Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርቀዳሚው የመንግሥት ዕርምጃ!

ቀዳሚው የመንግሥት ዕርምጃ!

ቀን:

በሞገስ ሰለሞን

በአገራችን የተከሰቱትን መጠነ ሰፊ ሕዝባዊ የፖለቲካ ተቃውሞዎችን ቅጽበታዊ አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያ በመንግሥት በኩል ይታያል፡፡ ከመንግሥት በኩል የሚሰጡት መግለጫዎችም ሆነ የአቋም ማብራሪያዎች ይህን ያትታሉ፡፡ በአገሪቱ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በግንጪ ከተማ የተነሳበትን ጊዜ እንደ መነሻ አድርገን ብንወስድ ከአሥር ወራት በላይ የቆየ ‹‹የተጠየቅ መንግሥት ተጋፍጦ›› ሕዝባዊ አመጾችን ‹‹የውጭ ኃይሎች ሴራ›› በሚል የተመለከተበት መንገድ በአንድ በኩል፣ ለሕዝብ ተጠያቂ ያልሆነ መንግሥት ምን ያህል ከሕዝቡ መራቁን አመላካች ነው፡፡ በተለመደው መንገድ ሕዝብን በግልጽ በመሳደብ የተሰጡ መግለጫዎች (ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ በተደጋጋሚ የሰጡዋቸው) ያለ ግልጽ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ሚኒስትሩን ከሚዲያው ገሸሽ በማድረግ ተድበስብሰዋል፡፡ ይህም የሕዝቡን የተቃውሞ ጥንካሬ አመላካች እንጂ ገዥው ፓርቲ ያለውን የተጠያቂነት አሠራር በፍፁም አያሳይም፡፡ ተጠያቂነት ማለት በተለመደው መልኩ ከከፍተኛ ጥቅም (በኮድ ስሙ መጠነ ሰፊ የሕዝብ ሀብት ብክነት) ጋር የተያያዙትን የሥልጣን ወንበሮች ልቀማህ ነው በሚሉ የይስሙላ ማስፈራሪያዎች የሚገለጽ ሊሆን አይችልም፡፡

የዚህ የተቃውሞ መሠረታዊ መነሻ ከሆኑት ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው፣ የፖለቲካ መድረኩን ሕወሓት/ኢሕአዴግ በብቸኝነት የተቆጣጠረበት መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገዱ የሕዝብን ድምፅ ማፈን፣ በሕዝቡ መካከል እኔ ከሌለሁ እንበታተናል ይባስ ብሎም እንጠፋለን እያሉ ሽብር መንዛት፣ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ለመሆን የሕዝብ ይሁንታን የሚያገኙ ግለሰቦችንም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመከፋፈል ማዳከምና ማመንመን፣ ይህም ካልተሳካ በአገራችን የሕግ ታሪክ አምሳያ ባልተገኘለት የሽብርተኝነት ወንጀል የማፈኛ መሣሪያ ወደ ወህኒ መወርመር፣ የራሱም ሆነ ሕዝባዊ አቋም ያለውን ጋዜጠኛም ሆነ ነፃ አሳቢ ከሥራ ማባረር፣ ማጥፋትና ማሰርና ሌሎችንም ያጠቃልላል፡፡ በዚህ መልክ አገሪቱ የያዘችውን የፖለቲካና የሐሳብ እስረኛ የትየለሌ ቁጥር፣ በዚህም የደረሰውን ግፍና በደል በየዕለቱም የሚፈሰውን እንባ የሕዝቡ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የማረሚያ ቤቶች አሠራር በሙሉ እኔን ያየህ ተቀጣ ነው፡፡ አዲሱን ዓለም በቃኝ ቂሊንጦን ሆነ ነባሮቹ ታሳሪዎች ከቤተሰብም ሆነ ከጠያቂ እንዳገናኙ በጥበብ የተሠሩ ናቸው፡፡ በእነዚህ በተጠያቂ ጠያቂ የሰቆቃ ጩኸት መካከል በዓይን ብቻ ተያይቶ በእስከ አሁን በሕይወት መቆየትህን ለማየት አበቃን ለማለት ብቻ የቆሙ ናቸው፡፡

የሕዝብና የአገር ጉዳይ እኔንም ይመለከተኛል ብሎ ከገዥው ፓርቲ የተለየ አቋም መያዝ፣ በአጭሩ በምንና እንዴት በሆነ መልኩ እንደተዋቀረ በማናውቀው የስለላና የፖሊስ ኃይሉ ወጥመድ ውስጥ በደቂቃ መግባት ነው፡፡ ይህ የስለላ ኃይል ያለተግባሩ በሕዝቡ በራሱ ላይ የተዘረጋ ወጥመድ ሆኖ ሳለ ‹‹የደኅንነት ኃይል›› የሚል ምግባረ ሰናይ ስም ወጥቶለታል፡፡ የዚህ ወጥመድ ማነቆ ጠበቅ ሲል ላልቷል፡፡ በመጠኑ ላላ ሲልም ለሚዲያ ያልበቁትን ስም የለሾችን እልፍ አዕላፍ እስካሁን አንገታቸውን ቀፍድዶ ይዟል፡፡ ከዚህ ወጥመድ የተረፈው ደግሞ ከማንነቱ ከራሱ ጋር በክፉ ተጣልቶ በባዕድ አገር እንደ ከብት ለምግብ ብቻ ይኖራል፡፡ ባደግንበት የትኛውም ኅብረተሰብ ውስጥ ምግብ ከሰው ጋር የሚካፈሉት ፍቅር ለአብሮነት መሰባሰቢያ ምክንያት እንጂ፣ ለምግብነቱ መብላት እንደ ከፍተኛ ነውር ተቆጥሮ አድጎ ይህ የባዕድ  አገር አመንዣጊነት አገሩን፣ ሕዝቡንና ማንነቱን እያጣና እንዳጣ በቀን ሦስት ጊዜ እንዳይሸሽ አድርጎ እያስታወሰው ይሰቃያል፡፡ ታዲያ ስደተኛውስ ከእስረኛው አልባሰም? የዚህ ሁሉ ፖለቲካዊ ቀውስ ወደ ማኅበራዊ ቀውስ መሸጋገር ለወደፊቱም አብሮን የሚኖር ተጨማሪ ጠባሳችን እንደሆነ እሙን ነው፡፡

አሰቃቂው እስር በምን ምክንያት እንደሚመጣ ብዙ ጊዜ አደናጋሪ ነው፡፡ ማደናገሩ በማናቸውም ምክንያት ሊመጣ መቻሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ በግልጽ በጠላትነት የታወጁትን ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኞች በሙሉ የኦነግ፣ የመኢአድ፣ የኦብኮ ወይም የቀድሞው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አባል መሆንን ወይም መደገፍን ትተን ማለት ነው፡፡ በሃይማኖት ተቋም ውስጥ የሚነሱ ውስጣዊ ልዩነቶች ወይም የአስተዳደር ችግሮች ይፈቱ ማለት (በታላቁ አንዋር መስጊድና በአዲስ አበባ ልደታ ቤተ ክርስቲያን ያስታውሱዋል) በብዙኃኑ እስር ይቋጫል፡፡ በወባ ወረርሽኝ በክፉ ለተጠቁ ገበሬዎች ትኩረት ይሰጥ ማለት (1985) ወይም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ከአዲስ አበባ/ፊንፊኔ ለማውጣት ሕዝብን አላማከራችሁም፣ ወይም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአካዳሚ ነፃነት ይከበር ፖሊስም ከግቢው ጥበቃነት ይውጣ ማለት በግፍ ለመታሰርና ለስቃይ ያጋልጣል፡፡

የተዋቀረው የፖለቲካ ሥርዓት ራሱ የዘረጋውን አሠራር ለእኛም ይገባል ማለት ለብዙኃን ሞት፣ እስርና ስቃይ ሰለባነት ይዳርጋል (ስለ ሲዳማ ክልል መሆን ጥያቄ በሐዋሳና አካባቢው የተደረገ ሠልፍ)፡፡ በማኅበራት ስም ተደራጅቶ መብትን መጠየቅ ምንም እንኳን ድርጅቱ የግል ቢሆንም እንኳን ወደማይቀረው እስር ይወስዳል፡፡ የልማት ድርጅት (ለምሳሌ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ) ለሠራተኛው ደኅንነት ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጉ የደረሰውን ቋሚ የአካል ጉዳት መጠየቅ ከሥራ መታገድ ብሎም መታሰር ያስከተላል፡፡ አንድ ባህታዊ መንግሥትን ነቅፈዋል በሚል ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ መታሰሩን እየተቃወመ ከኑግ ጋር የተገኘ ሰሊጥ በሚል ፈሊጥ ከ13 የሚበልጥ ሰው ተገድሎና ብዙዎች ቆስለው በዚያ ሳያበቃ ሌሎች ታስረዋል (ጎንደር)፡፡ አስደንጋጩ ነገር ባህታዊው በወቅቱ ያለመታሰሩን ስናስብ የፖሊስ ኃይሉ ምን ነበር ዓላማው የሚል የማይመለስ ጥያቄን በውስጣቸን ትቶ ሄዷል፡፡

ሕግና የሕግ የበላይነት የማስፈን አሠራር ጥቅሙ ለሕግ አስከባሪው ራሱ መሆኑ ይዘነጋል፡፡ በአንድ ጥፋት/ክስ ድጋሚ ቅጣት መጣል የሕገ መንግሥቱ ክልከላ የመፍቀድ ድንጋጌ ይመስል፣ በድጋሚ በአንድ ጉዳይ መቀፍደድ የብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አባሎችና መሪዎች ብሎም ጋዜጠኞች ዕጣ ፈንታ ሆኗል፡፡ ሥራ አጥነት በሕግ የተደነገገ የመታሰሪያ ወንጀል (አደገኛ ቦዘኔ በሚል) ሲሆን፣ ይህ ሕግ በ1997 ዓ.ም. ገዥው ፓርቲ የደረሰበትን የደጋፊ ማጣት ተከትሎ በወሰዳቸው ዕርምጃዎች መሻር ሲገባው አሁንም በሥራ ላይ አለ፡፡ ወገኖቻችን በባዕድ ምድር በሊቢያ ስለተገደሉ ቁጣን ለመግለጽ ሠልፍ መውጣት ከምክንያታዊ ጉዳዩ ጋር ተያይዥ የሆኑ መንግሥትን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ቢነሱም እንኳን ለመታሰር ሰበብ ይሆናል፡፡

ታዲያ ይህ መጠነ ሰፊ የሕዝብ ተቃውሞ እነዚህ በማረሚያ ቤቶች ታጉረው የሚገኙ ሳይታሰሩም በተለያየ መልኩ በአፈናና በክትትል የሚኖሩ የነፃነት አርበኞቻችን ከፊል የትግል ውጤት ነው፡፡ ለሰላማዊ ትግል የከፈሉት አምሳያ የሌለው መስዋዕትነት፡፡ በመንግሥት ጭምር የሚዘከረውን የጦርነት አዙሪት መዘዝ ለአገር እንደማይበጅ ተረድተው ያልተሄደበትን መንገድ የቀየሱ ጀግኖቻችን ናቸው፡፡ አሁን ላለንበት ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሔው ውስብስብ፣ መንገዱ እጅግ ጠመዝማዛ ቢሆንም ጠቋሚና ቀዳሚ ዕርምጃው ግን ቀላል ነው፡፡ ሁሉንም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ከእስርና ክትትል መፍታት መንግሥት ጊዜ የማይሰጠው ቀዳሚ ዕርምጃ መሆን አለበት፡፡ የሕዝብ ሐሳብ ሊታፈንና ሊታሰር እንደማይችል በታሪካችን ለአንዴና ለመጨረሻ የምንማርበት ምዕራፍ ሊሆን ይገባል፡፡ ፈጽሞ እንዳይደገም፡፡ ግለሰብና የፖለቲካ ቡድኖችን በማሰር የፖለቲካ አቋምን ለማመንመን የሚደረግ ጥረት (የኃይልና ግብታዊ ሥራ) በተቃራኒው የሰፊው ሕዝብ ሐሳብ ሁሉንም የሚመለከት ጉዳይ ሆኖ ይመጣል፡፡ በአጭሩ ጭቆና አብዮትን ይወልዳል፡፡

የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን መፍታት ወቅታዊና ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ የሚያደርገው፣ እነዚህ ሰዎች አሁን ላለንበት የፖለቲካ ቀውስ የሚኖራቸውን አዎንታዊ ተፅዕኖ በማሰብ መሆን የለበትም፡፡ ያ ተጨማሪና ወደፊት ለምናስባት የሁላችን ኢትዮጵያ የሚኖረው ፋይዳ በራሱ ቀላል የሚባል አይሆንም፡፡ ነገር ግን የቁምም ሆነ የዘብጥያ ታሳሪዎች መፈታት ያለባቸው የሐሳብ ልዩነቶች የሚስተናገዱባት አገር መወለድ ስላለባት ነው፡፡ የሐሳብ ልዩነቶች በጠመንጃና በጉልበት መስተናገድ ስለሌለባቸው ነው፡፡ የሐሳብ ልህቅና በጠመንጃ ብቻ መምጣት እንዳለበት የሚያሳዩና የሚጋብዙ አሠራሮችና አቋሞች ሁሉ አንዳዶቹ በሒደት አብዛኞቹ በፍጥነት መቀረፍ ስላለባቸው ነው፡፡ የሐሳብን ፋይዳ መመዘን ያለበት ሕዝብ እንጂ በሥልጣን ላይ የተቀመጠን አካል ጨምሮ ሌላ ማንም መሆን አይችልም፡፡ ይልቁንም የመንግሥት ዋነኛ ተግባር ግልጽና ላልተገደበ ሕዝባዊ ውይይቶች የመንግሥት የሚዲያ ተቋማትን ክፍት ማድረግ ነው፡፡ ይህ እስከ ገጠር ድረስ የወረደ ተቃውሞ ፈር እንደያዘ የለውጥ ኃይል በመሆን ሊጓዝ የሚችለው፣ እነዚህ የመንግሥት የሜዲያ ተቋማት ለሁሉም ሐሳብ እኩል ክፍት መሆን ሲችሉ ብቻ ነው፡፡

እስከ መቼ ለአገር ውስጥ ጉዳዮች በውጭ ባሉ የዜና አውታሮች ላይ ጥገኛ እንሆናለን? እስከ መቼስ የሚዲያ አውታሮች ከመዝናናት ባለፈ ይባስ ብሎ የወጣቱንና የሌላውን ዜጋ የማሰብ አቅም መስለቢያ ሆነው ይቀጥላሉ? ሰፋ ያለ አገራዊ ራዕይ በሚፈለገው መጠን አለመኖር ወይም እንዲኖረን ማድረግ ሌላ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ አገራዊ ሐሳቦቻችንን በበቂ ሁኔታ ምንም ያልበሰሉ ቢሆን በአንድ በኩል እንዲበስሉ አንዳችን ከሌላችን የምንማርበት መድረክ መፍጠር እንጂ፣ እነዚህን ከእኔ በላይ አዋቂ ላሳር በሚል መንፈስ ማንቋሸሽ መዳበር የሚገባው ሐሳብ እየቀጨጨና ሊቃና ወደማይችልበት ጠማማነት እየተቀየረ እንዲሄድ መንገድ ማመቻቸት ብቻ ይሆናል፡፡ እኔ እንደማስበው ሕዝባችን ታጋሽና ሆደ ሰፊ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የማያውቀውን ሁሉ ለመማር፣ የሚያውቀውንም ለማጎልበት የማይታክት ባለ ብሩህ አዕምሮ ነው፡፡

ኅብረታችን በልዩነቶቻችን እንዲያብብ ከተፈለገ ምን ጊዜም መሥራት ያለብን መተማመን ያለበት ልዩነት እንዲኖር ከመሥራቱ ላይ ነው፡፡ ልዩነት ማለት በሙዚቃና በቋንቋ የሚገለጽ አይደለም፡፡ እነዚህ ለማንነታችን መሠረት የሆኑ ቁልፍ ነገር ግን አንዴ ከተረጋገጡ በኋላ ወደኋላ የማንመለስባቸው መሠረቶች ናቸው፡፡ ለ25 ዓመታት በመጀመሪያው ቀን በተረጋገጡ የማንነታችን መሠረቶች ላይ ስንዘፍን በመኖራችን ዋናው ሥራ ሙሉ በሙሉ ተዘንግቶ ቀርቷል፡፡

አሁንም ቢሆን መንግሥት የተቃውሞ ሠልፍ አድራጊዎችን ከማሰር ይህንም እንደ ሕግ ማስከበሪያ ዋነኛ መሣሪያ ከማድረግ መቆጠብ አለበት፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ዋነኛው ሰላም ጠባቂ መሆን ያለበት ሕዝቡ ራሱ ነው፡፡ ያሉት አንዳንድ መጠነኛ የሰላም ችግሮች ሕዝቡን በማሳተፍ ሊቃለሉና ሊቀረፉ የሚችሉ ናቸው፡፡ የሕግ ማስከበር ሥርዓቱም ቢሆን በሰፊው ሊፈተሽ የሚገባው ነው፡፡ ተጠያቂነት የሌለበት የፖሊስ አሠራር ማለትም ሠልፈኛን በቆመጥና በጥይት መደብደብ ብሎም ማሰቃየት ተመልሶ እንደማይመጣ ማረጋገጫ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ የትዕዛዝ ፈጻሚው ፖሊስ ችግር ሳይሆን የአመራር ሰጪው እንደሚሆን አንጠራጠርም፡፡ ለመሆኑ አስለቃሽ ጭስ የሚባል ነገር ለአገራችን ፖሊስ አልተፈቀደም እንዴ? የከፋና ወደ አመፅ የሚሄድ ሠልፍ ነው ቢባል እንኳ እንደ ማንኛውም ዓለም የጎማ ጥይቶች የማንጠቀመው ለምንድን ነው? ሠልፎችስ እስከ መቼ የጦርነት አውድማ ይመስል በገዳይ ጥይቶች ይታጀባሉ?

መንግሥት የወቅቱን የፖለቲካ ሁኔታ አንገብጋቢነት ተገንዝቦ ዕርምጃዎቹ ሁሉ ማስተዋል የሚነበብባቸው ለወደፊቱ ሳይሆን፣ አሁኑኑ ከራሴ ውጪ የሚላቸውን የአገሪቱን ዜጎች በማማከር መጀመር አለበት፡፡ ወጣቱን እንዳማከረ ሰምተናል፡፡ ይህ ወጣት በኢሕአዴግ ሊግ የተደራጀ እሱ የሚፈልገውን ብቻ እንዲያወራ የተዘጋጀ ስለሆነ ዕርምጃውን ያቀጭጨዋል፡፡ የጋራ ጉዳይ የምንለው ሁሉ በተግባር የጋራ ይሁን፡፡

የፖለቲካና የሐሳብ እስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...