Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  አዳብና

  ቀን:

  ስለ ጉራጌ ሕዝብ ሲወሳ ወደ ህሊና ከሚመጡ በርካታ ነገሮች አንዱና ዋነኛው የመስቀል ክብረ በዓል ነው፡፡ መስቀል በጉራጌ ሕዝብ ዘንድ የተለየ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ለሥራ ባለው ትጋትና ታታሪነት እንደ ምሳሌ ለሚነሳው የጉራጌ ሕዝብ መስቀል ከቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና አብሮ አደግ መቀላቀያው ነው፡፡ ይህ እውነታ በሙዚቃ፣ በቴአትርና በሥነ ጽሑፍም ጎልቶ ይንፀባረቃል፡፡ በገሀዱ ዓለም ደግሞ መስከረም አጋማሽ ላይ ወደ ጉራጌ የሚያቀናው አውቶቡስ፣ ሚኒባስና የግል መኪና ቁጥርን መመልከት ይቻላል፡፡

  ለመስቀል በማንኛውም ዓይነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ያለ የጉራጌ ተወላጅ በተቻለው መጠን ሁሉ ወደ ቤተሰቡ ለመጓዝ ይወጥናል፡፡ መስቀል የሚከበርበት መስከረም 17 ቀንና በቀጣይ የሚመጡ ቀናትን በጉጉትም ይጠባበቃል፡፡ መስቀልን ተከትለው የሚመጡ ልዩ ልዩ ባህላዊ ክንውኖች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ሲሆን፣ የጉራጌ ማኅበረሰብም በድምቀት ያካሂዳቸዋል፡፡

  ከሁለት ዓመት በፊት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ ከተመዘገበው መስቀል ጋር ተያይዞ የሚከናወነው አዳብና በጉራጌ ማኅበረሰብ በጉጉት ከሚጠበቁ ባህላዊ ክንውኖች አንዱ ነው፡፡ ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዞ ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት ባሉት ቀናት ውስጥ ይካሄዳል፡፡ የአዳብና ባህላዊ ጭፈራ ሥነ ሥርዓት በገበያ ቦታዎች እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢ ይከናወናል፡፡

  በባህላዊው የመስቀል ጨዋታ አዳብና ከትውልድ ቀዬአቸው ርቀው የቆዩ ዘመድ አዝማዶችና ወዳጆች ይገናኛሉ፡፡ በአዳብና ናፍቆታቸውን ይወጣሉ፡፡ አዳብና የትዳር አጋር የሚመረጥበትም ነው፡፡ ክብ እየሠሩ የሚዘፍኑና የሚጨፍሩ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ከዜማና ዳንኪራ ጎን ለጎን ልባቸው የከጀለውን ያሳውቃሉ፡፡

  በአዳብና ወቅት አንድ ወንድ ለጭፈራ ከወጡት ኮረዳዎች መካከል ቀልቡ ያረፈባትን ሴት ሎሚ በመወርወር ያጫል፡፡ በባህሉ መሠረት በአዳብና ጭፈራ ለትዳር መተጫጨት የተለመደ ሲሆን፣ አንድ ወንድ የከጀላትን ሴት ለማሳወቅ ሎሚ ከወረወረ በኋላ የወንዱ ጓደኞች ስለ ልጅቷ ማንነት አጥንተው ለቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡ ይህን ሥርዓት ለጥምቀት በተለያዩ አካባቢዎች ካለው ሎሚ የመወርወር ሥርዓት ጋር ማነጻጸር ይቻላል፡፡

  በአዳብና ከሚካሄዱ ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል በወንዶች ብቻ የሚከናወን የዝላይ ትርዒት ይጠቀሳል፡፡ የሙየቶች ክውን ጥበብም በተያያዥ ይነሳል፡፡ ሙየቶች ለአዳብና ጭፈራ ከሚወጣው ታዳሚ የተለየ ቋንቋ፣ ዜማና ዳንኪራ የሚያቀርብ ማኅበረሰብ ነው፡፡ የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ ሙየቶች ወደ አናቱ በአደይ አበባ የተሽቆጠቆጠ ልምጭ ይዘው መሪያቸውን እየተከተሉ ሲያዜሙና ሲጨፍሩ ይስተዋላል፡፡

  በአዳብና ላይ ሙየቶች የደሟሚት ኮድ ብለው ለተመላኪዋ ድሟሚት የሚያቀርቡት ጸሎትም ይቀርባል፡፡ ስለአዳብና ሥርዓት ከዞኑ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተጨማሪ በርካታ አስጎብኚ ድርጅቶች በድረ ገጾቻቸው ያስተዋውቃሉ፡፡ በባህላዊ ፌስቲቫሎች የሚሳቡ የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ጎብኚዎች እንዲታደሙም ይጋብዛሉ፡፡

  ለምሳሌ የጉራጌ ዞን አዳብናን የሚያስተዋውቀው ከአካባቢው የተጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶች ጋር በማያያዝ ነው፡፡ በዞኑ ካሉ የቱሪስት መስህቦች መካከል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ጢያ ትክል ድንጋይ ተጠቃሽ ነው፡፡ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክና ጥንታዊ መስጅዶችም የአካባቢው ሀብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ በበርካታ የቱሪስት መረጃ አቀባይ ድረ ገጾች ይነበባሉ፡፡

  በአዳብና ላይ አንድ ወንድ ያጫትን ሴት ለቤተሰቦቹ ካሳወቀ በኋላ ትዳር እንዲመሠርቱ ቤተሰቦቹ ባህላዊ ሥርዓት ይጀምራሉ፡፡ ይህም የወንዱ ቤተሰቦች ለሴቷ ሽማግሌ መላክን ያካትታል፡፡ ሽማግሌ የመላኩን ሒደት ሰርቲን ሰንስ አስጎብኚ ድርጅት ጎብኚዎችን ይስባል ብሎ ካስቀመጣቸው ሥርዓቶች መካከል ይገኝበታል፡፡

  በጉራጌ ብሔረሰብ ከአዳብና ባህላዊ ጭፈራ በተጨማሪ መስቀልን የሚያደምቁ በርካታ ክንውኖች አሉ፡፡ በዓሉ ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ ማኅበራዊ ችግሮች የሚፈቱበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበትም ነው፡፡ አዳብና ለወጣቶች መተጫጫ በመሆን ለማኅበራዊ መስተጋብሩ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ አዳብና በማኅበረሰቡ የጋራ መሰብሰቢያ ቦታዎች ሲዘፈንና ሲጨፈር ከሎሚ በተጨማሪ ብርቱካንና ሸንኮራ አገዳም ለመተጫጫነት ይውላሉ፡፡

  በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች ለመስቀል ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ የሚወጥኑት ከበዓሉ አስቀድሞ ሲሆን፣ የማኅበረሰቡ የበዓል መሰናዶም ቀደም ብሎ ነው የሚጀመረው፡፡ በዓሉ ሲቃረብ ወንዶችና ሴቶች ሥራ ተከፋፍለው ዝግጅቱ ይጧጧፋል፡፡ እማወራዎች በተለይም እንሰት ፍቆ የማዘጋጀትና ሌሎችም ተያያዥ ኃላፊነቶቻቸውን ሲወጡ ይታያል፡፡ ከቡሄ በዓል በኋላ የመስቀል በዓል በጣም ስለሚቃረብ የመስቀል ደመራ ዝግጅት ይከናወናል፡፡

  የመስቀል በዓል ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ያሉት ቀናት በጭፈራና ለበዓሉ ተብሎ በሚዘጋጁ የምግብ ዓይነቶች ተከፋፍሎ ይከበራል፡፡ መስከረም 16 ላይ የአዳብና ባህላዊ ጭፈራ ከመጀመሩ በፊት የጀወጀ (የጀወቸ) በመባል የሚታወቀው ሥርዓት አማች የመጠየቂያ ጊዜ ነው፡፡

  መስከረም 16 የባንዳ ኧሳት (የጉርዝ እሳት) የሚባል ሲሆን፣ ደመራ የሚቃጠልበትና ሃይማኖታዊ ይዘት የተላበሰ ነው፡፡ ደመራው ከተለኮሰ በኋላ ወጣቶች የአዳብና ጭፈራቸውን ይያያዙታል፡፡ ከጭፈራው በኋላም ሁሉም ወደየቤቱ ገብቶ በጣባ ክትፎ ይበላል፡፡

  በደቡብ ብሔረሰቦችና ክልል ሰሜናዊ ጫፍ የሚገኘው የጉራጌ ዞን፣ በደቡብ ከሃድያና ከሥልጢ ዞኖች፣ በደቡብ ምዕራብ ከየም ልዩ ወረዳ፣ በምዕራብና በሰሜን ምሥራቅ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡

  በዞኑ የተመዘገቡ ባህላዊ ቅርሶች ሦስት ብሔረሰቦችን ማለትም ጉራጌ፣ ቀቤናና ማረቆን የያዙ ናቸው፡፡ ብሔረሰቦቹ የተለያየ አኗኗር ዘይቤ ያላቸው ከመሆኑም ባሻገር የየራሳቸው ቋንቋና ባህል አላቸው፡፡ ከጢያ ትክል ድንጋዮች በተጨማሪ የረጅም ዓመታት ታሪክ ያላቸው ትክል ድንጋዮች፣ መካነ መቃብሮች፣ ዋሻዎች፣ ገዳማት፣ አብያተ ክርስቲያናትና መስጅዶችም ይገኛሉ፡፡

  ባህላዊ ሥርዓቶችም ከእነዚህ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ መስህቦች መካከል ሲሆኑ፣ አዳብናም መስቀልን ለማድመቅ ይጠቀሳል፡፡ የክርስቶስ መስቀል መገኘት ጋር ተያይዞ የተጀመረው ዓመታዊው የመስቀል ክብረ በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (327 ዓ.ም.) ማለትም ከንግሥት ኢሌኒ አገዛዝ ጀምሮ እንደሚከበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡

  የበዓሉ አከባበር በእያንዳንዱ ብሔረሰብ ውስጥ የተለያየ ገፅታ የተላበሰ መሆኑንም ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡ በተለይም ከዘመን መለወጫ በኋላ ባሉ ጥቂት ወራት የሚከናወኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓሎች እንደየአካባቢው እሴት ሲተገበሩ ይስተዋላል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...