Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በዕንቁጣጣሽ ዋዜማ ጎዳና ላይ በሾላ ገበያ የወጡት የምግብ ዘሮች ብቻ ሳይሆኑ የትምህርት ቁሳቁሶች ጭምር ነበሩ::

ትኩስ ፅሁፎች

ፎቶ በመስፍን ሰሎሞን

**********

ያልተመለሱ ጥያቄዎች

ያሁኑ ጥያቄ፡-

ትናንትም ነበረኝ ዛሬም ጠይቃለሁ፣

ነገ እንዳልጠይቅ ግን አሁን መልስ እሻለሁ፡፡

በጤና፣ በልማት በሌሎችም ዘርፎች፣

በግልፅ ይታያሉ ያሉብን ችግሮች፡፡

ነገር ግን ችግሩን በማስወገድ ፋንታ፣

ሁል ጊዜ አያለሁ የጥናት ጋጋታ፡፡

ተጠንቶ ያለቀው እንደአዲስ ሲጠና፣

ከዚያም ይቀጥላል የማያልቅ ሥልጠና፡፡

በሥልጠናው ላይም ጥያቄ ሲነሳ፣

  • ይጠናል$ ይባላል እንዳዲስ ዳሰሳ፡፡

እስከ መቼ?

  • አፀደ ውድነህ “ድንጋይ መጽሐፍ ነው” (2005)

**********

‹‹ደመናውም ሸሸ እያጉረመረመ››

መስከረም ‹‹ከረመ›› ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ቀዳማይ፣ ለዓለም ሁሉ መጀመሪያ፣ ርእሰ ክራማት፣ መቅድመ አውራኅ ማለት ነው፡፡ መስከረም፣ ዐውደ ዓመት፣ የክረምት ጫፍ መካተቻ፣ የመፀው መባቻ ማለትም ይሆናል፡፡ መስከረም ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ለዓለም ሁሉ የመጀመሪያ ወር እንደሆነ ይታመንበታል፡፡

መስከረም በክረምት ውስጥ የሚካተት ቢሆንም የጨለማው ጊዜ አልፎ ብርሃን የሚታይበት፣ ዕፀዋትና አዝርዕት የሚያብቡበትና የሚያፈሩበት፣ እንስሳት የጠራ ውኃ እየጠጡ፣ ለምለም ሣር እየነጩ የሚቦርቁበት፣ በአጠቃላይ ምድር በአበቦች የምታጌጥበት፣ ሰማይ የደመና ቡሉከውን (ጋቢውን) ጥሎ ቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊት በከዋክብት ማጌጥ የሚጀምርበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ወር ናት፡፡ ለዚህም ነው በሰኔ መጨረሻ፣

‹‹ነው ወይ ልንለያይ ልንበታተን
ዳግመኛ ለመምጣት ተስፋ ሳይኖረን፤
እያለ በእንባ የተለያየው ተማሪ በመስከረም ወር ተመልሶ ትምህርት ቤት ሲገናኝ፤
መስከረም መስከረም መስከረም ለምለም
ከወራቱ ሁሉ እንደ አንቺ የለም
ደመናውም ሸሸ እያጉረመረመ
በመስከረም ማማር እየተገረመ፤››
በማለት የሚዘምረው፡፡

– ካሕሣይ ገ/እግዚአብሔር ‹‹ኅብረ-ብዕር›› (1998)

  •  

አዳም በለሱን ባይበላ ኖሮ ምን ዓይነት ሕይወት ይኖረን ነበር?

የሰው ልጆች የምንሰቃየው አዳም ባመጣው ኃጢአት ነው የሚሉ ወገኖች ይኖሩ ይሆናል፡፡ አዳም የተከለከለው ዕፀ በለስ በመብላቱ ወደ ምድር ተሰደድን ይሉ ይሆናል፡፡ ለኔ ግን አዳም ዕፀ በለስ መብላቱ ለበጐ ነው፡፡ አዳም ዕፀ በለስ ባይበላና እስከአሁን በገነት የምንኖር ብንሆን ምን ዓይነት ሕይወት ነበር የምንኖረው? በጣም አሰልቺ ሕይወት ነበር የሚሆነው፡፡ የሰው ልጅ ምንም ነገር ሣይሠራ መኖር ምን ያህል አሰልቺ እንደሆነ ከሕይወት ልምዳችን የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ከሥራ ፈትነት የገላገለን ግን አዳም ነው፡፡ ምንም ዓይነት ሥራ በሌለበት ዓለም ምንም ዓይነት ጣፋጭ ሕይወት ሊኖር አይችልም፡፡ እርስ በእርሳችን እንኳን ምንም ነገር ማውራት ሐሳብ ለሐሳብ መጋራት አንችልም፡፡ ሥራ ከሌለ ምንም ዓይነት ሐሳብ አይኖርም፡፡ የሐሳብ ልዩነት ከሌለ ደግሞ የሐሳብ መጋራት የለም ማለት ነው፡፡

  • አብርሃም ሐዱሽ ‹‹ነገር በምሳሌ …›› (2005)
  •  

ቻርልስ ደሞ ያበዛዋል

የመንደር ወሬ የማያመልጣቸው ስኮትላንዳዊው አያ ላዘንበሪ የሰሙትን ወሬ ለቡና አጣጫቸው ማክግሬገር እያወሩ ነበር፡፡ “የሚገርም እኮ ነው፤ አልሚራ ለእጮኛዋ ቻርልስ ቀለበቱን መለሰችለት አሉ፡፡ ይታይህ፣ ለስምንት ዓመታት ተጫጭተው ቆይተዋል፡፡ በዚያን ወቅት ደግሞ የቁጠባን ጥቅም ደጋግማ ስታስተምረው ነበር፡፡ ይሁንና በቅርቡ ከጋብቻቸው በኋላ 217 ጥንድ ካልሲዎቹን እንድትወሰውስለት ማስቀመጡን ባወቀች ጊዜ ትምህርቷ በደንብ እንደገባው በመገንዘቧ ግንኙነቷን አቋረጠች ‘ቻርልስ ደግሞ ያበዛዋል!’ አለች አሉ፡፡”

  • አረፈዓይኔ ሐጐስ “የስኮትላንዳውያን ቀልዶች” (2005)

ራስን ማክበር

አንበሳ ምድማዱ ላይ እንደተኛ በረሃብ ይሞታል እንጂ የውሻን ትራፊ አይበላም፡፡ በረሃብ ቸነፈርንና ችግርን ቻል፡፡ ከርካሽ ሰው ዕርዳታ በመጠየቅ ክብርህን በፍጹም በገዛ ራስህ አትጣ፡፡ መልካም ሥነ-ምግባር የሌለውን ሰው እርሳው፤ እንዲሁም ዋጋ-ቢስነቱን ዕወቅ፡፡

ወደ ልመና የሚያደላ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ምን ጊዜም ለማኝ ነው፡፡ በቃኝ ባይ አእምሮ ያለው ሰው ሁልጊዜ የተከበረ ነውና ስግብግብ አትሁን፡፡  የጉልበትህ ውጤት የሆነ ኾምጣጤና ጎመን ከባለ ሥልጣን እንጀራና ዝግን በእጅጉ ይበልጣል፡፡

  • በራስ መተማመን በሌለበት ቦታ አክብሮት የለም፡፡ አክብሮት በሌለበት ቦታም በራስ መተማመን ሊኖር አይችልም፡፡            (ሄንሪ ጊልስ)
  • ባይለየኝ ጣሰው ‹‹የሶኖዲ ጥበቦች›› (2004)

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች