Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርይድረስ ለአቶ እስማኤል አደም

ይድረስ ለአቶ እስማኤል አደም

ቀን:

መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንዎ እየተመኘሁ፣ ጳጉሜን 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ‹‹ይድረስ ለሚመለከታችሁ የፍትሕ አባላት›› በሚል ርዕስ በሪፖርተር ጋዜጣ ያሰፈሩትን ጽሑፍ በደስታና በአንክሮ ተመልክቼዋለሁ፡፡

አቶ እስማኤል ያቀረቡትን ሐሳብ የማይደግፍ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ ባላስብም በዴሞክራቲክ ዓለም ውስጥ የአንድ ሰው ሐሳብ ብቻ ጥሩ ነው ብለው እንደ ተሸበበ ፈረስ በአንድ አቅጣጫ ሁሉም ይሰለፋሉ ብዬ አላምንም፡፡ ሆኖም ብዙኃኑ ይደግፍዎታል ብዬ አምናለሁ፡፡

ምናልባት ስለ ትምህርት፣ ስለ አገልግሎት፣ ስለ ልምድ በሚወራው አካባቢ ኢትዮጵያውያን ከመንገድ እየራቅን መሄዳችንን ተገንዝበውት ይሆን? እዚህች ላይ ትንሽ ልጠይቅዎት እወዳለሁ፡፡ ይህም በድፍረት ሳይሆን በትህትና ነው፡፡

አንድ አውሮፕላን አብራሪ በመስኩ ስለሠለጠነ ብቻ ካፒቴን ሆኖ ብቻውን አውሮፕላን ይዞ አይበርም፡፡ ከዋናው አብራሪ ጋር ሆኖ እያየ፣ በበረረ መጠን ጊዜውን ጠብቆ ይደርስበታል እንጂ፡፡ አንድ ተማሪ ከዩኒቨርሲቲ ስለወጣ ብቻ በዚያ በሚመለከተው መስክ ዋና ዳኛ፣ ዋና ኢኮኖሚስት፣ ዋና መሐንዲስ፣ ዋና የሒሳብ ሹም፣ መሪ ሐኪም ወይም በመሳሰሉት መስኮች ተሰማርቶ መሥራት በሠለጠኑት አገሮች ያልተለመደና የማይሞከር ነው፡፡ የሥራውንም ፀባይ ስለሚያሳንሱ ያለተሞክሮ የሚጀመሩ አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ደረጃው ዝቅ እያለ እንደመሄዱ መጠን የአሠራሩም የአፈጻጸሙም ሁኔታ እየወረደ መጥቶ አሁን እርስዎ በሚሉት ልክ ከዩኒቨርሲቲ ወጥቶ ለምን ዳኛ አይሆንም የሚሉ ይመስላል፡፡ የሚገርመው ነገር በዱሮ ልማድ ከሆነ አንድ ወጣት አሥራ ሁለተኛ ጨርሶ ወደ አሜሪካ፣ ወደ እንግሊዝና ወደሌሎች አገሮች  እየተላከ እንደነ ኦክስፎርድና ሃርቫርድ ባሉት የትምህርት ተቋማት ገብቶ የሚያስደስት ውጤት በማምጣት፣ አስጠጉኝ ብሎ ሳይለምን በኩሩ ዜጋነቱ የሚመለስበት ዘመን ነበር፡፡

ዛሬ ዛሬማ ራሱን እንኳ በተማረበት ቋንቋ ራሱን ማስተዋወቅ የሚሳነው ተማሪ የተኮለኮለበት ዘመን መሆኑን ይገነዘቡት ይሆን አቶ እስማኤል? በአገራችን ምናልባት የሕግ ትምህርት ክፍል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ 50ዎቹ መጨረሻ ገደማ ፖል በተባሉ የሕግ ምሁር እስከተከፈተበት ድረስ እምብዛም የሕግ ምሁራን ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድና በኋላም ወደ ካናዳ ተልከው ከተማሩት አነስተኛ ቁጥር ካላቸው እንደ አቶ ተሾመ ኃይለ ማርያም፣ እንደ አቶ ተሾመ ገብረ ማርያምና ጥቂት ጓደኞቻቸው ሲሆኑ ብዙዎቹ ከእሰጥ አገባ ባህላችን የተወራረሱ፣ በልምድ የተራቀቁና ፈርኃ እግዚአብሔርን የተላበሱ፣ ፈሪና አክባሪ ከመዝገብ ቤት ጸሐፊነት ሲታሹ ፍርድ ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀው ተገንዝበው በልምድ በስለው የወገናቸውን ብሶት አውቀውና ተገንዝበው እንደ ቴፕ የሰሙትና ብቻ ተመርኩዘው ሳይሆን ሁኔታዎችን አመዛዝነው ትክክለኛ ፍርድን የሚሰጡ እንደ ዛሬ በሚሊዮን ብር የማይታለሉ ጥሩ ዜጐች ባለፉበት የፍርድ ገበታ ነው የዛሬዎቹ በስመ ትምህርት ወደ ከፍታው ወንበር ጉብ የሚሉት፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ከአሥራ ሁለተኛ ክፍል ሄደው ያገኙ የነበረው የዱሮው ክብር ዛሬ ጠፍቶ ከየትኛውም ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ቢላኩ እንኳ መልሰው በአዲስ ጀማሪነት ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ ይህንንም ማየት ቢፈልጉ ከዳኞች፣ ከጠበቆች፣ ከሐኪሞችና ከሌሎች የሙያ ዘርፎች ወደ አሜሪካም ሆነ እንግሊዝ ሄደው በተማሩት መስክ ሥራ ይዘው ውጤት አመጡ የሚሏቸው የዚህ ዘመን ተማሪዎች ካሉ ይግለጹልኝ፡፡ ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሕክምና መስክ ሲማሩ ቆይተው ወደ አሜሪካ ያቀኑ አንዳንዶቹ እኮ የሼሮም ሻራተን በረኛ ወይም ፖርተር ሆነዋል፡፡ እርግጥ ነው ጥረውና ግረው ወደ ሕክምና ትምህርት ቤት ገብተው ሐኪም የሆኑት ወጣቶችን አውቃለሁ፡፡ አማክሬያቸዋለሁም፡፡ ከፈለጉ የደካማ ውጤታማ ወገኖቼን ስም ለመጥራት አልደፍርም እንጂ ቢፈቀድልኝ ላቀርብ እችላለሁ፡፡ ‹‹ነዶ በዛ ፍሬ የለው፤ አጀብ እንጂ ጦር አይገታው›› እንዲሉ ነውና ነገሩ ይታሰብበት፡፡

በአሜሪካም ሆነ በሌሎች በሠለጠኑት አገሮች ከሕግ ትምህርት ቤት የሚወጡ ተማሪዎች ወደ ዳኝነት ከመሄዳቸው በፊት በየፍርድ ቤቱ ተዘዋውረው የሥራ ልምድ ያገኛሉ፡፡ ቀጥሎ የዳኛ ረዳት ጸሐፊ በመሆን ለተወሰነ ጊዜ ይሠራሉ፡፡ ይህንን ሁሉ ካደረጉ በኋላ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን በየዲስትሪክቱ መለስተኛ ፍርድ ቤቶች ተሰይመው ከታዩ በኋላ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ተመድበው ማገልገል ይጀምራሉ እንጂ  ገና ለገና ከዩኒቨርሲቲ ተመርቋል ተብለው የወጣትነት ጊዜያቸውን በተሞክሮ ሳያዳብሩ በቀጥታ ወደ ፍርድ አይሰማሩም፡፡ ትምህርት ላይ ተመክሮ፣ የማስተዋል ልምድና ፈርኃ እግዚአብሔር ተጨምሮበት ነው እንጂ ዝም ብሎ እንደ ቀልድ ዘው የሚባልበት የሰው ሕይወት ቀልድ አልነበረም፡፡

አቶ እስማኤል ስለ ንጉሠ ነገሥታችን ዘመን በአጭሩ እንደዘበት ነካ አድርገው አልፈዋልና ትንሽ ግንዛቤ እንድሰጥዎ ይፍቀዱልኝ፡፡ ለሁላችን ላሞች ባልዋሉበት ኩበት ለቀማ እንዳይሆን ከመሠረቱ እያስረገጥን ብንሄድ ለመጪው ትውልድም ነባሩን ታሪክ እያስጨበጥን መሄዱ ይበጃልና በዘመድ መጠቃቀም ነበር ብለው ፈንጠቅ ያደረጓትን አስረግጬ ለማለፍ እወዳለሁ፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ ዘረኛ፣ ወገንተኛና አድሏዊ ሳይሆኑ ለአገርና ለወገን ታጥቀው የተነሱ ታላቅ መሪ እንደነበሩ ከእነማን ይማሩ? ብለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታጥቀው ተነስተው ትምህርትን ለሁሉ ለማዳረስ የፈለጉና በግብር ያዋሉ በሹመት፣ በዘር፣ በሃይማኖት ሳይሆን በችሎታ ያደላደሉ ታላቅ መሪ እንደነበሩ ከዚህ በታች ላቀርብልዎትና እርስዎና መሰሎችዎ እንዲገነዘቡት ለማድረግ እጥራለሁ፡፡ ጥያቄ ካለዎትም በኢሜል አድራሻዬ [email protected] ይጠይቁኝ፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ ትምህርት ሲያስጀምሩ የመሳፍንት ወይም የመኳንንት ልጆችን መርጠው አልነበረም የጀመሩት፡፡ እንዲያው እንዲመለከቱትና እንዲያመዛዝኑት በማለት የመጀመሪያዎችን ተማሪዎች እንዴት እንደተመረጡና ለቁም ነገር እንደበቁ እንዲያዩትና አስተሳሰብዎን እንዲያስተካክሉ እነኚህን ሰዎች እጠቅሳለሁ፡፡

የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ልጆች መልካም ምሳሌዎች በ1937 ዓ.ም. ሚያዝያ 18 ቀን ባለዘውድ አንበሳ ያለበት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር፣ ጉዳዩ ለተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር የተጻፉ፤

 1. ጥላሁን አባተ
 2. ደምሴ አደፍርሰው
 3. በዛብህ ዓይናለም
 4. ደምሴ አበበ
 5. ተሾመ ገብረ ማርያም
 6. ደነቀ ተሰማ
 7. ጌታቸው ተክለ ማርያም
 8. ሳህሉ አበበ
 9. ሳህለማሪያም የሺነህ

ከብዙዎቹ በጥቂቱ ከያኔው ሲዳሞ ክፍለ አገር ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርገው ለጊዜው ማረፊያ ስለሌላቸው በአዳሪነት እንዲቀበሏቸው በአቶ ክብረት ዓለማየሁ ኃላፊነት የተላኩ ሲሆን ከቦረና 60 ተማሪዎች በማባበልና በግዴታ ጭምር ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንዲማሩ ሲደረግ በዓመቱ ለዕረፍት ሲሄዱ 60 የቅርብ ወገኖቻቸውን ይዘው መጥተው ትምህርት ተምረዋል፡፡ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 120 ተማሪዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ከከፋ

 1. ኪዳኔ አባቀስቶ
 2. ዳንኤል ሾኔ
 3. መንግሥቱ ቀጪ
 4. አገዘ አምደ ጊዮርጊስ
 5. መንግሥቱ ውዶ
 6. ወልደኪዳን ገብሬ
 7. ወልደማርያም ገረዮ
 8. ኃይለማርያም ውዶ
 9. ክፍሌ ገብረሥላሴ
 10. ታፈሰ ሺፈራው
 11. ተካ አባ ሲምቢ
 12. ሞጋ ፈሪስ
 13.  ዘውዴ አተሮ

እንዲሁም ከጊሚራና ኩሉ ኮንታ፣ ከአዳል፣ ከከረዩ፣ ከአርሲና ባሌ የመጡት ጃንሆይ በወገን ሳይሆን ለአገራቸው እኩልነትና አንድነት በመጣር ባደረጉት ውለታ ነው፡፡ የዛሬዎቹ ኤርትራውያን ሳይቀሩ ጃንሆይን በወገን በመሳፍንትነት ብቻ የሚሾሙና የሚሸልሙ አድርገው ዘመኑ ባመጣው ዘይቤ ብቻ የጽሑፋቸው ማሳመሪያና የአፍ ማሟሻ ሲደርጓቸው በማየቴ ይህንን ለማያውቁት እንዲያውቁ በአጭሩ አቀረብኩ እንጂ በሦስትና አራት ክፍላተ አገሮች ብቻ የተወሰነ እንዳልበር መግለጽ ይኖርብኛል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ሁሉ በነጠላ ስም የሚጠሩ ሳይሆን ከቀኛዝማች እስከ ደጃዝማች፣ ከ50 እልቅና እስከ ጄኔራልነት፣ ከመምህር እስከ ጵጵስና የደረሱ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ማናቸውም የጃንሆይ ዘመድ ወይም መሳፍንት አልነበሩም፡፡ ይህንን ለምሳሌ አነሳሁ እንጂ ስንቱ የአውራጃ ገዥዎች ናቸው? የመኳንንት ወይም የመሳፍንት ዘር? ሁሉንም በጥሞና ተመልክተን ከአስተያየታችን ብንቆጠብ ጥሩ ይሆናልና እንጠንቀቅ፡፡ ከላይ የቦረናን ወጣት ተማሪዎች በደፈናው ገልጬ ስላለፍኩ በአጭሩ ለትልቅ ደረጃ የደረሱትን የቦረና ልጆች ልንጠቅስና እዚህ ላቁም ገልገሉ ዶዮ፣ ሶራ አዲንና ዋርዮይ ጎዳናን መጥቀሱ በቂ ሲሆን፣ ከጠቀስኳቸው ወጣት የነበሩት ተማሪዎች ውስጥ ብዙ በሕይወት ያሉ ስለሆነ በምስክርነት መቅረብ ይችላሉ፡፡ ከኤርትራ እንደ በረከት ኃብተ ሥላሴ ዓይነቶቹም ቢሆን አይጠፉምና ጊዜ ይፍረደው ብለን እናልፈዋለን፡፡

(አሰፋ አደፍርስ፤ ከአዲስ አበባ)             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...