Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክበሌላ ክልል ለሚኖሩ ዜጎች በደልና ዕውቅና ለሚጠይቁ ማኅበረሰቦች ፍትሕ ሰጪ ተቋማት

በሌላ ክልል ለሚኖሩ ዜጎች በደልና ዕውቅና ለሚጠይቁ ማኅበረሰቦች ፍትሕ ሰጪ ተቋማት

ቀን:

የወልቃይት ጉዳይ እንደ ማሳያ

በውብሸት ሙላት

አገራችን ባሳለፍነው ዓመት ካጋጠሟት ፈተናዎች መካከል የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች ተቃውሞና አመጽ ዋነኛው ተጠቃሽ ነው፡፡ የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄን ተከትሎ በተከሰተው ተቃውሞ የትግራይ ተወላጆች ከሰሜን ጎንደር ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚዳስሰው በመጀመሪያ፣ የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነትን ጥያቄ በትግራይ ክልል እንዲፈታ የሚደነግገውን የሕግ ሥርዓት፣ ቀጥሎም የትግራዮች ብሔራቸውን መሠረት በማድረግ ከጎንደር በመፈናቀላቸው ምክንያት ለደረሰባቸው ጉዳት በአማራ ክልል ውስጥ ባሉት የፍትሕ ተቋማት ሥር በገለልተኝነት ሥርዓታዊና ፍትሐዊ ፍርድ ሊያገኙ መቻል ወይንም አለመቻላቸውን ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የክልል የሕገ መንግሥት ተርጓሚ ኮሚሽኖችን አወቃቀር በመመርመር በየክልሎቹ የሚነሱትን ከብሔር ጋር የተያያዙ የግለሰብንም ይሁን የቡድን መብቶችን ለማስከበር ያለባቸውን አወቃቀር ሁኔታ ይብራራል፡፡ ይሁን እንጂ ፍተሻ ለማድረግ የፌዴራሉንና የክልሎቹን ሕግጋተ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሠነዶችን እንዳስሳለን፡፡ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ የነበሩትን ብሔርን መሠረት ያደረጉ መፈናቀሎችንና የተወሰዱትን (የተወሰደ ካለ) ሕጋዊ መፍትሔዎችም በማነጻጸሪያነት ይነሳሉ፡፡    

የዜጎችና የብሔሮች መብቶች ግንኙነት

ጥሎብን ወደ አንድ ጽንፍ ሂደን ልግት ማለት ይቀናናል፡፡ አንዱን መርጦ ሙጭጭ ማለት ልማዳችን የሆነ ይመስላል፡፡ ሕገ መንግሥታችን ስለ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከያዘው ክፍል አብዛኛው ስለግለሰቦችና ዜጎች ነው፡፡ በጣም ጥቂቶቹ ደግሞ ስለብሔሮችና ሌሎች ቡድኖች (ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አርብቶ አደር ወዘተ) ነው፡፡ ይሄ ሕገ መንግሥታዊ ሀቅ ሆኖ እያለ ገዥውም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚዲያዎችም ይሁኑ ሲቪል ማኅበራት ትኩረታቸውም ንትርካቸውም ብሔሮች ላይ ያረፈ ነው፡፡

አሥርም ይሁኑ መቶ፣ ብሔራቸው አማራ የሆኑ ግለሰቦች ከደቡብ ወይ ከቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል ቢፈናቀሉ ጩኸቱ ሁሉ ‹‹አማራ›› በመሆናቸው ብቻ እንደደረሰ ግፍና ወንጀል ይቆጠራል፡፡ አሳዛኙ የመንግሥትም መልስ ይሁን ማስተባበያ ከብሔር ተኮርነቱ አይዘልም፡፡ ሁሉም በየፊናው ያራግበዋል፡፡ አባራሪዎቹም፣ ተባራሪዎቹም፣ ስለተባራሪዎቹ የሚዘግቡት ሚዲያዎችም ለማስረዳት የሚሞክሩት የበደሉ ምንጭ ከብሔርነት የመነጨ መሆኑን እንጂ ከዜግነት እንደሆነ አይደለም፡፡ በቅርቡም በጎንደር ወደ ትግራይ ክልል የተሰደዱት ትግራዮችን በተመለከተም የነበረውም በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ አካሄድ አብሮነታችንን፣ ወንድማማችነታችንና እህትማማችነታችንን የሚፈታተን ‹‹እኛና እነሱ›› የሚያባብል ብሎም ማለቂያ ወደሌለው አዘቅት የሚወስድ መንገድ ማንም የሚያስተው አይደለም፡፡ አዘቅቱን ለመወጣት የምናደርገው ጉዞና የምንከተለው መንገድ ካልተስተካከለ መቀመቅም ውስጥ የሚያስገባን ሊሆን ይችላል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አጻጻፍም ሐሳብም ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ለዜጎች የተሰጠውን  ክብር፣ ዋስትናና ጥበቃ በብሔር ጋርደነዋል፡፡ የብሔሮች መብት ሌላ የዜጎች ደግሞ ሌላ ሆኖ እያለ! ዘርዘር አድርገን ለማየት እንሞክር፡፡

የብሔሮችን መብት የማስቀደም አባዜ

እርግጥ ነው የሕገ መንግሥቱ ተዋዋዮች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንጂ ጅምላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን የብሔሮች መብት ከዜጎች መብት ቅድምና አለው ማለት አይደለም፡፡ አንዱ ከሌላው አያንስምም፣ አይቀድምም፡፡ ይሁን እንጂ የብዙዎች አረዳድም ይሁን አተገባበሩ በተቃራኒው ይመስላል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አጽዳቂ ጉባዔተኞች ስለ አንቀጽ 62 ሲወያዩ የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ከግለሰቦች መብት ጋር የሚጋጭ ከሆነ ወይንም ‹‹ከሁለቱ አንዱን መምረጥ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሲከሰት የሕዝቦችን መብት ማስቀደም ተገቢም ግዴታም እንደሆነ›› አቶ ዓባይ ፀሐዬ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ሐሳብ ደግሞ ጉባዔተኞቹ ሳይቃወሙት መደምደሚያ ሆኖ አልፏል፡፡ ከዚህ አንፃር የሕገ መንግሥቱ ሐሳብ ከላይ ከቀረበው የአናሳው አስተያየት ጋር ይመሳሰላል፡፡ ይህን ሐሳብ ትክክል ነው ብሎ መቀበል ግን ፈጽሞ አዳጋች ነው፡፡

የአቶ ዓባይ ፀሐዬ ገለጻ ትክክል የማይሆንበትን ተጨማሪ ሐሳብ ላቅርብ፡፡  ግለሰቦች መብታቸውን ለቡድኖች ጥቅም፣ በቁጥር ብዙ ስለሆኑ አሳልፈው መስጠት አለባቸው የሚል በእኛም ሕገ መንግሥት ይሁን በሌሎች ላይ የለም፡፡ የቡድን መብት መሠረቱም የግለሰብ መብት ነው፡፡ የግለሰቦች መብት እየተጣሰ የቡድን መብት ሊከበርም አይችልም፡፡ ለነገሩ የኢሕአዴግ ይፋዊ አቋምም እሳቸው እንደሚሉት አይደለም፡፡ ‹‹የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ›› ከሚለው ሰነድ ላይ አቋሙን እንዲህ እጠቅሳለሁ፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታችን የግለሰቦችን መብት በማስከበር ሽፋን የብሔር ብሔረሰቦች መብት መረገጥን እንደማይቀበል ሁሉ በብሔር/ብሔረሰቦች መብት መከበር ሽፋን የግለሰቦች መብት መታፈንን አይቀበልም፡፡ ግጭት በሚያጋጥምበት ወቅት አንዱ ከሌላው የበላይ ነው ብሎ በመፈረጅ አንደኛውን ረግጦ ሌላኛውን በማክበር መልክ መፍታት አይቻልም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ አካሄድ ዞሮ ዞሮ የሁሉንም መብቶች መሸርሸርንና መታፈንን ከማስከተል በስተቀር መፍትሔ ሊሆን አይቻልም፡፡››

በእርግጥ ኢሕአዴግ በፖሊሲ ሰነዱ ላይ ከአቶ ዓባይ ገለጻ ተጻራሪ የሆነ አቋም ቢያስቀምጥም በተግባር ግንየአቶ ዓባይ ገለጻ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አዋጆች በተለያዩ ክልሎች ጸድቀዋል፡፡

የዜጎች መፈናቀልና የተወሰዱት መፍትሔዎች

በተለያዩ ወቅቶች ብሔራቸው አማራ የሆኑ ግለሰቦች ከደቡብ፣ ከቤኒሻንጉል-ጉሙዝና ከኦሮሚያ ክልል እንደተባረሩ፣ በጋምቤላ ደግሞ ነባር ብሔረሰቦች መጤዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ የትግራይ ተወላጆች በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን፣ በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡ በተጨማሪም በአጎራባች ክልሎች የሚኖሩ አፋርና ኢሳ፣ አፋርና አማራ፣ ሶማሌና ኦሮሞ፣ ጉሙዝና ኦሮሞ ወዘተ. መካከል ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በቅርቡም በትግራይ ክልል የሚኖሩ አማራ ነን ያሉ ወልቃይቶች  እንዲሁም የትግራይ ተወላጆች ደግሞ በጎንደር ከብሔር ጋር በተያያዘ ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡ በ2007 ዓ.ም. መስከረም ወር እንኳን በጋምቤላ ክልል በመዥንግና በደገኞች/ በመጤዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ የእነዚህ ግጭቶች ምንጫቸውና ምክንያታቸው የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የተወሰኑት ግጭቶች መንስዔያቸው ከግጦሽ መሬት፣ ውኃና የእርሻ መሬት ጋር የተያያዙ ቢሆንም የተወሰኑት ደግሞ ከማንነትና ከራስን ዕድል በራስ መወሰን ጋር የተያያዙ መብቶችን ክልሎች ባለማክበራቸው ወይንም በመጣሳቸው ነው፡፡

ከጉራፋርዳ ብሔራቸው አማራ የሆኑ ግለሰቦች ሲባረሩ የተባረሩበት ዋናው ምክንያት በሕገወጥ መንገድ በመስፈር ደን ስለጨፈጨፉ ነው፤ ተባለ፡፡ በእርግጥ ብሔራቸው አማራ በመሆኑ ተባረሩ እንበል፡፡ ግን ጉራፋርዳ ላይ በሕገወጥ መንገድ ሰፍረው ደን የጨፈጨፉት ሲዳማዎች፣ ወላይታዎች፣ ሸካዎች ቢሆኑ ኖሮ ይባረሩ ነበር ወይ? ለመሆኑ ወደየት ነው የሚባረሩትስ? ጨፍጭፈዋል፣ አልጨፈጨፉም፣ አሊያም በሕገወጥ ወይንም በሕጋዊ መንገድ ነው የሰፈሩት የሚል አይደለም ክርክሬ! ይልቁንስ ማባራሩ ከየት መጣ? እነዚህ አማራዎች ደን የጨፈጨፉት አማራ ክልል ውስጥ ቢሆን ኖሮስ ወደየት ይባረሩ ነበር? ማባረር የሚባል የአስተዳደራዊም ይሁን የወንጀል ቅጣት የለም፡፡ ደን መጨፍጨፍ ወንጀል ነው፡፡ ወንጀል የፈጸመ ደግሞ ተከስሶ ጥፋተኛ ከተባለ በእሥራት ወይንም በገንዘብ ይቀጣል፡፡ ብሔሩ አማራም ይሁን ትግራዋይ ወይ ኦሮሞ ወንጀል ያው ወንጀል ነው፡፡ አንዱን አስሮ ወይ በገንዘብ ቀጥቶ ሌላውን ማባረር ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊም አይደለም፡፡ የሚያባርሩትንም ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል ላይ እንደተፈጸመው (እንደተሞከረው) በወንጀልና በአስተዳደራዊ መንገድ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ጉዳት ለደረሰባቸውም ሰዎች ተጠያቂ የሚሆኑት አባራሪ ባለሥልጣናት ካሳ መክፈል አለባቸው፡፡ መንግሥትም እነዚህ ባላሥልጣናት ጉዳት ሲያደርሱ በአርምሞ በማለፉ ኃላፊነት አለበት፡፡ በሌላው አካባቢ የተፈጸሙት ጥሰቶች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱና ሌሎች ሕጎች ላይ ያሉትን የዜጎች መብት ሥራ ላይ አለማዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥቱም ቢሆን፣ ብዙ ጊዜም የክልሎቹና የወረዳ ወይንም በሌላ እርከን ላይ ያሉ መንግሥታት የወሰዷቸውን ዕርምጃዎች ተገቢና ትክክል መሆናቸውን ማስረዳት ላይም ሲጠመድ ታይቷል፡፡ ከዚህ አንፃር የሰሞኑን የትግራይ ተወላጆች መፈናቀልን በተመለከተ ግን ለየት ያለ ነገር ተከስቷል፡፡ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ብሔር ላይ ተመሥርቶ መፈናቀል፣ ከክልል መባረር፣ የአካል ጉዳት እና የሕይወት መጥፋት በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ ተፈጽሟል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የአማራ ክልል መንግሥት ልክ አሁን የትግራይ ክልል እንዳደረገው ድጋፍ ሆነ የመቆርቆር እንዲሁም ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርግ አልታየም፡፡ ሌሎች ደግሞ ቢያንስ በአጋርነት መልክ የደረሰባቸውን በደል ሲኮንኑ አልተስተዋሉም፡፡ የገንዘብ እርዳታን በተመለከተ፣ እንኳን ሌሎቹ የአማራ ክልልም ሲያደርግ አልተስተዋለም፡፡ ይሁን እንጂ መፍትሔው ሕጋዊነት ማስፈን፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙ ማድረግ፣ በደልና ወንጀል ፈጻሚዎችን ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ጥበቃ ያላደረገው አስተዳደራዊ ተቋምም እንዲሁ ኃላፊነት እንዲኖርበት ማድረግ ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ነው የዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው የመሥራት መብታቸው የሚረጋገጠው እና ዋስትና እንዳላቸው የሚሰማቸው፡፡ ለሁሉም ብሔሮች ተመሳሳይ ጥበቃ እና ድጋፍ ማድረግም አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ይረዳል፡፡

የዜጎች መብት በሕገ መንግሥቱ

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 እና 41(1) ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብሔሩ ምንም ይሁን ምን፣ ገደብ በሌለው ሁኔታ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ፣ በማንኛውም የኢኮኖሚ መስክ ተሰማርቶ ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው፡፡ እነዚህ መብቶች በክልል ሕገ መንግሥቶቹም በድጋሜ ተረጋግጠዋል፡፡ በአገር ውስጥ ለመዘዋወር ደግሞ ፓስፖርት ወይንም የመኖሪያ ፈቃድ አያስፈልግም፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻውን በቂ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ መብቶች በሌሎች እንዳይጣሱ የማስከበር ግዴታ ያለበት መንግሥት ነው፡፡ መብታቸው ሲጣስ ግለሰቦቹም የመክሰስ መብት አላቸው፡፡ የመንቀሳቀስ መብት ሲጣስ ወይንም እክል ሲፈጠር፣ በተጨማሪም ከተሰማሩበት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት የሆኑ ሰዎችን ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ በፍርድ ቤት ማስወሰን ይቻላል፡፡

ችግር ፈጣሪዎቹ ባለሥልጣናት ከሆኑ፣ ዞሮ ዞሮ በመንግሥት ተቋም ውስጥ ስላሉ መንግሥት የዜጎችን መብት ማክበር ግዴታው ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች የእነዚህን ዜጎች መብት ሲጥሱ የማስከበር አሁንም ግዴታ አለበት፡፡ በመሆኑም እንደነዚህ ዓይነቶቹን የመብት ጥሰቶች የፖለቲካ አንድምታቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ ግለሰባዊ ማድረግ፣ መፍትሔያቸውንም በፍርድ ቤት በኩል እንዲሰጥ ማድረግ መቻል አለብን፡፡ መንግሥትም ይሄንን አካሄድ ማበረታታት ሲገባው ፖለቲካዊ መፍትሔ በመስጠት ተጠምዶ ኖሯል፡፡ መፍትሔው ግን የፍትሕ ተቋማትን ገለልተኛ እንዲሆኑ በማድረግ ሕጋዊነትንና የሕግ የበላይነትን ማስፈን ነው፡፡ ዜጎች የፍትሕ ተቋማትን እንዲጠቀሙ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባሉት የፍትሕ ተቋማት አወቃቀር ለዜጎች መተማመኛ ይሆናል ማለት የሚቻል አይመስልም፡፡

የፍትሕ ተቋማት ገለልተኝነት ጥያቄ

በየአካባቢው ያለው ፖሊስም እነዚህን ወንጀሎች ያለአድልኦ የመመርመር፣ ዓቃቤ ሕግም በገለልተኝነት ክሱን የመምራት ፍርድ ቤቶችም እንዲሁ ማድረግ አለባቸው፡፡ ፈተናው ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ሀ›› የተባለው ብሔር አባላት በኢትዮጵያዊነታቸው ሌላ ቦታ በመሔድ  ‹‹ለ›› የተባለ ብሔር በሚያስተዳድረው ወረዳ ወይንም ዞን ወይንም ክልል ውስጥ ሲኖሩ ከላይ የተገለጹት ወንጀሎች ቢፈጸሙ ከሳሽ የ‹‹ሀ›› ብሔር አባላት ተከሳሽ ደግሞ የ‹‹ለ›› ብሔር አባላት ሆነው ፖሊሱም፣ ዓቃቤ ሕጉም፣ ዳኛውም የተከሳሹ፣ የ‹‹ለ›› ብሔር አባላት፣ በመሆናቸው ገለልተኝነታቸው አጠያያቂ ነው የሚሆነው፡፡ምክንያቱም ትኩረታችን ሁሉ ብሔር ላይ በመሆኑ፡፡

እንዲህ  ዓይነቶቹን ወንጀሎችም ይሁን የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ከክልል የዳኝነት ሥልጣን ወጥተው ለፌዴራል ቢሰጡና ምርመራውንም የፌዴራል ፖሊስ፣ ከሳሽም የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤቱም እንዲሁ የፌዴራሉ ቢሆን ለገለልተኝነቱ የተሻለ ይሆናል፡፡ የፌዴራል ጉዳዮችን በውክልና የሚያዩ ክልሎች እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ሲጋጥሟቸው ራሱ የፌዴራሉ ፍርድ ቤት በራሱ ዳኞች ነገር ግን የአቤቱታ አቅራቢም ሆነ ክሱ በቀረበበት ብሔር(ክልል) አባላት ውጭ ያሉ ዳኞች ሊያዩት ይገባል፡፡ መርማሪ ፖሊሶችና ዓቃቤ ሕጎችም እንዲሁ፡፡

የክልል መፍትሔን አማጥጦ የመጠቀም ሸክም

የፌዴራሉን ሕገ መንግሥቱን የመተርጎምና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን  ጋር የሚያያዙ መብቶችን፣ ከመገንጠል በመለስ፣ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ተጥሷል የሚል ማንኛውም ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ብሔርና የመሳሰሉት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከማቅናቱ በፊት የክልል መፍትሔዎችን አሟጦ የመጠቀም ግዴታ አለበት፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚባሉት በዋናነት የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ የመጀመሪያው የማንነቴ ይታወቅልኝ ጉዳይ ነው፡፡ ስልጤ እውነተኛው ማንነቴ ጉራጌ ሳይሆን ስልጤ ነው እንዳሉት፣ የቅማንት ማኅበረሰብም አማራ ስላልሆን በቅማንትነታችን እንታወቅ ብለው በመጠየቃቸው እንዳስወሰኑት፣ የመንጃ ማኅበረሰብም የተለየ ማንነት የላችሁም ተብለው ዕውቅና ቢነፈጋቸውም እነዚህንና ሌሎች ቡድኖች በእውነተኛ ማንነታችን እንታወቅ በማለት ያቀረቡትን ጥያቄዎች የመሳሰሉት የማንነት ጥያቄ ናቸው፡፡

ሌላው ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው፡፡ ማንነቱ ታውቆ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ከሆነ በኋላ የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የልዩ ዞን ወይንም ክልል በመመሥረት ራስን የማስተዳደር መብት ነው፡፡ የሶማሌ ኢሳዎች በአፋር ክልል የራሳቸው ቀበሌ እንደመሠረቱ፣ ስልጤ ልዩ ዞን እንደመሠረተው መሆኑ ነው፡፡ የኮንሶ ብሔረሰብ ከሰገን ዞን ተለይተን የራሳችን ልዩ ዞን እንመሥርት ብለው እንደጠየቁት፡፡ ባህሌንና ታሪኬን እንዳላሳድግ መስተዳድሩ እንቅፋት ሆኖብኛል በማለትም ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ቋንቋዬን በትምህርትና በሥራ እንዳልጠቀም ሁኔታዎች አልተመቻቹልኝም፣ ወይንም መንግሥት ይህን መብቴን ክዶኛል የሚልም ሊሆን ይችላል፡፡

በተጨማሪም ማንነቴን መሠረት ያደረገ መገለልና ማዳላት ተፈጽሞብኛል የሚል ይዘት ሊኖራቸው እንደሚችል የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር የወጣው አዋጅ ላይ ተገልጾኣል፡፡ ማዳላትና መገለል ደግሞ በመንግሥት ሥራዎች እንዳይሳተፉ ማድረግን፣ በአካባቢው ባሉ መስተዳድሮችና ምክር ቤቶች ውስጥ እንዳይወከሉ ማድረግንም ያካትታል፡፡ በሌሎች ክልላዊ ሕጎችም ይሁን አሠራር የፌዴራሉን ወይንም የክልሉን ሕገ መንግሥት የሚጥሱ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ለዚሁ ምክር ቤት ሊቀርቡ ይችላል፡፡

ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ አቅራቢዎች፣ በተለይ ከማንነት ጋር የሚያያዙት የክልል መፍትሔዎችን አሟጥጦ የመጠቀም ግዴታ አለባቸው፡፡ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጋር የተነሳውን ጥያቄ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ከወልቃይት አማራዎች ውስጥ አምስት ፐርሰንቱ ስምና ፊርማ ያለበት አቤቱታ፣ በመስተዳድሩ (በወልቃይት ወረዳ አስተዳዳሪ እንደማለት ነው) ማህትም ተረጋግጦ ለትግራይ ክልል ምክር ቤት ወይንም የሕገመንግሥት ተርጓሚ ኮሚሽን መቅረብ አለበት፡፡ እነዚህ አካላትም በሁለት ዓመት ውሳኔ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ፣ የወልቃይት አስተዳዳሪ ማኅተም ማስደገፍ ግድ ነው፡፡ የሕዝብን ብሶት እና ችግር በቅንነት ከማየት ይልቅ የሻዕቢያ ተላላኪዎች፣ የትምክተኞች፣ የጠባቦች ወዘተ. ጥያቄ ነው የሚል መንግሥታዊ ግምት በሚወሰድበት አገር እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መሳካት መቻላቸውን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

 ከአማራ ክልል የተፈናቀሉት የትግራይ ተወላጆችም የክልሉ ሕገ መንግሥት ከደነገገው በተቃራኒው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ወይም ሌላ ወረዳ ተገቢውን ጥበቃ ባለማድረጉ ምክንያት የተለያዩ ጉዳት ደርሶብናል ማለት ቢፈልጉ፣ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወይንም ለአማራ ክልል ሕገ መንግሥት ተርጓሚ ኮሚሽን አስቀድመው ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል እንደማለት ነው፡፡ የክልል ሕገ መንግሥቶች ጋር የተያያዙ ትርጓሜዎችን ወይንም መፍትሔ የሚሰጡ ኮሚሽኖችን አወቃቀር በአጭሩ ማየት ተገቢ ነው፡፡

የክልሎቻችን የሕገ መንግሥት ተርጓሚ ኮሚሽኖች

ከላይ እንደተገለጸው የክልሎች ሕግጋተ መንግሥታትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሲነሱ የመተርጎም ሥልጣን የየክልሎቹ የሕገ መንግሥት ተርጓሚ ኮሚሽኖች ነው፡፡ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ በስተቀር፡፡ የኮሚሽኖቹን አወቃቀር ወይንም የኮሚሽኑ አባላት እንዴት እንደሚመረጡ እንመልከት፡፡

ትግራይ፣ አፋር፣ የኢትዮጵያ ሶማሊያ፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች ከየወረዳ ምክር ቤቶቹ የሚመረጡ አባላትን የያዘ ነው፡፡ በአማራ ክልል የአርጎባ ልዩ ወረዳን፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ የአዊና የዋግ ኽምራ ዞኖች ሥር የሚገኙ የእነዚህ ብሔረሰቦች አባላት ወኪልም አሉበት፡፡ የሌሎቹ ግን ልዩ ወረዳ ወይንም ዞን ስለሌላቸው የኮሚሽኑ አባላት ከትግራይዋይ፣ ከአፋር፣ ከሶማሌና ከኦሮሞ ውጭ ያለን ብሔር የማካተታቸው ዕድል ዝቅተኛ ነው፡፡ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች ደግሞ በውስጣቸው ካሉት አምስት፣ አምስት ነባር ብሔረሰቦች በእኩል ቁጥር የተውጣጡበት ኮሚሽን ነው፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ፣ ከነባር ብሔረሰቦች ውጭ ያለ ሰው አባል አይሆንም፡፡ የደቡብ ክልል ደግሞ እንደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ እያንዳንዱ ብሔር አንድ አባል ያለበት፣ ነገር ግን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቁጥር ካለው ለእያንዳንዱ አንድ ሚሊዮን ሌላ ተጨማሪ አንድ አባል ለኮሚሽኑ ይጨመርለታል፡፡ ሐረሪ ክልልን በተመለከተ፣ የሐረር ሕዝብ የፌዴሬሽንና ከክልሉ የተመረጡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሐረሪ ጉባዔ (አባላቱ ሐረሪዎች ብቻ የሆኑበት) እና ከክልሉ ምክር ቤት ሁለት ሁለት አባላት፣ እንዲሁም የቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንቶችን ያካትታል፡፡ የሐረሪን በተመለከተ፣ ለፌዴራሉና ለክልሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ውስጥ ኦሮሞዎች ሊወከሉ ስለሚችሉ ከኮሚሽኑ አባላት ውስጥ ሁለቱ ኦሮሞዎች የመሆን ዕድል አለ፡፡ የኮሚሽኖቹ አወቃቀር ይህን ከመሰለ እንደምን አድርጎ በተለይ ከራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ሊመልስ ይችላል? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡

በራስ ጉዳይ ዳኛ የሚሆኑት ኮሚሽኖች

ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚቀርቡት ጉዳዮች በተለይም የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች የክልል መፍትሔዎችን አሟጠው መጠቀም አለባቸው ብለናል፡፡ እናት ክልላቸው  ሌላ ክልል የሆኑ (ያው እናት አገር እንደሚባለው መሆኑ ነው) የሌሎች ብሔሮች አባላት ፍትሕ ሲፈልጉ የሚያገኟቸው ተቋማት የሚከተሉት ናቸው፡፡ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤት፣ የሕገ መንግሥት ተርጓሚ ኮሚሽን፣ እና የክልል ምክር ቤት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ አሁን ባለው አሠራር እነዚህ የክልል ተቋማት ውስጥ የሚሠሩት ደግሞ በየክልሎቹ የሚገኙ የነባር ብሔሮች አባላት ናቸው፡፡ ስለሆነም፣ ማንኛውም ግለሰብ ወይንም ቡድን ከእነዚሁ ተቋማት ነው ፍትሕን የሚሻው ማለት ነው፡፡

የክልል መፍትሔዎችን አሟጥጦ ከመጠቀም አኳያ የእነዚህ ተቋማት ከጅምሩ ያለባቸውን እንከን እንመለከት፡፡ ጥንተ አብሶ (Original Sin) እንደማለት ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ቢሆን ከዚሁ ጥንተ አብሶ የጸዳ አይደለም፡፡ ዝርዝሩን በሌላ ጽሑፍ ስለገለጽኩት ይቆየን! የፍትሕ ፍጥረታዊ ዋና ዋና መርሆች ውስጥ ሁለቱ  ‹‹አንድ ሰው በራሱ ጉዳይ ዳኛ መሆን የለበትም›› እና ‹‹ባለጉዳይ ሳትሰማ አትፍረድ›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የመጀመሪያውን መርሕ የሚያያዘው ከጥቅም ግጭት ጋር ነው፡፡ አንድ ሰው በዳይም ይሁን ተበዳይ በጉዳዩ ውስጥ ጥቅም ካለው ገለልተኛ ሆኖ ፍትሕ ሊሰጥ ስለማይችል  ዳኝነት ወይንም ውሳኔ አሰጣጡ ውስጥ ሊሳተፍ አይገባውም፡፡ ይህ አሠራር በዳኝነት ዓለም ውስጥ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ዳኝነት ወይንም በሌላ መልኩም ቢሆን ፍትሕ የተጠየቀበት ጉዳይ ብሔርን መሠረት ያደረገ ከሆነ ዳኞች ወይንም ውሳኔ ሰጪዎች እራሳቸውን ከዳኝነቱ ወይንም ውሳኔ ሰጪነቱ እንዲያገልሉ የሚያስገድድ ሕግ ቢያንስ በኢትዮጵያ የለም፡፡ በመሆኑ፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉ የወንጀል ጉዳዮች ላይ እንኳን ወንጀሉ ተፈጸመባቸው የተባሉት የብሔር አባላት በዳኝነት ሲሳተፉ አስተውለናል፡፡ በሐሳብ ልዩነት በፍርዶች ላይ ያስቀመጡት አስተያየት ይኼንኑ በራስ ጉዳይ ላይ ዳኛ ከመሆን የመነጨ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ይህንን መርሕ ለማስረዳት ሁለት ምሳሌ ብቻ ላቅርብ፡፡ የሶማሌ ኢሳዎች የአፋር ክልል በራሳችን እንድንተዳዳር አልፈቀደልንም፤ ራሳችንን የምናስተዳድርበት ወረዳ ወይንም ቀበሌ ክልሉ ስለነፈገን ሊሰጠን  ይገባናል ባሉበት ወቅት፣ አቤቱታቸውን ለአፋር ክልል አቅርበው የአፋር ክልል ፍትሕ እንዲሰጣቸው መጠበቅ፣ አፋር ክልል መንግሥት በገለልተኝነት ውሳኔ ይሰጣል ብሎ መጠበቅ ከሰው ባሕርይ የራቀ ነው፡፡ ለዚያም ነው፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ አፋር ክልል፣የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በጋራ እንዲፈታ ያደረጉት፡፡

የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄም ቢሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር በወጣው አዋጅ መሠረት የትግራይ ክልል ፍትሕ እንዲሰጥ መመለሱ በደል አድራሽ ዳኝነት ይስጥ እንደማለት ነው፡፡ ወይንም በራሱ ጉዳይ ዳኛ እንዲሆን የፍትሕ ፍጥረታዊ መርሕን በሚጥስ ሕግ ሥልጣን መሥጠት ነው፡፡ የወልቃይትን ጉዳይ አነሳን እንጂ የትኛውም ክልሎች ቢነሱ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ አድራጎት የራስን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ወይንም የሚያጠፋ በመሆኑ ነው፡፡ ፈረንጆቹ ራስን በራስ የሚያጠፋ ጋንታ (Suicide Squad) አድራጎት ይሉታል፡፡

በክልሎቹ ሕገ-መንግሥት መሠረት እነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚወከሉት ነባር ብሔረሰቦች ብቻ በመሆናቸው ‹‹ለመጤ›› ብሔረሰብ አባላት በገለልተኝነት ውሳኔ ይሰጣሉ ማለት አዳጋች ነው፡፡ ከሳሾቹም ፍትሕ እናገኛለን ብለው ያስባሉ ማለትም   እንዲሁ! ለፍትሕ አስፈላጊው የመጨረሻ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞም ፍትሕ ሊገኝ እንደሚችል ማመንና ማየትም የበለጠ አስፈላጊ ነው፡፡

በእንዲህ ዓይነት ሥርዓት ውስጥ ክስ ሲቀርብ ከሳሾቹ ሊሰማቸው የሚችለውን ስሜት በአንድ ታሪክ ልቋጨው፡፡ ወሎ ውስጥ ነው አሉ ታሪኩ የተፈጸመው፡፡ ሴትዮዋ፣ የቅንድቡ ፀጉር የገጠመ ሶብይ ልጅ ነበራት አሉ፡፡ ይማም አሊ የሚባል ጉልተኛ ሚስት የሆነች ሌላ ሴት ለሟርት ስትል በድብቅ ይሔንን ሶብይ ልጅ አሳረደችባት፡፡ ይህች ምስኪን ሴትዮ ወደየት አቤት እንደምትል ቢጨንቃትና ፍትሕ የምታገኝበት ገለልተኛ ዳኛ ቢናፍቃት እንዲህ ብላ ገጠመች፡-

ምኒልክ አባትሽ፣

ይማም አሊ ባልሽ፣

ለማንኛው ዳኛ አቤት ልበልብሽ፡፡

ከዚህ የሚከፋው ግን፣ በደል አድራሹ ራሱ ዳኛ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ አገርኛው ብሒል ‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› ይላል፡፡ በሁለቱ አባባሎች ውስጥ በደል ፈጻሚውና ዳኛው ይለያያሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዞሮ ዞሮ ግንኙነት አለ፡፡ የወልቃይት ዓይነቶቹ ጉዳዮች እንዲፈቱ የተቀመጠው ሕጋዊ አሠራር ግን ከእነዚህም ይከፋል፡፡ ሴትዮዋ፣ በደሏን ልጇን ለገደለችባት ሴት ለራሷ ሳይሆን ቢያንስ ለባሏ ወይንም ለአባቷ ብታቀርብ ከንቱ ልፋት እንደሚሆንባት ነው የገለጸችው፡፡ የቀማኛው ልጅ አባት ዳኛ ከሆነም እንዲሁ ነው፡፡ ለዚያም ነው፣ ፍትሕ መጨረሻ ላይ ከሚገኘው ውጤቱ በላይ ሊሠጥ ወይንም ሊገኝ እንደሚችል የሚያሳይ ሥርዓት ሊኖር ግድ የሚለው፡፡ በእንግሊዝኛው Justice must be seen to be done እንደሚባለው፡፡

በአጠቃላይ የፍትሕ ተቋማቶቻችንን ገለልተኛ አድርጎ በማዋቀር እና ሕገ መንግሥቱና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ላይ የተደነገጉትን የዜጎች መብቶችን በቅንነትና በፍጹም ቁርጠኝነት ማስከበርና መተገበር ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ኢሕአዴጋዊ ሳይሆን መንግሥታዊ፣ ፖለቲካዊ ሳይሆን ሕጋዊ፣ የአስፈጻሚው አካል ሳይሆን በዋናነት የዳኝነት አካሉ ላይ ትኩረት ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው፡፡ ሕጋዊነትን እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊነትን መንግሥት ሲያሰፍን ነው ሕዝቡ በእነዚህ ተቋማት ላይ አመኔታ የሚኖረው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...