Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያዊውን ለአፍሪካ ጉዳዮች በዳይሬክተርነት ሾመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክርስቲያን ለጋርድ በድርጀቱ ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩትንና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱትን ኢትዮጵያዊ አበበ አዕምሮ ሥላሴን፣ ለአፍሪካ ጉዳዮች በዋና ዳይሬክተርነት መሾማቸውን አስታወቁ፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1994 ጀምሮ በአይኤምኤፍ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት አቶ አበበ፣ የድርጅቱ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ዋና ዳይሬክተር ሆነው በመመረጥ ሲሾሙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡

በአዲሱ ሹመት አቶ አበበ ከሰኞ መስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የቀድሞ ዳይሬክተር የነበሩትን ኦንቶኒቴ ሳዬህን ተክተው ሥራ እንደሚጀምሩ፣ የገንዘብ ድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር መግለጻቸውን አይኤምኤፍ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹አፍሪካ ያጋጠሟት ፈተናዎችና ችግሮች በሚገባ እንዲታወቁ በማድረግ አቶ አበበ አመርቂ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዘመናቸው ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በቅርበት እየተነጋገሩ የአኅጉሪቱ ችግሮች ትኩረት እንዲያገኙ ሠርተዋል፤›› በማለት ላጋርድ የአቶ አበበን የካበተ ልምድ አብራርተዋል፡፡  

ከአቶ አበበ ጋር ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ አብረው እንደሠሩና ጥሩ ቀረቤታ እንዳላቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በውሳኔ አሰጣጥ ክህሎታቸው፣ ለሥራቸው ባላቸው ክብር፣ እንዲሁም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በሚሰጡት ትኩረት ደስተኛ መሆናቸውንና በዚህም ከልብ እንደሚደንቋቸው ገልጸውላቸዋል፡፡

ቀደም ብለው የሥራ ልምዳቸውን በኢትዮጵያ መንግሥት ሹመኝነት የጀመሩት አቶ አበበ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በዓለም የገንዘብ ድርጅት በተለያዩ ኃላፊነቶች ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ጨምሮ በተለያዩ አገሮች የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሙያ በመሆንና በተወካይነት ጭምር አገልግለዋል፡፡ ለአብነትም በኡጋንዳ የድርጅቱ ተወካይ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በኳትዲቯር፣ በጋና፣ በኬንያ፣ በቡርኪናፋሶ፣ በጊኒ፣ በላይቤሪያና በሴራሊዮን ለዓመታት ማገልገላቸውም ታውቋል፡፡

በቅርቡም በተለይ በአፍሪካ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ በዋናነት የመከታተል ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ሲሠሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ለድርጀቱ በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን ማበርከታቸው የተነገረላቸው አቶ አበበ፣ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተመድበው መሥራታቸውን ከድርጅቱ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የአውሮፓ አገሮች የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በገቡበት ወቅት በፖርቹጋል የአይኤምኤፍ ምክትል ተጠሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎም በቱርክና በፖላንድ የድርጅቱ ከፍተኛ ተወካይ በመሆን ሰፊ ልምድ ማካበታቸውም ይነገርላቸዋል፡፡

አቶ አበበን በቅርበት የሚያውቋቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለቦታው መመረጣቸውን በአድናቆት ሲቀበሉት፣ ለቦታው የሚመጥን ብቃት እንዳላቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡

የኧርነስት ኤንድ ያንግ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ የአቶ አበበን ሹመት አስመልክቶ ከሪፖርተር አስተያየታቸውን ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ‹‹ቦታውን በሚገባ የሚመጥኑ ችሎታ ያላቸው ኢኮኖሚስት ናቸው፤›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡

‹‹አቶ አበበ በዋሽንግተንም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ተመድበው ሲሠሩ እጅግ የሚመሰገን ብቃታቸውን ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡ በእኔ እምነት ለቦታው ትክክለኛ ሰው ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊም ሹመታቸው አስደስቶኛል፡፡ ምንም እንኳ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በከፍተኛ ቦታ የሚሠሩ ብዙ ወጣት ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ቢኖሩም፣ እንደ አቶ አበበ ዓይነት በለጋ ዕድሜ ላይ ያለ ሰው ለዚህ ዓይነት ቦታ መመረጣቸው ለሌሎች ወጣት ኢትዮጵያውያን መነቃቃትን የሚፈጥር ትልቅ ስኬት ነው፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች