Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያና በአማራ የድርቅ ተጎጂዎች ዕርዳታ ሊቀርብላቸው እንዳልቻለ የዓለም ምግብ ድርጅት አስታወቀ

በኦሮሚያና በአማራ የድርቅ ተጎጂዎች ዕርዳታ ሊቀርብላቸው እንዳልቻለ የዓለም ምግብ ድርጅት አስታወቀ

ቀን:

–  በነሐሴ ወር ከ51 በላይ ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ዕርዳታ ማግኘት አልቻሉም

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተቃውሞ ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች፣ በክልሎቹ በድርቅ የተጎዱ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ የዕርዳታ አቅርቦት ማግኘት እንዳልቻሉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ፡፡ 

በኢትዮጵያ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በክልሎቹ የሚገኙ የድርቅ ተጎጂዎች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እንዳይደርሳቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአዳማ ከሚገኘው ዋና መጋዘን ወደ እነዚህ ክልሎች ማሠራጨት ያልተቻለበት ምክንያት፣ ለማሠራጫ ጣቢያው በቂ የሰው ኃይል ባለመኖሩ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡

የሰው ኃይል እጥረቱ ከዋናው ማሠራጫ እስከ ወረዳ ድረስ የተንሰራፋ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህንን ጨምሮ በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት እስካለፈው ነሐሴ ወር ድረስ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ 51 ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ለተጎጂዎች ማዳረስ አልተቻለም፡፡ እስካሁን ለስድስተኛ ጊዜ የዕርዳታ ሥርጭት ቢካሄድም በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 17 ወረዳዎች ለሁለት ዙር ያህል ሙሉ ለሙሉ ዕርዳታ ለማዳረስ ሳይቻል ቀርቷል፡፡

በመሆኑም የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለሁለቱ ክልሎች የድርቅ ተጎጂዎች በሰባተኛው ዙር የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ሥርጭት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ሲጠይቅ፣ ብሔራዊ አደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የጋራ ድንገተኛ ኦፕሬሽን ዕቅድ አጋሮች ቡድን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለሚገኙ ተጎጂዎች ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

ሪፖርተር የብሔራዊ አደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳን ስለጉዳዩ በስልክ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁንና የዓለም የምግብ ፕሮግራም በ11ኛው ሪፖርቱ እንዳመለከተው፣ ከተያዘው ወር ጀምሮ እስከ መጪው ታኅሳስ መጨረሻ ድረስ ላለው ጊዜ ተጨማሪ 131 ሚሊዮን ዶላር መድቧል፡፡ ይህ ገንዘብ በአሁኑ ወቅት ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 9.7 ሚሊዮን የድርቅ ተጎጂዎች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ለማቅረብ፣ የተመጣጠነ ምግብ እደላ ለማካሄድ፣ እንዲሁም ለሴፍቲኔት ፕሮግራም ይውላል ተብሏል፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከአሥር ሚሊዮን በላይ የድርቅ ተጎጂዎች በአገሪቱ መመዝገባቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህን ወገኖች ለመርዳት ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ በወቅቱ መገለጹም ይታወሳል፡፡ ይሁንና ከዚህ ገንዘብ ውስጥ እስካለፈው ነሐሴ ወር የተለቀቀው 850 ሚሊዮን ዶላር ገደማ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህም መሠረት 612 ሚሊዮን ዶላር አሁንም ከለጋሽ አገሮችና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚጠበቅ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ