Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአገር አቀፍ ደረጃ ለተፈናቃዮች የሚሰጥ ካሳ የሚወስን ረቂቅ አዋጅ ሊዘጋጅ ነው

በአገር አቀፍ ደረጃ ለተፈናቃዮች የሚሰጥ ካሳ የሚወስን ረቂቅ አዋጅ ሊዘጋጅ ነው

ቀን:

በአገር አቀፍ ደረጃ በልማት ምክንያት ከነበሩበት ቀዬ የሚፈናቀሉ ዜጎችን ወጥ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ያስችላል የተባለ ረቂቅ የካሳ አከፋፈል አዋጅ ሊዘጋጅ ነው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የካሳ አከፋፈል ሥርዓት እንዲዘረጋና እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠው፣ በቅርቡ የተቋቋመው የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረት ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ነው፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ንጉሤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በልማት ምክንያት ለሚነሱ ዜጎች የሚሰጠው ካሳ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ አልነበረም፡፡ በልማት ምክንያት የሚነሱ ዜጎችም ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡

‹‹ኤጀንሲው በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ አሠራር ይዘረጋል፡፡ ክልሎችና የከተማ አስተዳደር አካላት ይህንን መነሻ በማድረግ የራሳቸውን የካሳ አከፋፈል ሥርዓት ይዘረጋሉ፤›› ሲሉ አቶ በቀለ ገልጸው፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት የመሠረተ ልማት ተቋማት ግን ኤጀንሲው በሚዘረጋው የካሳ አከፋፈል ይጠቀማሉ፤›› ሲሉ አቶ በቀለ አመልክተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በልማት ምክንያት ለሚያነሷቸው ዜጎች የሚሰጡት የካሳ ምጣኔ አነስተኛ መሆንና የተለዋጭ ቦታ አሰጣጥ ቅሬታ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡

የልማት ተነሽዎቹ የሚሰጣቸው ካሳና ምትክ ቦታ አነስተኛ በመሆኑ ኑሮአቸውን እያናጋ መሆኑን ተነሺዎች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ በአንፃሩ መንግሥት በአሠራር ግድፈት ሳቢያ ለካሳ የሚያወጣው ገንዘብ እየተበራከተ መምጣቱ ይነገራል፡፡

ባለፉት ዓመታት አዲስ አበባ ካላት አጠቃላይ መሬት (54 ሺሕ ሔክታር) ውስጥ 18,174 ሔክታር መሬት ላይ የሠፈሩ አርሶ አደሮች ተፈናቅለዋል፡፡ ከ1989 እስከ 1991 ተግባራዊ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ካሳ አፈጻጸም መመርያ ለአንድ ሔክታር የለማ የእርሻ መሬት በአንድ ካሬ 3 ብር ከ74 ሳንቲም ሒሳብ እንዲከፈል ያዛል፡፡ ለግጦሽ መሬት ደግሞ በአንድ ሔክታር 847 ብር ወይም በካሬ ሜትር 1 ብር ከ21 ሳንቲም መክፈል እንዳለበት ተደንግጎ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የወጡ የካሳ አከፋፈል መመርያዎችም የተፈናቃይ አርሶ አደሮችን ቅሬታ መሠረት ያደረጉ አልነበሩም፡፡

በስድስት ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ አርሶ አደሮች ያቋቋሙት ኮሚቴ ይህ ሥሌት የአርሶ አደሩን ኑሮ እያናጋ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡ የተሟላ የካሳ ክፍያ፣ የተሟላ መኖርያ ሥፍራ (ምትክ ቦታ) እና ቋሚ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ የተነሽዎችን ቅሬታ ለመፍታት ባካሄደው ማሻሻያ ለሰብል ካሳ ክፍያ 14 በመቶ፣ ለዛፍ ካሳ ክፍያ 42 በመቶ፣ ለጓሮ አትክልት ካሳ ክፍያ 45 በመቶ ጭማሪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የግንባታ ነጠላ ዋጋ ከነበረበት 115 ሺሕ ብር ወደ 144 ሺሕ ብር ማደጉንም የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን አምባዬ ገልጸው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የከተማው አስተዳደር ቀደም ሲል በቂ ካሳና ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ከቦታቸው በመፈናቀላቸው ለችግር የተጋለጡ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁሟል፡፡ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎችም እንደዚሁ በልማት ምክንያት ለሚነሱ አርሶ አደሮች የሚከፈለውን ካሳና የሚሰጠውን ምትክ ቦታ ለማስተካከል እንቅስቃሴ መጀመራቸው ታውቋል፡፡

ነገር ግን የመሠረተ ልማት ኤጀንሲው ከአዋጁ ጋር በሚያወጣው ደረጃ መሠረት፣ አዲስ አበባና ኦሮሚያን ጨምሮ ሁሉም የአስተዳደር አካላት ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከክልልና ከከተማ አስተዳደሮች በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት የመሠረተ ልማት ተቋማት በርካታ አርሶ አደሮችን ያፈናቅላሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኢትዮ ቴሌኮም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እነዚህ ተቋማት በልማት ምክንያት ነዋሪዎችን በሚያፈናቅሉበት ወቅት የሚከፍሉት ካሳ የተለያየ ነው፡፡ መንግሥትንም ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገ ነው የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ የኢትዮጵያን መንገዶች ባለሥልጣን በ2008 ዓ.ም. ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ መክፈሉም ተጠቁሟል፡፡

አቶ በቀለ፣ ‹‹እነዚህ የመሠረተ ልማት ተቋማት ሥራዎችን ከመጀመራቸው በፊት ኤጀንሲው በግንባታ ቀጣናው የሚገኙትን ተነሽዎች ይለያል፡፡ የሚከፈለውንም ካሳ በሚወጣው አሠራር መሠረት ይወስናል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ በቀለ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው ራሱን ለማደራጀት ሲያካሂድ የቆየውን ሥራ እያገባደደ በመሆኑ የካሳ አከፋፈል ሥርዓቱን የሚወስነውን ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀት ይጀምራል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...