Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበተሽከርካሪ አደጋ አራት ሰዎች ሲሞቱ 11 ሰዎች ቆሰሉ

በተሽከርካሪ አደጋ አራት ሰዎች ሲሞቱ 11 ሰዎች ቆሰሉ

ቀን:

ከፒያሳ ሾፌሩንና ረዳቱን ጨምሮ 15 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ሳሪስ ያቀና የነበረው አንድ ሚኒባስ፣ ከቴዎድሮስ አደባባይ በስተቀኝ በኩል በግምት 30 ሜትር ያህል ርቀት ካለው ገደል ውስጥ ከሚገኘውና ጥልቀቱ አምስት ሜትር ስፋት ደግሞ 60 ሜትር በሆነው ኩሬ ውስጥ ተገልብጦ፣ በአራት ሰዎች ላይ የሞት በሌሎች 11 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ አደረሰ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ይህንኑ አስመልክተው በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማክሰኞ መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት በደረሰው በዚሁ አደጋ የሞቱትን ሰዎች አስከሬኖች በአቅራቢያው የነበሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችና የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ሙያተኞች አውጥተዋቸዋል፡፡

ሾፌሩን ጨምሮ ከባድና ቀላል የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው አሥር ሰዎች በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መወሰዳቸውን፣ ረዳቱ ግን መጠነኛ የሆነ መላላጥ ብቻ ስለደረሰበት ወደ ተጠቀሰው ሆስፒታል እንዳልሄደ ረዳት ኢንስፔክተሩ አስረድተዋል፡፡

የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 42561 ኦሮ የሆነው ይኼው ሚኒባስ ቸርችል ጎዳናን ወርዶ የቀድሞው ባንኮ ዲሮማ አካባቢ እንደደረሰ አሽከርካሪው መኪናው እምቢ አለኝ የሚል ድምፅ ማሰማቱ፣ በዚህ ጊዜ ረዳቱና ሌሎች ሁለት ሰዎች ዘልለው መውጣታቸው፣ ተሽከርካሪው የቀሩትን ሰዎች ይዞ በአደባባዩ በስተቀኝ በኩል ባለው ገደል አፋፍ ላይ ያለውን የቆርቆሮና የብረት አጥሮችን ጥሶ ገደሉ ውስጥ ባለው ኩሬ ሊገባ መቻሉ ተገልጿል፡፡ የአደጋው መንስዔ ግን በመጣራት ላይ እንደሆነ ነው ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል መከላከል አባላትና የአካባቢው ማኅበረሰብ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን በመርዳት፣ ሚኒባሱን ከገባበት ኩሬ ውስጥ በማውጣትና አካባቢውን በማረጋጋት ላቅ ያለ ትብብርና አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ ደግሞ ከሞቱት መካከል ሦስቱ ሴቶች መሆናቸውንና አንደኛው ወንድ መሆኑን ገልጸው፣ የሁለቱ ሰዎች አስከሬን ከኩሬው ውስጥ የቀሩት ሁለት አስከሬኖች ደግሞ በውኃ ከተሞላው ሚኒባስ ውስጥ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡

አደጋው የተከሰተበት ሥፍራ ገደላማ መሆኑን የሚያሳይ የአደጋ ምልክት አለመኖር፣ በተጨማሪም ባለቤት አልባ የሆነው ኩሬ ለአደጋው መባባስ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ ንጋቱ አመልክተው፣ አራቱን ተሳፋሪዎች ለሞት ያበቃቸው ግጭት ሳይሆን ውኃው መሆኑንና አንድ ሰው ደግሞ ውኃ ውስጥ ከአምስት ደቂቃ በላይ በሕይወት ሊኖር እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ኩሬው ባይኖር ኖሮ የሕይወት አድን ሰዎች ተጎጂዎችን ከነጉዳታቸው ቶሎ ሊደርሱላቸው ይችሉ እንደነበር፣ በኩሬው አጠገብ 12 ፎቅ ሕንፃ በመገንባት ላይ እንደሆነና የኩሬው ባለቤትና ተጠያቂ ግን ማን መሆኑ እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡

ከአቶ ንጋቱ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው አዲስ አበባ ውስጥ ባለፈው ዓመት 312 የሚጠጉ የእሳትና የድንገተኛ አደጋዎች ደርሰው 111 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች 74 ሰዎች ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም አደጋ 104 ሚሊዮን 650 ሺሕ 550 ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን፣ ከደረሱትም ጠቅላላ አደጋዎች መካከል 284 ያህሉ የእሳት ሲሆኑ የቀሩት ልዩ ልዩ አደጋዎች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ ከልዩ ልዩ አደጋዎቹም መካከል ከፍተኛውን የሞት ቁጥር የያዙት ለካባ ተቆፍረው በተተውና ውኃ ባቆሩ ጉድጓዶች ውስጥ በልዩ ልዩ ምክንያት ገብተው የሞቱ ናቸው፡፡

ከመስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከዛሬ ድረስም አምስት ሰዎች ተቆፍረው በተተውና ውኃ ባቆሩ ጉድጓዶች ውስጥ በልዩ ልዩ ምክንያት ገብተው መሞታቸውን አቶ ንጋቱ ጠቁመው፣ ጉዳዩ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ለኮንስትራክሽንና ለካባ ተቆፍረው የተተው ጉድጓዶች እንዲደፈኑ እንዲያደርግ ወይም ሌላ መፍትሔ ሊፈልግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...