የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ከኅብረተሰቡ የሚደርሱትን ጥቆማዎች መሠረት በማድረግ ባደረገው ልዩ ክትትልና ምርመራ፣ ሦስት ከፍተኛ አመራሮችና 15 ፈጻሚዎች በሙስና መሳተፋቸውን በማረጋገጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ከኅብረተሰቡ የሚደርሱትን ጥቆማዎች መሠረት በማድረግ ከኃላፊነትና ከሥራ ማገዱን አስታወቀ፡፡
ከተቋቋመ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው ኢንተርፕራይዙ ከኅብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ዕጦትንና ብልሹ አሠራሮችን የሚመለከቱ ጥቆማዎችን መሠረት በማድረግ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል፡፡ ኮሚቴው ላለፉት አምስት ወራት ባደረገው ክትትልና ማጣራት፣ አመራሮቹና ሥራ ፈጻሚዎቹ ከሥራ ተቋራጮች ምልመላ፣ ሥምሪት፣ ከአማካሪ መሐንዲሶች የጨረታ ሒደት፣ ከዋና ዋና ግዢዎች አፈጻጸም፣ ከግብዓት አቅርቦትና ሥርጭት ጋር በተያያዘ፣ የሙስና ተግባራት መፈጸማቸውን ማረጋገጡን የኢንተርፕራይዙ የኮሙዩኒኬሽን የሥራ ሒደት መሪ አቶ ዮሐንስ ዓባይነህ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ኢንተርፕራይዙ በተደጋጋሚ ከኅብረተሰቡ በተለይ በጨረታ ከሚሳተፉ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪ መሐንዲሶች፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚመጣውን ቅሬታና አቤቱታ መመርመሩን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ኮሚቴው ከሕዝቡ ያገኘው ጥቆማ ትክክል ሆኖ ስላገኘው ሦስት አመራሮችና 15 ፈጻሚዎችን ከመስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነትና ከሥራ በማገድ፣ የማጥራት ሥራ እያከናወነ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ማን በምን ደረጃ ችግሩን እንደፈጸመ ተጣርቶ እንደተጠናቀቀ በሕግ የሚጠየቀውን በሕግ፣ በዲሲፕሊን ኮሚቴ የሚጠየቀውን በዲሲፕሊን ኮሚቴ እንዲጠየቅ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ከዋና ዋና ግዢዎች፣ ከኮንትራክተር ምልመላና መረጣ፣ ከአማካሪ ጨረታ ሒደት፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች አመጣጥ፣ ከሥራ ሥምሪትና የገበያ ትስስር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሙስና ተፈጽሟል የሚል ግምት መኖሩን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የኢንተርፕራይዙ ሠራተኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡