በሶሪያ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ሕዝቡ እጁን ለዕርዳታ ሰጥቷል፡፡ መድኃኒት፣ የትምህርት ቤት ቁሳቁስ፣ ስንዴ፣ ዘይትና ሌሎችም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት ለሕዝቡ እየታደሉ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በዕርዳታ ተሽከርካሪዎች መሣሪያ ይገባል፣ ዕርዳታ ወዳልተፈለገ ቦታ ይሄዳል የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ ከርመዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕርዳታውን አላስተጓጎለም፡፡ ሕዝቡንም ሲደርስ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ሰኞ መስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ዕርዳታ በጫኑ 18 የድርጅቱ ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ምክንያት፣ ምንም ዓይነት ዕርዳታ ወደ ሶሪያ እንዳይገባ አግዷል፡፡
ከሶሪያ አንደኛዋ ከተማ አሌፖ አቅራቢያ መድኃኒት፣ ስንዴ፣ የትምህርት ቁሳቁስ፣ ብርድ ልብስ፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ቫይታሚንና የተለያዩ አልባሳት ጭነው ሲገቡ ከነበሩ 31 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዕርዳታ ተሽከርካሪዎች 18 ያህሉ በአውሮፕላን ድብደባ ወድመዋል መባሉን ተከትሎ፣ ድርጅቱ ምንም ዓይነት ዕርዳታ ወደ ሶሪያ እንዳይገባ ማገዱ፣ ቀድሞውንም በጦርነት እየማቀቁና በዕርዳታ ጥላ ሥር ለወደቁ ሕፃናት፣ ሴቶችና ሌሎችም ፈተና ይሆናል፡፡
የአሁኑ ዕርዳታ ይጓዝ የነበረው ለመጨረሻ ጊዜ ከሁለት ወራት በፊት ዕርዳታ ወዳገኙና ቁሳቁስና ምግብ ላለቀባቸው ሶሪያውያን ነበር፡፡ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ጭነው ነበር ከተባሉት ባለተሳቢ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ 20 ሰዎች ሲሞቱ፣ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሶሪያ የቀይ ጨረቃ ከፍተኛ ባለሥልጣን ይገኙበታል፡፡
ቢቢሲ እንደሚለው፣ ድርጅቱ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ አጠቃላይ ዕርዳታ ወደ ሶሪያ ከመላክ መቆጠቡን አሳውቆ ለጥቃቱም የሶሪያን መንግሥት ኮንኗል፡፡ ሆኖም ለሶሪያ መንግሥት ወታደራዊ ዕርዳታ የምትሰጠውን ሩሲያ ተሽከርካሪዎቹ ላይ ጥቃት አለመፈጸሟን ስታሳውቅ፣ በሶሪያ በኩልም በተሽከርካሪዎቹ ላይ የአውሮፕላን ድብደባ እንዳልተካሄደ ተነግሯል፡፡
ሶሪያም ሆነች ሩሲያ በእንደዚህ ዓይነቱ ተግባር እንዳልተሳተፉ ሲገልጹ፣ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሺንኮቭ፣ ተሽከርካሪዎቹ በጦር በአውሮፕላን ሲደበደቡ ተቀርጸዋል የተባሉ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን መርምረው፣ ተሽከርካሪዎቹ በጦር መሣሪያ እንደተመቱ የሚያሳይ ምንም ምልክት ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ቪዲዮው የሚያሳየውም አማፂያን በአሌፖ ከፈጸሙት መጠነ ሰፊ ጥቃት ጋር ተያይዞ ከተነሳ እሳት ጋር ቀጥታ ግንኙነት መኖሩን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
የሶሪያ የመንግሥት ሚዲያ የአገሪቱን መከላከያ ኃይል ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ የሶሪያ ወታደሮች ተሽከርካሪዎቹን ዒላማ አድርገዋል መባሉን አጣጥሎ፣ ‹‹እውነት የለውም›› ብሏል፡፡ ቢቢሲ የዓይን እማኝ ጠቅሶ እንደሚለው ግን፣ የሩሲያ የጦር አውሮፕላን ተሽከርካሪዎቹ የሚያልፉበትን ሥፍራ ሲቀርፅ ነበር፡፡ የመጀመርያው የቦምብ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በተከታታይም የሮኬትና የመትረየስ ጥቃት ተፈጽሟል ብሏል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተሽከርካሪዎች ዕርዳታውን ጭነው ወደ ሶሪያ ከመግባታቸው በፊት በጄኔቫ የሚገኙ የዕርዳታ ሠራተኞች ሁሉንም የይለፍ ፈቃድ ጨርሰው ነበር፡፡ በሶሪያ የሚዋጉ ሁሉም አካላትም እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡ የሶሪያ መንግሥት፣ ሩሲያና አሜሪካም የዕርዳታ ቁሳቁስ የጫኑት ተሽከርካሪዎች እንደሚገቡ ያውቃሉ፡፡ ሆኖም ኃላፊነቱን እወስዳለሁ የሚል አካል ባይገኝም፣ ወደ ሶሪያ ከገቡት የዕርዳታ ተሽከርካሪዎች መካከል 18 ያህሉ መውደማቸው በሚዲያዎች ታይቷል፡፡ በውስጣቸውም ለ78 ሺሕ ሰዎች የሚሆን ቁሳቁስ ነበር የያዙት፡፡ ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የሶሪያ ቀይ ጨረቃ ጽሕፈት ቤት በሶሪያ ላይ የዕርዳታ ገደብ ጥለዋል፡፡ ይኼም ቀድሞውንም በስቃይ ውስጥ የነበሩትን ሶሪያውያን በዚሁ እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡
የተፈጸመው ጥቃት በሶሪያ የሰብዓዊ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያደናቅፍ ነው፡፡ ለዚህም በሶሪያ ለሳምንት ዘልቆ የነበረው ተኩስ አቁም መልሶ መጀመሩ ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ማን ጣሰው? ለሚለው የሶሪያ መንግሥትና አማፂያን እርስ በርስ ቢወነጃጀሉም፣ ጥሰቱን የፈጸሙት ጦርነቱን በሰው ምድር እያደረጉ ያሉት አሜሪካና ሩሲያ ናቸው የሚሉ መኖራቸውንም አልጄዚራ ዘግቧል፡፡
የመንግሥት ደጋፊዎችና አማፂያን በደቡብ ምዕራብ አሌፖ የእግረኛ ውጊያ ማድረግ የጀመሩ ሲሆን፣ ይኼም በአሌፖ የአየር ድብደባ እንዲያገረሽ አድርጓል፡፡ ከመስከረም 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሳምንት በዘለቀው ተኩስ አቁም ስምምነት የዕርዳታ ቁሳቁስ ለማስገባት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ በቀጣይም አሜሪካና ሩሲያ በመተባበር ተኩስ አቁሙ ቀጣይነት እንዲኖረው ከስምምነት እንዲደርሱ መንገድ ይከፍታል ተብሎ ነበር፡፡ ሆኖም የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለሳምንት ቢዘልቅም፣ ከዚህ ግን መዝለል አልቻለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶሪያ መንግሥት ዕርዳታዎቹ እንዳይደርሱ እንቅፋት ፈጥሯል ሲል፣ ሶሪያ ተሽከርካሪዎቹ ላይ ተኩስ የከፈቱት አማፂያን ናቸው ብላለች፡፡
አሜሪካና ሩሲያ በሶሪያ ጣልቃ መግባታቸው አገሪቷ ይባስ እንድትወድም እያደረገ ነው፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ 500 ሺሕ ሶሪያውያን ሞተዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተሰደዋል፡፡ 18 ሚሊዮን ያህሉ ጦርነት ባመሰቃቀላት ሶሪያ በሕይወትና በሞት መካከል መኖርን ቀጥለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 13.5 ሚሊዮን ያህሉ በዕርዳታ የሚኖሩ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል፡፡ 4.5 ሚሊዮን ያህሉን በዕርዳታ ለመድረስ በጣም አዳጋች ነው፡፡ በአገሪቷ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት 24.5 ሚሊዮን ነዋሪዎች የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ግን ስድስት ሚሊዮን ያህሉ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 500 ሺሕ ያህሉ ሞተዋል፡፡ ከ4 ሚሊዮን በላይም ተሰደዋል፡፡
የሶሪያ ጥናትና ምርምር ማዕከል እንደሚለው፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ አገሪቱ 255 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢኮኖሚ ውድቀት ገጥሟታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 በአገሪቱ የነበረው የሥራ አጥ ቁጥር 14 በመቶ ሲሆን፣ አሁን ግን 70 በመቶ ሕዝብ በድህነት ውስጥ ተዘፍቆ መሠረታዊ ምግብና መጠለያ እንኳን ማግኘት ተቸግሯል፡፡
አገሪቱ ትታወቅበት የነበረው የእርሻ ኢንዱስትሪ ዛሬ ተዳክሟል፡፡ አገሪቱም የምግብ አቅርቦት እጥረት ውስጥ ገብታለች፡፡ በመሆኑም ምግብ እንደ ጦር መሣሪያ እያገለገለ ነው፡፡ ሸማቂዎችን የደገፈ አካባቢ በምግብ አቅርቦት ይቀጣል፡፡ ሸማቂዎች ባሉበት መንግሥትን የሚደግፍ ካለም፣ ሸማቂዎች ነዋሪዎችን ምግብ እንዳይገባ በመከልከል ይቀጣሉ፡፡ ይኼም በአገሪቱ የምግብ ዋጋ ውድ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ከዩክሬንና ከሩሲያ ስንዴ በማስመጣት በእሳቸው ቁጥጥር ሥር ላሉ ግዛቶች የምግብ አቅርቦት በተነፃፃሪ የተሻለ እንዲሆን ቢያደርጉም፣ በአማፂያን ቁጥጥር ሥር ባሉ ሥፍራዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በሰቆቃ ውስጥ ናቸው፡፡
ሶሪያ በጦርነት ውስጥ ያለች ከመሆኗ አንፃር የሕክምና አገልግሎት ወሳኝ ቢሆንም፣ ሰዎች በጦር መሣሪያ ቆስለው ያለ በቂ ሕክምና የሚሰቃዩባት አገር ሆናለች፡፡ በአገሪቱ በሚገኙ 240 የሕክምና መስጫ ተቋማት ላይ 336 ጊዜ ያህል ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በጥቃቱ 679 የሕክምና ባለሙያዎች ተገድለዋል፡፡ አገሪቱ ካሏት 113 የሕዝብ ሆስፒታሎች 58 በመቶ ያህሉ በግማሽ ወይም ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት የማይሰጡ በመሆናቸው፣ 40 በመቶ ያህሉ ነዋሪዎች የሕክምና ዕርዳታ ለማግኘት ተቸግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2011 ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ሞተዋል፡፡ በአገሪቱ በመማር ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ቁጥርም ቀንሷል፡፡ ሰላም አላቸው በሚባሉ ከተሞች ከሚኖሩ ሕፃናትም 40 በመቶ ያህሉ ትምህርት ቤት አይሄዱም፡፡ የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት በጦርነት ተሽመድምዷል፡፡ 52 ሺሕ ያህል መምህራንም ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአገሪቱ በተከሰቱ ቀውሶች የተጎዱት ነዋሪዎች በዕርዳታ ለመድረስ ነበር የትምህርት፣ የሕክምናና የምግብ ቁሳቁስ ወደ ሶሪያ የሚልከው፡፡ ሆኖም በያዝነው ሳምንት እንቅፋት ገጥሞታል፡፡ የዕርዳታ ተሽከርካሪዎች በጦር መሣሪያ በመጋየታቸው የተነሳም ዕርዳታዬን አቁሜያለሁ ብሏል፡፡ የዕርዳታ ዕገዳው እስከ መቼ ይዘልቅ ይሆን? የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል፡፡