Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኮንሶ በተቀሰቀሰ ደም አፋሳሽ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል

በኮንሶ በተቀሰቀሰ ደም አፋሳሽ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል

ቀን:

በደቡብ ክልል የኮንሶ ሕዝብ በዞን ለመተዳደር ያቀረበው ጥያቄ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ መስተናገድ ባለመቻሉ፣ በአካባቢው ደም አፋሳሽ ግጭት ተከሰተ፡፡ በግጭቱ የሰው ሕይወት መጥፋቱንና ሕፃናትና ሴቶች አካባቢያቸውን ለቀው እየሸሹ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኮንሶ ሕዝብ ራሱን ችሎ በዞን ለመተዳደር ያቀረበውን ጥያቄ ከሚያስተባብሩ የኮሚቴ አባላት አንዱ የሆኑት አቶ ገመቹ ገምሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቁጥሩ ለጊዜው ባይታወቅም በርካታ የሰው ሕይወት አልፏል፡፡ በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡

‹‹በተካሄደ የማጥላላት መዘቻ ለዘመናት አብረው በኖሩት በኮንሶና በቡርጂ ሕዝቦች መካከል ግጭት ተነስቷል፤›› በማለት አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡ ከደቡብ ክልል መንግሥት የወጡ መረጃዎች እስካሁን 12 ሺሕ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ያሳያሉ፡፡

ይህንን ደም አፋሳሽ ግጭት ለማብረድ የክልሉ ልዩ ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት መሰማራታቸው አቶ ገመቹ አስረድተዋል፡፡

የኮንሶ ሕዝብ በዞን ለመተዳደር ጳጉሜን በ2007 ዓ.ም. ለደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አቅርቦ ነበር፡፡ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ጥያቄውን እንደማይቀበል በደብዳቤ ገልጿል፡፡

‹‹የኮንሶ ሕዝብ መሠረታዊና ቀጥተኛ ጥቅሞችና ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ዓላማዎችን ለማሳካት እንዲችል፣ ሕዝቡ አሁን ባለበት የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን እንዲቀጥል፣ ኮንሶ ለብቻው በዞን በመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ለጥያቄ አቅራቢዎቹ በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ኮሚቴው የኮንሶ ሕዝብን ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ሰሞኑን በሰጠው ምላሽ የቀረበው ጥያቄ የማንነት ሳይሆን በዞን ደረጃ ለመተዳደር በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባው በክልሉ መንግሥት ነው ብሏል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደማይመለከተው በመግለጹ የኮንሶ በዞን የመተዳደር ጥያቄ ወደ ክልሉ ተመልሷል፡፡

‹‹አቤቱታችን የሚሰማ አጥተናል፤›› በማለት አቶ ገመቹ የኮንሶ ሕዝብ ከፍተኛ በደል እየደረሰበት ቢሆንም፣ ችግሩን በኃይል ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የደቡብ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ግን ጥያቄው ለክልሉ ምክር ቤትም ሆነ ለክልሉ መንግሥት መቅረቡንና ምላሽ መሰጠቱን ይናገራል፡፡ ለግጭቱ መነሻ ምክንያትም የጥያቄ አስተባባሪው ኮሚቴ አባላት ነዋሪዎችን በማስገደድ ክፍያ በመጠየቃቸው በተነሳ ውዝግብ ነውም ይላል፡፡ አሁን ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር ዳግም ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳይከሰት እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የኮንሶ ሕዝብ በልዩ ወረዳ ሲተዳደር ቆይቷል፡፡ በመጋቢት 2004 ዓ.ም. ኮንሶ፣ ቡርጂ፣ አማሮ፣ አሌ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች አንድ ላይ ሆነው በሰገን ሕዝቦች ዞን እንዲተዳደሩ ተወስኗል፡፡

በተዋቀረው ዞን ውስጥ የኮንሶ ብሔረሰብ በሕዝብ ቁጥርም ሆነ በመልክዓ ምድር ስፋት ከሌሎቹ አንፃር አብላጫ ድርሻ አለው፡፡ ነገር ግን ዞኑ የተመሠረተው የአካባቢው ሕዝቦች መክረውበት እንዳልሆነ፣ ይልቁኑም የክልሉ አመራሮች ባቀዱት መሠረት የተዋቀረ መሆኑን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎችን ይጠቁማሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል መምህር የሆኑት አቶ ናሁሰናይ በላይ የጉዳዩን አሳሳቢነት በሚመለከት ለሚመለከታቸው አካላት በላኩት ጽሑፍ፣ ጉዳዩ ከወዲሁ መፍትሔ ካላገኘ የማያባራ ግጭት ውስጥ ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹የኮንሶ ሕዝብ ቅር መሰኘቱንም በተለያዩ ስብሰባዎችና አጋጣሚዎች ገልጿል፡፡ በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ አሠራርን ተከትሎ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ ብቻ የተመሠረተ የፖለቲካ ማኅበረሰብን የመገንባት መርህን ያልተከተለ ስህተት ተሠርቷል፡፡ በዞኑ ምሥረታ ወቅትም በክልሉ አመራር የልዩ ወረዳ መዋቅር ፈርሶ በክልሉ የሚገኙ ልዩ ወረዳዎች ወደሚቀርባቸው ዞኖች እንደሚቀላቀሉ ቃል ተገብቶ ነበር፤›› በማለት አቶ ናሁሰናይ በጽሑፋቸው ይገልጻሉ፡፡

‹‹ኮንሶ አብላጫ ያለው ከመሆኑ የተነሳ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ተነፍጌያለሁ በማለት ጥያቄ እያነሳ ቢሆንም ምላሽ ሰጪ አካል ባለመኖሩ ከዞኑ ምሥረታ ማግሥት ጀምሮ ባለው መዋቅር ደስተኛ አይደለም፤›› በማለት የሚገልጹት አቶ ናሁሰናይ፣ ለአብነት ፍትሐዊ የበጀት ክፍፍል አለመኖር፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርናና የማኅበራዊ ጥቅሞች መጓደል፣ ብሔርን መሠረት በማድረግ ጥቃቶችን ማድረስ፣ ከዞኑ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኮንሶን ብሔር ተወላጆች ማግለል፣ ነባር አርሶ አደሮችን ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር ማጋጨት፣ ከመሬት ማፈናቀል፣ ከሰው ክልል ውጡ ማለት ተጠቃሽ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የኮንሶ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በዋናነት የተነሳው በእነዚህና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ቢሆንም በ2004 ዓ.ም. ሕጋዊ ውሳኔ ያላገኘ የከተማ መዋቅር ካለ ሕዝብ ፈቃድ እንዲከለል መደረጉን አቶ ናሁሰናይ አስታውሰዋል፡፡ ሕዝቡ ቀድሞ በልዩ ወረዳ መዋቅር ራስ ገዝ በሆነ መዋቅር መተዳደር የተለማመደ በመሆኑ፣ የተሻለ አንፃራዊ ልማት ለማምጣት ምቹ እንደነበር ተከራክረዋል፡፡ ይህ በመቋረጡና በሕዝቡ ላይ የደረሱ በደሎች ተደማምረው ለተነሳው ጥያቄ መንስዔ መሆኑን አቶ ናሁሰናይ ያምናሉ፡፡

‹‹ለፌዴራልና ለክልል ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እንዲሁም ለሚመለከታቸው አስተዳደር አካላት በተደጋጋሚ ጥያቄው ቀርቧል፡፡ ተገቢ ምላሽ ግን አልተገኘም፤›› በማለት አቶ ናሁሰናይ አስረድተዋል፡፡

የኮንሶ ወረዳ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ራስን በራስ የማስተዳደርና በዞን የመዋቀር ጥያቄ ማቅረብን፣ እንዲሁም ያለ ምክር ቤቱ ዕውቅና ከወረዳው ላይ የተቆረጡ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ እንዲመለሱ፣ ሕዝቡ ያላመነባቸው አመራሮች ከሥልጣን እንዲነሱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ይህ ሒደት ፍጹም ሰላምና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ እየሄደ ያለ ቢሆንም፣ አንዳንድ የክልልና የዞን አመራሮች ከኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የክልሉን ልዩ ኃይል ወደ ወረዳው በማስገባት ድብደባ፣ ዘረፋ፣ እስራትና የሕዝብ ተቋማትን በመውረር ሰላማዊ አካባቢን ከማወክ በተጨማሪ ሁለት አርሶ አደሮች በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን አቶ ናሁሰናይ በጽሑፋቸው ያስታውሳሉ፡፡

ከራስ በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ጋር ብቻ በተያያዘ ከ250 በላይ ሰዎች ያለምንም ምክንያት ታስረው ተለቀዋል፡፡ ሕዝብ ያነሳውን ጥያቄ እንዲያስተባብሩ ከተመረጡ መካከል አንዱ የሆኑትን የጎሳ መሪ በአርባ ምንጭ እስር ቤት ያለምክንያት ማሰርና መፍታትና ባህልን ማንቋሸሽ ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸውን አቶ ናሁሰናይ ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች በወቅቱ መፍታት ካልተቻለ የከፋ ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ እንደሚገባም አስጠንቅቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...