Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናመንግሥት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆችን ሊያነጋግር ነው

  መንግሥት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆችን ሊያነጋግር ነው

  ቀን:

  ከረቡዕ መስከረም 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት ለአንደኛ፣ ሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዲሁም ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ላሉ ተማሪዎች ሥልጠና መስጠት እንደሚጀምር፣ በዘንድሮ ከትምህርት ማኅበረሰብ ጋር የሚደረግ የውይይት መድረክ ወላጆችም ተሳታፊ እንደሚሆኑ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

  የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ መስከረም 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የሥልጠናውና የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳዎች ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ልማት የትምህርት ድርሻ፣ የፌዴራል ሥርዓት፣ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርቶች የፈጠሩት ተፅዕኖ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ትምህርት ጥራትና የትምህርት ተሳትፎ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችም እንደሚነሱ ተገልጿል፡፡

  ሚኒስትሩ ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆችን ማነጋገር ያስፈለገው ለምንድነው? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦላቸው ሲመልሱ፣ ‹‹ወላጆች በውይይት መሳተፍ ያለባቸው በትምህርት ሥራ ውስጥ ትልቅ ባለድርሻ በመሆናቸው ነው፡፡ ተማሪዎች የወላጆች ነፀብራቅ በመሆናቸው በንግግርና በምክንያት የሚያምኑ እንዲሆኑ ወላጆች ልጆችን መምከር አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

  ዛሬ የሚጀመረው ከዩኒቨርሲቲ መምህራንና ከአስተዳደር ሠራተኞች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ለስምንት ቀናት እንደሚዘልቁ፣ ከወላጆች ከዚያም ከተማሪዎች ጋር የሚደረገው ውይይት እንደሚቀጥልና ከመጪው የመስቀል በዓል በፊት ውይይቶቹ እንደሚጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

  በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ተቃውሞና አለመረጋጋት በርካታ ወላጆች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የመላክ ፍርኃት እንዳደረባቸውና እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ እንዲልኩ መንግሥት እንዴት ሊያሳምን ይችላል የሚል ጥያቄም ለሚኒስትሩ ቀርቦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ለልጆቻቸው ደኅንነት ኃላፊነት እንደሚወስዱና መንግሥት ደግሞ ሥርዓት እንደሚያስከብር ወላጆች ማመን እንዳለባቸው በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

  መንግሥት በየዓመቱ የሚያወያየው በውይይት፣ በምክንያትና በሐሳብ ልዩነት የሚያምን የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሲሆን፣ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውይይቱ ውጤታማ ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹ዘንድሮ በሚካሄደው ውይይት ደግሞ ከወላጆች ጋር የሚደረገው ይበልጥ እንደሚሳካ ይታመናል፡፡ ትምህርት ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ተማሪዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች የሚኖሩ ከሆነ ተመሳሳይ መድረክ ለመፍጠር መንግሥት ዝግጁ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

  በቀጣዩ ሳምንት የአዳዲስ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ ይፋ የሚደረግ መሆኑን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ተማሪዎችም ሥልጠና ወስደው በመስከረም መጨረሻ በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ነባር ተማሪዎች ደግሞ ከመስከረም 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚጀምሩ ተገልጿል፡፡

  መንግሥት የውይይት አጀንዳ ይሆናሉ ካላቸው መካከል የፌደራሊዝም ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በቅርቡ የወልቃይትና የቅማንት ጥያቄዎች መነሳታቸው፣ ጥያቄዎቹን ተከትሎ ግጭቶች መፈጠራቸው አይዘነጋም፡፡ ይህንና በአጠቃላይ በአገሪቱ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ እንደሚያደርግና የሚያደርጋቸውን ለውጦችም በመስከረም መጨረሻ ለፓርላማ እንደሚያቀርብ መግለጹ ይታወሳል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...