Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየጀግናው ምሩፅ ይፍጠር የጥቁር ዓባይ ኒሻን ዋጋው እምን ድረስ ነው?

የጀግናው ምሩፅ ይፍጠር የጥቁር ዓባይ ኒሻን ዋጋው እምን ድረስ ነው?

ቀን:

ባለፈው ነሐሴ በሪዮ ኦሊምፒክ የ10 ሺሕ ሜትር ሴቶች ሩጫ ፍጻሜ ሲካሄድ አልማዝ አያና ከዚህ ቀደም ባልተፈጸመ አስደናቂ አሯሯጥ ዓለምን ባስደመመ መልኩ ድል ስትመታ፤ በተመሳሳይ ርቀት ከ36 ዓመት በፊት በሞስኮ ኦሊምፒክ ድል የመታው ምሩፅ ይፍጠር በፅኑ ሕመም በሆስፒታል ውስጥ ሆኖ ውድድሩንና የአልማዝን ድል ይከታተል ነበር፡፡ ‹‹በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ቢያዝም ምሩፅ ደስታውን ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡

ከ12 ዓመት በላይ በዓለም አትሌቲክስ አደባባይ በረዥም ርቀትና በግማሽ ማራቶን ተደጋጋሚ ድሉ በአሯሯጥ ስልቱ ማርሽ ለዋጩ ‹‹ይፍጠር ዘ ሺፍተር›› የተሰኘው ምሩፅ በካናዳ ሞንትሪያል በፅኑ ሕመም እየተሰቃየ በሆስፒታል ውስጥ ይገኛል፡፡

በአሯሯጥ ስልቱ ዓለም ጉድ ያለለት ምሩፅ ከአንድ ዓመት ወዲህ በሳምባው ላይ በደረሰ ጉዳት በካናዳ ሕክምናውን እየተከታተለ ቢቆይም ፈውስ አላገኘም፡፡ ሁለቱም ሳምባዎቹ በመጐዳታቸው ምክንያት በተገጠመለት የመተንፈሻ አካል (ኦክሲጅን) አማካይነት ነው እየኖረ ያለው፡፡

- Advertisement -

እነዛ ማርሽ ይቀያይሩ የነበሩት ተወንጫፊ እግሮቹ ዊልቸር ላይ መዋላቸውም እየተነገረ ነው፡፡

ጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ ‹‹በደራው ጨዋታ›› በተሰኘው የራዲዮ መጽሔት ፕሮግራሙ ምሩፅን ከነበረበት ሆስፒታል በስልክ ባነጋገረበት ጊዜ ምሩፅ ሳምባዎቹ ከጥቅም ውጪ ሆነው በኦክሲጅን እየተነፈሰ ‹‹ሕዝብ ኢትዮጵያ ጸልዩልኝ›› ሲል መናገሩ ተሰምቷል፡፡

ከሆስፒታል ወጥቶ በሌላ የጤና ማዕከል በኦክሲጅን ድጋፍ ክብካቤ እየተደረገለት ላለው ምሩፅ ይፍጠር ከነሐሴ መገባደጃ ጀምሮ ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ200 ሺሕ፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የ150 ሺሕ፣ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የ250 ሺሕ ብር፣ በድምሩ የ600 ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ ችግር የደረሰባቸው ወገኖቹን በመርዳት የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአትሌቱ ጐን በመሆን አጋርነቱን እንዲያሳይም ጠይቋል፡፡

ምሩፅ ይፍጠር ሲገለጽ

መስከረም 1961 ዓ.ም. አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴን የያዘው የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ አትሌቶች የመጨረሻ ጉዟቸውን ወደ ሜክሲኮ ሲቲ ከማድረጋቸው በፊት ለልምምድ ያረፉት አስመራ ከተማ ነበር፡፡ በአስመራ ንግሥተ ሳባ ስታዲየም ልምምድ ሲያደርጉ የተመለከተው የከተማዋ ነዋሪ ምሩፅ ይፍጠር ለወደፊት ሕይወቱ በር ከፋች አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ በልምምድ ሩጫ ውድድርም ከነማሞ ወልዴ ጋር ተወዳድሮ መጨረሻ ቢወጣም አሯሯጡንና አቅሙን ያስተዋሉት አሠልጣኝ ንጉሤ ሮባ በአየር ኃይል ስፖርት መምሪያ እንዲያዝና ልምምድ እንዲያደርግ አደረጉ፡፡ ቅጥሩንም ፈጸመ፡፡ ለ20 ዓመታት በአየር ኃይል ሲያገለግል እስከ ሻምበልነት ደርሷል፡፡

በአዲስ አበባው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም፣ ንብ የሚባለውን የአየር ኃይል ስፖርት ክለብን እየወከለ በብሔራዊ ሻምፒዮናና በጦር ኃይሎች ውድድር ውጤታማ መሆን የጀመረው ምሩፅ፣ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል ውድድሩ በ1962 ዓ.ም. በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታንዛኒያ ውስጥ በ1,500 ሜትር ከኦሊምፒክ ባለወርቁ ኬፕቾግ ኬይኖ ጋር ተወዳድሮ ሦስተኛ የወጣበት ውድድሩ ነበር፡፡

በ1963 ዓ.ም. በአሜሪካ በተካሄደው የአፍሮ አሜሪካን ውድድር በ10 ሺሕ ወርቅ፣ በ5 ሺሕ ሜትር ብር ሜዳሊያ በማግኘት ድሉን አሐዱ ብሎ ጀምሯል፡፡

የመጀመሪያው የኦሊምፒክ መድረኩ በሆነው 20ኛው ኦሊምፒያድ በሙኒክ ሲካሄድ ምሩፅ በ5 ሺሕና በ10 ሺሕ ሜትር ለመወዳደር ነበር ወደ ሥፍራው ያመራው፡፡ በ10 ሺሕ ሜትር በማጣሪያው አንደኛ ወጥቶ በፍጻሜው ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያን አግኝቷል፡፡ በ5 ሺሕ ሜትር ማጣሪያ በአሠልጣኞቹ ችግር ምክንያት በጊዜ ባለመድረሱ የተነሳ ሳይወዳደር በመቅረቱ ሌላ ሜዳሊያ የማግኘት ዕድሉ ተጨናግፎበታል፡፡

በ1965 ዓ.ም. በሌጎስ (ናይጄሪያ) በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በ10 ሺሕ ወርቅ በ5 ሺሕ ብር አሸንፏል፡፡ በዚያው ዓመት ከሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ከተውጣጡት መካከል የኢትዮጵያ ስፖርት ኮከብ አትሌት ተብሎ የተመረጠው ምሩፅ፣ በ1968 ዓ.ም. በሞንትሪያል (ካናዳ) በተካሄደው 21ኛው ኦሊምፒያድ ያለ ጥርጥር በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ሁለት ወርቅ ያገኛል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስፖርታዊ ግንኙነት የነበራት ኒውዝላንድ ከሞንትሪያል ኦሊምፒክ ባለመታገዷ ምክንያት አፍሪካውያን አንካፈልም በማለታቸው ሳይወዳደር ተመለሰ፡፡

በሙኒክ ኦሊምፒክ ምሩፅን ያሸነፈው ፊንላንዳዊው ላሲ ቨረን ዳግመኛ ድሉን ምሩፅ በሌለበት አጣጣመ፡፡

ምሩፅ የኦሊምፒክ ወርቅ ሕልሙን ያሳካው በ1972 ዓ.ም. ሞስኮ ባስተናገደችው 22ኛ ኦሊምፒያድ ሲሆን በሁለቱም ርቀቶች ወርቁን ያጠለቀው ፊንላንዳዊውን ላሲ ቨረንን ድል በመምታት ነበር፡፡

በሞስኮ ኦሊምፒክ ሲሮጥ ዕድሜው የገፋው (በፓስፖርት ዕድሜው 36 ዓመቱ በተለያዩ ሚዲያዎች እስከ 42 የሚያደርሱት) ምሩፅ፣ በ1969 ዓ.ም. እና በ1971 ዓ.ም. በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫዎች አፍሪካን በመወከል አራት ወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ ተወዳዳሪዎቹን በቀደመበት ርቀት ያህል በሞስኮ አልደገመውም፡፡ ዕድሜው ገፍቷልና፡፡

በሁለቱ የዓለም ዋንጫዎች በ5,000 ሜትር ውድድሩ ሊያበቃ 500 ሜትር ሲቀር፣ በ10 ሺሕ 600 ሜትር ሲቀር ነበር ማርሽ ቀይሮ በማፈትለክ ያሸነፈው፡፡ በሞስኮ ኦሊምፒክ ግን በሁለቱ ርቀቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው 200 ሜትርና 300 ሜትር ሲቀረው ነበር ማርሻ ቀይሮ ድል የመታው ምሩፅ በ1971 ዓ.ም. በዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክሎ ለመካፈል የበቃው የመጀመሪያው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዳካር (ሴኔጋል) ሲካሄድ ሁለት ወርቅ (በ5 ሺሕና 10 ሺሕ) በማግኘቱ ነበር፡፡

ምሩፅ 1971 ዓ.ም. ወርቃማ ዓመቱ ነበር፡፡ እጅግ የገነነበት ታላቅ ክብርንም የተቀዳጀበት፡፡ በዚያው ዓመት በቼኮዝሎቫኪያ በተዘጋጀው የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ዘጠኝ አትሌቶች ሲመረጡ አንዱ ምሩፅ ሲሆን ‹‹የኮከቦች ኮከብ›› ተብሎ መመረጡ በተዘጋጀው የተሸላሚዎች መድረክ ራሱ ከመሃል በከፍታ መቀመጡ ይታወሳል፡፡ የወርቅ ጫማም ተሸላሚ ነበር፡፡ ምሩፅ ድርብ ድሎቹን በዳካር፣ በሞስኮና ሞንትሪያል በተደረጉ አህጉራዊና ዓለማዊ ውድድሮች ስድስት ወርቅ ይዞ አዲስ አበባ በደረሰ ጊዜ ጋዜጠኛ ኃይሉ ልመንህ እንዲህ ገጥሞለት ነበር፡፡

‹‹አብዮቱ ፈካ አበባው አማረ

ያለም ሻምፒዮና በምሩፅ ሠመረ፡፡

ሞስኮ ላይ ቀደመ ዳካር ላይ ድል መታ

ሞንትሪያል ደገመ እንዳመሉ ረታ

ዓለም ይሁን አለ ድሉን ተቀበለ

እየደጋገመ ምሩፅ ምሩፅ አለ፡፡››

የመጀመሪያ ዓለም ዋንጫ በዱዞልዶርፍ (ምዕራብ ጀርመን) ሲካሄድ አፍሪካን ወክሎ ለመሳተፍ የበቃው የቅርብ ተቀናቃኙን ኬንያዊውን የዓለም ሪከርድ ባለቤት ሔንሪ ሮኖን በመርታት ነበር፡፡

የዛሬ 40 ዓመት ምሩፅ ያለም ዋንጫ ክብርን በሁለት ወርቆች አጅቦ አዲስ አበባ ሲደርስ ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉም ስንኞች አስሮለት ነበር፡፡

‹‹አቦ ምናይነት ፍጡር ነው?

ድካም የማይሰማው

ለአፍሪካ ሁለት ወርቅ

ማስገኘት የቻለው

ምሩፅ ሮጠ ገሠገሠ

ዝናውን በዝና አደሰ

ሔደ ተራመደ እጅግ ፈጠነ

ገነነ በዓለም ገነነ

አሸንፎ ሲገባ

ዝናው በዓለም አስተጋባ››

በማለት ከዜማ ጋር ተቀናብሮ በሬዲዮ ቀርቦ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት (የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ) ሻምበል ምሩፅ በቅድመ ሞስኮ ኦሊምፒክ ባገኛቸው አህጉራዊና ኢንተርናሽናል ድሎች ኢትዮጵያን ለታላት ግርማ ሞገስ በማብቃት ለፈጸመው አኩሪ ተግባር አምስተኛው የአብዮት በዓል ሲከበር ‹‹የጥቁር ዓባይ ኒሻን››ን ከርዕሰ ብሔሩ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እጅ መቀበሉ ይታወሳል፡፡

በ1,500 ሜትር መወዳደር የጀመረው ምሩፅ 5 ሺሕና 10 ሺሕ መደበኛ ውድድሮቹ ቢሆኑም በጎዳና ላይ ሩጫዎችም ተደጋጋሚ ድሎች ማግኘቱ አይሳትም፡፡

በተለይ በተከታታይ ዓመታት ድል የተጎናፀፈበት የፖርቶ ሪኮ ግማሽ ማራቶን ውድድር ለዓለም ክብረ ወሰን የበቃበት ነበር፡፡ ጥር 29 ቀን 1969 ዓ.ም. በፖርቶ ሪኮ ኮዓሞ የ21 ኪሎ ሜትር (ግማሽ ማራቶን) ውድድር ምሩፅና መሐመድ ከድር ተከታትለው ሲያሸንፉ ምሩፅ የገባበት 1 ሰዓት 02 ደቂቃ 57 ሰከንድ ያለም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡

በ1972 በፖርቶ ሪኮ ግማሽ ማራቶን አሸንፎ እንደተመለሰ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ‹‹የማተኩረው በሞስኮ ኦሊምፒክ ስለሆነ በፖርቶ ሪኮው ድሌ አልኮራም›› ማለቱ አይዘነጋም፡፡

በሞስኮ ኦሊምፒክ ለሦስተኛ ጊዜ ድሉን ለማጣጣም ቋምጦ የነበረው ፊንላንዳዊ ላሲ ቬረን በሞስኮ አየሩ ጥሩ ከሆነ እንደሚያሸንፍ መናገሩን ተከትሎ ምሩፅ በሰጠው አፀፋ ‹‹ሐሩርም ይሁን በረዶ እኔ ከማሸነፍ የሚገታኝ አንዳች ኃይል የለም›› ማለቱ ልበ ሙሉነቱን ያሳየበት አጋጣሚ ነበር፡፡

ከሞስኮ ኦሊምፒክ ድሉ በኋላ ጥንታዊ ኦሊምፒክ በተመሠረተበት ግሪክ ለኦሊምፒያዊ ሽልማት ከተመረጡ አምስት አትሌቶች ቀዳሚ ሆኖ የኦሊምፒክ ሎሬት አክሊልን ከርዕሰ ብሔሩ የተቀበለው ምሩፅ ይፍጠር ነበር፡፡

በዓለም ገናና ለሆነው ኃይሌ ገብረሥላሴና ለሞሮኮው ሰዒድ አዊታ አርአያ የሆነው ምሩፅ፣ ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር በ1973 ዓ.ም. በምዕራብ ጀርመን ባደን ባደን ጉባኤውን ሲያካሂድ የዓለም አትሌቶችን ከወከሉ ሁለት አትሌቶች አንዱ ርሱ ነበር፡፡ ሁለተኛው ተወካይ እንግሊዛዊው ያሁኑ የኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት የያኔው የሞስኮ ኦሊምፒክ የ1,500 ሜትር ባለድል ሰባስቲያን ኮ ነበር፡፡

ያ ስመ ገናና ‹‹ይፍጠር ዘ ሺፍተር››፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ከካናዳ ሆኖ በባዕድ መንግሥት እየታገዘ ያለውን ምሩፅ፣ እጅግ ውድና በገንዘብ የማይተመኑት ሽልማቶቹ በጨረታ ተሸጠው ለሕክምና እንዲውሉ ሲጠየቅ ‹‹ሽልማቶቼ የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው፤ ለሽያጭ አይታሰቡም›› ያለውን ምሩፅ፣ ፍጡነ ረድኤት ሆኖ የሚደርስለት ማነው? ከኢትዮጵያ መንግሥት ከነሙሉ ክብሩ ጥቅሙና ግዴታዎቹ ጋር ያገኘው የጥቁር ዓባይ ኒሻን የሚያስገኝለትን ጥቅም የአሁኑ መንግሥት ለምን ችላ አለው? ብለው የሚጠይቁ አሉ፡፡

‹‹የፊት ወዳጅህን በምን ቀበርከው በሻሽ፣ የኋላው እንዳይሸሽ›› መባሉን እዚህ ላይ ማስታወስ ያሻል፡፡    

የምሩፅ ይፍጠር ዓበይት ድሎች

ኢትዮጵያን በመወከል

ሜዳሊያ

እ.ኤ.አ.

ኦሊምፒክ ጨዋታዎች

ወርቅ

1980

ሞስኮ

5,000 ሜትር

ወርቅ

1980

ሞስኮ

10,000 ሜትር

ነሐሰ

1972

ሙኒክ

10,000 ሜትር

መላ አፍሪካ ጨዋታዎች

ወርቅ

1973

ሌጎስ

10,000 ሜትር

ብር

1973

ሌጎስ

5,000 ሜትር

አፍሪካን በመወከል

የአይኤኤፍ ዓለም ዋንጫ (የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ)

ወርቅ

1977

ዱዘልዶርፍ

5,000 ሜትር

ወርቅ

1977

ዱዘልዶርፍ

10,000 ሜትር

ወርቅ

1979

ሞንትሪያል

5,000 ሜትር

ወርቅ

1979

ሞንትሪያል

10,000 ሜትር

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...