Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ የአሥር ዓመት የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ይፋ ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚመራበትን ፍኖተ ካርታ (ማስተር ፕላን) ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በፍኖተ ካርታው የተካተቱ ዕቅዶችን ለመተግበር ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ይጠበቃል፡፡

ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ፣ ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት የሚተገብራቸው አሥር ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ የሥራ ዕቅዶችን ያካተተ ሲሆን፣ ለተዘረዘሩት ዋና ዋና የቱሪዝም ዘርፍ የልማት ተግራት 5.446 ቢሊዮን ብር ሊያስፈልግ እንደሚችል፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አጥንቶ፣ ለሚኒስቴሩ ያቀረበው ሰነድ ይመለከታል፡፡

የአገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ከአራት በመቶ በላይ ድርሻ መያዙ የሚነገርለት ይህ ዘርፍ፣ የኮሚሽኑ ጥናት መነሻውን ካደረገበት ከሦስት ዓመት በፊት የነበረው የዚህ ድርሻ አኃዝ እንደሚያሳየው ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው፡፡ ይህ መጠን ወደ 37 ቢሊዮን ብር አሊያም ወደ 4.5 ከመቶ ከፍ ማለቱም ይገመታል፡፡ በቱሪዝም መስክ ለሚታየው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሆቴሎች፣ የአስጎብኝ ድርጅቶች፣ የአየር መንገዶች፣ ሌሎች ተሳፋሪዎችን የሚያጓጉዙ የትራንስፖርት አገልግሎቶች አካቶ (የሰርክ መጓጓዣ አገልግሎቶችን ማለትም የከተማ አውቶቡስና ታክሲዎችን አይጨምርም) የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያደርገው አስተዋጽኦ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጥናት ተመልክቷል፡፡

ከእነዚህ የኢንዱስትሪው ሞተሮች ውስጥ ለአብነትም የጉዞና የጉብኝት ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከ4.8 በመቶ ያላነሰ ድርሻ እንደሚያበርክት ሲጠበቅ፣ በገንዘብ ደረጃም ከ59 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ የሚያደርግባቸው መጪዎቹ አሥር ኮሚሽኑ ያሰናዳው ፍኖተ ካርታ ያመለክታል፡፡ ይሁንና የአስጎብኝና የቱሪዝም መስኩ አጠቃላይ አስዋጽኦም 92.5 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ሲታመን፣ በአሥር ዓመት ውስጥም ወደ 150 ቢሊዮን ብር ገደማ፣ በመቶኛም የዘጠኝ ከመቶ ድርሻ በመያዝ እንዲያሻቅብ የሚያመላክት ትንበያ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስፍሯል፡፡

ምንም እንኳ የአገሪቱ የአስጎብኝና የቱሪዝም መስክ በዓለም ደረጃ በየጊዜው ለውጥ እያሳየ እንደሚገኝ ቢጠቀስም፣ ለውጡ ግን አዝጋሚና አነስተኛ የተወዳዳሪነት ለውጥ በማስገኘት ላይ እንደሚገኝ ጠቋሚ አኃዞችን ዋቢ በማድረግ የቀረበው የፍኖተ ካርታ ሰነድ ያሳያል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት የነበረው የአገሪቱ ዓለም የቱሪዝም የአስጎብኝ ዘርፍ ተወዳዳሪነት ሲታይ ከ140 አገሮች 120ኛ ደረጃን የያዘ ነበር፡፡ በአንፃሩ ኬንያ 96ኛ፣ ሩዋንዳ 105ኛ፣ ደቡብ አፍሪካ 64ኛ እንዲሁም ታንዛንያ 109ኛ ደረጃ በመያዝ ከኢትዮጵያ የተሻለ ተወዳዳሪነት የሚታይበት የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መገንባት እንደቻሉ ሰነዱ ይጠቁማል፡፡

ምንም እንኳ በአገሪቱ እየታየ ያለው የቱሪዝም ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢሆንም፣ በጎብኝዎች ቁጥር አሁንም ከሚታሰበው ይልቅ አነስተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ በ2008 ዓ.ም. አገሪቱን ይጎበኛሉ ተብለው ከሚጠበቁ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ውስጥ ከ700 ሺሕ በላይ በአማካይ የአምስት ቀናት ቆይታ በማድረግ መመለሳቸውን የባህልና ቱሪዝም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ከአራት ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱም ተመልክቷል፡፡ በአንፃሩ በአገሪቱ የተከሰተው ግጭት ለኢንዱስትሪው ሥጋት ሆኗል፡፡ አስጎብኝ ድርጅቶች፣ በኦንላይን የሚሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ የሆቴል ሪዘርቬሽን ሥራ የሚሠሩ ኩባንያዎች፣ ቱሪስቶች ለመምጣት የነበራቸውን ሐሳብ እየቀየሩ በመሆናቸው እያጋጠማቸው የሚገኙ ስረዛዎች በዚህ ዓመት የቱሪዝም ዘርፍ የሚያስመዘግበውን አፈጻጸም ደካማ እንደሚያደርጉት ይገልጻሉ፡፡

ተ.ቁ.

ስትራቴጂካዊ ተግባራት

ታሳቢ ወጪ   (በብር)

1

የፖሊሲ፣ የሕግና የተቋማዊ ማዕቀፍ ሥራዎች

166 ሚሊዮን

2

የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት

1.6 ቢሊዮን

3

የቱሪዝም ግብይትና ማስተዋወቅ ሥራዎች

951 ሚሊዮን

4

ለቱሪዝም ማዕከላትና አገልግሎቶች ኢንቨስትመንት

957 ሚሊዮን

5

የሰው ሀብት ልማት

606 ሚሊዮን

6

የቱሪዝም ጥናትና ምርምር

52 ሚሊዮን

7

በቱሪዝም መስክ የጸጥታና ደኅንነት ሥራዎች

130 ሚሊዮን

8

ለቱሪዝም ዘርፍ ደጋፊ መሠረተልማትና አገልግሎቶች ሥራዎች

155 ሚሊዮን

9

የተፈጥሮና የባህል ሀብቶች ጥበቃና ክብካቤ ሥራዎች

814 ሚሊዮን

10

ለቱሪዝም ልማት ፋይናንስ

23 ሚሊዮን

 

በጠቅላላው

5.466 ቢሊዮን

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች