በእነ አቶ በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ታሳሪዎች ለመከላከያ ምስክርነት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ቢጠሩም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመቅረብ ስላልቻሉ ታስረው እንዲቀርቡ ተከሳሾቹ ጠየቁ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግን በሥራ መደራረብ ምክንያት ለምስክርነት መቅረብ እንዳልቻሉ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡
እነ አቶ በቀለ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለምስክርነት የጠሩት እንደ ማንኛውም ግለሰብ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አክብረው የማይገኙ ከሆነ በፖሊስ ታስረው እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡
እነ በቀለ ለቀረበባቸው ክስ የመከላከያ ምስክር እንዲሆኗቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳንና የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓቢይ አህመድን (ዶ/ር) መጥራታቸው ይታወሳል፡፡