Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሰሜን ኮሪያ ኑክሌር ሙከራ ያስከተለው ውጥረት

የሰሜን ኮሪያ ኑክሌር ሙከራ ያስከተለው ውጥረት

ቀን:

ሰሜን ኮሪያ ባሳለፍነው ሳምንት ማብቂያ ላይ በሬክተር ስኬል አምስት ማግኒቲዩድ ንዝረት የፈጠረ የኑክሌር ሙከራ ማድረጓ በቀጣናው ውጥረትን ፈጥሯል፡፡ መሬት ለመሬት የሚምዘገዘግ የኑክሌር ሙከራ ስታደርግ አምስተኛዋ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሙከራዎችም የአሁኑ ኃይሉ ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡ ይህም ሰሜን ኮሪያ በጦር ኃይል ግንባታዋ ዕድገት እያሳየች፣ በኑክሌር የታገዘ ጦር እየገነባች መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ በደቡብ ኮሪያ ላይ ሥጋትን ፈጥሯል፡፡

ሰሜን ኮሪያ እ.ኤ.አ. በ2006 የመጀመሪያውን ኑክሌር ሙከራ ስታደርግ፣ የተመዘገበው የመሬት ንዝረት 3.9 ማግኒቲዩድ ሲሆን፣ አንድ ኪሎ ቶን የሚደርስ አቅምም ነበረው፡፡ ዓርብ ጳጉሜን 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአምስተኛ ጊዜ የተሞከረው ግን፣ የ10 ኪሎ ቶን ቲኤንቲ አቅም ነበረው፡፡ የአገሪቱ መንግሥትም ሙከራው እስካሁን ከነበሩ ሙከራዎች የላቀ እንደነበረም ገልጿል፡፡

በኤስያን ጉባኤ ላይ የተገኙት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሰሜን ኮሪያ ለቀጣናው ብሎም ለዓለም ሥጋት መሆኗን፣ አሜሪካና ቻይና በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ፅንፍ ለፅንፍ መቆማቸው ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆን ኡን ምላሽ ለመስጠት አዳጋች መሆኑን ተናግረው አንድ ቀን ሳይሞላ ነበር፣ የኑክሌር ሙከራው የተደረገው፡፡

በመሆኑም፣ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ሙከራም ሆነ የጦር ኃይል መጠናከር ተከትሎ ሥጋት ውስጥ የምትገኘው ደቡብ ኮሪያ የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባም አካሂዳለች፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዋንግ ዮ አን በጠሩት ስብሰባም፣ በላኦስ የኤስያን ጉባዔ በመካፈል ላይ የነበሩት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፓርክ ጉን ሄይ፣ ጉባዔውን አቋርጠው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡

የኑክሌር ሙከራው ቀድሞውንም ለተከፋፈለው የኮሪያ ባህረ ሰላጤ እንዲሁም ለእስያና ለሌሎች አገሮችም አስግቷል፡፡ አሜሪካም ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የሰሜን ኮሪያን ትንኮሳ ለማስቆም እየሠራች ቢሆንም፣ ሰሜን ኮሪያን ከኑክሌርም ሆነ ከሚሳይል ሙከራ ልታስቆም አልቻለችም፡፡ ይልቁንም ኮሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጡንቻ እያጠነከረች መጥታለች፡፡

ሰሜን ኮሪያ የኑክሌርም የሆነ የሚሳይል ሙከራ የምታደርገው ጡንቻ እንዳላት ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭው ዓለም ለማሳየት ነው በማለት የአሜሪካ ናሽናል ሴኪዩሪቲ ካውንስል ቃል አቀባይ ቢገልጹም፣ ሰሜን ኮሪያ አጫጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሎችን ጨምሮ፣ አነስተኛ የጦር መሣሪያዎችን በኑክሌር ልትሠራ ትችላለች የሚል ምልከታም መጥቷል፡፡ ሆኖም የኪም ጆን ኡን መንግሥት የሚያጋጥመው ማዕቀብ ነው፡፡ ምናልባትም የተጠናከረና ከባድ ማዕቀብና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መገለል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለወጣቱ ፕሬዚዳንት ኪም ግድ አይሰጣቸውም፡፡

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ቪንዞ አቤ የኑክሌር ሙከራውን ተከትሎ የደኅንነት ባለሙያዎቻቸው ማንኛውንም መረጃ እንዲሰበስቡና ያገኙትንም ለቻይና፣ ለአሜሪካ፣ ለደቡብ ኮሪያና ለሩሲያ እንዲያካፈሉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት መግለጫም የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ሙከራ ተቃውመዋል፡፡ ቻይና በኮሪያ ባህረ ሰላጤ የኑክሌር ጦር መሣሪያ እንዲመክን፣ የኑክሌር ክምችት እንዲገታ፣ እንዲሁም በሰሜን ምሥራቅ እስያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንደምትሠራም መግለጫው አትቷል፡፡

ሆኖም የቻይናው መሪ ጂን ፒንግ ፕሬዚዳንት ኪምን በከባዱ ለመቅጣት ከመወሰን ተቆጥበዋል፡፡ አሜሪካ ከቻይና ጋር ብትሠራ ሰሜን ኮሪያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድንጋጌን ጥሳ የኑክሌር መሣሪያ ሙከራ አታደርግም ነበር የሚል አመለካከት በአሜሪካ በኩል ቢኖርም፣ ቻይና ለአሜሪካ ጉትጐታ ይህንንም ያህል ቦታ አልሰጠችም፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ ቻይናና አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ አብረው ባለመሥራታቸው፣ ሰሜን ኮሪያ ጡንቻዋን በጦር መሣሪያ አጠንክራለች ብለዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ኮሪያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ቻይና እንድትተገብረውም ጠይቀዋል፡፡

ሆኖም ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት እንደቀጠለ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ ይህም አሜሪካና ቻይና በሰሜን ኮሪያ ላይ ያላቸው የተለያየ አቋም፣ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ፕሮግራም ለማስቆም እንቅፋት ሆኗል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የሰሜን ኮሪያ መውደቅ ሁለቱ ኮሪያዎች በጋራና በስምምነት የሚጠቀሙበት በአሜሪካ መከላከያ ሥር የሚተዳደር የኮሪያ ልሳነ ምድር እንዲመሠረት ያደርጋል የሚል ሥጋት በቻይና በኩል መኖር፣ ቻይና ሰሜን ኮሪያን እንዳትቃወም አድርጓል፡፡ ይህም አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት የምታደርገውን ጥረት አደናቅፎታል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ቁጡና በጦር መሣሪያ ራሷን እንድታበለፅግ ምክንያት የሆናት፣ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በልሳነ ምድሩ የሚያደርጉት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ መሆኑንም ትገልጻለች፡፡

በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ከቻይና ጋር የተለየ አቋም ያላት አሜሪካ፣ በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ የጦር ጀቶቿን በደቡብ ኮሪያ ሰማይ ስታበርም ውላለች፡፡ ዓላማውም ለደቡብ ኮሪያ ያላትን አጋርነት ለመግለጽና ለሰሜን ኮሪያ ያላትን ኃይል ለማሳየት ነው ተብሏል፡፡

አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ያለውን የኑክሌር ሙከራ ለማስቆም ከደቡብ ኮሪያ ጋር የምትመክር ሲሆን፣ ዓላማውም በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለማስጣል እንደሆነ ተዘግቧል፡፡

ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል የሚያደርገውን ሒደት ሩሲያና ቻይና በቸልታ ነው የተመለከቱት፡፡ ምክንያቱም አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ሰሜን ኮሪያን ለመቆጣጠር በባህረ ሰላጤው ዘመናዊ ፀረ ሚሳይል መሣሪያ ለመትከል በመወሰናቸው ነው፡፡

ሩሲያም ሆነች ቻይና የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ሙከራ አይደግፉም፡፡ በኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር እንደሚያደርግም ያምናሉ፡፡ ሆኖም የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያን አካሄድም አይደግፉም፡፡ በቀጣናው ውጥረቱ እንዲባባስ ያደረገውም በአንድ ወገን አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ፣ በሌላ በኩል ሰሜን ኮሪያ ኃይላቸውን ለማሳየት በመሞከራቸው ነው ይላሉ፡፡     

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...