Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአማራ ክልል አሁንም መደበኛ ሕይወት አልተመለሰም

በአማራ ክልል አሁንም መደበኛ ሕይወት አልተመለሰም

ቀን:

–  የፀጥታ ኃይሎች የእስር አደን እያካሄዱ ነው ተባለ

–  ክልሉ ደግሞ ማሰር ሳይሆን በብር ሸለቆ ሥልጠና እየሰጠሁ ነው ብሏል

በአማራ ክልል ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ እስካለፈው ወር የመጨረሻ ቀናት ተስፋፍቶ የነበረው ተቃውሞና አለመረጋጋት ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉ ተገለጸ፡፡ በጎንደርና ባህር ዳር ከተሞችን ጨምሮ በርከት ባሉ የክልሉ ከተሞች የፀጥታ ኃይሎች በተቃውሞው ወቅት ዋና አንቀሳቃሾች ናቸው ያሏቸውን በቁጥጥር ሥር እያዋሉ መሆኑ ሲገለጽ፣ ያላገኟቸውንም በማደን ላይ መሆናቸውን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የቤተሰብ አባላት ተይዘውብናል ያሉና በተለይ በሁለቱ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉትን የአብዛኞችን መታሰር እንጂ የታሰሩበትን ሥፍራዎች ማወቅ ባለመቻላቸው ለመጠየቅም ሆነ ደኅንነታቸውን ለማወቅ አልቻሉም፡፡

የክልሉ መንግሥት በበኩሉ ወጣቶችን ማሰሩን ሳይሆን ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጾ፣ በወንጀል የሚጠረጠሩትን ደግሞ ለፍርድ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በፀጥታ ኃይሎች እየተወሰደ ባለው የማሰር ዘመቻ የጎንደር ነዋሪዎች በተፈጠረባቸው ሥጋት ቤቶቻቸውን በጊዜ በመዝጋት የቤተሰቦቻቸውን አባላት ከማምሸትም ሆነ በምሽት ወጥተው ከመንቀሳቀስ ለመገደብ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከዚሁ ሥጋት ጋር በተገናኘ የጎንደር ከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንቅስቃሴ ከመስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ማቆማቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማ ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡

‹‹ማንኛውም የጎንደር ቤተሰብ አስተዳደር ቤቱን ገና መምሸት ሲጀምር እየዘጋ ነው፡፡ በተለይ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ማንም ሰው ቤቱ ቢንኳኳ በሩን አይከፍትም፡፡ ሁሉም ልጆቹ ላይ ዓይኑን ተክሎ እየጠበቀ ነው፤›› በማለት ሪፖርተር ያነጋገራትና ጎንደር ከተማ መስጊድ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር ነዋሪ የሆነች ወጣት ገልጻለች፡፡

ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀችው ይህች ነዋሪ ቤተሰቦቿ የምሽት እንቅስቃሴ እንዳታደርግ እንዳዘዟት፣ በሁለት ወንድሞቿ ላይ የተለየ የቤተሰብ ማዕቀብ ተጥሎ ዕለት ተዕለት በጥበቃ ላይ እንዳሉ ጨምራ አስረድታለች፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት ባለቤቷ በቁጥጥር ሥር እንደዋለባት የምትናገረው ሌላዋ የከተማው ነዋሪ፣ ፖሊሶች ባለቤቷን ከሦስት ተከታታይ ቀናት ፍለጋ በኋላ በጠዋት መጥተው ከቤት ሲወጣ እንደያዙት ብታመለከትም፣ የታሰረበትን ቦታ አለማወቋን ተናግራለች፡፡

‹‹ሦስት ቀናት ሙሉ በጨለማ ቤታችን ድረስ ተመላልሰው ቢያንኳኩም ቤታችን አልከፈትንላቸውም፡፡ ነገር ግን እዚያው እያደሩ በመጨረሻ በጠዋት ባለቤቴ ሲወጣ ጥቁር መስታወት ባለው መኪና መጥተው ይዘውት ሄዱ፤›› በማለት ባለቤቷን ለመያዝ የመጡ ፖሊሶች ማንነታቸው እንዳይታይ ጥረት ማድረጋቸውን ጨምራ ለሪፖርተር አስረድታለች፡፡

በጎንደር ከተማ ታሳሪዎች ያረፉበትን ቦታ ማወቅ የቻሉት ‹‹ዕድለኛ›› ቤተሰቦች ጥቂት መሆንና የአብዛኞቹ ሥፍራ ግን አለመታወቁ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ አለመረጋጋት መፍጠሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይም በባህር ዳር ከተማና በሌሎችም አጎራባች ሥፍራዎች ተመሳሳይ እስር እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል፡፡

አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ሌላው ቢቀር እስካሁን ድረስ ተኩስ ሳይሰማ ያደረበት ቀን አለመኖሩን ጨምራ ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

እንዲሁም ካለፈው ዓመት ኅዳር ወር ጀምሮ ብዙ ወራት ያስቆጠረው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የበረደ ቢመስልም፣ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ከተሞች ተቃውሞው ሙሉ በሙሉ አለመዳፈኑን የሚያሳዩ ምልክቶች እንዳሉና በፀጥታ ኃይሎች የሚደረጉ እስራቶች መኖራቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል በበኩሉ በጎንደር፣ በባህር ዳርና በምዕራብ አማራ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተሳተፉ ወጣቶችን ወደ ብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ማዕከል ሥልጠና ለመስጠት እንደወሰዳቸው አምኗል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለሪፖርተር፣ ‹‹ግጭቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳቶች ደርሰዋል፣ እንዲሁም ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡ በዚህ አመፅ ደግሞ ብዛት ያላቸው ወጣቶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተሳትፈዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ክልሉን ወደኋላ የሚጎትት ሥራ ላይ የተሰማሩትን በመያዝ ሥልጠና የሚያስፈልጋቸውን ወጣቶች በመለየት በብር ሸለቆ ሥልጠና እየሰጣቸው ነው፡፡ ሥልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ ወደየቤተሰቦቻቸው ይቀላቀሉ፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በወንጀል የሚጠረጠሩትን በመለየት ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንና ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን በማፈላለግ ላይ መሆኑን አቶ ንጉሡ አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ወደ 800 የሚጠጉ ወጣቶች መያዛቸውን እንደሚገምቱ የተናገሩት አቶ ንጉሡ፣ ትክክለኛውን ቁጥር ለመናገር አጠቃላይ መረጃውን ለጊዜው በእጃቸው እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ከመስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በጎንደር ሌላ የአድማ ጥሪ በመጠራቱ ኅብረተሰቡ ላይ ጫናም እየተደረገበት በመሆኑ የትራንስፖርት፣ የሆቴልና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውንም አቶ ንጉሡ አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን በባህር ዳር ሰኞ ዕለት ጠዋት ተመሳሳይ የአድማ ምልክት የታየ ቢሆንም፣ ከቀትር በኋላ ጀምሮ ግን ወደ መደበኛው ዕለታዊ እንቅስቃሴ ተመልሷል ብለዋል፡፡

‹‹ኅብረተሰቡ አምኖበትና አመዛዝኖ ሳይሆን በአድማው የሚሳተፈው በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች መንገዶች በሚደረጉ ጥሪዎች ተደናብሮ ነው፡፡ እነዚህ ጥፋቶች ደግሞ በአብዛኛው ወጣቶች የሚሳተፉባቸው በመሆኑ ወጣቱን ማስተማር፣ መምከር፣ ስለሕግ የበላይነት፣ ስለሕግ አከባበርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ማስተማር አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ የግርግር ተሳታፊ ወጣቶችን ምቹ የሆነ ቦታ ተመርጦ የክልሉ አመራሮች በተገኙበት በብር ሸለቆ አስቀምጦ ማስተማር አስፈልጓል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የማወያያ ሰነድ ተዘጋጅቶ የክልሉ አመራር በቅርብ እየተከታተለው ሥልጠና ይካሄዳል ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ከዚህ ባሻገር እነዚህን ነውጦች ያካሄዱ፣ ያስፈጸሙ፣ የኢንቨስትመንት ውድመት ያደረሱና ለቤቶች መቃጠል አስተዋጽኦ ያደረጉ በወንጀለኝነት የሚጠረጠሩ ለብቻ ተይዘው ለሕግ ለማቅረብ ጥረት እየደረገ ነው፤›› ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ተቆርቋሪዎች በበኩላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ለለጋሽ አገሮች የኢትዮጵያ መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጽመው እስራትና የመብት ጥሰት አጠናክሮ ቀጥሏል በማለት፣ ጩኸታቸውን በማሰማት ተፅዕኖ እንዲያደርጉ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም መንግሥትን ለመኮነን ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሠልፎች እያካሄዱ መሆኑን ዘገባዎች እያመለከቱ ነው፡፡ በቅርቡ በአውሮፓና በአሜሪካ በተደረጉ ተቃውሞ ሠልፎች የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችንና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችን ሰብሮ እስከ መግባትና ሰንደቅ ዓላማ እስከ መቀየር መድረሳቸው ይታወሳል፡፡

ሰኞ መስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ ብዛት ያላቸው ተቃዋሚዎች በአደባባዮች በመውጣት መንግሥትን ያወገዙ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳልፉ ጥሪ አድርገዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...