Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየዴሞክራሲ ለውጥ የጠማው ልማት

የዴሞክራሲ ለውጥ የጠማው ልማት

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

 “የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሻው ሰላምንና የልማቱን መቀጠል ነው… ወዘተ፣ ወዘተ” በሀተታና “የሕዝብ አስተያየት” በሚባል ፈሊጥ መወትወት የዕለት ቀለብ ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ይህን ያህል የሚባልለት ልማት ምን ያህል የዕለት ሕይወታችንን ነክቷል? የግል ንፅህና ጉድለት ለአገራችን አዲስ አይደለም፡፡ ውኃ ሳያፈሉ መጠጣት የኖረ ልማድ ነው፡፡ የመንደር እርድ የዛሬውን አያድርገውና የኑሮ ውድነት ሳያሸንፈን በፊት ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር በሽበሽ ነበር፡፡ በግ ቢቀር በየሠፈሩ ቅርጫ የማያስገባ አልነበረም፡፡ ክረምትና ጎርፍም ኢሕአዴግ ከመጣ በኋላ የመጡ አይደሉም፡፡ አተት (ኮሌራ) ግን ከዓመት ዓመት የሚያስጨንቅ ሥጋት በፊት አልነበረም፡፡ አሁን ግን በልማቱ ዘመን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ፣ ሥጋት  ሆኗል፡፡ ለምን?

በገፍ እስረኛ በሚታጎርባቸው ካምፖች፣ ስደተኛና የረሃብ ተጠቂዎች በሚከማቹባቸው የመጠለያ ሠፈሮች ውስጥ የጤናማ ውኃ እጥረት፣ የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ችግሮችና የትፍግፍግ ኑሮ ስለሚኖሩ የአተት ወረርሽኝ አደጋም አብሮ ይኖራል፡፡ ይህ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረና የታወቀ ነው፡፡ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ጊዜ ሰው ይጠርግ የነበረው ጥይትና ፈንጂ ብቻ አልነበረም፣ አተትም ነበር፡፡ ሄይቲ የከፋ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዳልነበረች ካደረጋት በኋላ፣ እስከ ዛሬ ድረስ የመሠረተ ልማት አውታራት በተጓደሉበት የትርክምክም ኑሮ ውስጥ ስለምትዳክር አተት ከዓመት ዓመት ያደቃታል፡፡

የሄይቲንና የመጠለያ ጣቢያን የመሰለ ለአተት የሚያጋልጥ ጣጣ በልማታችን ዘመን መባዛቱን አንድ ሁለት ብዬ ላስረዳ፡፡

 1. አዲስ አበባ ወደ ገጠር እየሰፋች ይህ ሁሉ ቤት ሲገጠገጥባትና የሕዝብ ቁጥሯ እየጋሸበ ሲሄድ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘመናዊ አውታር ዝርጋታ ጉዳይ አብሮ ስላልመጣ፣ ኢሕአዴግም ሥልጣን ከያዘ ወዲህ የፍሳሽ ሥርዓት ዝርጋታ ከአዲስ አበባ መልሶ ግንባታ ጋር የማይነጠል፣ ፍሳሿ ከራሷ አልፎ ለሌላም የሚተርፍ ትልቅ ችግር መሆኑን ስላላጤነው፣ ሌሎች እንደ አዲስ አበባ እየተስፋፉና እየታደሱ ያሉ ከተሞችም በካይ ባልሆነ የፍሳሽ ሥርዓት ላይ ስላልሠሩ፣ የፍሳሽ ቆሻሻ ለአተት አጋላጭ ነቀርሳ ሊሆን ችሏል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ካሉትና ከሚሠሩት ቤቶች መሀል የማያሳልፍ ጉድጓድ ገንብተው ሲሞላ የሚያስመጥጡ እጅግ ውስን ናቸው፡፡ ውስን መሆናቸውም አይደንቅም፡፡ ለማስመጠጥ ያለው አበሳ! (ሳይሞላ ሞላ ብሎ ወይም ጠጣር ነገር ቱቦ ውስጥ ገባ ብሎ ጉርሻ ለመገሽለጥም ሆነ ባልሞላ ገንዳ ተባራሪ ሥራ ለመሥራት የሚፈጠረውን ውዝግብ የደረሰበት ያውቀዋል፡፡) አንዳንዶቹ የገነቡት ጉድጓድ ባለክፍተቶች እንዲሆን አድርገው ወይም በበሃ ድንጋይ ጉድጓዱን ገንብተው ፍሳሽ እያዠ ወደ መሬት እንዲገባ ወይም እንዲሄድ ያደርጋሉ፡፡ ከጉድጓዱ በአንድ ግድግዳ በኩል ቱቦ ዘርግቶ ፍሳሽን ከከርሰ ምድር አፈር ጋር ማገናኘትም የዚህ ዘዴ ሌላ ቅርፅ ነው፡፡ ከዚህ ዓይነት ዘዴዎች ውስጥ “የሠለጠነው” ዘዴ ደግሞ፣ በጉድጓድ የሚገባውን ፍሳሽ በተወሰነ ከፍታ ላይ እየተቆጣጠሩ ዝናብ ጠብ ሲል በግልጽ ወይም በስውር ቱቦ መሸኘት ነው፡፡ ይህንንም የሚያስንቅ ሌላ ዘዴ አለ፡፡ የፍሳሽ ቆሻሻው በደንብ ጠሎና ንፁህ መስሎ ያለማቋረጥ የመንገድ ፍሳሽ መቀበያ ቱቦዎችንና መስኮችን እንዲመግብ የማድረግ ዘዴ፡፡ ወንዝ ዳር ላይ የተንጣለለ ሽንት ቤት መሥራት አብሮን ያረጀ ዘዴ ነው፡፡

ይህን በመሳሰለው የፍሳሽ አወጋገድ ዘይቤ ግለሰቦችን፣ የቤት ማኅበራትን ወይም መንግሥትን እከሌ ከእከሌ ብሎ መለየት አይቻልም፡፡ ገርጂ በመንግሥት ከተሠሩ ነጫጭ ቤቶችና በማኅበር ከተሠሩ የቁጠባ ቤቶች በቱቦ የሚወጣ ፍሳሽ ውስጥ ለውስጥ ሄዶና የፀዳ መስሎ ዲቦራ ትምህርት ቤት አካባቢ ያለን ሜዳ ሲያለመልም ኖሯል፡፡ በቧንቧ ውኃ የሚገለገሉ አነስተኛ መኪና አጣቢዎች ከመፈጠራቸውም በፊት መልኩን ያሳመረ የሽንት ቤት ፍሳሽ ለመኪና ማጠቢያ የድርሻውን ውኃ ሲያዋጣ ኖሯል፣ በገርጂም በሌሎች ሥፍራዎችም፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን የተሠሩ የጋራ ቤቶችም ፍሳሽ፣ በአዲስ አበባ እንደሚታየው ቢበዛ በቱቦ ወደ ወንዝ አካባቢ ተወስዶ እዚያ ግድም በተሠሩ ጉድጓዶች ውስጥ ከመግባት ያለፈ ማከሚያ የሌላቸው መሆኑን አንድ ሁለት ብሎ ማሳየት ይቻላል፡፡

በየትም ሥፍራ ወደ መሬት ውስጥ የገባ የሽንት ቤት ፍሳሽ ወደ ውስጥ ሰርጎ የከርሰ ምድር ውኃን/የጠበል ውኃን መበከል አንዱ ጥፋቱ ነው፡፡ ውስጥ ለውስጥ በሥርገት ተጉዞ ከወንዝ ጋር መገናኘት ሌላ መንገዱ ነው፡፡ ከዳገትማ መኖሪያ ሠፈሮች ወደ መሬት የገባ ፍሳሽ ውስጥ ለውስጥ “እየጠራ” ሄዶ ሄዶ ቁልቁለታማ ወይም ሜዳማ ሥፍራ ላይ መልካም ምንጭ መስሎ ይፈልቃል፡፡ ያልጠረጠረም ለብዙ ነገር ያውለዋል፡፡ በመሬት ውስጥ በተቀበረ ቱቦ የሚያመሩ የኮንዶሚኒየም ፍሳሾች የላይ ክዳን ፈንቅለው ወደ ላይ ሲንፎለፎሉ እንደሚያጋጥሙ ሁሉ፣ ከመንገድ ቱቦዎች ጋር የተገናኙ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሾችም ቱቦ ውስጥ የታጎረ ደረቅ ቆሻሻ መሄጃ ሲከለክላቸው ወደ ውጭ ወጥተው የአስፋልት ተጓዥ ይሆናሉ፡፡ አዲስ አበባ፣ ወደ ጎሮ ትምህርት ቤት መገንጠያ ላይ በጋ ከክረምት ከጉድጓድ እየወጣ ያለማቋረጥ በአስፋልት ጥግ የሚፈስ የመፀዳጃ ቤት መልከ መልካም ፍሳሽ አለ፡፡ ይህ የጎሮ ብቻ ገመና አይደለም፡፡

 1. ከዚህ ሌላ በጥልቀት ያልተቀበረ ወይም ጥንካሬ የሚያንሰውና መንገድ የሚያቋርጥ የውኃ መስመር በየሠፈሩ በሚገባ ከባድ ተሽከርካሪ እየተሰበረ በየጊዜው የመጠጥ ውኃ ከላይም ሆነ ከመሬት ሥር ከፍሳሽና ከሌላ ቆሻሻ ጋር ለመላላስ ይጋለጣል፡፡ ከዚህ በባሰ ደረጃ ደግሞ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የሚካሄደው የመንገድ ግንባታ የሚያለማውን ያህል ያጠፋል፡፡ ቧንቧዎች ይሰበራሉ (የሚጠገኑት ከላይ ሊታዩ የቻሉት ብቻ መሆናቸውን ልብ በሉ!)፡፡ ቤቶች ለመልሶ ግንባታ ሲፈርሱ የሽንት ቤት ጉድጓዶች እየተመጠጡ ጤናማ በሆነ መንገድ እንዲወገዱ አለመደረጉና ግንባታ ቶሎ አለመጀመሩ የሽንት ቤት ፍሳሾች ከዝናብ ወቅት ጋር እንዲገናኙ ዕድል ይሰጣል፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚገርመው ደግሞ፣ ሰውና መኪና ደህና ይገለገልበት የነበረ መንገድን የዝናብ ወቅት ሊመጣ ሲል ለማደስም ሆነ አስፋልት ለማድረግ ተብሎ አርሶና ፈነቃቅሎ፣ የቱቦ ጉድጓዶችን በገረጋንቲና በአፈር አስተጓጉሎ የሚተውበት ብልሹ ልማድ ሃይ ባይ ማጣቱ!! እንዲህ የተተው መንገዶች ሳይጠናቀቁ የዝናብ ወቅት የሚመጣበትና እንደገና ሌላ የዝናብ ወቅት እስኪቃረብ ድረስ ተዘንግተው የሚቆዩበት ጊዜ ሁሉ አለ፡፡ እንዲያውም ከሠፈር ሠፈር የሚደጋገምና አቤት ቢባልና ቢተችም የማይወገድ እንደመሆኑ በመመርያ የሚካሄድ መስሏል፡፡

እነዚህን በመሳሰሉ ሁኔታዎች የተስተጓጎሉ ቱቦች የሚተፏቸው ፍሳሾች፣ በየቦታው የሚመነጩትም ሆኑ ከቤት የሚለቀቁትና በየፍርስራሽ ውስጥ ተሸፋፍነው ዝናብ የሚጠብቁት ፍሳሾች በጎርፍ እየታፈሱ ለየሠፈሩ ይከፋፈላሉ፡፡ በተሰበሩና በላሉ ቧንቧዎች በኩል ጎርፍ ብክለትን ለመጠጥ ውኃ ይመግባል፡፡ ላዩን ሲያዩት ደህና ከሚመስል የጎርፍና የፍሳሽ ቅሪት ጋር ጫማ ይነካካል፡፡ እጅ ጫማን ይነካል፡፡ እጅ ጎርፍ ያናጠረበትን የየአጥር ሥር አፈርና አረም ይነካል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ንክኪ በመጨባበጥ ከሰው ወደ ሰው የሚሸጋገርበትም ዕድል አለው፡፡ ከመብል ውጪ ሳይታወቅ እጅ ወደ አፍና ወደ ጥርስ ይሄዳል፡፡ በመጠጥ ቧንቧ በኩል የገባ የፍሳሽ ብክለት ጤነኛ መስሎ ወደ ሆድ ይገባል፡፡ በሌላ ወገን የቤትና የፋብሪካ ፍሳሾች በየወንዙ እያቆራረጡ ወደ ገጠር ይዘምታሉ፡፡ ይህንን የመሰለው መግቻ ሥርዓት ያላገኘ የበሽታ አዘማመት በድንገተኛ አደጋ የተመታ አካባቢ ውስጥ ወይም የስደተኛ ሠፈር ውስጥ ከሚያጋጥም የተስቦ ተጋላጭነት በምን ይለያል?!

 1. በአዲስ አበባና በዙሪያው ፍሳሽ እየመነጨ በሚያለመልማቸው ሜዳዎች፣ በቤትና በፋብሪካ ፍሳሽ በተበከሉ የወንዝ ዳርቻዎች ላይ የሚካሄዱ የመብል አትክልት ልማቶች ከአተትና ከሌሎች የጤና ጉዳቶች ጋር ያላቸው ተያያዥነትስ ትኩረት አግኝቷል? ለመሆኑ ወንዞቻችን የሚያዘዋውሩት የቤትና የፋብሪካ ፍሳሽ ብክለት የሚያቆመው የትኛው ርቀት ላይ ነው? አሁን ስለአተት አጣዳፊ ችግር በሚወራበት ጊዜ መልኩ ባማረ የፍሳሽ ውኃ የሚለሙ የጎመንና የሰላጣ መደቦች አዲስ አበባ መሀል ውስጥ የሉም? ለመሆኑ በተመረዘ ውኃ የሚለማ አትክልት የሚያስከትለው የጤና ጉዳት ሁሉ አብስሎ በመብላት የሚገላገሉት ነው?

ባልተመረዘ ውኃና ሥፍራ የተመረተውስ አትክልት ፍራፍሬ ቢሆን ከእርሻ ለቅሞ፣ አሰባስቦ፣ አጓጉዞ፣ አውርዶ ለተጠቃሚ እስከ ማቅረብ ድረስ ለአተት የሚያጋልጥ የአያያዝ ችግር የለበትም? ሩቅ ሳይኬድ አትክልትና ፍራፍሬ ከመኪና ሲወርድና የነጋዴዎች የሽያጭ ገበታ ላይ ሲደርደር ምን ያህሉ የመንገድ ጉድፍና ፍሳሽ መውረጃ ላይ እየተንከባለለ እንደሚነሳ ማየት በቂ ነው፡፡ ገዢ ለመማረክ ብሎ የመጨረሻው ቸርቻሪ የሚደረድርበት ቄንጥ (መጠበቂያ የሌለውና በቀላሉ ተንዶ ሊወድቅ የሚችልበት) መታረም ያለበት ነው፡፡ ያንን ያስተዋለና በመውደቅ ጊዜ በማጠብ ብቻ የማያመልጡት የመበሳትና የመጋጥ ጉዳት ሊያጋጥም መቻሉን የተገነዘበ በላተኛ፣ ጠንካራ ቅርፊት ካለው ዱባ ዱብዬ በቀር ሌላውስ ይቅርብኝ ቢል አይደንቅም፡፡ ጉልት ውስጥ ስላለው የአትክልት አያያዝ ዝም ይሻላል፡፡ የጥሬ ሥጋና የዓሳ ንግድ ውስጥ ያለው ሁኔታ ለብቻው የሚወራ ነው፡፡

ሌላ ችግር ላንሳ፡፡ የሞቀሞቀና የብልሽት ጣዕምና ጠረን የጀማመረው ፍራፍሬ ሌላውን ሳይበክል ተለቅሞ የሚወገድበት ወይም ወደ ሌላ ቅንብር የሚለወጥበት ባህል በአገራችን አለ? የተለመደው ማስወገጃ መንገድ መለስ ያለውን ብልሹ፣ ከደህነኛ ጋር እየቀላቀሉ ለገዢ መሸጥና የገንዘብ ኪሳራን ወደ ገዢ ማስተላለፍ (የጤና ኪሳራን ጨምሮ)፤ የባሰበትን ብልሹ ደግሞ በሳጥን ሰብስቦ መንገድ ዳር ጎልተው ለሚቸረችሩ መሸጥ መሆኑ ይካዳል? እንዲህ ባለው ነውረኛ ንግድ የሚከተለውስ የጤና መመረዝ ብልሹውን በተመገቡ ግለሰቦች ላይ ያቆማል?

 1. በዚህ ሁሉ ላይ፣ በአጠቃላይ ኅብረተሰባችን ውስጥ የተንሰራፋውን የጨዋነት መላሸቅና መደንዘዝ ስንጨምርበት ህልውናችንን አስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ አንገት የገባ ሸምቀቆ እየሳቡ ራስን በራስ ከማነቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ፣ ራስ ወዳድነት ራስንም በማያስጥል ቂልነት ክፉኛ ተጠምዷል፡፡ ከወትሮ ጊዜ እስከ ዓውደ ዓመት ድረስ፣ በየመንገዱና በየአጥሩ ሥር ቆሻሻ የመጣሉ ነውረኝት ከሰው ግቢ ገብቶ መፀዳዳት ለመጀመር ትንሽ ነው የቀረው፡፡ ፅዳት ማለት ቆሻሻን ከግቢ ገፍቶ ማውጣት አድርጎ እስከ ማሰብ ድረስ አስተዋይነት ብሌኑ ጠፍቷል፡፡ ይህ በግል ንግድም ሆነ በመንግሥታዊ የሕዝብ አገልግሎት ሥራ ውስጥ ምን ያህል የደንታ ማጣት እንዳለም በተዘዋዋሪ ይጠቁሙናል፡፡ እዚህ ውስጥ ደግሞ፣ የአገልግሎት ቤቶችን ጤናማነት የሚመለከተው የፅዳት ተከታታይ ቁጥጥርና የመጠጥ ውኃ አገልግሎት አስተማማኝ ሕክምና ጉዳይ ሁሉ አለ፡፡

ከመሥሪያ ቤት እስከ ሠፈር የተዘረጋው የአምስት ለአንድና የሬዲዮ የቴሌቪዥኑ የፕሮፓጋዳ ንዝንዝ ከማስመረሩ የተነሳ በመንገድ አካባቢ ስለአተት ጥንቃቄ የሚሰጥ ትምህርትን እንኳ “ወደዚያ ተወን!!” ብሎ ጥሎ እስከመሄድ አድርሷል፡፡ ለፕሮፓጋንዳ የተዘጋ ጆሮና ልቦና አተትን የመሰለ አጣዳፊ የጥንቃቄ መልዕክትን በቅጡ ለማስተዋል ቢለግም አይደንቅም፡፡ በዚያ ላይ የሚያራውጠው የኑሮ ትግል ቀልብ ያሳጣል፡፡ ይህንን ሁኔታ አገናዝቦ አተት ገና ገብቶ ጥቃቱን ሲያበዛ፣ መንግሥት እንዳያሳጣ ብሎ ከመደባበቅ ይልቅ ፍጥነቱን ከነታማሚ ብዛቱ ለሕዝብ ማሳወቅ የሕዝብን ጆሮና የጥንቃቄ ደመ ነፍስ ከምንም ነገር (የጥንቃቄ ተግባሮችን በማስታወቂያ መልክ ሺሕ ጊዜ ከማነብነብ ሁሉ) በላይ የሚያነቃ መሆኑ ታውቆ ያልተሠራበት መሆኑም ያስተዛዝባል፡፡ (በእኛ አገር የድብቅነት ፅናት፣ የአተትን እውነተኛ የጥቃት ደረጃና ስፋት እነ ዩኒሴፍ እንኳ እቅጩን ስለማወቃቸው እጠራጠራለሁ፡፡)

እንቀጥል፡፡ በከተማና በገጠር በአምስት ለአንድ መዋቅርም ሆነ በሌላ መልክ ሲካሄድ የኖረው የልማት ሥራ በሰው ልማት ላይ መሠረታዊውን የግል ጤና አጠባበቅ እንኳ መትከል አልቻለም፡፡ የገጠር ልማቱ ከቀላል መፀዳጃ ቤት ጋር ቀላሏን ተንጠልጣይ የገላ መታጠቢያን አጎዳኝቶ ማስለመድ ተስኖት፣ ጭራሽ ሌሊት ለብሰው ያደሩትን ለቀን መገልገልን፣ ላብ የያዘ ልብስን ከታጠበ ጋር አጅሎ ማስቀመጥንና የታጀለ ልብስን መጠቀምን ማስወገድ እንኳ ከብዶት ዛሬም ድረስ ጠረን የገጠሬ መለያ እንደሆነ ነው፡፡ ጠረን ሽው ሲለው የአውቶብስ መስኮት ለመክፈት የሚሮጠው የከተሜ ግብዝ ሁሉ ደግሞ፣ ይኸው እስከ ዛሬ በመገናኛ ብዙኃን ቢባል ቢባል የእነ ነቀርሳና የእነ እንፍሌዌንዛ በሽታዎችን ለመፍራትና የአውቶብስ መስኮት መክፈትን ባህሉ ለማድረግ አልቻለም፡፡ ጨለምተኛ ነህ አትበሉኝና አሁን ባለው ሁኔታ “ከመብል በፊትና ከመፀዳዳት በኋላ በደንብ ታጠቡ፣ እጅግ ብዙ ሰው የሚነካውን ነገር (ለምሳሌ የአውቶቡስና የባቡር መያዣ ብረት) ጨብጣችሁ ቆይታችሁ ጣት ወደ አፋችሁ አታስገቡ … ወዘተ፣ ወዘተ” ተብሎ ቢወተውት እንኳ፣ የአተት ጥቃት ካለፈ በኋላ የቀድሞው ቸልተኛ የኑሮ ልማድ ውስጥ የሚነከር ብዙ ነው፡፡

እና ምንድነው ተስፋችን? በአጠቃላይ የመደንዘዝና የሆድ መባስ ሁኔታ ውስጥ ሆነን በሽታ ሲመጣ ወደ ሐኪም መሮጥ፣ ከዓመት ወደ ዓመት የዝናብ ወቅት መጣሁ ሲል የአተት በሽታን እየሰጉ መኖር መቀጠል አለብን? ጥሬ ሥጋ አለመብላት፣ ጥሬ አትክልትና ፍራፍሬ አለመብላት፣ የፍራፍሬ ጭማቂን መሸሽ፣ የቧንቧ ውኃን ጭምር እንደገና አክሞ ወይም አፍልቶ መጠጣት ዘለቄታ መፍትሔ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው? ዘላቂው መፍትሔ፡-

 • የመኖሪያ ቤትና የኢንዱስትሪዎች ፍሳሾች የከተማና የገጠር አካባቢዎችን መበከላቸውን የሚገታ የፍሳሽ አቀባበልና አወጋገድ  አውታር መዘርጋት ነው፣
 • በዚህም አማካይነት ወንዞችንና የወንዝ ዳር እርሻዎችን ከብክለት ነፃ ማውጣት ነው፣
 • የዓሳ፣ የሥጋ፣ የአትክልት ጥሬ ምርቶች እስከ ችርቻሮ ድረስ ባሉ ቅጥልጥል እርከኖች ሁሉ ጤናማነትን በሚያስተማምን ጥራትና ደረጃ የሚተላለፉበትን ሥርዓትና ባህል መገንባት ነው፣
 • አፍርሶ የመገንባትም ሆነ የማደስ ሥራዎች ለሰውና ለአካባቢ የሚተርፍ ብክለት እንዳያስከትሉ ሥርዓት ማስያዝ ነው፣
 • የመንገዶችና የሕንፃዎች ግንባታዎች ማፍረስ መደረትን እየመላለሰ ከሚያመጣ አዙሪት የሚላቀቁበትን ዘላቂ ዲዛይን እንዲያገኙ ማድረግ፣ በግንባታቸውም ረገድ ያልተዋከበ ግን ዘገምተኛ ያልሆነ፣ ቅልጥፍናንና ልቅም አድርጎ መሥራትን ያገናኘና እዚያም እዚያም ለኮፍ እያደረጉ መተውን ያስቀረ የሥራ ባህልን መሠረት ማስያዝ ነው፣
 • የውኃ መስመሮች ከፍሳሽ ቱቦዎችና ከተሸከርካሪዎች ጋር የማይደራረሱበትን አዘረጋግና ደንብ በተግባር ማሠራት ነው፤
 • በገጠርና በከተማ ያለ ጭርንቁሱ የወጣ ኑሮን የሚያነሳ ብስል መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ነው (በዚህ ውስጥ የድሃ ድሆች የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ ቤት ትርጉም ባለው የመቶኛ ድጎማ ሊያገኙ የሚችሉበት መፍትሔ ሁሉ መምጣት አለበት፤ የማይደርቅ የውስጥ ንዋይን ከውጭ ተራድኦ ጋር አጣምሮ በመጠቀም፡፡)
 • ማጠንጠኛው መፍትሔ፣ ይህ ሁሉ ተግባር ለጊዜያዊ ድጋፍ በሚሮጥ የይድረስ ይድረስ ሥራ ሳይውሸለሸል፣ በጠራ ዕቅድ፣ በከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነትና የምግባር ጨዋነት መከናወን የሚችለው፣ መደበቂያ ያሳጣ የፕሮፓጋንዳ ቅጥቀጣ፣ የፖለቲካ አድልኦና ጉንተላ ያኮማተሩትን ቅስምና ሐሞት የሚያነቃ፣ የተደፈነ ጆሮና ልቦናን መልሶ የሚከፍት ፖለቲካዊ ለውጥ ከመጣ ነው፡፡ ይህ ለውጥ ከአፈናና ከፕሮፓጋንዳ ቅጥቀጣ እፎይ ብሎ የዴሞክራሲ ነፃነትን፣ ከአጨበጫቢነት መፈታትንና በሥራ የማደግ መብትን የማጣጣም ምዕራፍ ነው፡፡  ዴሞክራሲን የሚጠይቅ ሰላማዊ ሠልፍና ቅዋሜ ሁሉ ከብጥብጥና ከሁከት ጋር ተሳክሮ እንዲታይ የምትሹ (ነጋ ጠባ “እኛ መንግሥታችን የጀመረው ልማት እንዲቀጥል ነው የምንሻው” እያላችሁ አንካሳውን ልማት ለኢሕአዴግ ገዢነት መስገጃ ለማድረግ የምትለፉ)Anchor ሁሉ ይህንን የመጨረሻ ቁልፍ ነጥብ ልብ በሉ!! ልማቱ ከልግመት፣ ከዝርፊያ፣ ከብክነት ተላቆና የሚያንገበግበውን ከማያንገበግበው አስቀድሞ ለመራመድ ይህን ያህል ፖለቲካዊ ለውጥን በመፍትሔነት ይሻል፡፡ ኅብረተሰቡ በመብቶች ውስጥ መኖር ሲጀምርና በፖለቲካ መንገዋለልና በጥቅም መደለል ዋና ዘይቤነቱ ሲቋረጥ ከደርግ ዘመን ጀምሮ እስካሁን የወረሰን የአድርባይነት ወረርሽኝም ይጠራረጋልና በዚህ ለውጥ የሚጠቀሙት የዛሬ እበላ ባዮችም ናቸው፡፡ ጣፋጩንና ክብር ያለውን በእውነተኛ መንፈስ የመኖር ዕድል ሁሉም ዜጋ ለማጣጣም ዕድል ያገኛል፡፡ መናፈቅ ያለበት ልማት ይህ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...