Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች 15 በመቶ የዋጋ አስተያየት ሳይደረግላቸው የብረት ጨረታ አሸነፉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጳጉሜን 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በተከፈተውና የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ባወጣው የብረት ግዢ ጨረታ አገር በቀል ኩባንያዎች የ15 በመቶ የዋጋ አስተያየት ሳይደረግላቸው አሸነፉ፡፡ በአንፃሩ አገር በቀል ኩባንያዎችን በዋጋ ንረት ሲከሱ የነበሩ የውጭ ኩባንያዎች ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ከፍተኛ ዋጋ በማቅረባቸው ተሸንፈዋል፡፡

የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ለመከላከያ ሚኒስቴር 22,167.6 ሜትሪክ ቶን አርማታ ብረት ለመግዛት ባወጣው ጨረታ አምስት ኩባንያዎች ተወዳድረዋል፡፡ ከአምስቱ ኩባንያዎች ለሲማር ኢንተርናሽናልና ሜታል ማርኬት የውጭ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ ስቲሊ አርኤምአይ፣ ኢስት ስቲልና ሲ እና ኢ አገር በቀል ኩባንያዎች ናቸው፡፡

በዚህ ጨረታ ስቲሊ ኤምአርአይ ለአንድ ኪሎ ግራም ብረት ዝቅተኛ የሆነውን 16 ብር ከ65 ሣንቲም በማቅረብ 20 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብረት ለማቅረብ አሸናፊ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ 288.2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ብረት ያቀርባል፡፡ ኢስት ስቲል ደግሞ ቀሪውን 2,263.7 ሜትሪክ ቶን ብረት በአንድ ኪሎ ግራም 18 ብር ከ89 ሣንቲም በማቅረብ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ኢስት ስቲል በአጠቃላይ 30.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ብረት ያቀርባል፡፡

ሁለቱ የውጭ ኩባንያዎች ደግሞ ለአንድ ኪሎ ግራም ከ22 ብር በላይ በማቅረባቸው መሸነፋቸው ታውቋል፡፡ የውጭ አገር ብረት አቅራቢዎችና በአገር ውስጥ የሚገኙ ብረት አስመጪ ኩባንያዎች በአገር በቀል አምራቾች ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከሁለት ወራት በፊት አቅርበው ነበር፡፡

ቅሬታቸውም መንግሥት ለአገር በቀል ኩባንያዎች የሚያደርገውን ጥበቃ ተገን በማድረግ፣ አገር ውስጥ የብረት ፋብሪካ ያላቸው ኩባንያዎች ከፍተኛ ዋጋ እያቀረቡ ተጠቃሚ መሆናቸው አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡

ኩባንያዎቹ በጋራ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹አገር በቀል ብረት አምራቾች ነን የሚሉ ጥቂት የአገር ውስጥ ባለፋብሪካዎችና የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ያቋቋሟቸው ፋብሪካዎች በመተባበር ከገበያ በላይ ዋጋ እያቀረቡ ነው፤›› ይላል፡፡ ደብዳቤው በመቀጠልም በአንድ ኪሎ አርማታ ብረት ከ300 በመቶ በላይ ወይም ከአንድ ኪሎ አሥር ብር ትርፍ እያገኙ በመሆኑ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ይጠይቃል፡፡

56 በመቶ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎበት የገባ ብረት በአገር ውስጥ በኪሎ ከ17.80 እስከ 18 ብር እየተሸጠ፣ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግን እስከ 22 ብር ከ50 ሣንቲም እያቀረቡ እያሸነፉ መሆኑን የሚገልጸው ደብዳቤ፣ ይህንን ዋጋ 56 በመቶ ቀረጥና ታክስ ቢቀነስበት ዋጋው እስከ አሥር ብር ድረስ ሊቀንስ እንደሚችል ይዘረዝራል፡፡

ሦስቱ አገር በቀል ፋብሪካዎች በአንድ ኪሎ ግራም 16 ብር ከ65 ሣንቲም፣ 17 ብር ከ48 ሣንቲም እና 18 ብር ከ85 ሣንቲም ሲያቀርቡ፣ የውጭዎቹ ኩባንያዎች ግን 22 ብር 25 ሣንቲም እና 22 ብር ከ15 ሣንቲም አቅርበዋል፡፡

ይህ ጨረታ በመጀመሪያ የወጣው ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ነበር፡፡ የዘገየበት ምክንያት ባይታወቅም የዓለም ነዳጅ ዋጋ እየቀነሰ በመምጣቱና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የብረት ዋጋም በመቀነሱ ተጫራቾቹ ዋጋ ከልሰው እንዲያቀርቡ በድጋሚ ተጋብዘዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች