Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የደቡብ አፍሪካው ስፐር ሬስቶራንት በዚህ ወር በአዲስ አበባ ሥራ ይጀምራል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከግሬት አቢሲንያ ግሩፕ ኩባንያ ጋር በፍራንቻይዝ ስፐር የተሰኘውን የደቡብ አፍሪካ ሬስቶራንት በአዲስ አበባ ለመክፈት ባለፈው ዓመት የተስማማው ስፐር ግሩፕ በዚህ ወር ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የደቡብ አፍሪካው ስፐር ኮርፖሬሽን፣ የግሬት አቢሲንያ ግሩፕ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ከሆነው ኩሽና የንግድ ኩባንያ ጋር የፍራንቻይዝ ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በሁለቱ ስምምነት መሠረት የመጀመሪያው የስፐር ብራንድ፣ ስፐር ስቴክ ራንችስ የተባለው ሬስቶራንት በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሊከፈት እንደሚችል በወቅቱ ስምምነቱን የተፈራረሙት አቶ ሙሉጌታ ደምሴ፣ የኩሽና ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የስፐር ኮፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፒዬ ቫን ቶንደር አስታውቀው እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

ይህ የቤተሰብ ሬስቶራንት ልዩ ልዩ የሥጋ ጥብስና ሌሎችም ከሥጋ የሚዘጋጁ ምግቦችን በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከቦሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው አቢሲንያ ፕላዛ ሕንፃ ላይ ሥራ ለመጀመር የተዘጋጀ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፓናሮቲስ ፓስታ ፒዛ የተባለው ሁለተኛው ሬስቶራንትም ስፐር ስቴክ ራንች በተከፈተ በዓመቱ ሊከፈት እንደሚችል ይጠበቃል መባሉም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በተደረገው ስምምነት መሠረት እንደ ኩሽና ያለውን አገር ለማግኘትና ኢትዮጵያ ውስጥ የስፐር ሬስቶራንቶችን ለመክፈት አራት ዓመታት እንወሰደ የገለጹት ቶንደር፣ የሁለቱ ስኬማታማነት ታይቶም በጠቅላላው ሰባት ስፔሻላይዝድ ሬስቶራንቶችን በአዲስ አበባ ለመክፈት ማቀዱን አስታውቀው ነበር፡፡

ምንም እንኳ በታሰበው የጊዜ ገደብ ውስጥ የደቡብ አፍሪካውን ሬስቶራንት ዕውን ማድረግ ባይቻልም፣ በተለየ አኳኋን ለልጆች ልዩ ልዩ መዝናኛዎችን በማካተት በዚህ ወር ሥራ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን የገለጹት የካሊብራ ሆስፒታሊቲና ማማከር ንግድ ሥራ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነዋይ ብርሃኑ ናቸው፡፡ ስፐር ኮርፖሬሽን ለኩሽና ከሚሰጣቸው የሙያ ድጋፎች መካከል ዘመናዊ የሆቴልና ሬስቶራንት አስተዳደርና አያያዝ ላይ ያጠነጠኑ ሥልጠናዎችም መካተታቸውን አቶ ነዋይ አብራርተዋል፡፡

ስፐር ስቴክ ሥራ ሲጀምር ከደቡብ አፍሪካ የሚመጡ ባለሙያዎች ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውንና በሥራ ወቅት የሚሰጡ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡ የተገለጸ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ 180 ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ እንዲችል ሆኖ ዲዛይን የተደረገው ስፐር ስቴክ፣ ኢትዮጵያዊ ምግቦችንም አዛምዶ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

ከ40 ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ ያለው ስፐር ኮርፖሬሽን፣ በመላው ዓለም ከ500 በላይ ልዩ ልዩ ብራንድ ያላቸው ሬስቶራንቶችን የሚያስተዳድር ትልቅ ኩባንያ ነው፡፡ 500ዎቹ ውስጥ 318 ስፐር ስቴክ ራንችስ፣ 79 ፓናሮቲስ ፒዛ ፓስታ የተባሉት ሲሆኑ፣ ስምንት ሁሳር ግሪል የተባሉ ብራንዶችን ያንቀሳቅሳል፡፡ በአፍሪካ በ12 አገሮች ውስጥ እነዚህን ሬስቶራንቶች በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች