Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አሁን ባለው አቅም ኤጀንሲው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሊቆጣጠር አይችልም››

ዶ/ር ተስፋዬ ሙህዬ፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

ዶ/ር ተስፋዬ ሙህዬ ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን የሠሩት በጂኦግራፊ ሲሆን፣ በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ደግሞ ማስተርስ አላቸው፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ሠርተዋል፡፡ የዓለም ባንክ ምሥራቅ አፍሪካ ሪሀብሊቴሸን ፕሮጀክት ማናጀርም ነበሩ፡፡ ከዚያም የአማራ ክልል የትምህርትና ሥልጠና አቅም ግንባታ ፕሮግራሞች መምሪያ ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሠርተዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል የተወሰነ ጊዜ ከሠሩ በኋላ እንደገና ወሎ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ ሙህዬ በአሁኑ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርትን ጥራት ለማሻሻል ተቋሙ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በሚመለከት ምሕረት አስቻለው ከዶ/ር ተስፋዬ ሙህዬ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

 

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ከባድ የጥራት ችግር እንዳለበት አጥኚዎች ይገልጻሉ፡፡ ኤጀንሲውም የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም ችግሩን መፍታት ሳይቻለው የትምህርት ጥራት እየወደቀ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኤጀንሲውን የመምራት ኃላፊነትን እንዴት ተቀበሉ?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት እየወረደ እንደነበር ተማሪዎቼን በመመልከት እገነዘብ ነበር፡፡ ስለዚህም ወደዚህ ኃላፊነት እንድመጣ ሲነገረኝ ደንግጬ ነበር፡፡ የምንቀበለው፣ አስመርቀን የምናመጣው ተማሪ እንዴት ያለ ነው? የሚለው ሁሌም የመምህራን መወያያ ነው፡፡ ከማኅበረሰቡ የምንሰማቸው ነገሮችም አሉ፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ያለፉና ችግሩን የሚያውቀው ባለሙያ ተቋሙን ካልመራው ሁኔታው ሊቀየር እንደማይችል በማመን ኃላፊነቱ ከባድ እንደሆነ እያወቅኩኝ ተቀብያለሁ፡፡ ወደ ኃላፊነት ስገባም ያልጠበቅኳቸው ችግሮች አጋጥመውኛል፡፡ ቢሆንም በተስፋና በቁርጠኝነት ለመሥራት ወስኛለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከወራት በፊት ኃላፊነት ሲቀበሉ ኤጀንሲው በመዋቅራዊ ለውጥ ሒደት ላይ ነበር፡፡ ሒደቱ አሁንም እንደቀጠለ ይመስለኛል፡፡ የመዋቅራዊ ለውጡ ዋነኛ ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- እኔ ከመምጣቴ በፊት የመዋቅርና ተጓዳኝ የደረጃ ማሻሻያ ተደርጎ ነበር፡፡ አደረጃጀቱ በጣም ጠባብ ነው፡፡ መደቦች ዝቅተኛ በመሆናቸው እንኳን ሌላ ባለሙያ መሳብ እዚህ ያለውንም ለማቆየት የሚያስችል አይደለም፡፡ እዚህ ላይ እየሠራን ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር መሻሻል ያለበት ነገር ቶሎ ተሻሽሎ ወደ ተግባር እንዲገባ ነገሮች እንዲፋጠኑና የትምህርት ጥራት ላይ ሊታይ የሚችል ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እየጠየቀን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲደረግ የሚጠበቀው ትልቁ ለውጥ ምንድን ነው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- አቅማችንን ማሻሻል፡፡ ምክንያቱም በዚህ የቀጨጨ አደረጃጀት በቁጥር፣ በሚሸፍኑት የሥልጠና ዘርፍ አድማስ ሰፊ የሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጥራት ማስጠበቅ የሚቻል አይሆንም፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ማሻሻል ቀርቶ ተቋማቱን መከታተል የምንችልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡ ስለዚህም የትምህርት ሚኒስቴር ውትወታ አቅም መፍጠሩ ነው፡፡ እኛም እዚህ ላይ እየሠራን ነው፡፡ አሁን ባለው አቅም ግን ኤጀንሲው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሊከታተልና ሊቆጣጠር አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- የኤጀንሲውን አቅም ለመጨመር ምን ዓይነት ነገሮች መደረግ አለባቸው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- የመጀመርያው የሰው ኃይል መሟላት ነው፡፡ ይህ የሰው ኃይል መምጣት ያለበት የከፍተኛ ትምህርት ሁኔታን፣ የማስተማር ሒደቱን ችግሩን ከሚያውቅ ከዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ነው፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ አስተማሪና አመራር ሆኖ ማሰብ የሚችል ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ደረጃ ያለን ሰው ለመሳብ ደግሞ ኤጀንሲው የሚሰጠው ደረጃ ቢያንስ ከዩኒቨርሲቲ መሻል ይኖርበታል፡፡ ሥራውም ጫና ያለው በመሆኑ ደረጃው ሳቢ መሆን አለበት፡፡ ሌላው አቅምን ለማሻሻል የሚያስፈልገው የኤጀንሲው ሥልጣን እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ኤጀንሲው የተቋቋመበት አዋጅን ለማሻሻል እየተሠራ ነው፡፡ አዋጁ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች፣ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስተያየት እንዲሰጥበት ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ኤጀንሲው የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በመቆጣጠር ረገድ ምንድረስ ሥልጣን አለው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- አንደኛው አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ጉዳይ ይህ ነው፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፕሮግራሞችን የመክፈት የማሠልጠን ሥልጣን  ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይልና በመሳሰሉት ተቋማዊ ኦዲት እናደርጋለን፡፡ በዚህ ኦዲት መሠረት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንችላለን፡፡ በራሳችን ለብቻችን ግን ዕርምጃ መውሰድ አንችልም፡፡ አዋጁ ቢሻሻል ግን ይህን ማድረግ፣ ፕሮግራሞች ሲከፈቱም የአግባብነታቸውን ጉዳይ በመመዘን ረገድ ሥልጣን ይኖረናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ያኔ ፕሮግራሞች እንዲከፈቱ የመፍቀድ የመዝጋት አቅም ይኖራል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በመቆጣጠር ረገድ የኤጀንሲው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- እዚህ ላይ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ተማሪዎች መቆየት ያለባቸውን ዓመታት ሳይቆዩ የማስመረቅና ባልተፈቀደ ካምፓስ ትምህርት የመስጠት ችግሮች አሉ፡፡ በዚህ መልኩ ተምረው ተመርቀው ሥራ የያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ ሲኦሲ ሳይወስዱ አስተምሮ የማስመረቅ ነገር በተቋማቱ በኩል ይታያል፡፡ በዚህ መልኩ ተምረው ለተመረቁ ዕውቅና አልሰጥም ያሉ ክልሎችም አሉ፡፡ ይህንን ተከትሎ ዕውቅና አለኝ ብሎ በአደባባይ ባስተዋወቀ የትምህርት ተቋም እንዴት እንዲህ እንጭበረበራለን? የሚል አቤቱታ ለእንባ ጠባቂ ሁሉ ቀርቧል፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት ያስችለናል ያልነውን ስትራቴጂ ለትምህርት ሚኒስቴር አቅርበን ነሐሴ መጨረሻ ላይ ፀድቆ ተሰጥቶናል፡፡ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ከሌለ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ አሁን የማስፈጸሚያ ስትራቴጂውን መፅደቅ እየተጠባበቅን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ አዲስ ዓመት ተቋማቱን በመቆጣጣር ረገድ የምትከተሉት አሠራር ምን ይመስላል?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- ተቋማቱ ከተፈቀደላቸው ውጭ መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ዕድል መዝጋት ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዓመት ሥልጠና መስጠት የሚችሉ ተቋማትን፣ የሥልጠና ዘርፎችና ካምፓሶችን ዝርዝር አውጥተናል፡፡ ይህን ዝርዝር በተለያዩ ቋንቋዎች ለራሳቸው ለተቋማቱ ለወረዳ መስተዳድሮች በሙሉ እናሠራጫለን፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ የወረዳ መስተዳድሮች ተቋማቱ አካባቢያቸው ላይ ሲንቀሳቀሱ ፈቃድ ይኑራቸው አይኑራቸው መጠየቅ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ ይህ በዚህ ወር ተግባራዊ መሆን ይጀምራል፡፡ ሌላው ከዚህ ቀደም የነበረ ቢሆንም፣ ከመንግሥትም ተቋማት ጋር በቅርበት መሥራት የዚህ ዓመት ትኩረት ነው፡፡ በቅርቡ የግልም የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶችና የጥራት ማረጋገጫ ኤክስፐርቶችን ጠርተን ተነጋግረን ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- የትምህርት ጥራት ወርዶ ወርዶ ወደቀ የሚባልበት ደረጃ የደረሰበት አገር ላይ የከፍተኛ  ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ የሚባል ተቋምን መምራት ምን ያህል አስቸጋሪ ነው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- እንደ ዩኒቨርሲቲ መምህር እኔም የጥራት ችግር ምን ድረስ እንደሆነ ተመልክቻለሁ፡፡ የአገሪቱ የትምህርት ጥራት ችግር ከቋንቋ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የተለያዩ ተመራማሪዎች አመልክተዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ችግር መንግሥትም አምኖበት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላ ነገር የሥነ ምግባር ነው፤ በአስተማሪም በተማሪም በኩል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአቻ ግመታ ጋር በተያያዘ ምን እየሠራችሁ ነው?

ዶ/ር ተስፋዬ፡- ይህ ነገር የውጭ አገር ዲግሪዎችን በኢትዮጵያ መስፈርት የት ላይ ናቸው? የሚለውን የመገመት ሥራ ነው፡፡ ተግባሩ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ተማሪ በትክክልም ከአንድ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲ ዲግሪውን አግኝቷል ወይ? የሚለውን ሁሉ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ የአቻ ግመታ ሥራ ሰፊ ነው፤ ጥያቄውን መመለስም ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ የተሳሳቱ ማስረጃዎችን ይዘው የሚመጡ አሉ፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...