምብዛም አይኖረውም፡፡

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት እየሞከረች ስትሆን፣ ለዚህ ልማት ትልቁ ግብዓት ኤሌክትሪክ ወይም የሰው ኃይል ሳይሆን፣ የፋብሪካ ሠራተኛ ሊገዛው የሚችለው ዝቀተኛ ዋጋ ያለው ምግብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚገኘው ከሰፋፊ እርሻዎች ብቻ ነው፡፡

ኢሕአዴግ አስፈላጊውን እርምት ማድረጉ ለሰላምም ለዕድገትም የግድ ጠቃሚ በመሆኑ፣ ሥልጣን የያዘው ኃይል ይህንን ወሳኝና ድፍረት የተሞላው ዕርምጃ ለመውሰድ ብቃቱን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡

ሌላው እጅግ አሳሳቢ የሆነውና ሕገ መንግሥታዊ ግድፈት ነው ብዬ የማምነው ክልሎች ተጠሪነታቸው ለራሳቸው መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ክልላዊ መንግሥታት የይስሙላ ሥልጣን ይዘው ለሕዝባቸው ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው፣ ሁሉም ክልሎች የግድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ለማዕከላዊ መንግሥት ተጠሪና ተጠያቂ መሆናቸው የግድ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ይህ የሕገ መንግሥት አንቀጽ በአስቸኳይ መታረም አለበት፡፡

እዚህ ላይ ሶማሌላንድን ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህች አገር የራስዋን ነፃነት ያወጀች ቢሆንም በማንም ዓለም አቀፋዊ ተቋም ወይም መንግሥት ዕውቅና ባለማግኘቷ፣ አንድም ዓይነት የኢንቨስትመንት ወይም የውጭ ብድር ዕርዳታ አግኝታ አታውቅም፡፡ የክልል መንግሥታት ራሳቸውን ማስተዳደራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተጠሪነታቸው የግድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ ጠቀሜታው በዋናነት ለክልሎች ነው፡፡ ፍትሐዊና ተመጣጣኝ ዕድገት በመላው አገሪቱ ለማየት፣ እንዲሁም በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል ጊዜ ሳይባክን ውሳኔ ለማስተላለፍ የሕዝብን እርካታ ለማምጣት ወሳኝ በመሆኑ በአፋጣኝ ሊተገበር የሚገባው ተግባር ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢዮጵያዊነት ቦሌ ኤርፖርትና ኦሎምፒክ መድረክ ላይ ብቻ እንጂ፣ ከቦሌ ኤርፖርት ወጥተን ወደ ቤታችን ስንሄድ ሁላችንም መንደርተኞች ነን፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ የሚለው ፓስፖርት የምንገለገልበት ቦሌ ኤርፖርት ብቻ በመሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ አንድ ገና ዕድሜው በሃያዎቹ ገደማ ያለ ወጣት የነገረኝን ላውጋችሁ፡፡ ወጣቱ የተወለደው በሐዋሳ ከተማ ነው፡፡ እናቱ የካፋ ብሔረሰብ አባል ስትሆን አባቱ ደግሞ የሲዳማ ብሔር አባል ነው፡፡ ይህ ልጅ ከልጅነቱ ጀምሮ የእናቱንና የአባቱን ቋንቋ ሳይሆን አማርኛ እየተናገረ ያደገ በመሆኑ ዕድሜው መታወቂያ ለማውጣት ሲደርስ ወደ ቀበሌ ጽሕፈት ቤት ሄዶ መታወቂያ ያወጣል፡፡ በዚህን ጊዜ ብሔርህ ምንድነው ብለው ሲጠይቁት ‘እናቴ ካፋ ነች፣ አባቴ ደግሞ ሲዳማ ነው፡፡ እኔ የምናገረው አማርኛ ብቻ ነው’ ብሎ ሲናገር መታወቂያ የሚሰጠው ግለሰብ ‘እንግዲያው አንተ አማራ ነህ’ ብሎ መታወቂያው ላይ ሞልቶ ይሰጠዋል፡፡

ልጁም ለነገሩ ብዙም ዋጋ ሳይሰጥ መታወቂያውን ተቀብሎ ሲገለገልበት ይቆይና አንድ ቀን የሐዋሳ ማዘጋጃ ቤት የሥራ ማስታወቂያ አውጥቶ ወጣቶችን ሲቀጥር፣ ይህ ልጅም እንደ ማንኛውም ወጣት ማመልከቻ ሞልቶ ሲወዳደር ፎርሙን የተቀበለው ሠራተኛ ‘አንተ ብሔርህ አማራ ስለሆነ አማራ ክልል ሄደህ ተቀጠር፡፡’ ይህ የሥራ ዕድል የሚፈቀደው ለክልሉ ተወላጆች ነው ሲለው፣ እኔ እዚህ ነው የተወለድኩት ብሎ ለመከራከር ቢሞክርም ሰሚ ባለማግኘቱ ተስፋ ቆርጦ አሁን አዲስ አበባ መጥቶ የታክሲ ሾፌር ሆኖ ለመሥራት እንደተገደደ አጫውቶኛል፡፡

እንግዲህ በእንዲህ ዓይነት አስገራሚ ሁኔታ ዜጐችን በገዛ አገራቸው ወይም በዜግነታቸው ሊያገኙት የሚገባን መብት መከልከል የመጨረሻው ውጤት ምን ሊሆን ይችላል? እኔ በግሌ ይህ ሁኔታ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡ ማንም አገሩን የሚወድ ዜጋም የእኔን ሐሳብ የሚጋራ ይመስለኛል፡፡ ምንጊዜም የሚጠቅመን ትልቅነት ብቻና ብቻ ነው፡፡ ትልቅ፣ ጠንካራና አንድ ስንሆን ብቻ ነው ትልቁን የችግር ቋጥኝ ልንፈነቅል የምንችለው፡፡ ልዩነት ይጨፍለቅ የሚል ሐሳብ ባይኖረኝም አንድነት ተገቢውን ትኩረት ይሰጠው የሚል የፀና እምነት የእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የሚሊዮኖች በመሆኑ በዚህ መልክ ብንራመድ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

እንደ ማጠቃለያ የመረጥኩት ርዕስ 26 አሮጌ ዓመታት ይለፉና 27ኛውን ዓመት እስኪ ሁላችንም በእርግጥ አዲስ ዓመት እንዲሆን ሁላችንም ቃል ኪዳን እንግባ፡፡ በዓለማችን ያሉ ሥልጣኔዎችን ሁሉ የወለደው ሳይንሳዊ የሆነ ሥርዓት ነው፡፡ ይህንን ሳይንሳዊ ሥርዓት ለመፍጠር ደግሞ እጅግ እልህ አስጨራሽ መንገዶችን መጓዝ ግድ ይላል፡፡ በወኔና በዓላማ የታጠቁ አርበኞች ብቻ ናቸው ለሕዝቦች፣ ለአገር፣ ለትውልድ የሚጠቅም ሥርዓት አውርሰው ያለፉት፡፡ ይህ ደግሞ ከማንም በላይ ሥልጣን ላይ ካለው አካል የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

ማንኛችንም ከእናታችን ማህፀን ስንወጣ የቋንቋ ችሎታ ይዘን የወጣን ሳይሆን ሆድ ነው ይዘን የወጣነው፡፡ ቋንቋ በምንኖርበት አካባቢ የሚለጠፍብን ክስተት ነው፡፡ በመሆኑም ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ የተሻለ ሕይወት ሊያኖረን የሚችለውን ጉዳይ በመሆኑ፣ በዚህ መልክ ብናስብ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የተለያዩ መብቶችን ላንዱ በማንኪያ ለሌላው በጭልፋ፣ ለሚፈልጋቸው ደግሞ በአካፋ እየሰጠ በሕዝቦች ዘንድ አመፅ ተረግዞ እንዲወለድ ተግቶ መሥራቱን በማቆም፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የሚወጡ ፖሊሲዎች ሁሉ በተቻለ መጠን ፍትሐዊ መሆናቸውን 100 ጊዜ ማረጋገጥ አለበት፡፡

በዚህ በያዝነው 21ኛ ክፍለ ዘመን ማንኛውም መንግሥት ሕዝብ ማስተዳደር የሚችለው የዜጐችን መብቶች አክብሮ ብቻ በመሆኑ፣ ይህንን ጉዳይ መንግሥት ተገንዝቦ በፖሊሲ አወጣጥና ትግበራ ላይ ሰፊው ያልተማረው ሕዝብ እስኪነግረው ሳይጠብቅ ምሁራንን እያዳመጠና ስህተቶች ቶሎ ቶሎ እየታረሙ መሥራት ምንም አማራጭ የሌለው ተግባር ነው፡፡ በእኔ እምነት ላልተማረ ኅብረተሰብ አመፅ ቋንቋ ነው፡፡ ሰዎች ብሶታቸውን የሚገልጹበት መድረክ ሲያጡ ንብረት በማውደምና ሌሎች አውዳሚ ተግባራትን በመፈጸም መልዕክት ለማስተላለፍ ይሞክራሉ፡፡ እንዲያም ሲል እንደ ቱኒዝያዊው መሐመድ ቡአዚዝ ራሳቸው ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ መልዕክት ለማስተላለፍ ይሞክራሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው መንግሥት ችግሮችን በራሱ መንገድ ፈልጐ ማግኘትና መፍትሔ ማፈላለግ ሲሳነው ነው፡፡ ሕዝባዊ አመፅ ደግሞ ልክ እንደተሰበረ ግድብ አንዴ ውኃውን መልቀቅ ከጀመረ የሚያቆመው ነገር ባለመኖሩ፣ ከወዲሁ እልህ አስጨራሽ ዕርምጃዎችንና እርምቶችን በመውሰድ ራስንም አገርንም ማዳን ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡

አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ በደቦ የምትመራ በመሆኑ አዲስ ሐሳብ በኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ማመንጨት ለከፍተኛ አመራሮች አደጋ ያስከትላል የሚል እምነት ቢኖረኝም፣ ውሳኔውን አለማስተላለፉ ከዚያ የከፋ ችግር ስላለው እዚህ ላይ ወገብን ጠበቅ ማድረጉ የግድ ይላል፡፡ አራቱ አንጋፋ ከፍተኛ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በቅርቡ በቴሌቪዥን መስኮታችን ብቅ ብለው አሁንም ሕገ መንግሥቱ ምንም እንከን እንደሌለውና አፈጻጸሙ ላይ ብቻ ችግር እንዳለ ነግረውን ነበር፡፡ ይህ ግን ጭልጥ ያለ ግትርነትና ኃላፊነት የጐደለው አመለካከት በመሆኑ፣ አሁንም በድጋሚ በጥልቅ አስቡበት እያልኩ 2009 ዓ.ም. ጨምሮ 26 ዓመታት አሮጌ ብለን እንውሰዳቸውና በ2009 ዓ.ም. ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጀምሮ እስከ ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ያለን ዜጐች ሁላችንም ለሰላምና ለእርምት ዝግጁ ሆነን ከሠራን፣ እውነተኛ መልካም አዲስ ዓመት የምናይበት ጊዜ በቅርብ ርቀት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...