Saturday, September 24, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ድምፅ ይሰማ!

  ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ከመንግሥት ተወካዮች ጋር እየተወያዩ ነው፡፡ የመወያያ አጀንዳው ባለፉት  25 ዓመታት በትምህርት መስክ በተመዘገቡ ስኬቶችና ባጋጠሙ ችግሮች ላይ እንዲያተኩር ቢፈለግም፣ መምህራኑ በወቅታዊው አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ በመመሥረት ያቀረቧቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ገበታ ላይ 30 ሚሊዮን ያህል ዜጎች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ ከትምህርት ጥራት፣ ከአካዴሚክ ነፃነት፣ ከመማር ማስተማሩ አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታና ከመሳሰሉት አንፃር ብዙ መባል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አሌ አይባልም፡፡ ነገር ግን በመላ አገሪቱ የሥጋት መነሻ የሆኑ በርካታ ቅሬታዎችን ወደ ጎን በመግፋት በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ መምህራኑን ተነጋገሩ ማለት አግባብ አይደለም፡፡ ስለሆነም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርት ዘርፍ በተጨማሪ በአገር ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚሉት መደመጥ ይኖርበታል፡፡

  በ1994 ዓ.ም. መንግሥት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ከምሁራን ጋር ስብሰባ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ በወቅቱ ምሁራኑ ለመንግሥት ያቀረቧቸው ጥያቄዎችና የሰጡዋቸው ምክረ ሐሳቦች ተድብስብሰው ቢቀሩም፣ በወቅቱ በችግርነት የተነሱ ሥጋቶች በአሁኑ ጊዜ በገሃድ እየታዩ ነው፡፡ ከ15 ዓመታት በኋላ መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን መድረክ ሲያዘጋጅ ውይይቶቹ  በተካሄዱባቸው የትምህርት ተቋማት በአመዛኙ ተመሳሳይ የሆኑ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ በአወያዮች ብቃትና ተቀባይነት ላይ የተነሱ ጥያቄዎችም አሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን አሁን ወቅቱ በአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመፍትሔ የሚበጁ ሐሳቦችን የሚያዋጡበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነን፡፡ በመሆኑም የምሁራኑ ድምፅ በሚገባ መሰማት አለበት፡፡

  ወቅታዊው አገራዊ ጉዳይ በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብለው የሚነጋገሩበት እንጂ፣ በአስመሳይነትና በአድርባይነት እያድበሰበሱ የሚያልፉት ተራ ጉዳይ የለም፡፡ መንግሥት በተቃውሞ ጎራ ያሉ ወገኖች ይሰገሰጉብኛል፣ ዕቅዴን ያከሽፉብኛል ወይም ውዳሴና ምሥጋናዬን ያበላሹብኛል ከሚል እሳቤ በመውጣት ለአገር ጠቃሚ አስተዋጽኦ የሚኖራቸውን ወገኖች ሊሰማ ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም አስመሳይና አድርባይ ምሁር ተብዬዎችን በማሰባሰብ በአገር ላይ የተደነቀደው ሥጋት ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነሆ ከ25 ዓመታት በኋላ በተለያዩ ዓውዶች ሲነገሩ የነበሩ ስኬቶች ከበስተጀርባቸው ያሉትን ጉድፎች መደበቅ አልቻሉም፡፡ ከዚህ ቀደም በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መዛባትና በሙስና ዙሪያ የሚያጠነጥኑት የአገሪቱ ችግሮች እንደ ልቃቂት እየተጎለጎሉ በርካታ ተግዳሮቶችን አሳይተዋል፡፡ መደማመጥ ባለመቻሉ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች መሆናቸውን ማመን ተገቢ ነው፡፡

  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመነሻው የትምህርት ጥራት አንደኛው ችግር ቢሆንም፣ የአካዴሚክ ነፃነት ጉዳይ ደግሞ ሌላው የዓመታት ችግር ነው፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እየተንሸራሸሩ ዜጎች የሚቀረፁባቸው የዕውቀት ማዕከላት መሆን ሲገባቸው፣ የበርካቶች አንደበቶች የተሸበቡባቸው ናቸው፡፡ የደርግ ዘመንን ከነአስከፊነቱ ትተን፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በተሻለ ደረጃ የአካዴሚክ ነፃነት የነበራቸው የትምህርት ተቋማት ምን ያህል እንደተሸበቡ ለማወቅ ዝምታቸው ብቻ በቂ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በአንድ ወቅት ሁሉም የፖለቲካ አጀንዳዎች የሚመነጩባቸው ተቋማት ከመሆን በዝምታና በምን አገባኝ ስሜት የተገለሉ ሰዎች መሰባሰቢያ መሆናቸው ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ እየሆነ ያለው የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን ሳልሸራርፍ እተገብራለሁ ብሎ ቃል በገባው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት መሆኑ በራሱ ተቃርኖ ነው፡፡  በተጨማሪም የብዙዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ብቃት ጉዳይም አጠያያቂ ነው፡፡ በትምህርት ተቋማት ውስጥ የመምህራኑ ምደባ፣ ዕድገት፣ ዝውውር፣ የትምህርት ዕድልና በመሳሰሉት ኃላፊነት በማይሰማቸው አመራሮች ምክንያት የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ በቡድን በሚፈጸሙ ዝርፊያዎች ምክንያት ተቋማቱ እንኳን ትውልድ ሊያበቁ አሳዛኝ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ውይይት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከ25 ዓመታት በኋላ ዕውቀትን፣ የሙያ ችሎታንና የሥራ ስሜትን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራር ውስጥ ማገናኘት አለመቻል በራሱ ከባድ ነው፡፡

  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሐሳቦች የሚፍለቀለቁባቸውና የሕዝብ ብሶቶች የሚንፈቀፈቁባቸው ትንሿ ኢትዮጵያ መሆን መቻላቸው የሚጠቅመው አገርን ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ነባር የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኘውን የዕውቀትና የብልኃት አቅም በአግባቡ አነቃንቆ ለመፍትሔ ለማዋል ፍላጎት መኖር ሲገባ፣ ይኼንን መልካም አጋጣሚ እንደገና ማዳፈን አይገባም፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የአካዴሚክ ነፃነት የሚያስናፍቅ እስኪሆን ድረስ ራስን ዝቅ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ ምሁራኑ ከአካዴሚክ ነፃነታቸው እስከ አገራዊው ዘርፈ ብዙ ችግር ድረስ መነጋገር ሲጀምሩ የገጠሙት ችግሮች መንስዔዎች በግልጽ ይታወቃሉ፡፡ ለመፍትሔ ፍለጋም ይረዳሉ፡፡ በተለመደው ሁኔታ ተገኙ በተባሉ ስኬቶች ላይ ብቻ ለመንጠልጠል ከመፈለግ ይልቅ፣ መሠረታዊ የሚባሉ ችግሮች ላይ በግልጽነትና በሀቀኛ መንፈስ መነጋገር ይበጃል፡፡

  በሰሞነኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውይይት ላይ የታየው ሌላው መሠረታዊ ችግር የመንግሥት ተወካዮች ተናጋሪ፣ ምሁራኑ ደግሞ አድማጭ እንዲሆኑ የመፈለግ አዝማሚያ ነው፡፡ ምሁራኑ ለበርካታ ዓመታት ማዳመጣቸውን በመግለጽ እነሱም መደመጥ እንዳለባቸው መናገራቸው ትክክል ነው፡፡ አንዱ ተናጋሪ ሌላው አድማጭ መሆን የጤናማ ሥርዓት ምልክት አይደለም፡፡ ይልቁንም በውይይቱ መሰልቸት ብሎም አለመሳተፍ ይመጣል፡፡ በሌላ በኩል ዝምታ የሰፈነባቸው መድረኮችም ታይተዋል፡፡ ብንናገር ምን እንፈይዳለን የሚለው እሳቤ ደግሞ የቅሬታውንና የብሶቱን መጠን ማሳያም ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ለአገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከአካዴሚያዊ ሙያቸውም ዘለል ያለ ነው፡፡ ከተለያዩ ምንጮች የሚቀዳው ዕውቀታቸው ለአገር ችግሮች መፍትሔ እንዲያመነጭ ማገዝ ሲገባ፣ የምንላችሁን ሰምታችሁ ሂዱ የሚባል አስተሳሰብ መኖር የለበትም፡፡ አይጠቅምም፡፡

  በቅርቡ መንግሥትን የሚመራው ገዥ ፓርቲ በጥልቀት በመታደስ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ በገለጸ ማግሥት ሕዝብ ብዙ ነገሮች እየጠበቀ ነው፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ብቃት አልባዎችን በብቁ አመራሮች ለመተካት ፊትን ወደ ምሁራንና በሳሎቹ ጎራ ማዞር የግድ ነው፡፡ በትምህርታቸው፣ በልምዳቸው፣ በሥነ ምግባራቸውና በአገር ፍቅር ስሜታቸው አመራር ለመስጠት የሚችሉ በርካታ ዜጎች አሉ፡፡ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በላይ ለአገራቸው ዕድገት እንቅልፍ አጥተው ለማገልገል ፍላጎት ያላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የአገር አደራ ሊሸከሙ የሚችሉ ዜጎች መፈለግ አለባቸው፡፡  ይህንን ፈቃደኝነት ለማሳየት ደግሞ ምሁራኑን ማበረታታት አስፈላጊ ነው፡፡ የሚናገሩትን በአንድ ጆሮ ሰምቶ በሌላኛው ማፍሰስ ሳይሆን፣ ለለውጥ የሚበጁ ምክረ ሐሳቦችን በአንክሮ መቀበል ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይቀርቡ የነበሩ ጠቃሚ ሐሳቦችን በማናናቅና በማጣጣል የተፈጸሙ ስህተቶች አሁን ሊያቆሙ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል በማኅበራዊ ሚዲያዎች የዘር ጥላቻ ቅስቀሳ፣ አሉባልታና ቧልት ከሚያንተከትኩ ምሁር ተብዬዎች ወጣ በማለት ለአገር ዘለቄታዊ ጥቅም የሚሰጡ በሳል ዜጎች መፈለግ ይበጃል፡፡ ለዚህም ነው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ድምፅ ይሰማ የሚባለው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ...

  ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

  የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ተመንን የተቃወሙ አምራቾች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሬታቸውን አቀረቡ

  ንግድ ሚኒስቴር በወጣው የዋጋ ተመን ብቻ መሸጥ እንዳለባቸው በድጋሚ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

  ለቻይናው ፖሊጂሲኤል ኩባንያ የተሰጠው ውል ተቋረጠ

  የማዕድንና ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ አልምቶ ኤክስፖርት...

  የሕግ ክልከላዎችና የሚያስነሱት ቅሬታ

  በኢትዮጵያ የአገርና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ተብለው የሚወጡ አንዳንድ ሕጎች፣...

  ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...

  ሴረኝነት የሰላም ጠንቅ ነው!

  በአዲሱ ዓመት የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት የሚያስጠብቁ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መተኮር ይኖርበታል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በወታደራዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ የሕዝባችንን ፍላጎት...