Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይብቃ ማለት ምነው ነውር ሆነ?

እነሆ መንገድ። ‹‹አንተዬ ባህር እንደሚያሻግር ሕገወጥ ደላላ ምነው ባትጠቀጥቀን? ሰው እኮ ነን…›› ትላለች ፊቷን ወደ ተሳፋሪዎች አዙራ ሞተር ላይ የተሰየመች የዋህ። ወያላው ሁለት ችፍርግ መፋቂያዎች በጥርሱ ነክሶ በላንቃውና በምላሱ ብቻ ያወራል። ‹‹ሰውማ ነሽ። ማን አይደለሽም አለሽ? ደግሞ ባህር ባታቋርጭም ስደተኛነትሽን እመኝ፤››። ይላታል። ‹‹ወይ ጉድ ከመርካቶ ፒያሳም ስደት ተባለ? ይብላኝ ለሚያሳድደን እንጂ እኛስ እግራችን ውሎ ይግባ፤›› ስትለው፣ ‹‹የአዲስ አበባን ነዋሪ ቀጥ አድርገን የያዝን እኛ ነን እኮ። ብሎ ሳበው አለ። ሾፌሩ፣ ‹‹እሷን ከምትነዘንዛት ለምን ጋዜጣ ላይ አትፅፍም? እኔስ አሁን የሰለቸኝ ያንተ ጉራ ነው፤›› ይለዋል። ‹‹ጉራ? ሕጋዊ ሌባ በነፃነት መኪና በሚለዋውጥበት አገር አግባብቼ፣ አጠጋግቼ በጫንኩ ሕገወጥ ደላላ ስትለኝ ዝም ልበል ታዲያ? ለደፈችብኝ እኮ…›› ብሎ ቁልቀል እያየ በዓይኑ ተቆጣት።

‹‹ተዋት እንጂ በቃህ። ምን አድርጊ ነው እሱ? አንተስ ብትሆን በገዛ አገሯ ከመርካቶ ወደ ፒያሳ ብትሳፈሪም ስደተኛ ነሽ፣ ተሳፋሪውን በአጠቃላይ ስደተኛ ነው እያልክ አልጠዘጠዝካትም?›› አለችው ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመች ወይዘሮ። ‹‹አቦ ተውኝ በቃ። ደካማ ላይ ትበረታላችሁ። ወኔ ካላችሁ የተበባሩት መንግሥታት ድርጅትን አታፋጥጡም?›› ብሎ ወያላው አንደኛውን መፋቂያ ግራ ኪሱ ውስጥ ከተተ። ወዲያው አጫጫኑን ለማየት ወደ መጨረሻ ወንበር ሲጠመዘዝ ከሰከንዶች በፊት በምራቁ ሲያርሳት የነበረችው ችፍርግ ጫማው ላይ ወደቀች። ‹‹ወይኔ መፋቂያዬ…›› ሲል ተሳፋሪዎች ተሳሳቁ። ‹‹ኪስህንም አታውቀው? ምናለበት መጀመሪያ ሰው በነገር ከምትሰፋ ኪስህን ብትሰፋው?›› ስትለው ደግሞ ያቺ ገራገር የሾፌሩ ሳቅ ባሰ። ዘመኑ መቼም የገዛ ቀዳዳቸውን ሳይሰፉ የሰው ካልሰፋን የሚሉ ሰዎች ሆኗል። የእኛም ሥራ ወይ ጊዜ ብሎ ማለፍ ሆኗል! ወይ ጊዜ!

ጉዟችን ተጀምሯል። ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመ ወጣት በተደጋጋሚ በረዥሙ እየተነፈሰ ተሳፋሪዎችን ሰላም ነሳ። ‹‹ጎበዝ በምግብ ዋስትና ራሷን ቻለች በምትባለው አገራችን የምግብ እጥረት የሚያሰቃየኝ ሳያንስ፣ ዓይናችን እያየ የአየር እጥረት ተከሰተ እንዴ?›› ብሎ አጠገቡ የተሰየመን ጎልማሳ ሆን ብሎ ሊያናግረው ቢሞክርም ወጣቱ አንገቱን እንዳቀረቀረ ተራ በተራ እያማተርን አየነው። ደብተር የምታህል ታብሌቱ ላይ ፈተና እንደደረሰበት ሰነፍ ተማሪ በተጨነቀ መንፈስ ተወጥሮ አፍጧል። ‹‹ኧረ ምን ጉድ ሰምተህ ነው?›› አለው ጎልማሳው ድምፁን ከፍ አድርጎ። ‹‹በትንፋሽ ሱናሚ ልትጨርሰን እኮ ነው፤›› ሲለው ወጣቱ፣ ‹‹ምን እባክህ ሳይሉኝ የማይሆን ኢምፓየር እገነባለሁ ብዬ ፍዳዬን አየሁ እኮ፤›› አለው። ጉድ ፈላ። ‹‹የምን ኢምፓየር?›› አለ ጎልማሳው በርግጎ።

መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ሁለት ዩኒፎርም የለበሱ ሴት ተማሪዎች ደግሞ፣ ‹‹አንቺ ኢምፓየርን ጨረሽው? ኦ ማይ ጋድ በዚህ ሙቪ…›› ብለው ጣቢያ ደባለቁ። ‹‹ቆይ እስኪ ልጆች። አንዴ እዚህ እንጨርስና ወደ እናንተ እንመጣለን። እዚህ ሰው በህቡዕ ኢምፓየር ሊመሠርት ሲያደራጅ እየሰማችሁ እናንተ ስለፊልም ታወራላችሁ?›› ጎልማሳው ቀልባቸውን ገፈፈው። ተማሪዎቹ ደንግጠው ዝም አላሉም። ‹‹ሲሪየስሊ?›› ብለው ጎልማሳውን በግልምጫ ጠረባ አጣጣሉትና ወሬያቸውን ቀጠሉ። ጎልማሳውም በረጂሙ እየተነፈሰ ያስጨነቀው ወጣት ኢምፓየር መሥራች ጉዳይ ቀልቡን አሸፍቶበት ወደሱ ዞረ። ‹‹አይ የዘንድሮ ልጆች። አየሃቸው? ሌላ ዝባዘዝንኬ ሳይናገሩ በኢግኖራስ ብቻ ቻታቸውን ሲቀጥሉ አየህልኝ? እኛ የመናገር መብት አለ ስንል እንውልና ስንናገር ስድብ። ስንናገር ጥላቻ። ስንናገር ዛቻ…›› ብላ ከጎኔ የተሰየመች ዘመናይ የቤት እመቤት ሹክ ትለኛለች። ‘በኢግኖራስና በብሎክ’ ከታጀበ ፖስት የንግግር ነፃነት ተግባራዊነትን አዳንቀን ካወራን እንግዲህ ምን ቀረን ይባል ይሆን? ወይ ታክሲና መንገደኛ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠው ወጣት ጎልማሳው አላስቀምጥ ሲለው፣ ‹‹ነገርዬው አገር የማስተዳደር ጌም ነው። ግን እንደምታስበው ቀላል አይደለም። ተለክፌያለሁ…›› አለው። ‹‹የማንን አገር ነው የምታስደዳድረው?›› ሰቅዞ ይዞታል። የራህን መሬት ይዘህ ሕዝብ እያሰፈርክ፣ ሕዝቡ በየጊዜው እንደየደረጃው የሚፈልገውን እያሟላህ ያለአመፅ ማስተዳደር አለብህ። አሁን እኔ ይኼውልህ እዚህ ጋ የሕዝቦቼን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ስላልቻልኩ እያመፁ ነው…›› እያለ ካንጀቱ ሲያብራራ አንዱ በጥቅሻ ሌላው በከንፈሩ እያሽሟጠጠ እንደ ተረት አባት ያዳምጠዋል። ጎልማሳው፣ ‹‹ጎሽ! ታዲያ መጀመሪያውንም እንደዚያ ብትለን ኖሮ ሌላው ቢቀር በትንፋሽ እናግዝህ ነበር። ግን እኔ ምልህ? የምትመራቸው የአንተ አገር ሰዎች እንደዚህ እንደኛ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲያነሱ እንዴት ነው የምትመልሰው?›› ሲለው ጋቢና የተሰየመ ተሳፋሪ ይኼን ሰምቶ እያሽካካ፣ ‹‹አዳሜ የቆመበትን መሬትና ርስት የራሱ ማድረግ ሲያቅተው በቁም ቅዠት የራሱን ምናባዊ አገር መፍጠር ጀመረላችሁ። ዕድሜ ለቴክኖሎጂ…›› እያለ አጅቡኝ ይላል።

መነጋገሪያ የሆነው ወጣት ግራ ቀኝ አያዳምጥም። የያዘው ጨዋታ ልቡን አጥፍቶት ስምጥ ብሎ ለጎልማሳው ያብራራል። ‹‹ይኼውልህ እዚህ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር የሚባሉ የቃላት ጨዋታዎች የሉም። ያለው የሕዝብ ፍላጎት ነው። የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት ትችላለህ? ከቻልክ ጨዋታው ይቀጥላል። ካልቻልክ የሠራኸው ሁሉ ይፈርሳል፤›› ይላል። ጎልማሳው ጭምር ሳያስበው ቀልቡ መሸፈት ጀምሯል። ‹‹ይኼውልህ ይህን ሁሉ ለመሥራት ሁለት ወራት ፈጅቶብኛል፤›› ሲለው ጎልማሳው በርግጎ፣ ‹‹ዳያስፖራ ነኝ በለኛ!›› ብሎ ተሳፋሪዎችን በሳቅ አንፈራፈራቸው። በገሃድና በተምኔት መሀል ያለችው ቀጭን መስመር ገና ብዙ የምታስተዛዝበን ይመስላል። በዘውድ ተጫወተ በጎፈር በዚህ የሕይወት ጎዳና ማንም ከትዝብት አያመልጥም!

ወያላችን ሒሳብ ተቀብሎን እንዳበቃ ጎልማሳው በስሜት ስለሆሊውድ ፊልም ወደሚጫወቱት ታዳጊዎች ዞሮ፣ ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ!›› አላቸው። ‹‹ዋት?›› አለችው አንደኛዋ። ‹‹የአንጎላ ዋና ከተማ ማን ትባላለች?›› ሲል ሁለቱም ከት ብለው ሳቁበት። ‹‹እንዲህ ካሳቅኩማ እንግዲህ ኮሜዲያን ልሁን፤›› ሲላቸው አንደኛዋ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ከዚያ እንደምንም አሜሪካ ገብተህ ‘አሳይለም’ ለመጠየቅ?›› ብላ ሽቅብ ስትመልስለት፣ ‹‹ከልጅ ጋር አትጫወት ይወጋሃል በእንጨት አሁን መጣ፤›› ብሎ ዝም አለ። ‹‹የምን እንጨት ነው? ሀቅ መሰለኝ። የጠየቅከን በምን ‘ሞቲቭ’ እንደሆነ ገብቶናል። ፊልሙና ሙዚቃው ላይ እንደምትንቀለቀሉት መጀመሪያ የአካባቢያችሁን፣ ከዚያ የአኅጉራችሁን ጂኦግራፊ አጥኑ ልትለን ነው። አገሬ አገሬ እያሉ መጨረሻው አሜሪካ መግባት ነው። ያ መሰለኝ የዘመኑ ትምህርት። ለዚያ ደግሞ አሜሪካና ባህሏን እያጠናን ነው፤›› ሲሉት ጎልማሳው ኩምሽሽ አለ።

ይኼኔ አጠገባቸው የተሰየመ ተሳፋሪ፣ ‹‹ወይኔ በደጉ ጊዜ አርቲስት መሆን ስችል እንቢ ብዬ ዛሬ ማንም ከኋላዬ ተነስቶ በጥበብ ስም ባህር ተሻግሮ መንግሥት ላይ አቃጥሮ መኖሪያ ፈቃድ ሲያገኝ እያየሁ ፈዝዤ ልቅር?›› ይላል። ‹‹ምን ያስፈዝዝሃል? አሁንም ቢሆን አልመሸም፤›› ይለዋል ከወይዘሮዋ ጎን። ‹‹ከዚህ በላይ እንዴት ይምሽብን? ለአገር ተቆርቋሪነት ሲነገድበት እያየን ከዚህ በላይ እንዴት ይምሽብን?›› ይጮሃል ያ። ‹‹ወይ ሰፊው ሕዝብ። ከምንም ነገር በላይ የሰፊው ሕዝብ አባል በመሆኔ እኮራለሁ፤›› ስትል ደግሞ እመቤቲቱ ከአጠገቤ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው ብለሽ ነው? የተረፈን በእኛ ምህላ በውጭና በውስጥ የጥቂቶችን ምቾት ማጣደፍ ነው፤›› አላት ጎልማሳው። ልማቱ ተረስቶ ለስደት የሚጣደፈው ከመቼው ጊዜ በዛ እኮ እናንተ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። የጥንት አራዶቹ ሠፈር ዝናና ወረቷ የተሟጠጠባት ዳንኪረኛ አሮጊት መስላለች። ‹‹አቤት ይኼ ጎዳና ስንቱን አሳየን?›› ይላል ጎልማሳው። ማየት ምን ዋጋ አለው ከላስተማረ? ልብ ካላስገዛ? ዘለዓለም ፌዝ፣ ዘለዓለም ዳንኪራ፣ ዘለዓለም ዋዛ ሕይወት አይሆን፤›› እመቤቲቱ ዕቃዋን እያሰናዳች አስተያየት ሰጠች። ‹‹መማር እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም፤›› ይላል ጋቢና የተየሰመው። ‹‹ያከበዱት ይከብዳል ያቀለሉት ይቀላል። ጊዜና ሥፍራ ሁሉን በሰዓቱ ያስተናግዳሉ፤›› ይላል ሌላው። ‹‹ወይ አራዳና የአራዳ ልጆች። በትርጉም ስህተት ይኼ ጎዳና ዝንት ዓለም ምስቅልቅሉ ሲወጣ ይኑር?›› ስትል ጎማ ላይ የተሰየመች ተሳፋሪ፣ ‹‹ኧረ ተውን እስኪ…›› እያለ ተሳፋሪው እርስ በእርሱ በደከመ መንፈስ ይተዛዘል ጀመር።

‹‹እስኪ አስቡት በዚህ በሠለጠነ ዘመን፣ ሳይንስ ለሁሉም ነገር በተጨባጭ፣ በተሞክሮ ማስረገጫ ማቅረብ በሚችልበት ዘመን ጉም እየዘገንን ስንጠላለፍ አያሳዝንም? አያሳዝንም?›› ጎልማሳው ጨርቁን መጣል ቀርቶታል። ማንን ሰምቶ፣ ማንን አምኖ፣ ማንን ተቀብሎ፣ ማንን ጥሎ መጓዝ እንደለበት የተወናበደበት ኅብረተሰብ ጭንቀት አምጦ ጭንቀት ሲተነፍስ ይውላል። ሁሉም ተነስቶ ያሻውን ሲወሸክት ይህን የምትለው አንተ ማን ነህ? ከወዴትስ ነህ? መሠረትህስ የት ነው? የሚል ጠፍቷል። የኑሮውን አቅጣጫ መሪ መጨበጥ አለመቻል የ21ኛው ክፍለ ዘመን አበሳ ሆኖ የመጣ ይመስላል። ስለዚህም ተሳፋሪው ግራ ተጋብቶ ወሬ ጠፍቶበት በግፊት ተሳፍሮ በግፊት ደህና ዋልክ ደህና አደርክ ተባብሎ በግፊት ይወርዳል። ወያላው በቃችሁ ብሎ መጨረሻ ብሏል። እኛስ በቃችሁ ብለን መጨረሻ የምንላቸው የሉንም? ይብቃ ማለት ምነው ነውር ሆነ? እስኪ እስከሚቀጥለው ፌርማታ እናስብበት! መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት