Friday, September 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገርን ለማዳን መፍትሔ የሚገኘው በመነጋገር ብቻ ነው!

በ2009 ዓ.ም. በጥይት መግደልም መሞትም ማብቃት አለበት፡፡ እሳት የሚተፉ ጠመንጃዎች የሚያዘቀዝቁበት፣ የሕዝብ አጀንዳ ያነገቡ ሰላማዊ ሠልፎች የሰላም ምልክት የሆነው  ዘንባባ ዝንጣፊ የሚታይባቸው፣ አላስፈላጊ የሆኑ የተቋጠሩ ቂሞችና ጥላቻዎች ተወግደው ለውይይትና ለድርድር የሚረዳ ሰላማዊ ድባብ የሚፈጠርበት ዓመት መሆን ይኖርበታል፡፡ ካለፉት የጭቅንና የመከራ ትዝታዎች ውስጥ በመውጣት ለብሔራዊ መግባባት ራስን ማዘጋጀትና ብሎም ሒደቱን መጀመር የመላ ኢትዮጵያውያን ድርሻ የሚሆንበት የአዲስ ዓመት ጅማሮ ላይ ነን፡፡ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን በአገሪቱ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ላይ በግልጽነት ለመነጋገር መነሳት የግድ ይላል፡፡ አገሪቱን የሚመራው ገዥው ፓርቲም ሆነ በተቃውሞው ጎራ ውስጥ ያሉ ወገኖች በአገሪቱ የፖቲካ ምኅዳር ውስጥ ያለውን የተበላሸ ግኙነት ወደ ጎን በማለት፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብርና ህልውና ሲሉ በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር አለባቸው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች በተሟላ መንገድ ምላሽ የሚያገኙት ሁሉንም ወገን በጋራ የሚያስማማ መፍትሔ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ጤናማ አልባው ፖለቲካ የሚድነው ተቃራኒ ሐሳቦች በነፃነት የሚፋተጉበት ምኅዳር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁጭ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡

በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ ተሁኖ የመልካም ምኞት መግለጫ ከመለዋወጥ ባሻገር፣ በአገርና በሕዝብ ላይ የተደቀኑ አደጋዎች እንዴት እንደሚወገዱ የጋራ መግባባት መፍጠር የሚያስችል መድረክ መፈጠር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በመጀመርያ ዕውቅና መሰጣጠት ያስፈልጋል፡፡ አንዱ የአገር ታሪካዊ ባለአደራ ሌላው አገር አፍራሽ እንደሆነ ተደርጎ መፈረጅ ጊዜ ያለፈበት ከመሆኑም በላይ ለማንም አይበጅም፡፡ ከፖለቲካ ሥልጣንና ከሚሰጠው ጥቅም በላይ ሊያሳስብ የሚገባው የአገር ጉዳይ ነው፡፡ ቅራኔው ገጽታውን እየቀያየረ በጦዘ ቁጥር የሚጎዳው ሕዝብ ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በ2008 ዓ.ም. በርካታ ዜጎች ሞተዋል፣ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱም ሆነ በመላ ሕዝቧ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ ለውይይትና ለድርድር አልመች ያለው በቂም በቀል የተሞላው የፖለቲካ ምኅዳር መሪ አልባ አመፆችን እየቀሰቀሰ የሰው ሕይወት እየጠፋ፣ ለሰላማዊ ውይይት አለመዘጋጀት በታሪክ ያስጠይቃል፡፡

አሁን የሚታየውን ውጥረት በማርገብና ለሰላማዊ ውይይት አመቺ ሁኔታዎችን የመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ኃላፊነት በሌሎች ወገኖች ካልተደገፈ የሚፈለገው ሰላም አይመጣም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሐሳብ ልዩነትን እንደ ፀጋ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ የጠቡንና የግጭቱን ጎዳና በመታው በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጫ መስጠት አለባቸው፡፡ ለመፍትሔ የማይበጁና ጠላትነትን የበለጠ የሚያጋግሉ ፉከራዎችና ቀረርቶዎች ተወግደው ሥልጡን በሆነ መንገድ ልዩነትን ይዞ ለመነጋገር መትጋት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ሰላማዊው መንገድ ተዘጋግቶ አገሪቱ በደም እንድትጨቀይ የሚፈልጉ ኃይሎች ይታያሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ፈጽሞ ሊቆጣጠሩት የማይችሉትን ግጭት አስነስተው አገሪቱን በደም ለመለወስ ጥረት ሲያደርጉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ወገኖች ግንባር ቀደም በመሆን ለሰላማዊ ውይይት  ፋና ወጊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም መባል አለበት፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን የሚሆነው በሠለጠነ መንገድ በመነጋገር እንጂ ከጠመንጃ ቃታ አይደለም፡፡

መንግሥትም ሆነ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚታገሉ ወገኖች ካላስፈላጊ እሰጥ አገባ ወጥተው ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ንግግር ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት ሸፍጥ የበዛበት የፖለቲካ ቁማር ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ የሕዝብን ፍላጎትም አይወክልም፡፡ በሸፍጥና በአጭበርባሪነት ላይ ብቻ የተመሠረተ የፖለቲካ ቁማር ውጤቱ ግጭትና የእርስ በርስ መፋጀት ነው፡፡ ነገር ግን በሠለጠነ መንገድ በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ልዩነትን ይዞ መነጋገር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት የሚጥሉ መፍትሔዎችን በመፈለግ ሕዝብን ያረጋጋል፡፡ አገርን ከጭንቀት ያወጣል፡፡ ቅድመ ሁኔታዎችን እያስቀመጡ ለሰላም መሰናክል መሆንም ለአገር አይበጅም፡፡ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከተፈለገ ለመነጋገር መቀራረቡ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ የሰላሙ መንገድ በተገፋ ቁጥር የጠመንጃ ተኩስ ይቀጥላል፡፡ ዕልቂትም እንዲሁ፡፡ ይህ ለዚህ ዘመን የማይመጥን መግደልና መሞት ሕዝብን ከማሸበርና አገርን ትርምስ ውስጥ ከመክተት ውጪ ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በጥልቀት በመታደስ ለአገሪቱ ዙሪያ ገብ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ቃል ገብቷል፡፡ ይህ የተገባ ቃል በተግባር ካልተደገፈ ዋጋ የለውም፡፡ በመጀመርያ ገዥው ፓርቲ ራሱን ማጥራት አለበት፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ህልውና የሚተጉ አባላቱን ከራስ ወዳዶችና ከፀረ ዴሞክራሲዎቹ ሊለይ ይገባል፡፡ ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ‹እምቢ ላለ ሰው ጥይት አጉርሰው› የሚሉና ለሰላማዊ ውይይት በሩን የሚዘጉ የራሱን ሰዎች እንዲበቃቸው ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ችግሮች መኖራቸውን እያመኑ በማድበስበስ ግምገማና በሸፍጥ በማለፍ መጠጋገን የሚፈልጉ ለአገርና ለሕዝብ ስለማይጠቅሙ ገለል ቢደረጉ ይመረጣል፡፡ ራስ ወዳዶችና ሙሰኞች የለውጡ አካል መሆን አይችሉም፡፡ አሁን ሁሉንም ነገር በነበረበት ማስቀጠል ፈፅሞ አይቻልም፡፡ የሌላውን ልሳን እየዘጉ የራስን ብቻ ማግነን የሕመም ምልክት ነው፡፡ በጥልቀት መታደስ ማለት የነበረውን ማስቀጠል ሳይሆን ለለውጥ ዝግጁ መሆን ነው፡፡ ይህ ለውጥ ለአገሪቱ ጠቃሚ በመሆኑና የተጋረጡ ሥጋቶችን ለማስወገድ የሚረዳ ስለሆነ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ ከተፎካካሪዎች ጋር መደራደርም ሆነ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መምከር የሽንፈት ምልክት መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለዘላቂ የአገር ጥቅም የሚከፈል መስዕዋትነት እንደሆነ ማመን ተገቢ ነው፡፡ ከአገር በላይ ምንም የለም፡፡

በተቃውሞ ጎራ የተሠለፉ ኃይሎችም አገርንና የፖለቲካ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ አጀንዳ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተወደደም ተጠላም ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ በቂምና በጥላቻ የተለወሱ የዓመታት ቁርሾዎችን ገለል በማድረግ ለሥልጡን ፖለቲካ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ፈፅሞ ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ነገር ግን በተሳሳተ አቅጣጫ ከሄደ አገር የሚያጠፋ አደጋ አለ፡፡ ይህንን ሥጋት በመጋራት በኃላፊነት ስሜት ራሳቸውን ለሰላማዊ ሒደት ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዓመታት ከሚቋሰሉት ኢሕአዴግ ጋር ባላቸው ቁርሾ ምክንያት ኢሕአዴግን በመፍትሔ አካልነት ያለመቀበል ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች፣ በያዙት አቋም ገፍተው የሚቀጥሉ ከሆነ የማይወጡት ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ አንድም አገር እንድትፈራርስ የሚያደርግ አፍራሽ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠር የበኩላቸውን ሚና መጫወት የማይችሉ ደካሞች መሆናቸው ይረጋገጣል፡፡ ከዚያ አልፎ ተርፎም የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶችን ፍላጎት እያወቁም ሆነ ሳያውቁ አስፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ሳቢያ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ይፈጽማሉ፡፡ በመሆኑም ለሥልጡን ፖለቲካ ራሳቸውን ያስገዙ፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን መንታ መንገድ ላይ ቆማ እያለች ዝም ብሎ ማየት ማንንም ቢሆን ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ሕዝብ እየሞተ፣ የአካል ጉዳት እየደረሰበትና የአገር ሀብት እየወደመ በነበረበት መቀጠል አይቻልም፡፡ በሥጋት ውስጥ መኖር ማብቃት አለበት፡፡ በዚህ አዲስ ዓመት አሮጌና ኋላቀር አስተሳሰቦች ለአገሪቱ አይመጥኑም፡፡ አገሪቱን ከማፍረስና ሕዝቡን ለዕልቂት ከመዳረግ የማይመለሱ ፅንፍ የረገጡ አስተሳሰቦች መርገብ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ ውይይት መቅደም አለበት፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነት፣ እኩልነት፣ ነፃነትና ብልፅግና የሚኖሩት ለአገር የሚበጁ አስተሳሰቦች በእኩልነት ሲንሸራሸሩ ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎች ሲደመጡ ነው፡፡ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ለሕዝብ ጥቅም ሲቆሙና እሳት የሚተፉ ጠመንጃዎች መተኮስ ሲያቆሙ ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ቀርበው አጥጋቢ ምላሽ ሲያገኙ ነው፡፡ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ በቀጥታ ወይም በትክክለኛ ወኪሎቻቸው ሲሳተፉ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚባለውን ትልቁን ምሥል እያደበዘዙ በሰላምና በፍቅር ለዘመናት የኖረን ሕዝብ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በመሳሰሉት መከፋፈል ነውር ነው፡፡ በዚህች አገር ልዩነትን እያከበሩ ከመኖር ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖር አይገባም፡፡ በዚህ በያዝነው አዲስ ዓመት በጥይት መግደልም ሆነ መሞት መቆም አለበት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረቱ ይጣል፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለውይይት ይዘጋጁ፡፡ አገርን የማዳን መፍትሔ የሚገኘው በመነጋገር ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...