በፓራሊምፒክ ታሪኳ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የብር ሜዳሊያ በ1,500 ሜትር (በዓይን ጉዳተኞች ምድብ) አገኘች፡፡ በሪዮ እየተካሄደ በሚገኘው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች በ1,500 ሜትር መስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በተደረገው ውድድር ሁለተኛ የወጣው ታምሩ ደምሴ የገባበት ጊዜ 3፡48.59 ደቂቃ ነው፡፡ ውድድሩን አልጀሪያዊው አብደላቲፍ ባካ በ3፡48.29 ደቂቃ ሲያሸንፍ፣ በሦስተኛነት ኬንያዊው ሄንሪ ኪርዋ (3፡49.59) አጠናቋል፡፡
ታምሩና ባካ የመጨረሻው መስመር ላይ ያደረጉት ትንቅንቅ የዓለም ክብረ ወሰን እንዲሰበር ያደረገ ሲሆን፣ በሲድኒ ኦሊምፒክ ኃይሌ ገብረሥላሴና ፖልቴርጋት ያደረጉትን ፉክክርም ያስታወሰ ነበር፡፡ በውድድሩ ላይ አራተኛ የወጣው የአሸናፊው አልጀሪያዊ ወንድም ፉአድ ባካን ጨምሮ አራቱም አትሌቶች የገቡበት ሰዓት ከወር በፊት በሪዮ ኦሊምፒክ በ1,500 ሜትር ያሸነፈው አሜሪካዊው ማቲው ሴንትሮዊትዝ ከገባበት 3፡50.00 ደቂቃ የተሻለ ነው፡፡ ታምሩ ውድድሩ በሁለተኛነት ባጠናቀቀበት ቅፅበትና በኋላ እንዲሁም በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እጁን አመሳቅሎ ታይቷል፡፡
በሪዮ ኦሊምፒክ ማራቶን ሁለተኛ ወጥቶ ተቃውሞውን እንዳንፀባረቀው ሌሊሳ ፈይሳ ታምሩም ደግሞታል፡፡ ኢትዮጵያ ከአራት ዓመት በፊት በለንደን በተካሄደው ፓራሊምፒክ በ1,500 ሜትር እጅ ጉዳተኛ ውድድር ወንድዬ ፍቅሬ እንደልቡ ሁለተኛ ወጥቶ የብር ሜዳሊያ መሸለሙ ይታወሳል፡፡ በሪዮ ፓራሊምፒክ ደረጃ ቻይና በ50 ወርቅ 40 ብርና 28 ነሐስ በአንደኛነት ስትመራ፣ ኢትዮጵያ እስከ ትናንት ድረስ በታምሩ ብር 60ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡