Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየካርድ ስጦታዎች

የካርድ ስጦታዎች

ቀን:

ከአምስት ዓመታት በፊት የነበረው የሠርጓ ዝግጅት በሕይወቷ ከማትዘነጋቸው ጊዜዎች የመጀመሪያው ነው፡፡ በሠርጓ ሰሞን የቤተሰቦቿ ቤት ለሠርጉ ሽርጉድ በሚሉ ጎረቤቶችና ዘመድ አዝማድ ተሞልቷል፡፡ እሷም ከሚዜዎቿ ጋር ሆና ስለ ሠርጉ ዝግጅት ይወጥናሉ፡፡ በዚህ መሀል ከዘመዶቿ መካከል የሆኑ ጥንዶች ከሠርጉ ዕለት ቀድመው ስጦታ ሊያበረክቱላት እንደፈልጉ ገለጹላት፡፡ የሠጧት የ2,000 ብር የስጦታ ካርድ ነበር፡፡ ካርዱ እስከሚችለው ድረስ የምትፈልጊውን የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ከሴፍዌይ ሱፐር ማርኬት መግዛት ትችያለሽ አሏት፡፡ ከዛን ዕለት በፊት ስለ ስጦታ ካርድ በፊልም ከተመለከተችው የዘለለ መረጃ አልነበራትም፡፡

‹‹እኛ አገር የስጦታ ካርድ አገልግሎት መኖሩን አላውቅም ነበር፡፡ ለሠርጌ ግን የ2,000 ብር የስጦታ ካርድና ሌላም የ500 ብር የስጦታ ካርድ ተሰጥቶኛል፤›› ትላለች ከአምስት ዓመት በፊት ጋብቻዋን የፈጸመችው ወይዘሮ ለዓለም መሠረት፡፡ ብዙዎች ለሠርግ ስጦታ የሚሰጡት የራሳቸው ምርጫ የሆኑ ቁሳቁሶችን ሲሆን፣ የስጦታ ካርድ የሰጧት ጥንዶች ግን እሷና ባለቤቷ የሚፈልጉትን ዕቃ ቢመርጡ የበለጠ እንደሚጠቀሙበት ነገሯት፡፡ የስጦታ ካርዱ ከ15 ቀን በኋላ አገልግሎት ስለማይሰጥ ሠርጉ ባለፈ በሳምንቱ ለሸመታ ወደ ሱፐር ማርኬቱ አቀናች፡፡

ቡና ማፍያ ማሽን፣ ካውያ፣ የራስጌ መብራት፣ ፀጉር መሥሪያና ሌላም ለአዲሱ ጎጆዋ ያስፈልጋል ያለችውን ወሰደች፡፡ ‹‹የስጦታ ካርድ የሚበረከትለት ሰው በጣም ይጠቀማል፡፡ ከቤቱ የጎደለውን የሚያውቀው ባለቤቱ በመሆኑ ጥሩ የስጦታ ምርጫ ነው፤› ትላለች፡፡ ለአንድ ሰው የሚሰጠው ስጦታ ቀድሞ ከነበረው ወይም ከሌላ ሰው ከተሰጠው ዕቃ ጋር እንዳይመሳሰል የስጦታ ካርድ አማራጭ ይፈጥራል፡፡

አንድ ሰው የሚፈልገው ወይም የሚወደው ነገር ስጦታ ሲሰጠው መደሰቱ ዕሙን ነው፡፡ ወይዘሮ ለዓለም፣ ስጦታ ቅርብ ከሆኑ ሰዎች ሲሰጣት የበለጠ ትርጉም እንዳለው ይሰማታል፡፡ ሰዎች የምትወደውን አውቀው ስጦታ ሲያበረክቱላት ደስ ይላታል፡፡ የስጦታ ካርድ ግን ይህንን ዓይነት የመቀራረብ ስሜት የሚፈጥር አይመስላትም፡፡

‹‹ሰጪው ማንኛውንም ነገር የመግዛት መብቱን ለተቀባዩ ሲሰጥ ስጦታ የመለዋወጥ ቅርርቡን ያሳሳዋል፤›› ትላለች፡፡ የስጦታ ካርዶች አገልግሎት የሚጨርሱበት (ኤክስፓየር የሚያደርጉበት) ቀን ያላቸው መሆኑም፣ ስጦታ መለዋወጥን ከስሜታዊነት ወደ ቁሳዊነት ያወርደዋል ብላ ታምናለች፡፡ የስጦታ ካርድ ለአንዳንዶች ብልህ ምርጫ ቢሆንም፣ በጣም ለሚቀራረቡ ሰዎች ላይሠራ ይችላል የሚል ሥጋት አላት፡፡

የስጦታ ካርድ፣ ከካርድ አገልግሎቶች አንዱ ሲሆን፣ የአገራችን የስጦታ ዝርዝር ውስጥ ከተቀላቀለ ሰነባብቷል፡፡ ከስጦታ ካርድ (ጊፍት ካርድ) በተጨማሪ የቅናሽ (ዲስካውንት ካርድ) እና የደንበኝነት (ሎያሊቲ ካርድ) ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡

እንደ ካርድ አገልግሎት ሁሉ የሰዎችን የዕለት ከዕለት ሕይወት ለማቅለል የሚረዳ ግልጋሎት የሚሰጡ ተቋሞች እየበዙ መጥተዋል፡፡ እንደ ኦን ላይን ግብይትና ዴሊቨሪ ሰርቪስ ያሉ በተቀረው ዓለም የተለመዱ አገልግሎቶች ዛሬ ዛሬ የብዙዎችን በር እያንኳኩ ነው፡፡ ከከተሜነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ የበርካቶች አኗኗር ዘዬ እየተለወጠ ነውና፡፡ የብዙዎች ሕይወት በሩጫ እንደመሞላቱም ጊዜና ገንዘብ የሚቆጥቡ አማራጮች ቀና ምላሽ ይሰጣቸዋል፡፡ ከአማራጮቹ አንዱ የስጦታ ካርድ፣ በተለያየ ገንዘብ እርከን ይዘጋጃል፡፡ የሚሰጠው ሰው ካርዱን ካዘጋጀው ተቋም ካርዱ ላይ በተጠቀሰው ገንዘብ መጠን የሚፈልገውን ይሸምታል፡፡ በሱፐር ማርኬቶች፣ የውበት ሳሎኖችና ሌሎችም ተቋሞች አገልግሎቱ ሊሰጥ ይችላል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ተቋሞች ለረዥም ዓመታት ደንበኞቻቸው ልዩ የደንበኝነት ካርድ ያዘጋጃሉ፡፡ ካርዱ ደንበኞቻቸው ቅናሽ ወይም የቅደሚያ መስተንግዶ እንዲያኙ ያስችላቸዋል፡፡ የአንድ ተቋም ደንበኛ ያልሆኑ ግለሰቦችም የቅናሽ አገልግሎት የሚያገኙበት የካርድ አሠራር አለ፡፡

ተቋሞች ለደንበኞቻቸው ወይም ደንበኛ እንዲሆን ለሚፈልጉት ግለሰብ የሚሰጡትን ካርድ ሁሉም ተጠቃሚ በሙሉ ልብ ይቀበለዋል ማለት ይከብዳል፡፡ በቅናሽ ወይም በነፃ አገልግሎት ማግኘት በቀላሉ የማይዋጥላቸው ሰዎች ገጥመውናል፡፡ አቶ በላይነህ ሰለሞን በቅርቡ ለሥራ ወደ ባቦጋያ ሎጅ ሄዶ ነበር፡፡ ሥራውን ሲያጠናቅቅ የሥራ ባልደረባው ከትዳር አጋራቸው ጋር ለሁለት ቀን በነፃ በሎጁ እንዲያዝናኑ ከሎጁ አስተዳደር ጥሪ ቀረበላቸው፡፡

ካርዱ የሁለት ቀን ሙሉ መስተንግዶ እንዲያገኙ ቢፈቅድም፣ አቶ በላይነህ ደፍሮ ሊጠቀምበት እንዳልቻለ ይናገራል፡፡ ‹‹ካርዱ ቢሰጠኝም ለመጠቀም ድፍረቱን አላገኘሁም፡፡ በነፃ ሙሉ አገልግሎት ማግኘት የሚለውን ሐሳብ ልቤ አልተቀበለውም፤›› ይላል፡፡ ይሉኝታ ይዞት ካርዱን እስካሁን ባይገለገልበትም፣ ጓደኞቹ ካርዱን ጥቅም ላይ እንዲያውለው እያበረታቱት ነው፡፡ እሱ ግን ካርዱን ይዞ ከባለቤቱ ጋር ወደ ሎጁ ለመዝናናት ቢሄድ ነፃነት የሚሰማው አይመስለውም፡፡ በተቃራኒው የሥራ ባልደረባው ካርዱን ከባለቤታቸው ጋር እንደሚጠቀሙበት ነግረውታል፡፡

አሁንም ካርዱን ልጠቀም ወይስ ልተወው የሚለው ላይ ባይወስንም፣ የደንበኝነት ካርድ ለተጠቃሚዎች ልዩ ስሜት እንደሚሰጥ ያምናል፡፡ ከክፍያ ነፃ ወይም የቅናሽ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ወደ ተቋሙ እንዲመለሱ ያበረታታል፡፡ አቶ በላይነህ ከ12 ዓመት በፊት ሲያገባ አንድ ወዳጁ ከኖቪስ ሱፐር ማርኬት የሚፈልገውን እንዲገዛ የ500 ብር የስጦታ ካርድ ሰጥቶት እንደተጠቀመበት ያስታውሳል፡፡ ያኔም ጉዳዩ ባይዋጥለትም ገንዘቡ አነስተኛ ከመሆኑም አንፃር በድፍረት በካርዱ እንደተገለገለ ይናገራል፡፡

በሌሎች አገሮች የካርድ አገልግሎት ዓመታትን በማስቆጠሩ የሰዎች የዘወትር መገልገያ ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ በተሠራ ጥናት፣ የስጦታ ካርድ በአገሪቱ በብዛት ከሚሰጡ ስጦታዎች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ካናዳ ውስጥ ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ በዓመት ለስጦታ ካርድ ሸመታ ይውላል፡፡

በተያያዥ የተቋሞች ልዩ የአባልነት ካርድ (ሜምበርሺፕ ካርድ) የተለመደ ነው፡፡ የቱርኩ ተርኪሽ አየር መንገድ ‹‹ማይልስ ኤንድ ስማይልስ›› በሚል ብዙ ለሚጓጓዙ ደንበኞቹ ያዘጋጀውና የኢትዮጵያ አየር መንገረዱ ሼባማይልስም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሆንግ ኮንግ ሰፊ የካርድ አገልግሎት የሚሰጠው በትራንስፖርት ዘርፍ ሲሆን፣ ኢንዶኔዥያውያን ደግሞ የውበት ምርቶች ላይ ያተኩራሉ፡፡ አንዳንድ አገሮች የካርድ አገልግሎትን ለወታደሮች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለተማሪዎች ይሰጣሉ፡፡ በአገራችን ደግሞ እንደ አንበሳ አውቶቡስ ያሉ ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው እስከ ዕድሜ ልክ ነፃ የትራንስፖርት ካርድ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

ሴፍዌይ ሱፐር ማርኬት ላለፉት ስድስት ዓመታት የስጦታና አባልነት ካርድ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ደንበኞቻቸው በሚፈልጉት ገንዘብ መጠን የስጦታ ካርድ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ሦስት የአባልነት ካርዶችም አሏቸው፡፡ ሲልቨር (የብር)፣ ጎልደን (የወርቅ) እና ኮርፖሬት ጎልደን በተለያየ ደረጃ ላሉ ደንበኞቻቸው የሚሰጡ ካርዶች ሲሆኑ፣ ደንበኞች በየአባልነት ደረጃቸው ከ2.5 በመቶ እስከ አሥር በመቶ ቅናሽ ያገኛሉ፡፡ ካርዱ ሰልፍ በሚኖርበት ጊዜ ከሌሎች ሸማቾች ቀድመው እንዲስተናገዱም ያስችላቸዋል፡፡

የሱፐር ማርኬቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ከበደ እንደሚናገሩት፣ የግብይት ሥርዓቱን ቀላልና ፈጣን ለማድርግ የኤሌክትሮኒክስ ካርድ አገልግሎት ለመስጠት እየተዘጋጁ ነው፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ኤሌክትሮኒክስ የካርድ አገልግሎት ቤተሰብና ድርጅቶችም ወርሃዊ ወጪያቸውን አቅደው እንዲጠቀሙ ምቹ መንገድ ይፈጥራል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋሞችም የደንበኞቻቸውን ቁጥር መጨመር ይችላሉ፡፡ ‹‹የካርድ አገልግሎቶች የዘመናዊ ግብይት አንድ አካል ናቸው፡፡ የስጦታ ካርድ የተቀባዩን ተጠቃሚነት ከማስፋቱ ባሻገር የሰጪውን ጊዜም ይቆጥባል፤›› ይላሉ፡፡ ከግለሰቦች በተጨማሪ ድርጅቶችም ለሠራተኞቻቸው ካርዱን ይገዛሉ፡፡ ለገና፣ ለአዲስ ዓመትና በመደበኛ ቀን ሠራተኞችን ለማበረታታትም ይሰጣሉ፡፡

ለሠርግ፣ ልደት፣ ምርቃትና በዓላት ካርዶችን የሚጠቀሙ ሰዎች መብዛታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በሌሎች አገሮች ለእናቶች ቀን፣ የፍቅረኞች ቀንና ሌሎችም ቀኖች የካርድ ተጠቃሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ የካርድ አገልግሎት (የቪዛ ካርድና ማስተር ካርድ) መዋቅር ሙሉ በሙሉ በተዘረጋባቸው አገሮች ነገሮች ቀላል ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠቀሰው የሸዋ ሱፐር ማርኬትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥምረት ነው፡፡ ስጦታ የተባለው የካርድ አገልግሎት 500፣ 1,000፣ 2,000 ወይም 5,000 ብር ካርድ መግዛት ያስችላል፡፡ የንግድ ባንክ ድረገጽ እንደሚያመለክተው፣ ባንኩ የፖስ ማሽን በሸዋ ሱፐር ማርኬቶች በመግጠም፣ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን እንዲያኙ ያደርጋል፡፡ አገልግሎቱ ጥሬ ገንዘብ ከመጠቀም ይልቅ ካርድን የሚመርጥ ማኅበረሰብ የመፍጠር አንድ ዕርምጃ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ቅምሻ ካርድ፣ ተጠቃሚዎች የሚፈልጉት ነገርን የሚያገኙበትን ቦታ ከመጠቆም በተጨማሪ የቅናሽ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ የቅምሻ ካርድን የሚገዙ ግለሰቦች፣ ከቅምሻ ካርድ አዘጋጅ ድርጅት ጋር ስምምነት ካላቸው ተቋሞች ብቻ ከ10 እስከ 15 በመቶ ቅናሽ ያገኛሉ፡፡

ተጠቃሚዎች ለመዝናናት ወይም ውበትና ጤናቸውን ለመጠበቅ የተሻለ አማራጭ የሆኑ አገልግሎት ሰጪዎችን ከቅምሻ ካርድ አዘጋጁ ብርሃኑና ጥሩነህ ማስታወቂያና ግንኙነት ድርጅት መጠየቅ ይችላሉ፡፡ የካርዱ ዋነኛ ጠቀሜታ ግን የቅናሽ አገልግሎት ማግኘት ነው፡፡

የቅምሻ ቅድመ ክፍያ የቅናሽ አባልነት ካርድ የፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ኪሩቤል ግርማ እንደሚናገረው፣ የአንድ ሬስቶራንት ወይም ፀጉር ቤት ባለቤት በፈለገው ቀንና ሰዓት ለካርዱ ተጠቃሚዎች ከመደበኛ ክፍያው ላይ ዋጋ ለመቀነስ ይስማማል፡፡ ካርዱ አገልግሎት እስከሚሰጥበት ጊዜም ተጠቃሚዎች ቅናሽ ያገኛሉ፡፡ ካርዱ የሚዘጋጀው በተጠቃሚው ስም ሲሆን፣ ካርዱ ለሦስት ወር በ345 ብር፣ ለስድስት ወር በ517 ብርና ለዓመት በ775 ብር ይሸጣል፡፡

ኃላፊው ‹‹አገልግሎት ሰጪዎች ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ተጠቃሚዎች ደግሞ በቅናሽ አገልግሎት ለማግኘት ያውሉታል›› ሲል ይናገራል፡፡ ሐሳቡ ባለመለመዱ ተቋሞች ቅናሽ እንዲያደርጉ ማሳመን ከባድ ነበር፡፡ የቅናሽ ካርድ ሲተዋወቅ ከተቋሞች ባለቤቶች በተጨማሪ ሠራተኞቻቸው ግንዛቤው እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች ቅናሽ ስለሚያደርጉበት ቀንና ሰዓት ለካርዱ ተጠቃሚዎች ግልጽ መረጃ ማስተላለፍም አለባቸው፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች ቅናሽ ሲያደርጉ ለመንግሥት የሚያሳውቁበት መንገድ ከሌለ ቫት ሲቆረጥ አስቸጋሪ ስለሚሆን ጥንቃቄ እንደሚያሻም ያክላል፡፡

ካርዱ የሚገኘው በጅማሮ ደረጃ ቢሆንም ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ተጠቃሚዎችን ቁጥር የማስፋት ዕቅድ እንዳለ ይገልጻል፡፡ የካርድ አገልግሎቶች ለብዙዎች እንግዳ በመሆናቸው በቀላሉ እንደማይለመዱና ለማስፋፋት ጠንካራ እንቅስቃሴ እንደሚጠይቅም ያምናል፡፡ አሁን የቅምሻ ካርድ ላላቸው ግለሰቦች ቅናሽ ከሚያደርጉ ተቋሞችና ግለሰቦች መካከል ሞናርክ ሆቴል፣ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ ሰንበርድ ካፌ፣ ዚሊዮን ፀጉር ቤት፣ ስጦታ ፎቶ፣ ኤርታሌ አስጎብኚ ድርጅት፣ ዲጄ ሳሚና ዲጄ ዊል ይገኙበታል፡፡

ወይዘሮ ልዕልት ፍሬው የካርድ አገልግሎቶችን በብዛት ትጠቀማለች፡፡ ሰዎች እንዳላቸው የቅርበት መጠን የተለያየ ዋጋ የሚያወጣ የስጦታ ካርድ ካርድ ትሰጣለች፡፡ የቅናሽ አገልግሎት የምታገኝባቸው የካርድ አገልግሎቶችም ቢስፋፉ ደስተኛ ናት፡፡ አንዳንዶች ለስጦታ ተጨንቆ አንዳች ነገር መግዛት ተቀባዩን ያረካል ቢሏትም አትስማማም፡፡ ‹‹ሰዎች የስጦታ ዋጋ አይጠየቅም ይላሉ፡፡ ስለዚህም የስጦታ ካርድ የተወሰነ ገንዘብ መጠን በመያዙ ደስተኛ ላይሆኑ ይችላሉ፤›› ትላለች፡፡ እሷ ዘመናዊና ቀላል መንገድ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

ተቋሞች ለደንኞቻቸው የቅናሽ ወይም የአባልነት ካርድ ሲያዘጋጁ፣ ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን ትልቅ ቦታ ያሳያታል፡፡ ከእያንዳንዱ አገልግሎት መጠነኛ ቅናሽ ቢገኝ፣ ሸማቾች አትራፊ ይሆናሉም ትላለች፡፡ የካርድ አገልግሎት ካለው ጥቅም አንፃር ተገልጋዮች ውስን እንደሆኑም ታነሳለች፡፡ ሐሳቡ የበለጠ መተዋወቅና ከከተማ ቀመስ አካባቢዎች መዝለል እንዳለበትም ታምናለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...