Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጥሬ ቆዳ ዋጋ ከፍተኛ ማሽቆልቆል አሳየ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ምክንያቱ የዓለም ገበያ መቀዛቀዙ ነው ተብሏል

በአንድ ወቅት እስከ መቶ ብር ያወጣው የጥሬ ቆዳ ዋጋ በማይታመን መጠን አሽቆልቁሏል፡፡ በተለይም የበግ ጥሬ ቆዳ በርካታ አቅርቦት ከሚታይባቸውና ከፍተኛ የቁም ከብት እርድ ከሚካሄድባቸው በዓላት መካከል አንዱ የዘመን መለወጫ ነው፡፡

በእንቁጣጣሽ በዓል ወቅት የታየው የእርድ ጭማሪ ግን ከዚህ ቀደም የነበረውን የጥሬ ቆዳ ዋጋ በእጅጉ ወደ ታች በማውረድ እስከ አሥር ብር እንዳወጣ ከየአባቢው የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለሪፖርተር ስለጉዳዩ የጻፉም የቆዳ ኢንዱስትሪው የቁልቁል እየተጓዘ እንዳይሆን ሥጋታቸውን አስፍረዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ አብዲሳ አዱኛ እንዳሉት፣ የዓለም የቆዳና ሌጦ ገበያ ባስከተለው ጫና ምክንያት የዋጋ መቀነስ ታይቷል፡፡ ምንም እንኳ የበግ ቆዳን ያህል ተፈላጊነታቸው እምብዛም ይሁን እንጂ የበሬና የፍየል ቆዳዎችም ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ታይቶባቸዋል፡፡ በተለይ የፍየል ቆዳ እስከ ሦስት ብር መሸጡ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ይህም ቢባል ግን የቆዳ ኢንዱስትሪዎች የበግ ሌጦ የገዙት ከ25 ብር ጀምሮ እንደሆነ፣ እስከ አሥር ብር ወርዷል የሚለው የተጋነነ የዋጋ ቅናሽ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች እንደ ቆዳው የጥራት ደረጃ ከ25 ጀምሮ ባለው ደረጃ ወደ ላይ እየጨመረ የሚሔድ ዋጋ በማስቀመጥ ሲቀበሉ መቆየታቸውን አቶ አብዲሳ ገልጸዋል፡፡

የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የግብይት ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ት ብርቅነሽ ጎንፋ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነም፣ የወቅቱ የዓለም ገበያ መቀዛቀዝ በኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳ ገበያም ሆነ ባለቀላቸው የቆዳ ውጤቶች ላይ ተንጸባርቋል፡፡ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንደ ቅንጦት ዕቃዎች የሚታዩ በመሆናቸው ከፍተኛ የገበያ ጫና እንደሚያርፍባቸው ሲያብራሩም፣ በአሁኑ ወቅት በተለይ ቆዳን የሚተኩ ሲንቴቲክ ምርቶች መበራከታቸው የቆዳ ገበያ ላይ ጫና እያሳደሩ ነው፡፡

ይሁንና ምን እንኳ የጥሬ ቆዳ ዋጋ የቱንም ያህል ቢቀንስ፣ ፋብሪካዎች የቀረበላቸውን ቆዳ እንዲያነሱ ድጋፍ እየተደገላቸው በመሆኑ፣ ለቀረበው ቆዳ ሳይበላሽ እንዲነሳ ለማድረግ እየተሞከረ ነው ያሉት ወ/ት ብርቅነሽ፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ለቆዳ ፋብሪካዎች የሥራ ማስኬጃ በመመደብ እንዲያግዛቸው እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ይህም ቢባል ግን ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት ለአንድ የበግ ጥሬ ቆዳ እስከ 100 ብር ይጠየቅ የነበረበት የገበያ ሁኔታ ይታወሳል፡፡ ይህ ዋጋ እርግጥ የቆዳ ፋብሪካዎችን ያስቆጣና የተጋነነ በማለት ትችት ሲቀርብበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ዋጋው የተወደደውን የጥሬ ቆዳ በአቅርቦት በሚፈለገው መጠን ለቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብና እጥረትን ለማስቀረት ተብሎ ከውጭ እንዲገባ ለማድረግ ሲሞከር እንደነበር ይታወሳል፡፡

አቶ አብዲሳ እንዳረጋገጡት በአሁኑ ወቅት ከውጭ እየገባ ባይሆንም የጥሬ ቆዳ ጥራት ችግር ግን ሊቀረፍ አልቻለም፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ለቆዳ ፋብሪካዎች እየቀረበ ከሚገኘው ጥሬ ቆዳ ውስጥ ግማሽ በመቶ ያህሉ የበዛ የጥራት ችግር የሚታይበት በመሆኑ ውድቅ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በእርድ ወቅት በሚፈጸም የጥንቃቄ ጉድለትም እስከ 60 በመቶ የሚሆነው የቆዳው የላይኛው ክፍል ጉዳት እየደረሰበት ጥራቱ እንደሚበላሽ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥራት ያለው የደጋ በግ ቆዳ ያላት መሆኗ በመረጋገጡ፣ የኢትዮጵያ የቆዳ መለያ ምልክት በመሆን ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ የጃፓን መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግበት ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ጋር በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

የአገሪቱን የበግ ቆዳ ከፍተኛ ጥራት እንዲኖረው በማድረግ ለውጭ ገበያ የማዕቀረቡ ሥራ ቅድሚያ ከጃፓን ገበያዎች እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ የበግ ቆዳን በመጠቀም ልዩ ልዩ አልባሳትና ጌጣጌጦችን በማምረት ላይ የሚገኘው፣ ሂሮኪ የተሰኘው አነስተኛ የጃፓን ኩባንያ የቆዳ ፋብሪካ ከፍቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ሌሎችም የቻይናው ኋጂዬን ግሩፕ፣ የእንግሊዙ ፒታርድስና ሌሎችም ከ24 ያላነሱ ቆዳ ፋብሪካዎች በአብዛኛው የውጭ ገበያዎች ላይ በማተኮር እንዲሠሩ ቢደረግም፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኤክስፖርት አፈጻጸም በዚህ ዓመት ጥሩ ውጤት እንደማያሳይ አመላካች ሁኔታዎች ከወዲሁ እየታዩ ነው፡፡ ወ/ት ብርቅነሽ እንደሚገልጹትም የጥሬ ቆዳው ገበያ መዋዠቅ ያለቀለት የቆዳ ኤክስፖርትም ሆነ ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን የወጪ ንግድ እንደሚያውክ ይጠበቃል፡፡

ምንም እንኳ የጥሬ ቆዳ ዋጋ ከሚገመተውም በታች ቢያሽቆለቁልም፣ እንደ ባንግላዴሽ ባሉ አገሮች የታየው የጥሬ ቆዳና ሌጦ ዋጋ ከኢትዮጵያ በመጠኑ ሻል ያለ እንደነበር ታይቷል፡፡ ለአብነትም፣ በሰሞኑ የኢድ አል አዳሃ በዓል ወቅት ለአንድ ካሬ ጫማ ቆዳ የተተመነው የገበያ ዋጋ 16 ብር ያህል እንደነበር ከባንግላዴሽ የተገኙ የዜና ምንጮች አመላክቷል፡፡ ከአንድ የበግ ቆዳ በአማካይ ከአራት እስከ 4.5 ካሬ ጫማ ቆዳ ማግኘት እንደሚቻል ሲታሰብ፣ የባንግዴሽ የበዓል ሰሞን ገበያ ከኢትዮጵያ ይልቅ ጥሩ ዋጋ የታየበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች